“ብልሹ አሠራርን በተከተሉ 400 የሚጠጉ ግለሰቦች ላይ ርምጃ ተወስዷል” – አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ

– አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ የአ/አ/ከ/አ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፤ በዋናነት የሚያከናውነው በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡ ሕንጻዎች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው ግንባታ እንዲኖር ማረጋገጥ ነው:: ለዚህም ያመቸው ዘንድ መመሪያና ደንቦችን ያሻሻለ ሲሆን፣ በእነርሱም መሰረት ወደ ሥራ ገብቷል:: ስለሆነም የዝግጅት ክፍላችን መመሪያው ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ ባለስልጣኑ፣ የመዲናዋ ሕንጻዎች ስታንዳርድን እንዲያሟሉ ከማድረግ አኳያ ምን ሠራ? ሕግን በሚተላለፉ አካላት ላይስ ምን አይነት ርምጃ ወሰደ? በሚሉና መሰል ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ ጋር ቆይታ አድርጓል::

አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት ምን አቅዶ ምን ፈጸመ? የሥራ ክንውኑ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ገዛኸኝ፡– ከተልዕኳችን አንጻር በዋናነት የሠራናቸው ሥራዎች ከከተማ ስታንዳርዳይዜሽን በሚገናኝ ዋና ዋና ቁልፍ የውጤት ማመላከቻዎቻችን ሲታዩ በአማካኝ 90 በመቶ የሚሆን አፈጻጸም አለን:: የሠራናቸው ብለን ከምናነሳቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንደኛው የመሰረተ ልማት ቅንጅት ነው:: ይህ ሲታይ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ አንድ ተቋም መሰረተ ልማት ዘርግቶ ከሄደ በኋላ ሌላኛው ተቋም መጥቶ የሚያፈርስበትና የሚያበላሽበት ሁኔታ ነበር:: ይህ ደግሞ በበጀትና በጊዜ ብክነት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ተጠቃሚነት ጭምር የሚፈትን ነበር:: ስለዚህ በዚህ በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ነው ተብሎ የተገመገመና በከተማ ደረጃ እውቅና ያለው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የመሰረተ ልማት ቅንጅት ሥራ ነው::

ይህንንም ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት እንደ ቴሌ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ትራፊክ ማኔጅመንት እንዲሁም መንገዶች ባለስልጣን በጋራ በመሆን ቀድመው ዲዛይናቸውን በጋራ መጥተው በመሰብሰብ በዲዛይኑ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ዲዛይናቸውን አቅርበው አጽድቀንላቸው ወደ ሥራ ተገብቷል::

ስለዚህ የዚህ ተቋም ዋና ሥራው መቆጣጠር ነው:: ይህ ስለሆነ ጸድቆ የመጣው ዲዛይን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባለሙያዎች በመመደብ ይሠራል:: የመሰረተ ልማት ቁጥጥርና ክትትልም በዘርፍ ደረጃ የተደራጀ ስለሆነ በሪፎርሙ በተደረገው የማሻሻያ ሥራ ያልነበሩ የሥራ ክፍሎችም ጭምር የተደራጁለት ስለሆነ በዲዛይኑ መሰረት ስለመከናወኑ ክትትልና ቁጥጥር ሲያደረግ ቆይቷል::

ከሕዝብ ጋር ባደረግናቸው ውይይቶችም በሕዝቡ ዘንድ የነበረው ግብረመልስ ‹‹አሁን ገና አንድ መንግሥት ሆናችሁ›› የሚል ነው:: ይህ ማለት በፊት ቴሌ መስመር ይዘረጋል፤ መንገዶች በማግሥቱ የሆነ ነገር አለኝ ይላል፤ መንገዶች አስፓልት ሰርቶ ሲሄድ መብራት በተራው መጥቶ እዚህ ቦታ ላይ እምቆርጠው አለኝ ይል እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም የተረበሸ አሠራር ነበር:: አሁን ላይ በጋራ በዲዛይን ከተግባባን በኋላ ክትትልና ቁጥጥሩ እንዲመለስ ተደርጓል::

በኮሪደር ልማቱ የተሠሩ ሥራዎች ለተመለከተው አንድ አካባቢ ከለማ በኋላ ተመልሶ የሆነ ጉዳይ ያልሠራሁት አለ ብሎ የሚነካ ተቋም የለም:: ስለዚህ ውጤት የመጣበት አንዱ ቁልፍ ተግባር የመሰረተ ልማት ቅንጅት ሲሆን፣ ለውጤቱ መገኘት ዋና መሰረቱ የሪፎርም ሥራ ነው::

ሥራው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር አለባቸው ተብሎ ከተለዩት 16 ተቋማት አንዱ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ነው:: ስለዚህ በሪፎርሙ በአሠራር፣ በመመሪያ እንዲሁም በሰው ኃይል ከተሻሻለ በኋላ በሪፎርሙ መሰረት እየተገበርን ስለሆነ በመሰረተ ልማት ቅንጅት በኩል የመጣው ለውጥ አንድ ለውጥ ነው ተብሎ ይወሰዳል::

በሌላ በኩል የስታንዳርዳይዜሽን ሥራ ሲሆን፣ በከተማ ውስጥ የሚገነቡ ሕንጻዎች የዚህን ከተማ ገጽታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሚቀይር መልኩ በተለይም የውስጥ ቦታዎችና የኮሪደር ሥራው በሚነካቸው ሥፍራዎች የሕንጻ ቀለም ስታንዳርድ፤ የሕንጻ መብራቶችና የአጥር ስታንዳርዶች ወጥተዋል:: ለምሳሌ አራት ኪሎ አካባቢ የሚታዩት አጥሮች ደረጃን፣ ዲዛይንና የውጭ ማስታወቂያን ስታንዳርድ አዘጋጅቶ የሚተገብረው ይህ ተቋም ነው:: ስለዚህ በሥራችን ከሕዝብ ምላሽ አገኘን ያስባለን ባለፈው በኮሪደር አተገባበር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ የግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው::

ተቋሙ፣ ስታንዳርድን 24/7 በማስጠበቅ ረገድ የተቋሙን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ወደ እቅዳችን እየሄድን ነው የሚለውን ያረጋገጥንበት ነው:: ከዚህ በፊት በቦሌ፤ ፒያሳና አንዳንድ አካባቢዎች ከስታንዳርድ ከሕንጻ ቀለም ጋር፤ ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘ በተለይም ውጭ ማስታወቂያ ላይ መሰረታዊ ለውጥ አምጥተናል::

በከተማ ሕግና ፕላን የሚታወቀው ልክ ለሰው ልጅ ሳንባ እንደሚስፈልገው ሁሉ ግሪነሪዎች (አረንጓዴ) ሥፍራዎች የሚታወቁት ለከተማ ወሳኝ ናቸው ተብለው ነው:: ስለዚህ እነዚህን አረንጓዴ ሥፍራዎች ሳይቀር ከሪፎርሙ በፊት የውጭ ማስታወቂያዎች የከተማ ውበት ማበላሸት ብቻ ሳይሆን የሚሠሩት ከቢልቦርድ ባነር የሚለጠፉ፣ የሚሰቀሉና የሚንጠለጠሉ ስለነበሩ ጸሃይና ዝናብ ሲመታው የመበተን ባህሪ ነበረው:: ይህ ደግሞ የጽዳት ሥራ በሚሠሩ ዜጎች ላይ ተጨማሪ ሥራ ሆኖባቸው ነበር፤ የትራፊክ ዕይታን የሚከልል እንዲሁም በዝናብ ወቅት መውደቅ ጭምር ያጋጥም የነበረበት ነው:: አልፎ ተርፎም አንድ ቦታ ላይ 40 እና 50 ማስታወቂያዎች ስለሚደረደሩ አንዱ ማስታወቂያ አንዱን የመሸፈን፤ እንዲሁ በአካል ብረቱ የመቆም እንጂ ምን እንደሆነ የማይታወቅበት የነበረ ነው::

አሁን ላይ ግን ለመንግሥት ምስጋና ይግባና በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስታንዳርዱን ለማስጠበቅ በተሠራው ሥራ ከዚህ በፊት በዚህ መልኩ የተሰጡ የማስታወቂያ ፈቃዶች በሙሉ እንዲወገዱ አደርገናል:: በመቀጠልም የሀገሪቱን ገጽታ ሊቀይሩ የሚችሉ መግቢያ የሆኑ የ‹ቪአይፒ› በሮችን በሙሉ በአውሮፓ ስታንዳርደ መሰረት 3ዲ የሆኑ በጣም ዘመናዊ የሆኑ ድጂታል ስክሪኖች እንዲገጠሙ ተደርጓል::

ይህ ጥቅሙ የከተማውን ውበት መጨመር ብቻ ሳይሆን እንግዶች፤ የሀገራት መሪዎች በሚመጡበት ወቅት፤ ሀገራዊ በዓላት ሲከበሩ እንዲሁም ባሕላዊ የሆኑ ሥፍራዎች በስክሪን ይለቀቃሉ:: ስለዚህ እነዚህ ስማርት ፖሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው:: ማኅበረሰቡ የሚያውቀው መብራት ብቻ እንደሚሰጡ ነው፤ ነገር ግን ማኅበረሰቡ በእግሩ ሲጓዝ እየተዝናና መረጃ የሚያገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል::

በጥቅሉ በዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ትልቁ ሥራችን ከመሰረተ ልማት ቅንጅት ቀጥሎ የከተማ ስታንዳርዳይዜሽን ነው:: ይህም የሕንጻ ደረጃ ሲባል ከተማ አስተዳደሩ ስማርት ሲቲን እገነባለው ብሎ አስቀምጧል::

ስማርት ሲቲ ሲባል አጠቃላይ የሚሠሩ ሥራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ እንቅስቃሴ መኖር አለበት:: እነዚህን ለማስተግበር በአዋጅና በመመሪያ ኃላፊነት የተሰጠው ለዚህ ተቋም ነው:: በሕንጻው ላይ የቀለምም መብራትም ለውጥ ሲደረግ የከተማውን ገጽታ ቀይሯል:: ሕንጻዎች ድሮም ነበሩ፤ ነገር ግን አሁን እንዲገለጥ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል::

ከዚህም ሌላ አገልግሎት አሰጣጣችን ከዚህ በፊት በደላላ የሚዋከብ ከፍተኛ ብልሹ አሠራር ያለበት ነው፤ ውክቢያው የነበረባቸው ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ቀጥሎ የፕላን ተግባር የሚያከናውኑ ተቋማት ናቸው። ከተማ አስተዳደሩ ችግር ያለባቸውን ተቋማት ከመሰረቱ ሪፎርም እንዲያደርጉ አድርጓል። በዚህም አሁን ላይ የአዲስ አበባ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ከነበረበት ችግር ወጥቷል።

ወደ እኛ ተቋም ስንመጣም ከዚህ በፊት የነበረውን አገልግሎት ቀይረናል። ከማንዋል አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ድጂታል ከወሰድነው አገልግሎት አንዱ የግንባታ ፈቃድ ነው። ካርታ ይዞ የሚመጣ አገልግሎት መጀመሪያ የሚመጣው የግንባታ ፈቃድ ነው። ስለዚህ አገልግሎቱ በኦንላይን እንዲሆን ተደርጓል። ሌላው የግንባታ ቁጥጥር ሲሆን፣ የሚሰጠውን መረጃ በመያዝ ወደ ስሚንቶ ሱቆች በመሄድ ወደ ግንባታ እንዲገባ የመጀመሪያ የግንባታ ማስጀመሪያ ቅጽ ይሰጣል:: ይህን ለማስቀረት ‹‹ኪው.አር ኮድ›› እንዲኖረው ተደርጓል። ከድጂታል አገልግሎቱ ቀጥሎ እኛ በምንሰጣቸው ፈቃዶች የሀሰት መረጃን ለመከላከል ከአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የ‹‹ኪው. አር ኮድ›› እንዲለማ ተደርጐ ወደ ሥራ ገብተናል።

አገልግሎት ፈላጊው ወደ ተቋማች በምሳ ሰዓት እንኳ ቢመጣ ተገልጋይ እንዳይንገላታ በሚል አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል። ምንም እንኳን ወደ ቢሯችን የተማሩም ያልተማሩም አገልግሎት ፈላጊዎች የሚመጡ ቢሆንም የኦንላይን አገልግሎት መጠቀም የማይችሉ በ11ዱም ክፍለከተሞች የኦንላይን ሰርቪስ አገልግሎት ድጋፍ እንዲሰጡ የአይሲቲ ባለሙያዎች ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን:- ተቋሙ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት የሚገጥሙት ማነቆዎች ምንድን ናቸው? እንዴትስ እየፈታችሁት ነው?

አቶ ገዛኸኝ:- ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠን ቢሆንም በርካታ ፈተናዎች አሉ። በዘጠኝ ወሩ አመጣናቸው ብለን ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው ናቸው። የስታንዳርዳይዜሽን፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በአጠቃላይ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የሠራነውን ሥራ በጥሩ መልኩ የሚጠቀሱ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- የግንባታ ፈቃድ የሚሰጠው ጠያቂው ምን ምን ሲያሟላ ነው? የተሰጠውንስ እምትከታተሉት በምን መልኩ ነው?

አቶ ገዛኸኝ:- ከተማ አስተዳደሩ የሚተገብረው የፈቃድ አሰጣጥ እንደ ፌዴራል 2002 የወጣውን የሕንጻ አዋጅ መሰረት በማድረግ ነው። ስለዚህ አጠቃላይ አዋጁ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚተገበር ሆኖ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚተገበረው ከዚያ አዋጅ የሚመነጭ ነገር ግን የራሱ መመሪያ፤ የሕንጻ ኮድ እና ስታንዳርድ ያለው ነው::

ይህ እንደተባለው ከሪፎርሙ በፊት አንደኛ የሚሰጠውን አገልግሎት ግልጽ ከማድረግ አንጻር፤ ሁለተኛ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ በተቀመጠው ስታንዳርድ አንድ የግንባታ ፈቃድ መቼ ገብቶ መቼ አገልግሎት ያገኛሉ? የሚሉ እጥረቶች የነበሩበት ሁኔታ አለ።

ባስቀመጥናቸው ስታንዳርድ ብቻ ለእይታ ማቅረባችን በቂ አይደለም:: የሁሉም አመራር ከእነ ማዕረጉ፣ ከእነ ሥራ ኃላፊነቱ የግል ስልክ ቁጥር ጭምር እንዲለጠፍ አድርገናል::

ስለዚህ ማንኛውም ተገልጋይ በምንሰጣቸው አገልግሎቶች ምን ያስፈልጋል? የሚለው ለምሳሌ ግንባታ ፈቃድ ሁለተኛው ወለል ላይ ነው፤ እዚያ ሲኬድ በ‹‹ኤል.ኢዲ›› ግንባታ ፈቃድ ለመውሰድ ዋና ዋናዎቹን ለማንሳት ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የጸደቀንና የተረጋገጠ ካርታ ይዞ ይመጣል:: የፕላን ስምምነት ያስጠይቃል::

ይህ የፕላን ስምምነት ማለት አንድ አልሚ መሬትና ካርታ ወስዶ ወደ ግንባታ ሊገባ ሲል የሚገነባውን ግንባታ የሕንጻውን ከፍታ የሚወስን ነው:: የት አካባቢ መገንባት እንዳለበትም ይወስናል:: የግንባታ ፈቃድ ተገኘ ተብሎ ሁሉም አካባቢ መገንባት አይፈቀድም:: ለምሳሌ አየር መንገድ፣ ብሔራዊ ደኅንነትና መሰል ተቋሞች አካባቢ የሕንጻ ከፍታዎች የተገደቡ ናቸው:: የፕላን ስምምነት አገልግሎት ወሰደ ማለት ገንቢው አካል በጠየቀው ቦታ ላይ መገንባት ይችላል ማለት ነው:: የጠየቀው ቦታ ደግሞ የአረንጓዴ ቦታ አለመሆኑንም ያረጋግጣል:: በአጠቃላይ በአካባቢው መሥራት የሚያስችል መሆኑን የሚገልጽ አሠራር ማለት ነው::

አዲስ ዘመን፡- የግንባታ ዘርፍ ቁጥጥሩና ክትትሉ ምን ይመስላል?

አቶ ገዛኸኝ፡- ያለን ሁለት አይነት ክትትልና ቁጥጥር ነው:: አንደኛ ከመሬት አስተዳደር የተረጋገጠ ካርታ፣ የይዞታ ማረጋገጫ፤ ፕላን ስምምነት ይዞ መጥቶ፤ ግንባታ ፈቃድ በስትራክቸራል ፕላኑ መሰረት ከተፈቀደለት በኋላ ይመጣና የግንባታ የመጀመሪያ እርከን ይወስዳል:: ከወሰደ በኋላ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ባለሙያ ይመደብለታል:: ይህ ባለሙያ የግንባታው ሒደት ማለትም ከአፈር መቆፈር ጀምሮ ገንቢው አካል እስኪያጠናቅቅ ድረስ ክትትል የሚያደርግና ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል::

ሕንጻው ማካተት የተገባቸውን ሁሉ ማካተቱን ያረጋግጣል:: ገንቢው አካል ባጸደቀው ዲዛይን መሰረት ስለመሥራቱ የሚከታተለው ባለሙያ ማለት ነው:: ለዚሁ ክትትል ዓላማ የተዘጋጀው ቅጽ ተሞልቶ ካለቀ በኋላ ግንባታውም የሚጠናቀቅ ይሆናል:: ሪፖርትም ያደርጋል::

ግንባታውን ተከታትሎ ካጠናቀቀ በኋላ ከአምስቱ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሕንጻ መጠቀሚያና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ፈቃድ ይጠይቃል:: ተጠናቋል ተብሎ ሲመጣ የሕንጻ መጠቀሚያ መጀመሪያ የተፈቀደው ዲዛይን ይያዝና ኢንስፔክት ይደረጋል::

ከሪፎርሙ በፊት የሕንጻ መጠቀሚያ የሚል እንጂ የሕንጻ መጠቀሚያና ኢንስፔክሽን የሚል አልነበረውም:: ስለዚህ ፈቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል ማለት ነው:: ስለሆነም ዳይሬክቶሬቱ ይህንንም ለማድረግ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ማለት ነው:: ስለዚህ በዲዛይን ወቅት ያልነበሩ ነገሮች ከተካተቱ የሕንጻ መጠቀሚያ አያገኙም:: ሌላው ቀርቶ በሪፖርቱ ወቅት የነበረው ባለሙያ ያጭበረበረው ነገር ካለ በዚህ ጊዜ ይያዛል ማለት ነው::

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ተጀምረው ለዓመታት ሳይጠናቀቁ የቆሙ ሕንጻዎች ይታያሉ፤ አንዳንዱ ቦታ ሕንጻው ተሰርቶ ሳይጠናቀቅ ሥራ የተጀመረባቸው ናቸው፤ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ያሉ ሕንጻዎች ላይ ምን ማስተካከያ ርምጃ ወሰዳችሁ? ለምን ያህሉስ ፈቃድ ሰጥታችኋል? አዋጁን በጣሱ ላይ የወሰዳችሁት ምን አይነት ቅጣት ነው?

አቶ ገዛኸኝ፡- እኔ ያነሳሁት የሪፎርሙን ጅማሮ ነው:: ነገር ግን ብልሹ ከሆኑ አሠራሮች ሙሉ በሙሉ ወጥተናል የሚል ግምገማ የለንም:: የኮንስራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የጥፋት መጠኑ ሊቀንስ ይችላል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከብልሽት የጸዳ ነው ማለት ያስቸግራል:: ብልሽቱ ሊመጣ የሚችለው ከቸልተኝነት አሊያም የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በሚሞከርበት ጊዜ ሊሆን ይችላል::

አስቀድሜ የጠቃቀስኳቸው ለውጦች እንደተጠበቁ ሆነው የሕንጻ አዋጁን በመጣስ፤ ባለሙያውም በተመደቡበት ሥራ የሚገባውን ክትትል ባለመወጣት ከቢሯችን ጀምሮ ርምጃ የተወሰደባቸውና ፈቃዳቸው የታገደባቸውም ኮንትራክተሮች አሉ:: አጠቃላይ ሠራተኛ፣ ኮንትራክተር እንዲሁም ኮንሶልታንት በተባሉ ወደ 400 በሚጠጉ ግለሰቦች ላይ ርምጃ ተወስዷል::

ወደ ገንዘብ ሲመጣ ደግሞ ከዚህ በፊት በዓመት ውስጥ የሕንጻ አዋጁን ጥሰው የሚገኙ የተለያዩ አካላት ቅጣታቸው ከሶስት፣ አራትና አምስት ሚሊዮን ብር አያልፍም:: ለዚህ ደግሞ አንዱ ችግር ቀድሞ የነበረው የሕንጻ አዋጅ ያለበት የአሠራር ክፍተት ነው:: በመሆኑም አንዱ ያሻሻልነው ነገር፤ አልሚው ከኮንትራክተር፣ ከኮንሶልታንትና ከባለሙያ ጋር ሆኖ ትልቅ ተንኮል ሰርቶ ከሁለት እስከ አምስት መቶ ሺ ብር ቢቀጣ እስከ 40 እና 50 ሚሊዮን ብር የሚያገኝበት ጉዳይ ስለሚሆን ስሜት ላይሰጠው ይችላል::

በእርግጥ የከተማውን ስታንዳርድ ማስጠበቅ እንጂ መቅጣት ዓላማችን ባይሆንም የሕንጻ አዋጁን ጥሰው የሚገኙ አካላት ላይ አስፈላጊ የሆነ ቅጣት አሁን ላይ ያሻሻልነው መመሪያ ላይ እንዲካተት አድርገናል:: ቅጣቱ ባለሙያውንም፣ ኮንትራክተሩንም ሆነ ኮንሶልታንቱንም እንዲያካትት አድርገናል::

አንዳንዶቹ ኮንትራክተሮችም ከመንግሥት ተቋም የወጡ በመሆናቸው እኛ እንመራዋለን በሚል የመዳፈር ሁኔታዎች እንደነበሩ ገምግመናል:: በመሆኑም ያደረግነው ነገር ኮንትራክተሮች ፈቃዳቸው እንዲታገድና የቅጣቱ አካል እንዲሆኑ፤ በውስጡ ያለው ባለሙያ ድግሞ ከትኩረት ማነስ ጀምሮ ሆነ ብሎ ጉዳዩን የፈጸመ ከሆነ የቅጣቱ አካል እንዲሆን አድርገናል::

ከማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ርምጃ የተወሰደባቸው አሉ:: ከዚህ በተጨማሪ የተለየ ጥቅም ለማግኘት ብለው ሲደራደሩ የነበሩትን ደግሞ ባለጉዳዮች ወይም ደንበኞቻችን በሰጡን መረጃ ላይ ተንተርሰን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ርምጃ መውሰድ ችለናል::

ወደ እኛ በምንመጣበት ጊዜ አገልግሎቱን በአፋጣኝ መስጠት ሲገባን ሎከር ውስጥ ቆልፎ የሚያቆይ እንዳይኖርም የተቀመጠ የጊዜ ሰሌዳ አለ:: ስለዚህም የመጣን ጉዳይ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ አከናወነ የሚል አሠራር ተመዝግቦ እንዲቀመጥ አድርገናል:: ማስተናገድ የማይችልበት ሁኔታ ካለ፤ አመልክቶ የሚቀርብበት ሁኔታ ካለ እንኳ ሎከሩ ውስጥ የሚያስቀምጠው ሳይሆን ወደመዝገብ ቤት ተመላሽ አድርጎ ሪፖርት ማድረግን ይጠይቃለል:: ርምጃ እየወሰድን ባለበት ሁኔታ እንኳ ብልሽቶች ያጋጥሙናል:: በፊት ያስቸግረን የነበረው ደንብ ማስከበር ነበር:: አሁን ግን የጋራ አሠራር በመዘርጋታችን ችግሩ ተቀርፏል:: እኛ ምንም እንኳ የመሻርና የመሾም ስልጣን ባይኖረንም ተሿሚው ችግር በፈጠረ ጊዜ ግን ወዲያውኑ በመሻር ርምጃ የተወሰደበት ሁኔታ አለ::

አዲስ ዘመን፡- በተገባደደው በጀት ዓመት ውስጥ የምን ያህሉ ኮንትራክተሮች ፈቃዳቸው ታገደ? ተሻሩ የተባሉ ተሿሚዎችስ ምን ያህል ናቸው?

አቶ ገዛኸኝ፡- ተሿሚን በተመለከተ ከግሪነሪ ጋር በተገናኘ እና ባለጉዳይን ከማንገላታት አንጻር የሠሩት ሥራ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሁለት ተሿሚዎችን አንስተናል:: ኮንትራክተሮችን በተመለከተ ግን ከቁጥጥርና ክትትል ዘርፍ መረጃውን መውሰድ ይቻላል:: ነገር ግን ባለሙያ፣ ኮንትራክተርና ኮንሶልታንት በጥቅሉ በዚህ ዓመት ብልሹ አሠራርን የተከተሉ ወደ 400 የሚጠጉ ግለሰቦች ላይ ርምጃ ተወስዷል:: ይህ 11ዱንም ክፍለ ከተማ የሚጨምር ነው:: ይህ የሚያመላክተው ሪፎርም የተደረጉ ነገሮች ቢኖሩም በቀጣይ ከባድ ሥራ እንደሚጠብቀን ነው:: የመጡ ለውጦች ግን አሉ፤ በተለይ በውጭ ማስታወቂያ፣ በመሰረተ ልማት ቅንጅት እና በሕንጻ ስታንዳርዳይዜሽን ለውጥ መምጣት የተቻለባቸው ዘርፎች ናቸው::

አሁንም ይህን የመጣውን ለውጥ ሊያጠለሹ የሚችሉ አልፎ አልፎ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች አሉ:: እነዚህን ተሿሚውን የፖለቲካ ርምጃ በማስወሰድ፤ በአሠራር የሚዘጉትን በአሠራር እየዘጋን የምንሔድ ይሆናል:: በአሁኑ ጊዜ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ስልካቸው በግልጽ በየመግቢያው ተቀምጧል፤ የትኛውም ጥያቄ ያለው አካል በቀላሉ እንዲያገኘው ተደርጓል:: ምንም አይነት ድብብቆሽ የለም::

ለውጦች የመኖራቸውን ያህል ልንሻገራቸው የተገቡ ችግሮች አሉ:: ከችግሮቹ አንዱ አገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ወጥ ማድረግ የሚለው ተጠቃሽ ነው:: ይህም ሲባል ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለውን አሠራር ሲሆን፣ በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራም እየተጀማመረ ነው:: አሁን የአገልግሎት መስጫ ቢሯችንን ምቹ በማድረግ በኩል ጥሩ የሚባል ሥራ እየተሠራ ነው::

በጥቅሉ ከምንሰጣቸው አምስት ዋና አገልግሎታችን አንጻር የሪፎርም ውጤቱ ምን አመጣ የሚለውን ገምግመናል:: የማያስፈልጉ አደረጃጀቶችን አጥፈናል፤ የሚያስፈልጉትን ደግሞ አካትተናል:: ይህ ያስገኘልን ጥሩ የሚባል ለውጥ ነው:: ሌላው ለውጥ ያመጣንበት አሠራር ላይ ነው:: በዚህ አሠራር ውስጥ አላስፈላጊ የነበሩ አካሔዶች እንዲመክኑ ተደርገዋል:: በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ የአስፈጻሚ አካላትን ለመደንገግ የወጣው መመሪያ ሙሉ በሙሉ የምንተገብረው ከሆነ ውጤታማ ሥራ ይሆናል::

እስካሁን በዘጠኝ ወር ውስጥ ከገመገምናቸው ሥራዎች ውስጥ በሪፎርሙም ጥሩ ውጤት አምጥተናል ብለን የምንናገረው ከአደረጃጀት፣ ከአሠራር እና ከገቢ አንጻር የተሠሩ ሥራዎችን ነው:: ከዚህ ቀደም የሕንጻ አዋጁን የሚጥሱ አካላት ይቀጡ የነበረው በአማካይ ከሶስት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ነው:: በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ እንደ 11ዱም ክፍለ ከተማ ወደ 61 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ቀጥተናል:: ይህ ማለት መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል እንደማለት ነው:: ከሚቀጡባቸው ነገሮች ውስጥ ለምሳሌ የወለል ጭማሪ፣ ያስፈቀደው የአስር ወለል ሆኖ ሳለ አንድ ወለል ሊጨምር ይችላል:: የሰውን እንቅስቃሴ ሊገድብ በሚችል መልኩ መንገድ የመዝጋት፣ የሌሎችን ግላዊ መብት ለመጋፋት መስኮቶችን ወደሌላኛው ቤት አዙሮ መስራት እና ሌሎችም ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- አንድ ሕንጻ ርምጃ ሲወሰድበት ሕንጻው ከዲዛይን ውጪ ሲገነባ ቁጥጥር የሚያደርግ ባለሙያ ይኖራልና የወለል መጨመርም ሆነ ሌላ ጥሰት ሲፈጸም ባለሙያውን እራሱ መከታተያና መጠየቂያ ስልታችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ገዛኸኝ፡- ይህን በተመለከተ በቅድሚያ ከባለሙያ እስከ ተሿሚ ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች ላይ ርምጃ ተወስዶባቸዋል ብዬ ጠቅሻለሁ:: ከዚህ ቀደም ሕንጻ መጠቀሚያ አንዴ ከተሰጠ በኋላ ዞር ብሎ የሚመለከተው አልነበረም:: አሁን ግን በሪፎርሙ መሰረት የሕንጻ መጠቀሚያ ፈቃድና ኢንሲፔክሽን ነው::

ስለዚህ በቋሚነት ይጠቀምበት የነበረውን በሁለት ዓመቱ እንዲሆን አድርገናል:: ምክንያቱም የዛሬ ሁለት ዓመት ትምህርት ቤት የነበረውን ሕንጻ ዛሬ ለማንም ሳያሳውቅ ወደሌላ ቀይሮት ሊሆን ይችላል:: ወይም ደግሞ የመኪና መቆሚያ የነበረውን ቦታ ወደባሕላዊ ምግብ ቤት ቀይሮት ሊሆን ስለሚችል በየሁለት ዓመቱ የሚታይ ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- የሕንጻ ደህነት (ሴፍቲ) ላይ የሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች አሉ:: ለምሳሌ ሕንጻ ተደርምሶ የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ የሕንጻው የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የሚፈጠሩ በርካታ ጉዳቶች አሉና የዚህ ክትትል እንዴት ይገለጻል?

አቶ ገዛኸኝ፡– የሕንጻ ደህንነት (ሴፍቲ) ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ያሉበት ነው:: አንደኛ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ሔልሜት፣ ቀበቶና የመሃንዲስ ሳይት ቁጥጥርና ስምሪት ግንዛቤ የሚሰጥ ሁኔታ ችግር ውስጥ ነበር:: ስለዚህ የቀን ሥራ የሚሠሩ የጉልበት ሠራተኞች ጀምሮ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ክትትል የሚደረግበት መዝገብ ተዘጋጅቶ አማካሪ መሃንዲስ የተባለው ከእኛ ጋር ውል ይገባሉ:: የሚገቡት ውል ደግሞ ከአልሚው ጋር ኢንሹራንስ እና ወደግንባታ መግባት የሚችሉት የባለሙያውን ፈቃድ ጭምር አያይዘው ሲመጡ ነው:: የባለሙያው ፈቃድ መያያዙ ደግሞ በሕንጻ ላይ አንዳች ችግር ቢፈጠር ኃላፊነቱን የሚወስደው እራሱ በመሆኑ ነው:: ከላይ ርምጃ ተወሰደባቸው ያልኩት አንዱ ርምጃ ያስወሰደባቸው ጉዳይ የሕንጻ ሴፍቲ (ደህነት) ባለማሟላታቸው ነው::

ሌላው እንደ ችግር የፈተነን ነገር ቢኖር፤ ሠራተኛው <ጓንት አጥልቄ ምስማር መምታት አልችልም፤ ሔልሜት አድርጌ የምሠራ ከሆነ ስለሚሞቀኝ ወደላይ ይለኛል> የሚል በመሆኑ ነው:: እንዲያም ሆኖ መልበስ ግዴታ ነው በሚል ከለበሰ በኋላ ግን ዞር ብሎ የሚያወልቅበት ሁኔታ በመኖሩ ፈታኝ አድርጎብናል የሚሉ አሉ:: ስለዚህ ሠራተኛው ባለማድረጉ ምክንያት መቀጣት ያለበት አልሚው ብቻ ሳይሆን ኮሶልታንቱም ኮንትራክተሩም ጭምር ነው::

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ቦታ ከላይ ግንባታው እየተካሔደ፤ ሊፍትም ሳይኖራቸው ከስር ለኪራይ አገልግሎት የዋሉ ሕንጻዎች አሉ፤ ለሕንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ሲሰጥ የሚያሟላው ምን ምን ነገርን ነው?

አቶ ገዛኸኝ፡– የሊፍትና ሌሎች አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ በሕንጻ አዋጅ አሠራር መሰረት ሲታይ አዲስ አበባ ወደ 140 አካባቢ ዕድሜ ያስቆጠረች ከተማ ናት:: ስታንዳርዱን የማያሟሉ በርካታ ሕንጻዎች አሉ:: ተቋማችን ከመሬትና መሰል ተቋማት ጋር ተነጥሎ ራሱን የቻለው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ነው:: የምናነሳቸው ሕጎችና መመሪያዎች ከ2002 ወዲህ ያሉ ሕጎች ናቸው:: ስለዚህ ስታንዳርድ የማያሟሉ የመኪና መቆሚያና ሊፍት የሌላቸው ብዙ ሕንጻዎች ናቸው:: እነዚህን በተቻለ መጠን ሕንጻውን በማይጎዳ መልኩ ግለሰቦችን በማግባባት ለማሠራት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ:: ነገር ግን ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ ስለማይሠራ 1997፤ 1960ዎቹ የተገነቡ ሕንጻዎች አሁን በምንፈልገው ዲዛይን ለማሠራት አዳጋች ናቸው::

ቢሆንም ግን አሁን ላይ እያፈረስን ያለነው የከተማ ስታንዳርድን የማያሟላና የከተማ ፕላንን መሰረት ተደርገው ስላልተሠራ ነው:: ይህም የመጣንበትን መንገድ የሚያሳይ ነው:: እነዚህን እና መሰል ችግሮች በአሠራር ተፈተዋል:: ቀለም ከዚህ በፊት ምንም የቀለም ስታንዳርድ የሚባል አልነበረም:: አዲስ አበባ አታውቀውም:: አሁን ለካቢኔ የሚቀርበው የአበባ ማስቀመጫ ስታንዳርድ እየተዘጋጀ ነው:: ከአሁን በኋላ የሚፈቀደው የሕንጻ ቀለሙን የመጋረጃ ችግር የግንባታ ፈቃዱ ሲሰጥ በፕላን ስምምነት መሰረቱ አብሮ የሚሰጥ ነው:: ይህ ሲሆን፣ የከተማው ስታንዳርድ ያስጠብቃል፤ እኛንም ከስቃይ ይገላግለናል:: መጋረጃው እና የሚቀመጠው አበባ እንዲህ አይነት ነው ተብሎ ከዚያ ውጭ ቢያደርግ ርምጃ እንደሚወሰድበት የአሠራር አካል ይደረጋል::

የሕንጻ አዋጁ የሚያስቀምጠው ሁለት አይነት የሕንጻ መጠቀሚያ አለ:: ቋሚና ጊዚያዊ ብሎ ያስቀምጠዋል:: ቋሚ የሕንጻ መጠቀሚያ ማለት ሕንጻው አገልግሎቱን አጠናቅቆ አጠቃላይ የአደጋ ጊዜ መውጫዎችን ማለት ለሕንጻው የተፈቀደውን በሙሉ ገጥሞ ከጨረሰ በኋላ የሚሰጠው ቋሚ የሕንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ነው::

ጊዜያዊ ግን ዝቅተኛ የወለል አማካይ በማየት የሚሰጥ ነው:: ለምሳሌ ሕንጻው ባለ 20 ወለል ከሆነ ዝቅተኛው ወለል ካሟላ የሕንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ይሰጠዋል:: ይህ ታሳቢ የሚያደርገው የባንኮች ብድርንና ባለ 20 ወለል ሕንጻን በአንድ ጊዜ መገንባት ስለማይችል ገቢ እያመነጨ ገንብቶ እንዲያጠናቀቅ ለማስቻል ነው:: ስለዚህ ከአዋጅ አንጻር ሳይጠናቀቅ ፈቃድ መስጠቱ ምንም ክፍተት የለበትም:: በተግባር ግን ከስር የምግብ ቤት፤ ሲሠሩ ብሎኬትና እንጨት የሚወድቅበት ሁኔታ እያጋጠመን ነው:: በዚህ ሳቢያም ‹‹ስካፎልዲንግ›› ሳይወርድ የመጠቀሚያ ፈቃድ እንዳይሰጥ በሰርኩላር ታግዷል::

አዲስ ዘመን፡- በከተማው ውስጥ ቆመው የቀሩ ሕንጻዎች አሉ፤ ለአብነት ያህል አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አንድ ሕንጻ ለአሥራ ምናምን ዓመት ሳይጠናቀቅ ቆሟል፤ ቦታውን መንግሥትም ግለሰብም አልተጠቀመበትም፤ ይህን መሰል ሳይጠናቀቁ የቆሙ ሕንጻዎች እጣ ፈንታቸው ምንድን ነው?

አቶ ገዛኸኝ፡– የሕንጻ ስታንዳርድ እናረጋግጥ ስንል ከ15 እስከ 20 ዓመት የቆሙ ባለቤቶቻቸው በተለያየ ምክንያት ማለትም ገሚሱ በፍርድ ቤት፤ ገሚሱ ደግሞ በውል ስምምነት ወይም ‹‹ኮላተራል›› በማስያዝ የባንክ ጉዳይ ያለባቸው እና አልሚዎቻቸው ውጭ ሀገር ያሉ ናቸው:: ምክንያቶቻቸው ሁሉ ተለይተዋል:: በኮሪዶር ልማቱ ምክንያት እነዚህ ሕንጻዎች በስታንዳርዱ መሰረት ለሚመለከተው አካል ተወስነው እንዲተላለፉ ተደርጓል:: በተለይም የጸጥታ ችግር የሚፈጥሩና የቆሻሻ መድፊያ ሆነው ስለተገኙ ልዩ የንቅናቄ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ በመገባቱ ታሪካቸው እየተቀየረ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማራሪያ ከልብ እናመሰግናለን::

አቶ ገዛኸኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

በአስቴር ኤልያስና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You