የተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የህውሀት ስራ አስፈፃሚ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ስለ ብልፅግና ፓርቲ ውህደት፣ ሂደት እና የውህደቱ እንከኖች እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ስርአት ስኬትና ጉድለት በስፋት እንደገለፁልን ሁሉ በአንፃሩ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ ማብራሪያ ሰጥተውናል። ማብራሪያውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዘመን፡- ከለውጡ በፊት ኢሕአዴግ በመራው የፌዴራል መንግሥት ውስጥ የሥርዓቱ አተገባበር ችግሮች አንደነበሩበት ይነሣል። እነዚህ ችግሮችና መንሥዔዎቻው ምን ምን ነበሩ?
አቶ አወሉ፡- በመጀመሪያ ብልፅግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ነገሮችን ሲያስብ ከዚህ በፊት የነበሩንን ጠንካራ ጎኖች እንዲስፋፉ፣ እንዲጎለብቱ፤ ወደፊትም ሊቀጥሉ የሚገቡ ነገሮችን እንዲታቀፉ ነው። መታረም ያለባቸው በውስንነት የሚታዩ ነገሮች ካሉ ደግሞ በአግባቡ ይታረሙ የሚል አቋም አለው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቀጣዩን የአገራችን፣ የዜጎቻችንን እድል በአግባቡ የሚያይበት አሠራር አለው።
የፌዴራል ስርአቱን በአገራችን ወደ ሃያ ስምንት ዓመታት ገደማ በዚህ አገር ላይ ቆይቷል። ነገር ግን ስርአቱ በአግባቡ ማከናወን ያሉበትን ነገሮች አከናውኗል ወይ? ምንስ ችግሮች ነበሩት? ብለን በአጠቃላይ ማንሣት እንችላለን። ይህን ስንል ሙሉ በሙሉ ባዶ ነበር የሚል ግምገማ የለንም። የተሰሩ ለውጦች አሉ። በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማህበራዊው ዘርፍ በርካታ የታዩ ለውጦች አሉ። በዛው ልክ ደግሞ ውስንነቶች አሉ። ውስንነቶቹ ደግሞ ወሳኝ የሆኑ ውስንነቶች ናቸው ብለን ነው የምናምነው። ይሄ ደግሞ ማንም ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ ገምግሞ እነዚህ ችግሮቼ ናቸው ብሎ በራሱ ጊዜ ወጥቶ ህዝብ ጭምር ይቅርታ ጠይቆበታል። ኢህአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ተሀድሶ አደርጋለሁ ብሎ መጀመሪያ የ1994ቱ ተሀድሶ አለ፣ ዳግም ተሀድሶ አለ፣ጥልቅ ተሀድሶ አለ። በተለያዩ ጊዜያት ተሀድሶዎች ሲካሄዱ ነበር። ነገር ግን ከተሀድሶ ማግስት ወደ ተግባር የሚለወጡ ነገሮች ስላልነበሩ በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች፣ የህዝብ አመፆች የነበሩበት ሁኔታ ነበር።
ከዚህ በመነሳት ኢህአዴግ ተገዶ ወደ ሪፎርም የገባበት ሁኔታ ነበር። ወጥቶ ይቅርታ ጠይቆ አስተካክላለሁ ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለለውጡ ሲሉ መልቀቂያ ጠይቀዋል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ዝምብለው የመጡ ነገሮች አይደሉም። ዋና መነሻቸው መሰረታዊ የሆነው ቀደም ሲል ሲተገበሩ የነበሩ የፌዴራሊዝም ስርአት ውስንነቶች በጣም እየጎሉ የመጡበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ነው። ይህ አንዱ ሲሆን ሁለተኛው ከፌዴራሊዝም ጋር ስናይ ለምሳሌ የማንነት ጉዳይን መውሰድ እንችላለን። ኢህአዴግ በጣም ሲጨፍር ሲያቅራራ የነበረው የማንነት ጉዳይን መልሻለሁ፣ እንዲህ አድርጊያለሁ ይል ነበር። በእውን የማንነት ጉዳይ በአግባቡ ተመልሷል ወይ? ከተመለሰ ዛሬ ይቺ አገር በቋፍ ላይ ያለችው ለምንድን ነው? ለምሳሌ የሲዳማ ህዝብ ሲቀጠቀጥም፣ ሲገደለም፣ ሲፈናቀልም የነበረው በማንነቱ ጉዳይ ነው። የማንነት ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ነበር። አልተመለሰም። ሀረሪ ተመልሷል፣ የሲዳማ ለምንድን ነው ያልተመለሰው? ሲታፈን ነበር። ጥያቄውን ሲያነሱ የነበሩ ኃይሎች ሲገደሉ፣ ሲጨፈጨፉ ነበር። ይሄ ብቻ አይደለም። በአገራችን ሰው በማንነት ምክንያት መንቀሳቀስ ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ሱማሌ ውስጥ ያ ሁሉ ኦሮሞ ሲጨፈጨፍ፣ ሲገደል፣ እንደከሰል በትራክተር ሲጫን፣ ምን ስላደረገ ነው ? ወንጀል ስለፈፀመ ነው? ያውም ከአገራቸው፣ ያውም ከመሬታቸው፣ ከእርሻቸው፣ ከበጎቻቸው፣ ከፍየሎቻቸው ያሁሉ ምን ስላደረጉ ነው የተፈናቀሉት? እናም የፌዴራል ስርአቱ በአግባቡ የማንነት ችግርን ስለፈታ ነው? ህዝቦች በጋራ የመኖር፣ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንፃር ስራ ስለሰራ ነው? አይደለም። ከጉሙዝ የተፈናቀለው ኦሮሞ ምን ስለሆነ ነው? ከኦሮሚያ የተፈናቀለው ጌዲዮ ምን ስለሆነ ነው? ጉሙዞች የተፈናቀሉት ምን ስለሆኑ ነው? ለምን? ምንድን ነው ችግሩ? እነዚህ መሰረታዊ የሆኑ የፌዴራሊዝም አተገባበር ስርአቱ ውስንነቶች ናቸው። ውሸት ነው አልተመለሰም። እነዚህ ተመልስው ቢሆን ኖሮ እርግጠኛ ነኝ አሁን በማንነትህ ደረትህን ነፍተህ አገሪቱን ከጫፍ እስከጫፍ አትሄድም አንተ ራስህ እንደጋዜጠኛ። እውነት እንነጋገር ከተባለ። እኔም አልሄድም። ለምን? በአግባቡ ያልተሰሩ እንደውም የተቀበሩ ፈንጂዎች ናቸው። ስለዚህ በማንነት ጉዳይ አልተሰራም። እነዚህ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።
የድንበር ጉዳይንም እንውሰድ ኦሮሞና ሱማሌ 1 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ይዋሰናሉ። ይህንንም ጉዳይ ራሱ በሚፈልገው አካሄድ እንዲሆን ሌሎችን ያላሳተፈ የድንበር አከላለል ስርአት ነበር። አማራና ትግራይ መካከል ያውም በአንድ ግንባር ስም የሚሰሩ ብሄራዊ ድርጅቶች ለአንድ አላማ የሚታገሉ፣ ለአንድ ጭቁን ህዝቦች የሚታገሉ ሁለቱ ድርጅቶች እስከ ጦር መማዘዝ የደረሱት ለምንድን ነው?
ዘመን ፡- ይህንን ያደረገው የኢህአዴግ መንግስት አይደለም?
አቶ አወሉ ፡- እና ማን ነው ያደረገው? እና የማን መንግስት ነው ያደረገው ?
ዘመን ፡- ኢህአዴግ በአራት ብሄራዊ ድርጅቶች የተዋቀረና አጋር ከሚላቸው ፓርቲዎች ጋር በመሆን የሚሰራ ግንባር ነበር። ግንባሩን ካዋቀሩት ድርጅቶች ውስጥ የተለየ ስልጣን የነበረው አካል ነበር?
አቶ አወሉ፡- እሱን እመለስበታለሁ። ነገር ግን እንደ ኢህአዴግ የነበረው ዋና ዋና መሰረታዊ ችግሮች በርካታ ነበሩ። ህዝባችን እኮ የዋህ ሩህሩህ በመሆኑ ይቅርታ አድርጎልን አሁንም ሪፎርሙን ቀጥሉ ብሎ እድል ሰጠን። ይህን የዋህ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም እናመሰግናለን። እውነት ለመናገር እድል ሰጠን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ምን ያላደረግነው ነገር አለ? በድንበር ጉዳይ እንደሌሎች ባላንጣ ሁለት አገሮች ትግራይና አማራ ሲማዘዙ፣ ሚሊሻ፣ ልዩ ኃይል ወደ ድንበር ሲያሰለጥኑ ህዝቡ ውሀ የሚጠጣበት የለውም። ትምህርት ቤት መቀመጫ የለውም። ጤና ኬላና ሆስፒታሎች መርፌና ኪኒን የላቸውም። ነገር ግን ለጦር ሰራዊት፣ ለመሳሪያ መግዣ፣ ለቦምብ፣ ለፈንጂ በተለያዩ ቦታዎች ለሚሰሩ የውንብድና ስራዎች የሚውሉ ስንት ነገሮች አሉ። ከድንበር ጋር በተያያዘም መሰረታዊ ችግር አለ። ሁለተኛ ከቋንቋ ጋር እንውሰድ። በቋንቋ ይቺ ሀገር በጣም ሀብታም ነች። የባህል፣ የቋንቋ ሀብታም ሀገር ነች። የትም ሀገር የሌለ ባህል፣ ቋንቋ፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ መቻቻል ያለባት ሀገር ነች። ኢህአዴግ ገብቶበት አበላሸው እንጂ። ችግራችን በአግባቡ ሳንናገር በመቅረት ተናግረንም መፍታት ባለመቻል እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ገባን እንጂ።
ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ስድስት የስራ ቋንቋ አላት። ናይጄሪያ አርባ ምናምን አላት። ካናዳ ሁለት የስራ ቋንቋ አላት። ኢትዮጵያስ? ለምንድን ነው? ኦሮሚያን በምሳሌ ብንወስድ ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ለዓመታት ትግል ሲደረግበት የነበረ ጉዳይ ነው። ብዝሀነት ይላል። ብዝኃነት በተግባር ካልተተገበረ ምን ያደርጋል። ስለዚህም ውሸት ነው። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ናቸው። የኢኮኖሚውም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ብትወስድም እንደዛው ነው። የማይዋሸው ነገር ኢኮኖሚው አድጓል። ሰው ተኮር ሆኖ እያንዳንዱ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ የሀብት ክፍፍል አለ? የሚለውን አብረን እያየነው ነው። ኢኮኖሚው በፍጥነት አድጓል፣ መንገዶች ተሰርተዋል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ተገንብተዋል። የተማረ ስራ አጥነትን በዛው ልክ አስፍነናል። ፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ስርአት እንዲኖር ግን አልተደረገም። አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል። ከተሜነት ተስፋፍቷል። ከተሜነት ሲስፋፋ ደግሞ የእኛ አርሶ አድር በዛው ልክ በቂ ካሳ ሳይከፈለው ተፈናቅሏል። ተመልሶ በአግባቡ እንዲቋቋም ሳይደረግ ተፈናቅሏል። ዘበኛ ሆኖ ቀርቷል። ሌላው ደግሞ ደብዛው ጠፍቷል። አዲስ አበባ ዙሪያን መውሰድ ይቻላል። ኢንቨስትምንት፣ ኢንቨስተሮች አሉ። ይህ አይካድም ትክክል ነው። ነገር ግን ከኢንቨስትመንቱ ማን ነው የተጠቀመው? የሚለውን ነው ማየት። ህዝቡ ጋር የደረሰ ነገር አለ ወይ? ህዝቡን ኩርፊያ ያመጣው ይሄ ነው። ሌላ ነገር አይደለም። መሰረታዊ ችግር ማለት ፍትሀዊ ሀብት ክፍፍል ነው። ለምሳሌ ኢንፖርት ኤክስፖርት ላይ ስንት ሰው ነው ያለው? የማን ነው ያለው? ይሄ ሁሉ አዲስ አበባ ውስጥ የተሰራው ህንፃ የማን ነው? በአጠቃላይ እንቁጠር ቢባል የሀገር ሀብት ነው። ህንፃውም፣ መንገዱም ተሰርቷል። ነገር ግን የማን ነው?
ዘመን ፡- የማን ነው ?
አቶ አወሉ ፡- የማን መሆኑን ሄዶ መቁጠር ይቻላል። ለማንኛውም ደሃው ህዝብ አልተጠቀመም። በአጭሩ ደሀውን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የኢኮኖሚ ስርአት አይደለም። ይሄ አንደኛው መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄ ነበር። ደሀውን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል አልነበረም። ዋናው አሁን የአገሪቱ ፀጥታ ቸግር የስራ አጥነት ችግር ነው። ኢኮኖሚው አደገ ከዚያስ ምንድን ነው? ለምሳሌ አሜሪካ በአንድ በመቶ ኢኮኖሚ ሲያድግ ስንት በመቶ የስራ አጥ ቁጥር ይቀንሳል። የኢኮኖሚ እድገትና ስራ አጥነት መቀነስ ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። እርስ በርስ ይመጣጠናሉ። ወደ እኛ ስትመጣ ኢኮኖሚው በአስር በመቶ አደገ ይባልና የስራ እድል የለም፣ ትክክለኛ የገበያ እና የኢኮኖሚ ስርጭት የለም። እነዚህ መሰረታዊ የሆኑ ተግዳሮቶች ናቸው። ሙስናም በዛው ልክ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም። የተወሰኑትን ሰምታችኋል። ለአገር ደህንነት ሲባል ዝም ያልናቸው መአት ነገሮች አሉ። መብራት ሀይል አካባቢ፣ ግድቡ አካባቢ፣ ኢንፖርት ኤክስፖርት፣ ባንኮች፣ ሜቴክ፤ ስንቱ ይነሳል! ይህ ብቻ አይደለም። የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ደግሞ በዛው ልክ ናቸው። ብልፅግና ፓርቲ ‹ያጠፋ ሰው አይታሰር› የሚል አቋም የለውም። ግዴታ መታሰር አለበት። ያጠፋ ሰው አሁንም እየታሰረ ነው። አሜሪካኖች ያስራሉ፣ ስዊዲን እና ኖርዌ እንደውም አሰቃቂ እስር ቤቶች አሉ። አንድ ቀን እዛ ስታድር እንደ ሶስት ቀን ይቆጠርልሀል። ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለምን ይካሄዳሉ? ቶርቸር ለምን ይፈፀማል? አካል ማጉደል፣ ጥፍር መንቀል፣ ብልት ላይ ሌላ ነገር ማንጠልጠል፣ ከዱር እንስሳት /ከአውሬዎች/ ጋር ማሰር፣ ለምን ተደረገ? በጭራሽ ሰዋዊ የሆነ ተግባር አይደለም። ፌዴራሊዝም እንዲህ አድርጉ ይላል? ስለዚህ እነዚህ ዋና ዋና የሆኑ የፌዴራሊዝሙ መሠረታዊ ችግሮች ነባሩ:: ስለባለፈው ፌዴራሊዝም አሁን ሕዝቡ ያለው ሥዕል እንደዚህ ነው። ኢህአዴግ ችግሮቼ ናቸው ብሎ ገምግሟል።
ዘመን፤ የጠቀሷቸው ችግሮች ምንጭ ሕወሓት እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። እነዚህ ተግባራት ለበርካታ ዓመታት ሲከናወኑ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ምን ያደርጉ ነበር?
አቶ አዎሉ፣ እኛ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ሕወሓት ብቻ መውሰድ አለበት የሚል ግምገማ የለንም። መውሰድም የለበትም። ግን የአንበሳው ድርሻ የሕወሓት ነው። ምክንያቱም የሆኑ ችግሮችን ስታነሳ፤ ሌላ ሌላ ታርጋ እየተለጠፈልህ ከኦሮሚያ ከሆንህ ኦነግ ትባላለህ፤ ከአማራ ከሆንህ ደግሞ ሌላ ትባላለህ፤ ሌላ ከሆንህ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ ትባላለህ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሆነ ታርጋ ይለጥፉልህና ደብዛህን ያጠፉሃል ። በዚያን ሰዓት አምርረው ሲታገሉ ከነበሩ እስከ መሰደድ የደረሱ ኃይሎች ነበሩ። አሁንም የገቡበት የጠፉ ኃይሎች አሉ። ኢህአዴግም ወስጥ ሆነው በኦህዴድ፣ በብአዴን ወይም በደኢህዴን ዝም የተባለበት ጊዜ አልነበረም። ነገር ግን ችግሩ የነበረው የውስጥ ትግል ብቻውን ፍሬ አያመጣም። ከውጭ ካንተ ጎን ሊሰለፍ የሚችል ሕዝብ መኖር አለበት። አሁን ምንድን ነው የተሠራው መጨረሻ ላይ በተለይ አማራ እና ኦሮሞ ላይ የተገነባውን ግንብ አፍርሶ ወደ ድልድይ ተቀይሮ ሕዝቡ መገናኘት ሲጀምር፤ አንድነት መፍጠር ሲጀምር፣ ታጋይ የሕዝብ ልጆች በሚዲያዎች የራሳቸውን ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ሲመጡ፣ ነገሮች በራሳቸው መውጫ ቀዳዳ እያሳጡ ሲመጡ መጨረሻ ወደዚህ መጣ እንጂ በወቅቱ የውስጥ ትግል ነበረ።
ስለዚህ ሕወሓት ሲባል፤ ሕወሓት ብቻውን አድርጓል አይደለም። ተላላኪዎችም አሉ፤ ተንበርካኪዎችም አሉ። ከኦህዴድም አለ፤ ከብአዴንም አለ፤ ከሁሉም ቦታ አለ። እነዚህ ኃይሎች ያው በተለያየ ምክንያት ዝምታን የመረጡም አሉ። በዝምታ የሚተባበሩም አሉ። በመሸሽም የተባበሩ አሉ። በዚያን ሰዓት የሕዝባችን ንቃተ ሕሊና በዚህ ደረጃ ጎልቶ አልመጣም። ሕዝቡን በማሳተፍ መታገል ላይ ውሱንነቶች ነበሩ። ይሄ ነው ችግሩ የነበረው እንጂ፤ ችግሩ ሕወሓት ብቻ የፈጠረው አይደለም። ይሄ ሁሉ የመሬት ወረራ ሲዘረፍ ሕወሓት ፈርሞ አይደለም። ብትፈልጉ እኮ አንድ ሰውም አታገኙም። ግን አስፈርመዋል። ግን ይሄ ሁሉ ባንክ ሲዘረፍ እኮ ሕወሓት ፈርሞ አይደለም። ግን አስፈርሟል።
ዘመን፣ በዚህ ሂደት ለበርካታ ዓመታት የሞግዚት አስተዳደር በኢትዮጵያ ነግሦ ነበር ማለት ይቻላል?
አቶ አዎሉ፣ አዎ፤ በትክክል የሞግዚት አስተዳደር በኢትዮጵያ ነግሶ ነበር። ማን ክልል ነው ራሱን ችሎ ሲያስተዳድር የነበረው? እንዴ ድጋፍ ያድርጉ ተብለው በየክልሎቹ ነበሩ። ኦሮሚያ ላይ እነ ጢሞቴዎስ ሁሉ ነበሩ። ደቡብ ላይም እንደዚያ ነበረ፤ አማራም ላይ ነበር፤ ትግራይ ላይ ብቻ ነው ራሱን ሲያስተዳደር የነበረው። አፋር፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል እነዚህ እንዳውም በኮሎኔል ነበር ሲተዳደሩ የነበሩት። ኮሎኔሎቹ ናቸው ሲዘርፉም፤ ሲሾሙም ሲሽሩም የነበሩት። ስለዚህ ይሄ የሞግዚት አስተዳደር ካልተባለ ምንድን ነው የሚባለው?
ዘመን፣ አሁንም የብልፅግና ፓርቲ በተመሳሳይ መልኩ ወደ ክልሎች የሚልካቸው ተወካዮች አሉ ይባላል እኮ!
አቶ አዎሉ፤ ውሸት። ለምን ሲባል?
ዘመን፣ እንደከዚህ ቀደሙ አራት አራት ሰዎች ወደ ክልሎች አይላኩም?
አቶ አወሉ፣ ውሸት፤ የለም። ለምን ይልካል? ዐቅም ያለው ይሄንን ሀገር ማስተዳደር የሚችል ሰው ከእነዚያ ክልሎች ውስጥ አለ። ሀገር እንኳ ማስተዳደር የሚችል። በጣም ጠንካራ ሰዎች አሉ። ዐቅም ያላቸው ሰዎች አሉ። ብስለቱ ያላቸው ሰዎች አሉ። ተገለው ነው፤ ተገፍተው ነው። የተሳሉት ኢትዮጵያዊነት እንኳ እንዳይሰማቸው ተደርገው ነው። አጋር ተብለው ነበር፤ ስለዚህ አጋር አንድ ቀን ይሄዳል ወይም ይመለሳል፤ ራሱ አይወስንም። በሀገር ጉዳይ ላይ አይወያይም። ምንም አያደርግም። ስለዚህ ይሄ ሁሉ እኮ ነው ውሱንነት የምንለው።
ዘመን፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ተጠቅሞ ሕወሃት የተሻለ የኢኮኖሚ የበላይነት ወስዷል ማለት ይቻላል?
አቶ አወሉ፣ ሕወሓትን እንደ ድርጅት የምንለው አይደለም። እንደ ሕወሓት ሳይሆን ሕወሓትንም ጥላ ያደረጉ ሌቦች አሉ። ኢህአዴግ በሙሉ
ደግሞ ሌባ አይደለም። ኢህአዴግን ጥላ ያደረጉ ሌቦች አሉ። ከባለ ሀብቱም፣ ነጋዴውም ከተለያዩ ማኅበረሰቦች አሉ። ሕወሓት ውስጥም
ንፁህ ታጋዮች አሉ፤ ንፁህ ታጋዮች። ለሀገር አንድነት፣ ለልማት፣ ለለውጥ የሚታገሉ በርካታ ኃይሎች አሉ። በዚያው ልክ ደግሞ ሌሎች
በኢህአዴግ ስምም የተሰገሰጉ አሉ።
ዘመን፣ ሕወሓት ያቋቋማቸው ድርጅቶች ግን በቢልዮን ካፒታል እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ ሕወሓት የኢኮኖሚ የበላይነት ይዟል ማለት አይቻልም?
አቶ አወሉ፣ አሉ በጣም ፈርጣማ። እኔ እንደ ሕወሓት የሚል አቋም ግን የለኝም። እሱን አውጣው። ለምን ድርጅቱ ሲቋቋም ዛሬም ነገም ለወደፊቱም ሕዝባዊ ዓላማ አንግቦ የተነሣ ድርጅት ነው። ነገር ግን ያንን ጥላ ከለላ አድርጎ፣ ውስጥ ገብቶ ለሌላ ዕኩይ ዓላማ የሚያውሉ ኃይሎች አሉ። አሁንም እያልን ያለነው በዚያ ስም የሚነግዱ አሉ ነው። ለምሳሌ የኢፈርት ድርጅቶች አሉ። እርግጠኛ ነኝ በሀገሪቷም ትላልቆቹ ቢሊየነር ኩባንያዎች እነሱ ናቸው። ከየት አመጡት? ወደ 80 ምናምን የሚጠጉ አሉ። ኦሮሚያ 5 ነው። እዚያ ላይ ትግራይ ላይ 80 ቢሊየነር ሲቋቋም ኦሮሚያ መሐል ሀገር ሆኖ እያለ ለምንድን ነው ቢሊየነር ያልሆነው? አማራም በጣም ትንሽ ነው 12 ነው፤ ቁጥሩን በትክክል አላውቀም ግን በጣም ትንሽ ነው።
ዘመን፣ በትግል ዘመን ያገኘነው ሀብት ነው የሚሉት?
አቶ አወሉ፣ በትግል ዘመን ከየት ነው የተገኘው? ከየት መጣ? በትግል ዘመን ሰው እንኳን የሚበላው የሚገባበትም የለም፤ ውሸት ነው። የተዘረፈ ነው። ከተለያዩ ባንክ ጭምር ተበድረው ያልከፈሉት ብዙ ቢሊዮን ብር አለ። እናወጣለን። መረጃዎች አሉን።
ዘመን፣ ውሕደቱ የተፈጸመው የኢህአዴግን ፕሮግራም እና ዓላማ በማይቀበል ኃይል ነው የሚል ክስም ይሰማል። ይሄን እንዴት ያዩታል?
አቶ አወሉ፣ ሲጀመር ውህደት የፈፀመው ራሱ ኢህአዴግ ነው። ውህደቱን የፈፀሙት ፕሮግራሙን እና ዓላማውን በአግባቡ የሚቀበሉ ኢህአዴግን ሕልውናውን እንዳያከስም ሌጋሲውንም ጭምር እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው። እንደዚህ ያለ ክስ የሚያቀርቡት ሰዎች ደግሞ ክህደት የፈፀሙ ከሃዲዎች ናቸው። ለምን! አንደኛ በኢህአዴግ 5ኛ ብሔራዊ ጉባዔ፣ 6ኛ፣ 7ኛ፣ 6ኛ ጉባዔ ስለ ውህደት ሲነሳ ነበር። በትላልቅ ኃላፊዎች፤ አንጋፋ መሪዎቻችን ጭምር ሳይቀር። ነፍሳቸውን ይማራቸውና ጠ/ሚኒስትር መለስም እኮ ውህደትን አያስፈልግም አይደለም ያሉት። ትንሽ መሥራት ያለብን ነገሮች አሉ እንሥራ እና ወደ ውህደቱ እንምጣ ነው። እነ ሥዩም መስፍንም ተመሳሳይ ሲያነሱ ነው የነበሩት። እስከ መቼ ነው በዚህ የምንቀጥለው? ለምንድን ነው ግንባርነት የተፈለገው? ለምን ውህደት አንፈጥርም? ስለዚህ በ9ኛው ጥያቄው እየገፋ መጣ። 10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔም መቀሌ ላይ ነው የተደረገው። በተመሳሳይ ጥናቱ ቶሎ እንዲካሄድ እና ምክረ ሐሳብ እንዲቀርብ ተባለ። በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ሃዋሳ ላይ ሲካሄድ ደግሞ በአስቸኳይ ጥናቱ ተካሂዶ ውህደቱ እንዲፈፀም የሚል አቅጣጫ ነው የተቀመጠው። ሁሉም እጁን አውጥቶ ነው አጀንዳውን፣ አቅጣጫውን ተቀብሎ የወጣው።
ዘመን፣ ጥናቶች ነበራችሁ በአጀንዳዎቹ ላይ?
አቶ አወሉ፣ በአብዛኛው እንዳውም ከለውጡ አመራር በፊት የተኬዱባቸው ነበሩ።
ዘመን፣ ጥናቶቹን ገምግመው እንዲመጡ ለእያንዳንዱ ድርጅት ዕድሎች በበቂ ተሰጥተው ነበር?
አቶ አወሉ፣ አዎ።
ዘመን፣ የገመገሙት ግምገማ በሥርዓት ተሰምቷል?
አቶ አወሉ፣ አዎ! አካሄዱ እንዴት ነው መሰለህ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ሃዋሳ ላይ ይሄንን ሲወስን በዘርፉ ልምዱ፣ ዕውቀቱ ያላቸው ምሁራኖች ጥናቱን እንዲያካሂዱ ነው፤ ያውም ገለልተኛ ምሁራኖች። ምሁራኖቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሁሉም በተለይ የፖለቲካ ዲፓርትመት አካባቢ ልምድ ያላቸው ሰዎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮም ተጨምሮበት እንዲሰራ ተደረገ። ከዚያ የጥናት ምክረ ሀሳቡ ቀረበ፤ ጥናቱ አልቆ ወደ ስምንት- ዘጠኝ ወር አካባቢ ከተጠና በኋላ የጥናቱ ውጤት መጣ። የጥናቱ ውጤት ያቀረባቸው የምክር ሀሳቦች አንዱ ውህደቱን በአስቸኳይ መፈጸም ነው። ጥናቱ ተመጣጣኝ የናሙና አካባቢ ተወስዶ ትግራይ ላይ ተካሂዷል፤ኦሮሚያ ላይ ተካሄዷል፤አጋር ድርጅቶችም ጋር ተካሂዷል። ሁሉም ክልሎች ላይ ናሙና ተወስዶ ማንኛውም ሳይንሳዊ ጥናት የሚወስደውን ጥናት በማድረግ ተካሂዷል። ከዚያ በኋላ ሊቃነመናብርቱ ተወያዩበት። ምክትሎቹ ተወያዩበት። ሁሉም ባሉበት በስራ አስፈጻሚው ወረደ በየደረጃው እንዲታይ አስተላለፉት። ከዚያ ወደራሳቸው ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲወስዱ ተደረገ፤ ወሰዱ። ኢህአዴግ ወደ ግንባር ልምጣ የሚል ውሳኔ ይወስዳል እንጂ እነዚህ ግንባር ውስጥ ያሉ ብሔራዊ ድርጅቶች የራሳቸው ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች ናቸው። ህጋዊ ሰውነታቸውን ግን ሄደው ማክሰም ያለባቸው በራሳቸው ጉባኤ ነው። ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ምክር ቤት ቀረበ ተቀባይነት አገኘ። ውህደቱን አስራ አንደኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት ውህደቱን አጸደቀ። ውህደቱ ከጸደቀ በኋላ እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት ወደራሱ ክልል ሄዶ እራሱን ማክሰምና ውህደቱን ለመቀላቀል መወሰን አለበት። ሌሎች ስምንት ብሔራዊ ድርጅቶች አጋሮችን ጨምሮ ወደራሳቸው ክልል ሄደው ከራሳቸው አባላት ጋር ተነጋገሩ፤አስቸኳይ ጉባኤ ጠሩ። መጥራት የሚቻለው መደበኛ ጉባኤና አስቸኳይ ጉባኤ ነው። አስቸኳይ ጉባኤ ተጠራ፣አጀንዳ ቀረበ፣ተወያዩ፣ አምነው አጸደቁ። ወደ ውህደቱም ለመቀላቀል ወሰኑ። ይሄ ነው።
ዘመን- የህወሃት ሰዎች የሚያነሷቸው አንደኛ ጥድፊያ ነበር። ጉባኤ አጠራሩም፣ አካሄዱም ቢሆን ስርዓት ያለው አልነበረም። ጉባኤ የሚጠራበት አካሄድ አለ፤የጎደሉ አባላት እንኳን ይኑሩ አይኑሩ ሳይጣራ የተካሄደ ነው፤ እነዚያ ሁሉ ባልተሟሉበት ሁኔታ ነው የሚል አለ?
አቶ አወሉ- እንግዲህ መክሰስ የፈለገ ኃይል ብዙ ስንክሳር ይሰበስባል። እውነታው ግን እሱ አይደለም። ጉባኤ ጋ ለመድረስ ስምንት ደረጃዎች ተኬዷል። ጥናቱ ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ጥናት ነው። በገለልተኛ ምሑራን ለዚያውም በጋራ የተወሰነ፤ ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርትና የአጋር ድርጅቶች አምስት አምስት ስራ አስፈጻሚ አባላት የተሳተፉበት በጋራ የወሰኑት ነው። እሱ አለቀ። ሊቃነ መናብርት ለብቻ ተወያዩ፣ምክትል ሊቃነ መናብርት ባሉበት ተወያዩ። ስራ አስፈጻሚ ከአንድም ሁለቴ ተወያየ። ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሁለቴ ተወረደ ። ከዚያ በኋላ ጉባኤ ተጠራ። ይሄ ሁሉ ሰንት ወር መሰለህ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር። አባልና ድርጅት ለማወያየት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር በጣም ተጣድፏል ከተባለ መነጋገር ይቻላል። የተዘጋጀ ጥናት ነው፤በጥናቱ ውጤት ላይ ነው። በምሁራን የቀረበ ነው። ሊቃነ መናብርቱ ወስነዋል። ኢህአዴግ ምክር ቤት ወስኗል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስኗል። የተወሰነው በጋራ ነው፣ የተወሰነው በዴሞክራሲያዊ መንገድ በአብላጫ ድምጽ ነው። የሚፈልግ ተቃውሟል፤የሚፈልግ ደግፏል። ከዚያ በኋላ ወደ ብሔራዊ ድርጅት ውሰዱ ተባለ፤ወሰዱ። እነሱ ዋና አላማቸው ጊዜ ማብዛት፣ጊዜ እየገዙ ሌላ የማጭበርበር ተንኮል ለመስራት ነው እንጂ ስድስት ወር እስከ ዘጠኝ ወር በላይ ተወስዶ በቂ ጊዜ ተሰጥቶ የተሰራ ነው፤ ጥድፊያ አይደለም።
ሁለተኛ የጎደሉ አባላት የሚለው ጉባኤ ለመጥራት ሃምሳ ሲደመር አንድ አባል ከተገኘ በቂ ነው። ለምሳሌ እኔ ያለሁበት ኦዴፓ ጉባኤ አንድ ሺህ ስልሳ ስድስት ሰው አለ። የተገኘው ዘጠኝ መቶ ሃያ ስድስት ሰው ነው። ይሄ ሰው ጎድሏል ከተባለ መነጋገር ይቻላል። የፈረሙት አለ፤ቃለ ጉባኤ አለ። የተጠራው ስርዓቱ የሚፈቅደው አስቸኳይ ጉባኤ ነው። አስቸኳይ ጉባኤ ማለት ከመደበኛ ጉባኤ መሃል ላይ የሚጠራ ነው። ያንን ለመጥራት ደግሞ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ጥያቄ መቅረብ አለበት ይላል። ማዕከላዊ ኮሚቴያችን ደግሞ ተሰብስቦ በሁለት ሦስተኛው ድምጽ አይደለም በሙሉ ድምጽ አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ ይሄ አጀንዳ ይቅረብ ተብሎ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እሱም በፊርማ ጥያቄውን አቀረበ። ጥሪ ተደረገ፤ ወደ ዘጠኝ መቶ ሃያ ስድስት ሰው ተገኘ። የተገኙ አባላት መጀመሪያ የተካሄደውን እርቀትና አስፈላጊነት ላይ ውይይት አደረጉ፤ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ጉባኤ ተካሄደ፤ ጉባኤው ደግሞ በሙሉ ድምጽ ያለአንድ ድምጽ ልዩነት ተወስኗል። ሌሎችም እንደዚያ ይመስለኛል፤ ባለኝ መረጃ። ስለዚህ የጎደለ አባል የለም። ተገዶ ተገፍቶ ማን ነው ሥራ የሚሠራው ይሄ ውሸት ስለሆነ በዚህ ሌላ የሌለ የፖለቲካ ድምጽ ሸመታ ካልሆነ በስተቀር ይሄ ወንዝ የማያሻግር ምክንያት ነው።
ዘመን- የህወሃት ስራ አስፈጻሚ አቶ አስመላሽን ስናነጋግር እነዚህ በተለይ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ያደረገው ነባራዊ ሁኔታ ሳይቀየር አሁን መዋሃድ ተገቢ አይደለም ብለዋል። የተለያዩ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ያደረገው ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሮ ነው የተዋሃዱት?
አቶ አወሉ- 27 ዓመት፣ሩብ ምዕት ዓመት እውነት ስራ ሠርተህ ቢሆን ኖሮ፣ ሩብ ምዕት ዓመት አገር መርተህ መጀመሪያ ስትነሳ ይዘህ የነበረው የብሔር ጥያቄ ካልመለስክ፤ ወይ ውሸትህን ነው፣ ወይም እራሱ ውሸት ነው። አንድ ችግር እሱ ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ ጽንፈኝነት ጫፍ ላይ ወጥቷል። ጽንፈኝነት፤ ጽንፈኝነት። በአካባቢያዊ ጉዳይ ላይ በጣም ተጠምደን በአገራዊ ጉዳይና በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ኢትጵያዊነት ላይ በጣም ችግር ተፈጥሯል። አገር ሊኖረን ይገባል። ያለችን አገር አንድ ናት። እንደዚህ እየገፉ በጽንፈኝነት ላይ ጫፍ ለጫፍ እያቆሙ አገርን ለማፍረስ የታለመ ነው። አገርን ያፈረሰው ሌላ አይደለም እኮ እራሱ ኢህአዴግ ነው፤ አሁንም ወደፊት እርግጠኛ ነኝ ስጋቴ እቺን አገር እንዳያፈርስ ነው፤እውነት እንነጋገር ከተባለ። ስለዚህ ነባራዊ ሁኔታ ማለት የኦሮሞ ሕዝብ እኮ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ የማይደራደር በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ሕዝብ ነው እንጂ ኢትዮጵያዊነቱን የሚጠላ ሕዝብ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ እኮ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚደራደር ሕዝብ አይደለም፡፤ የሌለ አጀንዳ ይዞ እዛ ውስጥ ውለው ለማደር ይፈልጋሉ፤ ማጦዝ ይፈልጋሉ። የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ይደራደራል? አይደራደርም። አሁን ውህደቱ እነዚህን ነባር የሆኑ ሕዝቦች ጥያቄ ይደፈጥጣል ወይ? ይጨፈልቃል ወይ ነው? በጣም ትርጉም ባለው መልኩ አንደኛ እራስን በራስ የማስተዳደር ከዚህ በፊት በሞግዚትነት፣በጀነራል፣በኮረኔል ሆነን የምናስተዳድረውን እጃችንን አውጥተን በትክክልኛ መንገድ ክልሎች እራሳቸውን እንዲያስዳድሩ የሚደረግበት ስርዓት ነው። ሁለተኛ ብዝሃ ቋንቋ ነው። ሌሎች ተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋዎች የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ እየታገለ ነው። ለምሳሌ በድርጅት ቢያንስ አምስት ቋንቋ እንዲሆኑ ተደርጓል። አማርኛ፣ኦሮምኛ፣ትግርኛ፣አፋርኛ እና ሶማሊኛ አለ። ብዝሃ ቋንቋ ነው። ስለዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚባሉት በመሰረቱ ስህተቶች ነበሩ። እውነት እንነጋገር ከተባለ በአግባቡ እነዚያን ጥያቄዎች ለሩብ ምዕተ ዓመት ሰርቶ ያልተመለሰ ታዲያ መቼ ነው የሚመለሰው? ሩብ ምዕት ዓመት ተሰጥቶህ ያልመለስከውን በአግባቡ ተደራሽ ያላደረከውን ነገር መቼ ነው የምትመልሰው? ስለዚህ አሁን ያለው ውህደት በትክክል እነዚያን ነባራዊ ሁኔታዎች መመለስ የሚችል ውህደት ነው ብለን እናምናለን። በትክክል ፕሮግራማችን ውስጥ አስቀምጠናል። መሰረታዊ የሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ የሚያስችል መሰረታዊ የሆኑ የብዝሃነት ጥያቄዎችን፣አጀንዳዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚችል ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ ነው እንጂ በዚያ አካሄድ ይሄው 27 ዓመት ሄደናል እኮ! በኢኮኖሚም የወሰድክ እንደሆነ የእኛ ኢኮኖሚ ማለት በትክክል 49% የዓለም ዕዳ ነው፤ አሁን ይሄ የባቡር ሃዲድ በእኛ እድሜ ዕዳ የማይከፈልበት ፕሮጀክት ነው። ለዚያውም ውስጡን ለቄስ ነው።
ዘመን- በውህደቱ ፕሮግራሙ እንዲቀየርስ ታስቦ ነበር ?
አቶ አወሉ- አንተ ሪፎርም ስትሰራ ፕሮግራም ለውጥ አታደርግም ? ጥናቱ እራሱ ፕሮግራም ለውጥ እንድታደርግ አይደለም እንዴ?
ዘመን- ጥናት ተጠንቶ ውህደት በምን መልኩ እንደሚካሄድ ጥናቱ እንዲቀርብ እንጂ ፕሮግራም እንድንቀይር ውክልና ለምክር ቤት አልሰጠንም ነው የሚሉት።
አቶ አወሉ – አንተ ውህደት ስትፈጥር ዝም ብለህ አየር ላይ ትፈጥራለህ እንዴ! ውህደት ስትፈጥር መሰረታዊ የሆኑ ነጥቦችን ይዘህ ውህደቱ ደግሞ ግንባሩ በምን አይነት ፕሮግራም ይመራል። እዚህ አገር እኮ የፖለቲካ፣ የሴኩሪቲ፣ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ ሪፎርም አለ። ጥናቱ ይዞ የመጣቸው ነገሮች አንዱ ይሄንን ነው። ውህደት ፈጽመህ ፕሮግራሙን እንዳለ ታስቀጥላለህ? ሲጀመር ፕሮግራሙ መጠነኛ ለውጦች ለምሳሌ ኢኮኖሚ ላይ በፊት ግብርና መር ኢንዱስትሪ ነው የሚለው አሁን ግን ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ነው፡፤ ለምን ግብርናም ጭምር 27 ዓመት ጮኸን ጮኸን ያመጣነው ምንድነው? አሁን ስንዴ አይደለም ዳቦ ከውጭ እያመጣን ነው። 27 ዓመት ግብርና መር ግብርና፣ ግብርና እያልን አንዴ ውሃ ማቆር፣አንዴ ውጤት ተኮር ምናምን እያልን፤ ግን አሁን ከዳቦ ሰልፍ አልወጣንም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በተለይ በውስንነት የታዩ ነገሮችን ሪፎርሙ ጥናቱ ለራሱ ይዞ የመጣቸው ነገሮች አሉ። እንጂ መደመር እኮ ሙሉ በሙሉ ያንን ደፍጥጦ ዜሮ አድርጎ አይደለም የመጣው። ከዚያ ወደዚህ መሻገር መጎልበት ያለባቸውን ነገሮች ይዞ መጥቷል። አሁንም ደግሞ መታረም ያለባቸው ነገሮች እየታረሙ ይሄዳሉ።
ዘመን፤ ውሕዱ ፓርቲ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምን እንዴት ይመለከተዋል? እስከመገንጠል መብት መስጠትንስ አንዴት ያየዋል?
አቶ አወሉ፤ ብልፅግና ፓርቲ በህብረ ብሔራዊነት ላይ ያለው አቋም ግልጽ ነው። ሲጀመር እነዚህ ነገሮች መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። የብልፅግና ፓርቲ እሴቶች የምንላቸው ነገሮች አሉ። አንዱ ኅብረ ብሔራዊነት ነው። ኅብረ ብሔራዊነት እኮ በኢሕአዴግ ዘመን የውሸት ፉከራና ዘፈን ነበር። በትክክል ምላሽ ያገኘ ጉዳይ አልነበረም። አሁን ግን በእውነት እና በእውቀት የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ምላሽ እንስጥ፤ ራስን በራስ የማስተዳዳር ጉዳይ ምላሽ እንስጥ፤ የማንነት ጉዳይ ምላሽ እንስጥ እያልን ነው። የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን አቋቁመናል። የኢሕአዴግ አንዳንድ ድርጅቶች እኮ ለምን ይሄ ተቋቋመ ብለው የሚቃወሙ ጀግኖች ናቸው! ስለዚህ ይሄንን ያለምንም ማቅማማት፣ ማንጠባጠብ በአግባቡ መሬት አውርዶ ሊሠራ የሚችል ትክክለኛ ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ ነው። ሁለተኛ መገንጠልን ልታደርግም ላታደርግም ትችላላህ። በማድረግ ባላማድረግ የምታስቀረው ነገር አይደለም። ዋናው ነገር ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ከቻልክ አንቀጽ 39 ምንም ማለት አይደለም። ስለጻፍክም ዝምብለህ መገንጠልን አትፈቅድም፤ ስላልጻፍክም መገንጠል ይቀራል ብሎ ማሰብ አይቻለም። ለምሳሌ የሱዳን ሕገመንግሥት ራስን በራስ ማስተዳዳር እስከመገንጠል የሚል ነገር የለውም። ያ መሆኑ ደቡብ ሱዳንን ከመገንጠል አላዳናትም። ካናዳ ኩቤክ እንደዚህ ዓይነት አንቀጽ የላትም ነገር ግን እነዚህ ኩቤክ የሚባሉት በራሳቸው ጊዜ ሦስት ጊዜ ድምጸ ውሳኔ አድርገዋል። በሕዝበ ውሳኔ ሦሰት ጊዜ 49 በመቶ ደርሰዋል። ግን ሕገመንግሥታቸው ላይ አልነበረም። ነገር ግን ያንን ለማድረግ ሞክረዋል። አንቀጽ 39 ስለመገንጠል ያለው ቃል መቀመጡ አለማስቀመጡ አይደለም። አንቀጹ ለብሔር ብሔረሰቦች ዋስትና ሆኖ የተቀመጠ ነው። ነገር ግን አንድ መሆን፣ ገበያ መሆን፣ ጉልበት መሆን ከቻልን ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ከቻልን አንቀጹ ትርጉም የለውም። አንድ ቀን ሕዝቡ ራሱ አንሡልን ይላል። አንቀጹ ደግሞ ባይኖር እንኳን ከአንድነትም መገንጠል ተሽሎ ከተገኘ አትከለክለውም።
ዘመን፡- ብልፅግና ፓርቲ ከህወሃት ጋር ያለው መሠረታዊ ልዩነት ምንድነው?
አቶ አወሉ፤ እኛ በግልጽ በመድረክ የተወያየንበት የልዩነት ሐሳብ የለንም። መጨረሻም ላይ ስንነጋገር የጊዜው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ነበራቸው። ነገር ግን ከበቂ ጊዜ በላይ ተሰጥቷል። አሁን ወደ ምርጫ እየሄድን ነው። ኢሕአዴግ አሁን ባለበት ሁኔታ ከዚህ በላይ መሄድ አይችልም። ሕወሃትና ብአዴን እዚህ አራት ኪሎ መጥተው አንድ ነገር ያወራሉ፤ በጋራ ይወስናሉ፤ አንዱ መቀሌ ሔዶ አንዱ ባህርዳር ሔዶ ደግሞ ሌላ የአቋም መግለጫ ነው የሚያወጡት። ስለዚህ ጠንካራ የሆነ ማዕከላዊ ፓርቲ አልነበረንም። እንደዚህ ከቀጠለ ሀገር ማስተዳደር ቀርቶ ለራሱም መኖር አይችልም። ራስን ማጥፋት ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ጠንካራ ማእከላዊ ፓርቲ መፍጠር ግዴታ እንደሆነ ተስማምተንበታል። እንደፈለጉ መፈንጭት የሚፈልጉ አንዳንዶች ማዕከላዊ ፓርቲውን መመሥረት የማይፈልጉ አሉ። እዚያ ውስጥ ተደብቆ ደግሞ ሌሎች ነገሮችም ሊመጡ ስለሚችሉ ይሄን የማይፈልጉ አሉ። ዞሮ፣ ዞሮ እኛ ‹ጉዳዩ የጊዜ ጉዳይ ከሆነ እናንተ ሲመቻችሁ በጨረሳችሁ ጊዜ ኑ!› አልን። ሌላው ደግሞ በጊዜው ጨርሶ መጥቶ ወደ ውህደቱ ተቀላቀለ። እኛ እስከ አሁን ድረስ ያለን ሐሳብ የሚጨርሱትን ጨርሰው መጥተው ይቀላቀላሉ የሚል ነው። አንዳንዶች የግለሰብ አቋሞቻቸውን ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። የግለሰብና የድርጅት አቋም ግን የተለያዩ ናቸው።
ዘመን፤ የሕወሃት መሪዎች ግን ተክደናል እያሉ ነው። አጋሮችም ይሁኑ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ውስጥ ሕወሃት የተለየ ተጽእኖ እንደነበረው የሚሰነዝሩት ትችት ሁሉ የታሪክ ክህደት ነው የሚል ሐሳብ አላቸው፤…
አቶ አወሉ፤ ክህደት የሚባል ነገር እኔ አላውቅም። በፓርቲው ውስጥም የለም። ይሄንን በመድረክ ላይ አምጥተው ያወሩት ነገር የለም። በዚህ፣ በዚህ ተካክደናል ብለው በመረጃ በማስረጃ ያወሩት ነገር የለም። ብልፅግና ፓርቲም ሆነ የለውጥ ኃይሉ እያወራ ያለው በኢሕአዴግም ሆነ በመጋቢቱ የ17 ቀናት ግምገማ ሲነገሩ የነበሩ ከሰማይ በታች፣ ከምድር በላይ የነበሩት ነገሮችን ሁሉ በይፋ ለሕዝብ ወጥተን ተናግረን ሕዝቡን ደግሞ አሁን ይዘን ማሻገር አለብን ብለው የተስማሙትን ነው ያወሩት። እኔ እስከገባኝ ድረስ። እነሱ መድረክ ውስጥ ሌላ ያወራሉ፤ ወጥተው ሌላ ያወራሉ። መቀሌ ሄደው ሌላ ያወራሉ፤ ባህርዳር ሄደው ሌላ ያወራሉ። ይሄ የለመደባቸው ነገር ቸገራቸው እንጂ፤ ምንም ክህደት የሚባል ነገር የለም። አንዳንድ የግምባሩ አባልት የሚያወሩት እርግጠኛ ነኝ የግላቸውን ነው እንጂ የፓርቲ አይደለም። በፓርቲ ደረጃማ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ነው። እንደውም እኮ በውስጥ የተወራው ነገር 20 በመቶ እንኳን ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም። ስለዚህ ክህደት ተፈጽሟል ሲባል አንዳንዴ ቆመህ ማየት ያለብህ ራስህን ነው። ስለዚህ በድርጅት ደረጃ ስለክህደት የተወራ ነገር የለም፤ የግላቸውን ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን እንኳን ራሳቸውን ነው መፈተሸ ያለባቸው። እነሱ ምን ስላደረጉ ነው ሌሎቹ ግንባር ፈጥረው ይካዷቸው። ምን ስላደረጉ ነው? ራስን መፈተሽ ነው።
ዘመን፤ በውሕደቱ ጥናት የሕወሃት ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?
አቶ አወሉ፤ የአንበሳው ድርሻ የእነሱ ነበር። ምክር ቤት አብረን ወስነናል። አጀንዳ አብሮ ነው የተያዘው። አዋሳ ላይ አጀንዳው ሲወሰን እኩል ደምጽ ነው። አንዳች በልዩነት ይያዝ የተባለ ነገር የለም። ከዚያም ናሙና ከሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች እኩል እኩል ነው የተወሰደው። ምክረ ሐሳቡንም በጋራ እኩል ነው ቁጭ ብለን ያየነው። ብቸኛ የእነሱ ጉዳይ የነበረው የጊዜ ጉዳይ ነው። ይህ የማንዋሸው ነው። በእውነትና በእውነት ነው ይቺን ሀገር ማሻገር የምንፈልገው። የጊዜ ጉዳይም ከበቂ በላይ ተሰጥቷል። ‹ተጨማሪ እንፈልጋለን ካላችሁ ሄዳችሁ ራሳቸሁ በራሳችሁ ጊዜ ተወያዩ፤ ስትወስኑ ኑ› ፤ እኛ የምናውቀው አስከዚህ ድረስ ነው።
ዘመን፤ በመጨረሻ ማስተላልፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ
አቶ አወሉ፤ በመጀመሪያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ለደጋፊዎቻችን ለአባሎቻችን እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልእክት አለኝ። ብልፅግና ፓርቲ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የሚሆን ራእይ ሰንቆ፣ በቁርጥ ቀን ታጋዮች ተመርቶ የወደፊት ጉዞውን ቀጥሏል። ዕውቅናም አግኝቷል።
ሀገራችንን በኢኮኖሚ በፖለቲካ በማኅበራዊና በውጪ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻግር የሚችል ፖሊሲ ስትራቴጂ በሀገር በቀል አስተሳሰብ እና ሌሎችም ተራማጅ የሆኑ አመለካከቶች እንዲሁም ከማንኛውም ዓለም ጥሩ ጥሩ ነገሮችን እየወሰደ ሊሠራ ተዘጋጅቷል። ሁሉም ዜጎች ሀገራችንን የእኛም ናት ብለው ሊኖሩባት ሊታገሉባት ወደው ፈቅደው በጋራ ሊኖሩባት የሚችሉባት አንዲት ኢትዮጵያን የብሔር ብሔረሰቦችን የማንነት መብት፣ የቋንቋ እኩልነት የተከበረባት ሀገር ሆና በጋራ ለመራመድ በጋራ እየተሠራ ነው ያለው። ከዚህ ቅዱስ ዓላማና ራዕይ ጎን በመሰለፍ ከግቡ እንድታደርሱ በዚሁ አጋጣሚ እኔም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
ዘመን፤ እናመሰግናለን
አቶ አወሉ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
ሳሙኤል ይትባረክ እና ማለደ ዋስይሁን