
በጎጃም ክፍለ ሀገር በቢቸና አውራጃ ጨው ሰቅሊ ማርያም ቀበላ ውስጥ በ1942 ዓ/ም አንድ እንቁ እና ብርቱ ደራሲ ተወለደ:: ስሙም ኀሩይ ሚናስ ተባለ፡ በልጅነቱ የቤተ ክህነት ትምህርት ጎጃም ውስጥ ባለ ታዋቂ ቅኔ ቤቶች እየተዘዋወረ ተምሯል:: ኀሩይ ሚናስ አቡጊዳ፣ ቅኔ እስከ ዋዜማ እና ፆመ ድጓን ከተማረ በኋላ በድቁና ተቀጥሮ ቤተ ክርስቲያንን አገልግሏል።
የቅኔ እውቀቱን ለማሳደግ ጎጃም ውስጥ ዲማ ጊዮርጊስ ከአለቃ ማርቆስ ዘንድ ተመዘገበ:: ዲማ ጊዮርጊስ ረዥም ዓመታት ያገለገለ ቤተክርስቲያን ነው:: ገዳሙ ከጥንት ከእነ አባ ተክለ አልፋ እስከ እነ አለቃ አያሌው ታምሩ ታላላቅ የቤተ ክህነት ሊቃውንት ጉባኤ ዘርግተው አስተምረውበታል::
ኀሩይ ሚናስ ልሳኑ የሚባል የቅኔ ቤት ባልንጀራ ነበረው:: ልሳኑ ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ከመምጣቱ በፊት አዲስ አበባን ያውቀው ነበር:: በአንድ ወቅት ልሳኑ ኀሩይን አዲስ አበባ ቢሄድ የተሻለ ትምህርት እንደሚማር እና በድቁና ሥራ ተቀጥረው መሥራት እንደሚችል ነገረው:: ኀሩይ በሃሳቡ ተስማማ:: ሁለቱ የቅኔ ተማሪዎች ደጀን ከተማ ድረስ በእግራቸው ከኼዱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በእግር ለመኼድ አድካሚ ከመሆኑም በላይ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ተገንዝበው የትራስንፖርት ብር ለማግኘት ከደጀን ከተማ ዝቅ ብላ ከምትገኘው ቆላማ ሰፈር ከአርሶ አደሮች ቤት ስለ ማርያም አሉ:: አርሶ አደሮቹም እነ ኀሩይ ጥጥ ሽጠው እንዲጠቀሙ ሰጧቸው::
ከአርሶ አደሮች የተቀበሉትን ጥጥ በመሸጥ የትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ አገኙ:: በጭነት መኪና አዲስ አበባ ገቡ:: አዲስ አበባ ቀጨኔ መዴኃኒዓለምም ተጠጉ:: በወቅቱ የቅኔ ተማሪዎችን የሚያበረታታ አፈ ንጉስ ነሲቡ የተባለ ግለሰብ ተማሪዎች በወር ሦስት ብር እንዲከፈላቸው ያደርጉ ነበርና ኀሩይ ሚናስም በወር የሚከፈላቸውን ብር እየተቀበለ ኑሮውን በዚያው አደረገ::
ኀሩይ ወር ጠብቆ የሚያገኛት ሦስት ብር በቁጠባ አሳደጋት:: በርከት አለች:: ኀሩይ ያችን በጊዜ ሂደት የተጠራቀመች ገንዘብ ለአንድ ወዳጁ በአደራ ሰጠው:: ሰውዬው የአደራ ግዴታውን አልተወጣም:: የኀሩይን ገንዘብ ይዞ ጎጃም ገባ:: ኀሩይ የዋዛ ሰው አይደለምና ተከትሎት ጎጃም ውስጥ ይስማ ደጀን ተብሎ የሚጠራ ቅኔ ቤት በመሄድ አቤቱታውን ለቅኔ ቤቱ መሪጌታ አቀረበ:: ባለዕዳው ግን ካደ:: በዚህ ጊዜ ኅሩይ ከቤተሰቦቹ የትራንስፖርት ገንዘብ ተቀብሎ ተመልሶ አዲስ አበባ ሄደ:: አሁን እንደ መጀመሪያው ቀጨኔ መድኃኒዓለም አልኼደም:: ወደ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በመሄድ ኑሮውን ቢጀምርም ሕይወት ቀላል አልሆነችለትም::
ከቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ወጥቶ ብዙ የመከራ ሕይወትን ገፋ:: የአዲስ አበባ በረንዳ አዳሪዎችን ተቀላቀለ:: የበረንዳ አዳሪነት ሕይወት ግን ፈታኝ ሆነበት:: ጠኔው፣ እርዛቱ፣ ውሃ ጥሙን አልቻለውም:: ሆኖም በርካታ ውጣ ውረዶች እየተጋፈጠ እና ትምህርቱንም እየተከታተለ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደረሰ::
በ1969 ዓ/ም አስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈትኖ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን መቁረጫ ነጥብ አመጣ:: በ1970 ዓ/ም ገናናውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቀለ:: ይሁንና በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ከዓመት በላይ መግፋት አልቻለም:: ኀሩይ በውቅቱ የኢሕአፓ አባል ስለነበረ “ትምህርት ከድል በኋላ” በሚለው የኢሕአፓ ታጋዮች መርህ መሰረት ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ቀድሞ የሕይወት መስመር ውስጥ ገባ:: መፅሔት፣ የጸሎት መጽሃፍ እና ጋዜጣ አዟሪነትን መተዳደርያውን አደረገ::
የመፅሀፍ ንግዱ አዲስ መስመር ውስጥ ከተተው:: ከተላቁ ደራሲ ስብሃት ገብረእግዛብሄር ጋር አስተዋወቀው:: ከደራሲ ስብሃት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሰረቱ:: መፅሀፍ ነጋዴ የነበረው ኅሩይ ሚናስ ደራሲ ሆነ:: ወይ አዲስ አበባ የሚለውን መፅሀፉን አውግቸው ተረፈ በሚል የብዕር ሥም በየካቲት መፅሔት ላይ ወጥቶ ለንባብ በቃ:: የትውልድ ሥሙን ትቶ ለምን በብዕር ሥም እንዳደረገ ሲጠየቅ “መጽሃፍ አዟሪ ስለነበርሁ ሰዎች ይተርቡኛል (በአራዳዎች አነጋገር ይፎግሩኛል) ብዬ ነው” ሲል ለሸገር ሬዲዮ መናገሩ የሚታወስ ነው::
“ወይ አዲስ አበባ” የተሰኘውን ድርሰት ካሳተመ በኋላ “አነወተቴ” እና ”እያስመዘገብኩ ነው” የሚሉትን ሁለት ድርሰቶች እንዲያትሙለት አታሚ ድርጅቶችን ቢጠይቃቸው ሁለቱም በዘመኑ የነበረውን የሳንሱርን ሕግ ማለፍ ባለመቻላቸው የሕትመት ብርሃን ተነፈጉ:: በዚህም አውግቸው ተበሳጨ:: የአዕምሮ እክል የገጠመውም በዚህ መነሻነት ነው:: ደጋግሞ መጻፍ እንደሌለበትም ራሱን አሳመነ:: ሙሉ ትኩረቱን መፅሀፍ ንግድ እና ንባብ ላይ አደረገ::
ደራሲ ስብሃትን ተዋውቆ ስለነበረ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፈ መፅሀፍትን እያሳደደ ማንበቡን ተያያዘው:: ከዓመት በኋላ ሌላ የዕድል ብርሃን ወደ አውግቾ ተረፈ መጣች:: ከታላቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ዳኛቸው ወርቁ ጋር ተገናኙ:: ደራሲ እና ጋዜጠኛ ዳኛቸው ወርቁ በወቅቱ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የቦርድ አባል ነበሩ:: የአውግቸውን የሥነ ፅሐፍ እውቀት የተረዱት ዳኛቸው ወርቁ አውግቸውን ኩራዝ ማተሚያ ድርጅት በመጽሀፍ አርታኢነት አስቀጠሩት:: በርካታ የድርሰት ሥራዎችንም የአርትኦት ሥራ ሠራ:: በዚህ ድርጅት ውስጥ ሆኖም “የአንገት ጌጡ” እና ሌሎች የትርጉም ሥራዎችን ሰርቶ ለሕትመት አበቃ::
ደራሲው ከሃያ በላይ ድርሰት እና የትርጉም ሥራዎችን ሰርቷል:: ባይተዋር፣ ንፁህ ፍቅር፣ ደመኛው ሙሽራ፣ አንድ ሺ አንድ ተረቶች፣ የቀልዶች ማዕበል፣ ጣፋጭ የግሪም ተረቶች፣ ጩቤው፣ የፕሮፋሰሩ ልጆች፣ የትውልዱ እልቂት፣ የአማልዕክትና የጀግኖች ታሪክ፣ ስለሽና ስምንተኛው ሽህ፣ የግሪን ተረቶች፣ የሕንድ ተረቶች፣ ቤቱ፣ የፍቅር ትንሳኤ፣ አስደናቂ የዓለም ምርጥ ተረቶች ከአውግቸው ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው:: መከራና ችግርን ተጋፍጦ ይኼንን ሁለ ሥራ መሥራት የሚደንቅ ነው:: ከአውግቸው ወጪ ማን ሊያደርገው ይችላል ? ሲል ፀሀፊ- ጌታ በለጠ ደበበ አድናቆቱን አኑሯል::
‹‹አውግቸው ተረፈን (ኅሩይ ሚናስ) የማውቀው ከ1970ዎቹ ጀምሮ ነው። ቦታው መርካቶ በጎ አድራጎት ካሠራው የገበያ አዳራሽ በስተምሥራቅ ከሚገኙት የባንያኖችና የዓረብ ሱቆች በስተጀርባ ነው። ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ ዱባይ ተራ በሚባለው ቀጭን የእግር መንገድ ከበስተደቡብ ጫፍ ላይ አሮጌ መጻሕፍት ሲሸጥ አውቀዋለሁ።›› ሲል ደራሲ እና ጋዜጠኛ ተሾመ ብርሃኑ ሃሳቡን ይጀምርና ይቀጥላል::
ያኔ የኅሩይ መጻሕፍት ብዙ አልነበሩም። ኅሩይ መጻሕፍቱን የሚያስቀምጣቸው በአንዲት አነስተኛና ቀጠን ያለች ቁም ሳጥን ውስጥ ነበር። ምን ጊዜም የማገኘው ሲያነብ ነበር:: የምፈልገውን መጽሐፍ የሚሸጥልኝ በኪሴ ባለው ትንሽ ገንዘብ ነው። ሲል አውግቸው ተረፈ ለደንበኞቻቸው ያለውን ስሱ ልብ ያወሳል::
እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስም መጽሐፍት አንባቢ ሁሉ የሚሄደው እነ ኅሩይ ወደሚገኙበት (ዱባይ ተራ) የተሰጣ ሜዳ ወይም መወጣጫ ደረጃዎች ላይ ይደረደር በነበረ መሸጫ ሥፍራ ነው።
ቢቢሲ አማርኛ አውግቸው ተረፈን በተመለከተ በሠራው ሰፊ ዘገባም የሚከተሉትን ሃሳቦች አስፍሯል:: በአጫጭር ልብወለድ፣ በትርጉም፣ እንዲሁም በአርታኢነት የሚታወቀው ኅሩይ ሚናስ ውልደቱ አዲስ አበባ አይደለም። ከጎጃም ደጀን ነው፤ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አይነ ሥውራንን ይመራ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ራሱን ለማኖር በረንዳ ላይ አድሯል። ቀስ በቀስ የፀሎት መጻህፍትን ወደ መሸጥ ከዚያም በሂደት የትምህርትና የልብ ወለድ መጻህፍትን ሸጧል።
አውግቸው መርካቶ አሮጌ መጽሐፍትን ከመሸጥ ተነስቶ፣ ከ20 በላይ መጽሐፍት በድርሰት እና በትርጉም ለአንባቢዎች አበርክቷል። ከ’ወይ አዲስ አበባ’ ውጪ በዓለም ላይ የታወቁ ደራሲዎችን ሥራዎች በመተርጎምም ይታወቃል ኅሩይ ሚናስ። ‘የአንገት ጌጡ’ በዓለም ላይ የሚታወቁ ደራሲዎች ሥራ ስብስብ ነው ሲሆን ‘ምስኪኗ ከበርቴ’ን በመተርጎምም ዝናን ማትረፉን ብዙዎች ይናገራሉ።
አውግቸው በ70ዎቹ ውስጥ አእምሮው ታውኮ ነበር። አውግቸው ስለ ሕመሙ ሲናገር ለበርካታ ጊዜያት በር ዘግቶ መፅሐፍ ስለሚያነብ፣ ስለሚቆዝም እንዲሁም ያለማቋረጥ ይቅም ስለነበር መታመሙን የእነዚህ ነገሮች ሁሉ ድርብርብ ውጤት ይሆናል የሚልም ግምት አለ::
አውግቸው አእምሮው በታወከበት ወቅት የሆነች ሴቴ መንፈስ ታዝዘው እንደነበር ይናገራል። ያቺ መንፈስ ማሪያም ነኝ ትለኛለች። ጩቤ ይዘህ ዙር ራስህን ተከላከል እንደምትለው ይናገር ነበር።
ይህንንና በወቅቱ ያለፈበትን በማስታወሻው ላይ አስፍሮ ካቆየ በኋላ ነበር ያሳተመው። ይህ ሥራው የኅሩይ የግል ሕይወት ገጠመኝ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መርካቶ መሳለሚያ ይኖር የነበረው አውግቸው ኮንዶሚኒየም ደርሶት ቃሊቲ ገላን ኮንዶሚኒየም ይኖር ጀመረ።
የፕሮፌሰሩ ልጆች የሚል ቤሳ ልብወለድ፣ አረቢያን ናይት ሦስተኛውን ክፍል እንዲሁም እብዱን አሻሽሎ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ነበር።
ከቤቱ መራቅ ከጤንነትም ሁኔታ ጋር በተያያዘ ብዙ መንቀሳቀስ እና ከሰዎች ጋር መገናኘት ያዳግተው እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ይናገራሉ::
በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሄደው 4ተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓ/ም በአቤሌ ሲኒማ ተከናውኗል:: በዕለቱ ደራሲ አውግቸው ተረፈ በሥነ ፅሁፍ ዘርፍ ለሀገርና ሕዝብ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ በኪነ ጥበብ (ድርሰት) ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆኖ ሽልማቱን ከደራሲ አያልነህ ሙላቱ እጅ ተቀብሏል::
ደራሲ አውግቸው ተረፈ የትዳር እና የቤተሰብ ሁኔታ በተመለከተ በ1969 ዓ/ም ጎጃም ቤተሰብ ጥየቃ እንደሄደ ቤተሰቦቹ የመጀመሪያው የሆነችውን ሚስቱን ዳሩት:: ትዳራቸው ዓመት ብቻ ነበር የዘለቀው:: በኋላ በ1987 ዓ/ም ሁለተኛ ሚስቱን አገባ:: ልጆችንም ወለደ:: አውግቸው የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ቤት ደርሶት ቃሊቲ ገላን ኮንዶሚኒየም ሲኖር ቆይቶ ሞት የሰው ሌጅ ሁለ የማይቀር ዕዳ በመሆኑ ያ ታላቅ የኪነ ጥበብ ሰው ሰኔ 10/2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስቶ ለአበርክቷቸው ክብር በሚሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን ዓምድ ደራሲ አውግቸው ተረፈ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሁፍ ዕድገት ላከናወነው ስኬታማ ጉዞ ምስጋናውን መግለጽ ይወዳል። ሰላም!
ይህንን ጽሁፍ ስናጠናክር ተሾመ ብርሃኑ ለሪፖርተር ጋዜጣ የጻፉትን ጽሁፍ ፤ቢቢሲ አማርኛ፤ እና በለጠ አበበ ስለደራሲው ያሰፈሩትን ጽሁፍ በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል ::
በእስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም