የዐይነ ስውሩ ወጣት ቅሬታ እና የሚመለከተው አካል ምላሽ

ከቅሬታ አቅራቢው አንደበት

መፍትሔ ፍለጋ በመንገድ ላይ በመንከራተት ላይ እያለሁ ከአንድ መንገደኛ ጋር ስለችግሬ አወጋሁ ይላል ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ተቋማችን የመጣው የዛሬው የፍረዱኝ ዓምዳችን ቅሬታ አቅራቢ ዐይነ ስውሩ በዳሶ መሐመድ። ከምስራቁ የሀገራችን ክፍል ሐረር ወደ አዲስ አበባ የመጣው በ2009 ዓ.ም ነው። መጀመሪያ መቀመጫውን ያደረገው ቡራዩ ነው። ቡራዩ እየኖረ ሳለ እንደአጋጣሚ ይወድቅና አደጋ ይደርስበታል። መውደቁ ያደረሰበት አደጋ ደግሞ ሽንቱን መሽናት እስከመከልከል ያደረሰው ነበር።

በዳሶ፣ ይማርበት የነበረው ትምህርት ቤት፤ ጉዳቱን በማጤኑ ድጋፍ እንዲደረግለት ለጳውሎስ ሆስፒታል ይጽፍለታል። በሆስፒታሉም ሕክምናውን ተከታትሎ በመጨረሱ ከሆስፒታል በወጣበት ጊዜ የሚረዳው ሰው ስላልነበር ወደዬት እንደሚሔድ ግራ ይጋባል። ማንም የሚያግዘኝ ሰው ባለመኖሩ በረንዳ ላይ መኖር ጀመርኩ ያለን ባለጉዳያችን፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ወረዳ ዘጠኝ በመሄድ ሕክምና ሲከታተል መውጣቱንና የአካል ጉዳተኛና የሚረዳው ዘመድ ባለመኖሩ መጠለል የሚችልበት ሥፍራ እንዲተባበሩት መጠየቁን ይናገራል።

ወረዳ ዘጠኝ ጉዳዩን አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ ያገኝ ዘንድ ለአራዳ ክፍለ ከተማ መጠየቂያ መጻፉን ያስረዳል። ክፍለ ከተማውም የወጣቱን በዳሶ ችግር አስተውሎ መታገዝ እንዳለበት ስላመነ፤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስለላከው ቢሮውም የዐይነ ስውሩ በዳሶን ጉዳይ አጢኖ ሊረዳ የሚገባው እንደሆነም ተገንዝቦ በቢሮው ስር ወደሚተዳደረው የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል እንዲገባ ማድረጉን ይጠቅሳል።

በማዕከሉ አንድ ዓመት ያህል ከተቀመጠ በኋላ እንዳባረሩት ያስረዳል። እርሱ እንደሚለው የተባረረበትን ምክንያት አያውቅም፤ ያባረሩበትን ምክንያት ሲናገሩ ‹‹ቅጥር ግቢውን ትረብሻለህ›› በሚል ነው ይላል። ይሁንና በዳሶ ረብሻ እንዳልፈጠረ ያስረዳል። እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድ ቀን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አምሽቼ ወደግቢው መጣሁ፤ በዕለቱም ጥበቃዎች አላስገባ አሉኝ፤ የመሸብኝ ምክንያት አውቶቡስ ለረዥም ሰዓት ጠብቄ በማጣቴ ነው፤ የዛሬን በይቅርታ አስገቡኝ ብዬ ይቅርታ ጠይቄ ገብቻለሁ ይላል። ይሁንና የጥበቃ ሰራተኞች ካስገቡኝ በኋላ አምሽቼ መምጣቴን ለቢሮ በማሳወቃቸው ከምጠለልበት ማዕከል አስወጡኝ ሲል ቅሬታውን ይናገራል። በወቅቱም “ካጠፋሁ ይቅርታ” ቢላቸውም በጀ ሊሉ ስላልወደዱ ግቢውን ለቅቆ መውጣቱን ያስረዳል።

እርሱን ካስወጡት በኋላ ማስወጣታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈው ለከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ላኩ። ጉዳዩ ወደ ቢሮ መድረሱን በመስማቱም ወደዚያው አቅንቶ ጉዳዩ በትክክል ወደሚመለከታቸው ኃላፊ በመቅረብ የተፈጠረውንና ያለበትን ችግር ለማስረዳት ሞከረ፤ በወቅቱም ኃላፊዋ፣ ‹‹ሁለተኛ ወደ እኔ ቢሮ እንዳትመጣ›› ብላ አባረረችኝ ሲል ይናገራል። እኔ የተባረርኩበትን ምክንያት ዘርዝሬ ሳልነግራትና ምክንያቱን ሳትረዳኝ ‹‹ሒድ›› አለችኝ ይላል።

ይህ በመሆኑ ቀጥታ ያመራው የቢሮው አማካሪ ዘንድ ነው። እዚያም ገብቶ “እኔ በአሁኑ ጊዜ በረንዳ እያደርኩ ነው፤ ችግሬንና ምክንያቴን ሊረዳኝ የፈለገ ሰው የለም። ከዚህ ቀደም ያጠፋሁት ነገር የለም። እንደዚያ ሆኖ ቢሆን ኖሮ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንኳ ይደርሰኝ ነበር፤ የሰጡኝ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያም ሆነ አጥፍተሃል ብለው ያስፈረሙኝ ፊርማ የለም፤ ይህን አጥፍተሃል ብለውም የሰጡኝ ምንም አይነት ወረቀት የለም። እሱ ባልሆነበት በአንድ ቀን ስሕተት ከግቢው ተባርሬ አሁን ከጎዳና ላይ ወድቄያለሁ። ” ሲል አቤቱታውን በመግለጹ፤ አማካሪው፣ ማዕከሉን ወደሚመሩት ሥራ አስኪያጅ ደውለው ስላለው ሁኔታ ካነጋገሯቸው በኋላ ‹‹ሒድና ግባ›› ስላሉት በቀጥታ ወደማዕከሉ መግባት መቻሉን ያስረዳል።

አቤቱታ አቅራቢው በዳሶ፣ ወደማዕከሉ ተመልሶ እየኖረ ሳለ፤ የማዕከሉ ኃላፊዎች በማዕከሉ ለምትኖር የአዕምሮ ታማሚ ለእርሷ የተሻለ ሕክምና የሚሆናትን ቦታ በማፈላለግ ላይ ነበሩና አንድ ተቋም ተገኘ በመባሉ ወደዚያ እንድትሔድ ተወሰነ፤ ይሁንና እርሱንም፤ “አንተም ሒድና አዕምሮህን መመርመር አለብህ” ይሉታል። እርሱም የአዕምሮ ሕመም እንደሌለበት ነግሯቸው ካስፈላጋቸውም በአንድ ቀን ተመርምሮ ውጤት ይዞላቸው መምጣት እንደሚችልም ያስረዳቸዋል። ይህን ሐሳቡንና አለመታመሙን ቢነግራቸውም “ሒድና ታይ፤ ምንም ችግር ከሌለብህ ተመልሰህ ወደዚሁ ትመጣለህ፤ በዚያውም ለዐይንህ ሕክምናም ታገኛለህ፤ ከዚያ ትመጣለህ” እንዳሉት ይናገራል።

በመሆኑም የአዕምሮ ሕመም አለባት ከተባለችው ግለሰብ ጋር ተገኘ ወደተባለው ተቋም ይወስዱትና በተቋሙ አማካኝነት የአዕምሮ ምርመራ በግል የሕክምና ማዕከል ከተደረገለት በኋላ ተቋሙ የአዕምሮ ሕመም የለብህም። ስለዚህ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንመልስሃለን ብለው ለቢሮው ደውለው ‹‹ልጅቷ የአዕምሮ ችግር ስላለባት በእኛ ተቋም መቆየት ትችላለች፤ እርሱ ግን የአዕምሮ ችግር የሌለበትና ዐይነ ስውር ስለሆነ እዚህ መቆየት አይችልምና ውሰዱት›› እንዳሉ ይገልጻል። ይህ ተቋም ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ እና ማገገሚያ ማዕከል ነው።

ይሁንና ውሰዱት ቢባሉም ትንሽ ይቀመጥ በማለታቸው አንድ ወር ያህል በጌርጌሴኖን ተቀመጠ። ነገር ግን ጌርጌሴኖን መልሶ ቢሮውን በደብዳቤ እንዲወስዱት ጠየቀ። ይሁን እንጂ ‹‹ወደፈለገበት መሔድ ይችላል፤ ዘመድም አለው›› መባሉን ጌርጌሴኖን፣ ለበዳሶ ይነግረዋል። ስለዚህ ‹‹ዘመድ ካለ ወደዘመዶችህ መሔድ ትችላለህ›› አለው። ‹‹አሊያም ወደመጣህበት ማዕከል ሒድ›› ብለው እንዳስወጡት ያስረዳል።

ከጌርጌሴኖን ከወጣ በኋላም ወደነበረበት ማዕከል ለመመለስ ስልክ ቢደውልም “አንዴ ከማዕከሉ የወጣ ሰው ተመልሶ ወደማዕከሉ መግባት አይችልም” የሚል ምላሽ ተሰጠው። እርሱ ግን “ቀድሞውንም የላካችሁኝ ለሕክምና በሚል ሰበብ እንጂ በእራሴ ፍላጎት አይደለም” ብሎ ተከራከራቸው። ይሁንና ‹‹ሕጉ አይፈቅድልህም›› አሉት።

ይህ በመሆኑ ወደ ቢሮው ሔዶ በጠየቀበት ጊዜ የቅሬታ ደብዳቤ እንዲያስገባ ተነገረው። እንደተባለው አደረገ። በመሆኑም በማዕከሉ የሚገኘው ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይቶ የደረሰበት የውሳኔ ሐሳብ ግቢውንም በግቢ ውስጥ ያሉ ተገልጋዮችን እንደሚረብሽ ተነገረው። ስለዚህም ‹‹ጥፋተኛ ነው” መባሉ ተነገረው። ከዚያም ባለፈ ሌላ በፍጹም እኔ ያልፈጸምኩትን ነገር ፈጽመሃል ተባልኩ። ይህንን ደግሞ እውነታውን ፈጣሪ ያውጣልኝ እንጂ እኔ አቅም የለኝም። ይህ የሚዲያ ተቋም እኔን ሊተባበረኝና ሐቁ እንዲወጣልኝ ከፈለገና የእኔን ጉዳይ እንደጉዳይ ይዞ ከተንቀሳቀሰ እስከ ማዕከሉ ድረስ ሔዶ እውነቱን እንዲያወጣልኝም እሻለሁ ሲል ቅሬታውን በቃል አቅርቧል።

ስለዚህ ቢሮው፣ ጥፋተኛ የተባልከው ይህንንና ያኛውን ጥፋት ስለፈጸምክ ነው ከማዕከሉ አናስገባም ያለው ብሎ ኮሚቴው የደረሰበትን አሳወቀኝ፤ ስለዚህ በረንዳ ላይ ከምታድርና ቀደም ሲል በደረሰብህ ጉዳት ቀዶ ሕክምና ያደረገህ በመሆንህ ጥፋተኛ ነኝ፤ ይቅርታ አድርጉልኝ ብለህ ወደማዕከሉ ግባ፤ እንዳሉት ያመለክታል። ይሁንና እኔ ጥፋት ባለማጥፋቴ ይቅርታ የሚያስጠይቀኝ ነገር የለም ቢልም ቢሮው ያንን ብታደርግ ለአንተ መልካም ነው በማለታቸው ይቅርታ መጠየቁን ያስረዳል።

ቀጥሎም ቢሮው ደብዳቤ ወደ ማዕከሉ ይልካል፤ማዕከሉ ግን ኮሚቴው ውሳኔ በማሳለፉ አንቀበልም ይለዋል። በዳሶ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለሁት በረንዳ ላይ ነው ይላል፤ ከምንም በላይ ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመምጣቴ ምክንያት እውነቱ ይወጣልኝ ዘንድ ነው ሲል ያስገነዝባል። እስከ ዛሬ ድረስ ከምንም በላይ አዕምሮዬን እየከነከነኝ ያለው ነገር በረንዳ ላይ መጣሌም ሳይሆን በፍጹም ያላደረግኩትን ነገር አድርጓል በመባሌ ነው የሚለው በዳሶ፣ ጉዳት አድርሶብኛል የሚለውን አካል በግንባር ቀርባችሁ እንድታነጋግሩልኝ እፈልጋለሁ ሲል ይማጸናል። በተጨማሪ ችግር የፈጠረብኝ ቢሮው ሳይሆን ማዕከሉ እንደሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል ይላል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምላሽ

ጉዳዩን ያጤነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የየምርመራ ዘገባ ቡድን፤ ስለ ወጣቱ በዳሶ ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣውን አነጋግሯቸዋል።

ወይዘሮ ገነት እንደተናገሩት፤ በዳሶ ማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ውስጥ ከሚኖሩ ተገልጋዮች መካከል አንዱ ነበር፤ በማዕከሉም ከ182 በላይ ተገልጋዮች ይገኛሉ። ከእነዚህ ተገልጋዮች መካከል አንዱ የሆነው በዳሶ፣ ተደጋጋሚ ችግሮችን በተገልጋዮች ላይ ሲያደርስ ቆይቷል። የሌሎችን ተገልጋዮች መብት ይጋፋል። በግቢው ውስጥ ያሉ ተማሪዎች እንዳያጠኑ ይረብሻል። ቤተ መጻሕፍ ውስጥ ገብቶ ይጮሃል። የቤተ መጻሕፍ ሰራተኞችንም ይረብሻል። ሞግዚቶችን የምግብ ቤት ሰራተኞችን ያስቸግራል። እነዚህን ችግሮቹን ብዙ ጊዜ በምክር ለማለፍ ሞክረናል።

በዳሶ፣ ግቢው ውስጥ በሚጮኽበት ጊዜ በእራሱ አንደበት “እኔ የአዕምሮ በሽተኛ ነኝ” ሲል መደመጡን ኃላፊዋ ይናገራሉ። በማዕከሉ ያሉ የተለያየ አይነት የማኅበራዊ ችግር ያላባቸው ናቸው፤ በተጨማሪም በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በዳሶ በመረበሹ የተደረገው ነገር ቢኖር ወደ ጌርጌሴኖን መሔድ እንዲችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ወደጌርጌሴኖን እንዲሄድም ያደረገው በማዕከሉ ያለው የጤና ባለሙያ ነው። ጌርጌሴኖንም በዳሶን ተቀበለው። ይሁንና በዳሶ፣ ጌርጌሴኖን ከደረሰ በኋላ የአዕምሮ በሸተኛ አይደለሁም ሲል ተናገረ። ከዚያ ወጥቶ ጎዳና ላይ ሲወድቅ ዐይነ ስውር ነውና ወደማዕከሉ መለሱት። በማዕከሉ የተወሰነ ከተቀመጠ በኋላ ሴቶችን መተናኮል ጀመረ፤ ከሴቶችም በዊልቸር የሚጠቀሙ ወጣቶች ሴቶችን እራሳቸውን እንኳ በአግባቡ ከጥቃት መከላከል የማይችሉትን ወደ መተናኮል ሔደ ይላሉ።

ይህ በመሆኑ ሌሎቹን ማዳን ስለሚያስፈልግ ከተቋሙ መውጣት አለበት ወደሚለው ውሳኔ መደረሱን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ በማዕከሉ መብት እንዳለ ሁሉ ግዴታም መኖሩን ያስታውሳሉ።

ተገልጋዩ ግዴታውን ሳያውቅ ቀርቶ በተደጋጋሚ ግዴታውን ጥሷል። በመሆኑም የመጨረሻው ውሳኔ ከተቋሙ እንዲወጣ ማድረግ ነበርና እሱ ተግባራዊ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደዚያ አይነት ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ “እስኪ እንደገና እንየው” በሚል የቢሮ ኃላፊዋ ተጨማሪ እድል እንዲሰጠው በመደረጉ እንደገና እንዲገባ መፈቀዱን ምክትል ኃላፊዋ ወይዘሮ ገነት ያስረዳሉ። ይሁንና በተመሳሳይ ሴቶችን መተናኮል በመጀመሩ ከማዕከሉ እንዲወጣ ተደረገ ይላሉ።

በዳሶ፣ በማዕከሉ ውስጥ ባለበት ጊዜ ወጥቶ ሲለምን እናገኘው ነበር፤ የማዕከሉን አገልግሎት የሚያገኝ ሰው ወጥቶ መለመን የለበትም። እየለመኑ ወደማዕከሉ ገብቶ ማደር አይቻልም፤ እርሱ ግን ለምኖ በሚያገኘው ገንዘብ ጠጥቶበት ይገባል። በዚህ መልኩ ተደራራቢ ችግር በመፍጠሩ ከማዕከሉ ወጥቷል ሲሉ ያመለክታሉ።

በዳሶ፣ ቅሬታ ይዞ ብዙ ቦታ ተንቀሳቅሷል፤ በቢሯችንም በኩል የተደራጀ ቅሬታን የሚቀበል አደረጃጀት አለ የሚሉት ወይዘሮ ገነት፣ እዚያም ቅሬታውን አቅርቦ ታይቶለታል ይላሉ። በእነርሱ በኩል በዳሶ ቅሬታ አያቅርብ እንደማይሉም ጠቅሰው፤ ዋና ሐሳባቸው በእርሱ ምክንያት የሌሎቹ ተገልጋዮች መብት እንዳይጣስና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።

ስለዚህ እርሱ የትኛውም ተቋም እንዲገባ ሁኔታዎች  አይመቻቹለትም፤ የትኛውም ተቋም አይገባም ሲሉም ተናግረው፤ በቅርብ ርቀት እናቱ እንዳሉም መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ምላሽ

የምርመራ ዘገባ ቡድኑ፤ ማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በማዕከሉ ውስጥ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን፤ እንዲሁም የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ እና ማገገሚያ ማዕከል የጤና ባለሙያዎቸችን አጋግሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፤ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራ እንደሚሉት፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስር የሚተዳደር የማኅበራዊ ተጐጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል በጥቅሉ የሚሰጠው አገልግሎት ማኅበራዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጐች እንዲያገግሙ ማድረግ ነው። በተለይም ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ ዜጐችን በመቀበል ሁለንተናዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ወደ ተቋሙ የሚገቡ ተገልጋዮች በመንግሥት ተቋማት እውቅና ባላቸው አካላት በተለይም ባለበት አካባቢ ምንም ራሱን መጠበቅ የማይችል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። ማኅበራዊ ችግር እንዳለበት ተረጋግጦ ወደ ክፍለ ከተማ ተልዕኮ ክፍለ ከተማው ወደ ከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ በመላክ ሲረጋጥ ወደ ማዕከሉ እንደሚገቡ ያስረዳሉ።

ወደ ማዕከሉ የገባ ሰው ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚያገኝ እነደሆነ የሚገልጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በማዕከሉ ያሉ ተገልጋዮች የስጋ ደዌ ሕሙማንን ጨምሮ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ያካትታል። ለምሳሌ ዐይነስውር፣ መስማት የተሳናቸው እና መሰል አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን የሚያካትት ሲሆን፣ መንግሥት በተቻለው አቅም የአካል ድጋፎችን ጭምር ያበረክታል።

ቅሬታ አቅራቢው በዳሶ መሐመድ፣ በቢሮ በኩል ወደ ማዕከሉ በመምጣት እንደማንኛውም ማኅበራዊ ተጎጂ፤ ተቀብለን ሲገለገል የቆየ ነው። ባለን መረጃ ወደ ማዕከሉ ሲመጣ የአእምሮ ሕመም ያለበት እንደሆነና መድሃኒት እየተጠቀመ እንደነበር ነው። ከመጣ በኋላ ግን መድሃኒቱን ሙሉ በሙሉ አቋረጠ። ሲነሳበት ግቢውን ይረብሽ ነበር።

በዳሶ፣ በደህና ጊዜ እንደማንኛውም ሰው ቁጭ ብሎ ሲታይና ሀሳቡን ሲናገር ችግር አለበት ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ድርጊቱ ግን ከመደበኛው ሁኔታ የወጣ ነው። ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በተገልጋዮች ዘንድ ቅሬታዎች ነበሩ። ድርጊቱ በተገልጋይ ኮሚቴና በአስተዳደር ሰራተኞች የተያዙ ቃለጉባኤ ማስረጃዎች አሉ።

እኛ እንደ ሰራተኛ በልጁ ላይ የምናያቸው በርካታ በጐ ያልሆኑ ሥነምግባር ድርጊቶች አሉ። ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ እናቴን ጠይቄ ልምጣ ብሎ በመጀመሪያ ዙር አስፈቅዶ ሂዶ ነበር፣ ጊዜውን ጨርሶ ከመጣ በኋላ እናቴ በጣም ታማለችና ድጋሚ እነርሱን ማስፈቀድ ስለማልችል አሁን አንተ ፍቀድልኝ ብሎ ሲጠይቀኝ የማኅበራዊ ዘርፍ ሰራተኞችን ፍቀዱለት ብዬ ሄደ፤ ከሁለት ወር በላይ ቆይቶ ከመጣ በኋላ ከንግግሩ ጀምሮ ሁሉም ነገሩ ተለወጠ። የማጨስ፣ የመቃምና መጠጣት ባህሪ ይስተዋልበት ጀመር። ይሁን እንጂ ድርጊቱን በማየት በምክር አገልግሎት እንዲተው ድጋፍ እንደተደረገለት አቶ መስፍን ያስረዳሉ።

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት፤ በዳሶ ብር ይዞ መጥቶ ሲፈልግ ይጠቀምበታል፣ ካልፈለገ ቀዳዶ ይጥለዋል። ከውጭ መጠጣቱ ሳይበቃ በሃይላንድ መጠጥ ይዞ በመግባት እንዲሁም የሰራተኞች ስታፍ ይዞ በመግባት ያልተገባ ባህሪ ያንጸባርቃል፤ በተገልጋዮች ላይም ስጋት ፈጥሮ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ዐይነስውር ነኝ ይላል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያያል። እንደሚያይ ደግሞ መረጃው አለን።

ራሳቸውን መቋቋም በማይችሉ የማኅበራዊ ተጎጂዎች አረጋውያን ላይ ድብደባ ይፈጽማል። ሴቶች ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ለማድረስ ሙከራ አድርጓል። ይህ ድርጊት ለአንድ ጊዜ ሳይሆን በተደጋጋሚ ሲያደርገው የነበረ ተግባር ነው። ይህን በሚያደረግበት ጊዜ እንደ አመራር ማድረግ ያለብንን በአግባቡ ማድረግ አለብን። በዚህ ተግባሩ ተከታታይ ቅሬታዎች ከተገልጋይ እስከ አመራሩ ድረስ መጥተዋል። እኔ ወደ አመራር ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ አቤቱታዎች ይመጡ ነበር። ልጁ ቤተሰብ ያለው እና በሱስ ምክንያት ከቤት የወጣ እንደሆነ የማኅበራዊ አገልግሎት ሰራተኞች እንደሚናገሩ ኃላፊው ያስረዳሉ።

የአዕምሮ በሽታ ስላለበት ወደ ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መላኩን የጠቆሙት አቶ መስፍን፣ ይህን ያደረግንበት ምክንያት የማኅበራዊ ተጎጂዎች እንጂ የአዕምሮ ሕሙማን የተመለከቱ ባለሙያዎች በማዕከሉ ስሌሉ ነው ብለዋል።

በዳሶ፣ ከማዕከሉ እንደወጣም በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተቋሙ የተገልጋዮች ቅሬታ ሰሚ ስላለ ቅሬታውን አቅርቦ የቢሮ ኃላፊዎች ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደርጓል።

በየጊዜው እየጠጣ ይገባል። ቢከለከልም ገንዘብ ስላለው ወደ ውጭ ለሚወጡት እየላከ በማስመጣት ይጠጣል። መጠለያ ላይ የሚኖረው ተገልጋዮች ስለሚረብሽ ብቻውን ክፍል ተሰጥቶት ነበር። በዳሶ ከወጣ በኋላም በሰብአዊነት ካሻሻለ ተብሎ ተመልሶ ገብቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከገባ በኋላ ተመልሶ መምጣቱ በራሱ ጥረት እንደሆነ በመረዳት የባሰ ምን ታመጣላችሁ የሚል ስሜት አድሮበት መረበሽ በመጀመሩ ከማዕከሉ እንዲወጣ ተደርጎ ወደ ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከል ተልኳል፤ ከተቋሙ የወጣው መጋቢት 09/08/2017 ዓ.ም እንደሆነም አቶ መስፍን አስረድተዋል።

በዳሶ፣ የአዕምሮ ሕመምተኛ ነው ተብሎ ከማዕከሉ ወደ ጌርጌሴኖን የተላከበት ምክንያት የአዕምሮ ሕመም እንዳለበት በእናንተ በኩል ተረጋግጦለት ነው? የአዕምሮ ሕመምተኛ ነው ያስባለው ምክንያት ምንድን ነው? ይወስድ የነበረው የአዕምሮ መድሃኒትም ካለ ብታብራሩልን? ሲል ቡድኑ ጠይቋል።

በማዕከሉ የሕክምና እና ጤና አገልግሎት ቡድን መሪ የሆኑት መላኩ እንዳሻው እንደተናገሩት፤ ማዕከሉን ከተቀላቀሉ ገና ዓመት አልሞላቸውም፤ ስለዚህም በማዕከሉ ውስጥ ከአዕምሮ ችግር ጋር ያለውን ነገር አያውቁም። ነገር ግን በዳሶ የሚያሳያቸው አንዳንድ ድርጊቶቹ ከሱስ ጋር ተያይዞ የመጣ ይመስለኛል፤ በዳሶ ሱስ ያለበት ነው። ለምሳሌ እንደ ሲጋራ እና ጫት ከግቢው ወጥቶ እንደሚጠቀም እኛም እናውቃለን።

አንዳንዴ የሚታዩበት ምክንያቶች የጤነኛ አይደለም። አንዳንዴ ደግሞ የሚያወራው ትክክለኛ ነገር ነው። በእኔ እይታ ይህ ሁኔታው ከሱስ ጋር በተያያዘ የሚመጣ የአዕምሮ ችግር ነው ይላሉ።

እንደሰማነው ከሆነ ማኅበራዊ አገልግሎት ቢሮ ውስጥ ለመሽናት መሞከሩን ነው የሚሉት አቶ መላኩ፣ ይህ ከአንድ ጤነኛ ሰው የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። ለመሽናት መሞከሩን በመስማት ደረጃ እንጂ በዐይናቸው አለማየታቸውን አስረድተዋል። እንደዚህ አይነት ምልክቶች ስላሉበት አዕምሮውን ይታከም ዘንድ እና የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኝ ታስቦ ወደጌርጌሴኖን እንዲሄድ መደረጉን ነው የሚያስረዱት።

ከበዳሶ ጋር አብራ የሔደችው ተገልጋይ ግን በትክክልም የአዕምሮ ሕመም ያለባት በመሆኗ ከእርሷ ጋር በዳሶን ወደጌርጌሴኖን እንዳደረሷቸው ገልጸዋል። የሚያውቁትም እዚህ ድረስ መሆኑን አመልክተዋል።

ሌላው በማዕከሉ የነርስ ባለሙያ የሆኑት ደረሰ እሸቱ በበኩላቸው፤ እንደ ጤና ባለሙያ ስለበዳሶ ባህሪ የራሳቸውን ጥናት ሲያካሒዱ እንደነበር ጠቅሰው፤ ያገኙበትም ግኝት የሱስ ተጠቂ መሆኑን እንደሆነ ገልጸዋል። የሱስ ተጠቂ መሆን የጎንዮሽ ጉዳት አለበት። በዳሶ፣ አንዳንዴ በጣም እንደሚደሰትና፤ አንዳንዴ ደግሞ ድባቴ ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህ አይነቱ ስሜት በሕክምናው ‘ባይፖላር ዲስኦርደር’ ተብሎ ይጠራል ሲሉ ይገልጻሉ። እርሱም ያለበት የዚህ ችግር ነው ይላሉ።

ነርሱ እንደሚሉት፤ ልጁን በተደጋጋሚ ለመምከር ሞክረዋል። ለጤናውም ድጋፍ አድርገዋል። ምግብም እንዲበላ አግዘውታል። ይሁንና ካለበት ችግር ሊወጣ አልቻለም። የአዕምሮ መድሃኒት አልጀመረም፤ ምንም አይነት የአዕምሮ መድሃኒትም አልታዘዘለትም። ነገር ግን የሥነ ልቦና ችግር ስላለበት ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ይሒድና ሕክምና ይጀምር ብለው ነበር። ቢሆንም ለሕክምናውም ልጁ ፈቃደኛ አይደለም። በዚህ ጉዳይ በፍጹም አይተባበርም። ወደ ጌርጌሴኖን እንዲሔድ የተደረገውም ከዚህም አኳያ ነው።

የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ እና ማገገሚያ ማዕከል ምላሽ

የዝግጅት ከፍላችን የበዳሶ መሐመድን ጉዳይ በተመለከተ በማዕከሉ የማኅበረሰብ ሕክምና አጠባበቅ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ አሰሙ ዋሴን ያናገረ ሲሆን ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ በዳሶ ወደ ማዕከሉ የመጣው በአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል ነው። ይህም የሆነው ማዕከሉ የአዕምሮ ሕሙማን የሆኑት ዜጎች በመቀበል እንዲያገግሙ የሚያደርግ ሥራ ስለሚሠራ ነው።

በወቅቱ በበዳሶ ያገኙት የአዕምሮ ሕመም ግኝት ነበር፤ ነገር ግን ልጁ ያለበት (substance abuse) ችግር ነው። ይህ ማለት እንደ ጫት፣ ሲጋራ፣ መጠጥ የመሳሰሉት ሱሶችን ይጠቀማል። ስለሆነም የነበረበት ችግር ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው። በዚህ ሳቢያ ወደ ማዕከሉ እንደመጣ ቶሎ መድሃኒት መጀመር ሳይሆን የምልከታ (observation) ሥራ እንሠራለን። በዚህም ስንከታተል ያገኘነው የእዕምሮ ችግር ሳይሆን ሱስ እንዳለበት ነው።

ስለዚህ ማዕከሉ የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል እንጂ የሱስ ተጠቂዎች ማገገሚያ አይደለም። ነገር ግን ረዳት ከሌለው በማዕከሉ እንዲቆይ ተወስኖ እያለ ራሱ ማመልከቻ ጽፎ ሰበታ ዐይነስውራን ማዕከል እስከ 600 ሺ ብር የሚደርስ ርዳታ አለኝ እና ካልሸኛችሁኝ ብሩ ያመልጠኛል የሚል ማመልከቻ አስገባ። ከዚያም በኋላ ማዕከሉ ለማቆየት ሞከረ። ነገር ግን ተፅዕኖ እየደረሰብኝ ነው በሚል ይረብሽ ጀመር። ይህን በመረዳት ቤተሰቦቹ እንዲያስገቡት በማዕከሉ ትራንስፖርት ቤተሰቦቹ ዘንድ አድርሰናል።

በማዕከሉ ለአንድ ወር እንደቆየ የገለጹት የጤና ባለሙያዋ፤ ወደ ማዕከሉ ስለመጣ ጫና የደረሰበት መስሎ ስለሚታየው በማዕከሉ ያሉ የአዕምሮ ሕሙማን ሲታመሙ ሕመማቸውን እንጂ ሌላ ባህሪ አያሳዩም። በዳሶ ግን ጉዳትን ያውቃል። ለምሳሌ ከዚህ ቤት ካልወጣሁ ብሎ የመመገቢያ እቃዎችን እንደ ሳህን ያሉ ቁሳቁስን ይሰብራል፤ ይጮሃል። ትወጣለህ ሲባል ግን ተረጋግቶ ይቀመጣል። በጥቅሉ ልጁ ምን ማድረግ እንዳለበት ነገሮችን በሚገባ ለይቶ ያውቃል።

የሰነድ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፤ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል በቀን 21/6/2017 በደብዳቤ ቁጥር 1157 ማ/ች/ተ/ማ/ል/ማ ለአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ በጻፈው ደብዳቤ በማዕከሉ ያሉ የአዕምሮ ሕሙማን የሆኑ ተገልጋዮችን በሚመለከት የተሻለ አገልግሎት ወደሚያገኙበት ተቋሚ እንዲዛወሩ ትብብር ጠይቋል።

በዚህ ደብዳቤው በዳሶ መሐመድ የአዕምሮ ሕመም ያለበት በመሆኑ መድሃኒት ተጠቃሚ ስለነበር መድሃኒቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኑና መድሃኒቱን በማቋረጡ ምክንያት ሕመሙ እየከፋበት በምጣቱ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ግቢ ውስጥ ሁከትና ረብሻ እየፈጠረ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ በንብረትና በሌሎች ተገልጋዮች ላይ ጉዳት እያደረሰ ከመሆኑም በተጨማሪ ሴት አካል ጉዳት ያለባቸውና አረጋዊ ለሆኑ ሌሎች ተገልጋዮችና ሰራተኞች ከፍተኛ የደህንት ስጋት ሆኖብናል።

ስለሆነም የተሻለ ሕክምና ወደሚያገኝበት ተቋም ቢገባ ለእሱም ሆነ ለተገልጋዮች የተሻለ አማራጭ ስለሆነ ወደ የወደቁትን አንሱ ድርጅት የሚላክበት ሁኔታ በቢሮ በኩል እንደመቻችለት ማዕከሉ በደብዳቤ አሳውቋል።

ሰነድ ሁለት፡- የአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ማዕከሉ በጻፈለት የትብብር ደብዳቤ መሰረት ቢሮው በመጋቢት በቀን 09/08/2017 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ሴ/ህ/ማ/ጉ/ቢ/1/3/13/6/3 ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃና ማገገሚያ ማዕከል አስፈላጊው ትብብር ስለመጠየቅ በሚል አርእስት እንደሚገልጸው የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ለቢሮው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት በዳሶ መሐመድ የአዕምሮ ሕመም ያለበት መሆኑን ጠቅሶ የተሻለ ሕክምና ወደሚገኝበት ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል እንዲገባ መጠየቁን ጠቅሶ ድርጅቱ ለልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተጋላጭ ዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍ በመጠየቅ ድርጅቱ እንደተቀበለው መረጃው አመላክቷል።

ሰነድ ሶስት፡- በዳሶ መሐመድ በቀን 08/08/2017 ዓ.ም ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ሽኝት እንዲደረግልኝ በሚል አርዕስት በጻፈው ማመልከቻ በማዕከሉ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ችግር እንደሌለበት መረጋገጡን ጠቅሶ ማዕከሉ በገዛ ፈቃዱ ወደ ቤተሰቦቹ እንዲሄድ እንዲሸኘው በማመልከቻ በጠየቀው መሰረተ ወደ ቤተሰቦቹ ተሸኝቷል።

የአዕምሮ ሕመምተኛ_opt

በአስቴር ኤልያስና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You