የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ የኤርትራውን ሆሮታ ሪፍራል እና ቲቺንግ ሆስፒታል ጎበኙ፡፡
ለነፃ የህክምና አገልግሎት ወደ ኤርትራ የተጓዘውን የሀኪሞች ቡድን በመምራት ወደ አስመራ ተጉዘው የነበሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ፣ በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ኤርትራ የተላከው የሀኪሞች ቡድን በአስመራ በሚገኘው ኦሮታ ሪፈራል እና ቲቺንግ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱም የኤርትራ አጠቃላይ የጤና ስራ ገለጻ የተደረገ ሲሆን ለነጻ አገልግሎ አስመራ የደረሱት ዶክተሮችም ለሁለት ወራት አገልግሎት የሚሰጡባቸውን አስመራ፣ ከረን፣ ጊንዳ፣ ደቀ መሐሪ፣ አዲ ቋላ እና መንደፈራ ከተሞች ወደሚገኙ 7 ሆስፒታሎ ተመድበዋል፡፡
በስነስርአቱ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት ከወንድም የኤርትራ ህዝብ ብሎም ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ጥብቅ እና መተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን አውስተው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በከፍተኛ ፍላጎት 35 ሀኪሞችን ወደ ኤርትራ ማምጣቱን ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ የተጀመረው ትብብርም ላቅ ባለ ደረጃ እንደሚቀጥል የተናገሩት ሚንስትር ዴኤታዋ የሆሮታን ሪፈራል ቲቺንግ ሆስፒታል በጎበኙበት ወቅት ኤርትራ የዜጎቿን የጤና ፍላጎት ለሟሟላት ባላት ሀብት ከጤና ማእከል ጀምሮ እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
ኢትዮጵያውያን ሀኪሞችም ኤርትራ በሚኖራቸው ቆይታ ከሚሰጡት አገልግሎት ባሻገር ከሀገሪቱ ባለሞያዎች ልምድ እንደሚለዋወጡ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የኤርትራ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሚና ኑርሁሴን በበኩላቸው አሁን ለተጀመረው የጤናው ዘርፍ ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ሀቀኛ ፍላጎት ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም የህክምና ባለሙያዎችን በማስተማርና በማሰልጠን፣ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ እና በሌሎች ዘርፎችም ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር ለኤርትራ እና ኢትዮጵያ ህዝቦች ለጋራ ተጠቃሚነት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ለሁለት ወራት በኤርትራ የሚቆዩ ሀኪሞችም ለሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት መሻሻል የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው የተናገሩት ሚኒስትሯ የባህርዳር ዩኒቨርስቲም ላደረገው አስተዋፆ ምስጋቸውን አቅርበዋል፡፡
በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንም ወደ አስመራ የተላከው የሀኪሞች ቡድን ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ሁለንተናዊ ግንኙነት አንዱ አካል እንደሆነ ገልጸው በሚኖራቸው ቆይታም በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የሕክምና ኮሌጅ ችፍ ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሽጌታ ገላው የዩኒቨርስቲው ምሩቃን እድሉን አግኝተው ለነጻ አገልግሎት ኤርትራ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው በአስመራ የነበረው አቀባበል ደግሞ ደስታቸውን እጥፍ እንዳደረገው ገልዋል።
ወንድም ለሆነው የኤርትራ ህዝብ የጤና አገልግሎት መስጠት እጅግ እንደሚያኮራ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ ሀኪሞቹ በሚኖራቸው ቆይታም የተጣለባቸውን ሀላፊነት በብቃት እንደሚወጡት እተማመናለሁ ብለዋል።
በቀጣይም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት ለኤርትራውያን ሀኪሞች ትምህርት እና ስልጠና ለመስጠት ጭምር ዩኒቨርስቲው እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ሀኪሞች በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት እንዲጠናከር የድርሻቸውን ለመወጣት ያገኙትን የታሪክ አጋጣሚ በአግባቡ እንደሚጠቀሙበት ተናግረው የኤርትራ መንግስት እና ህዝብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።