
የኢፌዲሪ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዙሪያ ያደረገውን የጥናት ውጤት በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ይፋ አድርጎ ነበር። የዚህ ተቋም ጥናት ውጤትም መገናኛ ብዙኃኑ የታዘዙትን ብቻ የሚሰሩ “ባሬስታ” ሆነዋል፤ በአስፈጻሚው ተፅዕኖ ስር ወድቀዋል፤ የማይታየው እጅ ሚዲያው ውስጥ አለ ሲል ደምድሟል። የነበረው እውነታ ይህ ነው። ይህ ስህተት ነው ብሎ የሚከራከር ካላ አንድም መገናኛ ብዙኃኑን አያውቃቸውም፤ ወይንም አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ባይ መሆን አለበት።
ዛሬስ
ዛሬ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ይብዛም ይነስም የለውጡ ተቋዳሽ ሆነዋል። ይህ ዝም ብሎ ለማለት ያህል የሚባል አይደለም። ቁጥሮች የሚጠቀሱበት የእውነት ሰበዞችም ሊመዘዙበት የሚችል ሀቅ ነው። ጸረ.. የሚል ቅጥያ ተጨምሮባቸው ሲወገዙና ሲረገሙ የኖሩ መኖሪያቸው ከባህር ማዶ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ዛሬ አገር ቤት ናቸው። ይህንን እውነት ከሁለትና ሶስት አመታት በፊት እውን ይሆናል ብሎ ማሰብ በብዙ መልኩ ቅዠት ነው ያስብል ነበር። እንደመታደል ሆኖ ግን ይህ እውነት እውነት ሆኗል።
ይህ ለውጥ እንደ አገር ሲታወጅ መገናኛ ብዙኃኑም የተቀዳጁት አንድ በጎ ቱሩፋት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። መገናኛ ብዙኃን ነጻ ሆነው እንዳይሰሩ በማይታዩ እጆች አስሮ ይዟቸዋል የተባለው መንግስት በዚህ ደረጃ መገናኛ ብዙኃኑን ፈረሱም ሜዳውም ያው ብሎ በሩን መክፈቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። ከዚህ ነጻነት መልስ ግን መገናኛ ብዙኃኑ ነጻነት አግኝተናል በሚል ሰበብ የሙያውንም የአገሪቷንም ህግ መጣስ አለባቻው ተብሎ አይታመንም። ትክክለኛ መገናኛ ብዙኃንም የሚፈተነው በዚህ አይነት ወቅት ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ መገናኛ ብዙኃኑ አካሄዳቸው አንድን ወገን አወዳሽ ሌላውን ወገን አንኳሳሽ፤ ስሜታዊነትና ወገንተኝነት የሚታይባቸው እንደሆነ ደበበ ኃይለገብርኤል የህግ ቢሮ እና ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሞክራሲ በጋራ ባደረጉት ጥናት አረጋግጠናል ሲሉ አስታውቀዋል።
ይሄው “የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ሚና ለዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሂደት በኢትዮጵያ” በሚል ከስድስት ብሮድካስት የመገናኛ ብዙኃን ላይ 88 ዘገባዎችን በናሙናነት በመውሰድ በተሰራው ጥናት ውጤት መሰረትም፤ በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የተከሰቱ ግጭቶችን አስመልክቶ የሰሯቸው ዘገባዎች ወገንተኝነት፣ ስሜታዊነትና ጽንፈኝነት የሚታይባቸው ነበሩ።
ይህ ፍጹም መታረም ያለበት አካሄድ ነው። ግጭት በአንድም በሌላም ሊከሰት ይችላል። ከግጭት የሚያተርፈው ቀስቃሹና ግጭት ነጋዴው አካል ብቻ ነው። ብዙኃኑ የሚያተርፈው አንዳች ነገር አይኖርም። ይህንን የማይረዳ መገናኛ ብዙኃንን መገናኛ ብዙኃን ብሎ መጥራት ይከብዳል። ስለሆነም ሁሉንም በዕኩል መመልከትና መዘገብ ሃላፊነት ከሚሰማው ተቋም ይጠበቃል።
በተለይም እንደ አገር ወደ ምርጫ 2012 እየተቃረብን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ስራዎቻችን ሁሉ ህግና መርህን የተከተሉ መሆን አለባቸው። ይህንን ማድረግ አለመቻል ኪሳራው ብዙ ነው። የመጀመሪያው ከሳሪ ራሳቸው መገናኛ ብዙኃኑ ናቸው። ምክንያቱም በዚህ አይነት ጊዜም ጭምር ነውና ገለልተኝነት የሚፈተነው።
የመንግስትም ይሁን የግለሰብ አሊያም የሌላ አካል የሙያው መርህ አንድ ነው። ይህንን መርህ አክብሮ መስራት ራስንና ተቋምን ማክበር ነው። ከምንም በላይ ቅድሚያ ለአገርና ለህዝብ መሆን አለበት። ህዝብና አገር ደግሞ የሚፈልጉት ሰላምን ነው። ስለሆነም የሁሉም መገናኛ ብዙኃን መዝሙር ሰላም ሊሆን ይገባል።
መጪው ምርጫ ሀቀኛ መገናኛ ብዙኃንን በአያሌው ይሻሉ ስንልም በብዙ ምክንያቶች ነው። ከብዙ ምክንያታችን ሚዛኑን የሚደፋው የአገራችን ሰላም ጉዳይ ነው። ዛሬ እንደዘበት በስህተትም ይሁን በስሌት የምንሰራው አንድ ተገቢ ያልሆነ ዘገባ ነገ የሚያመጣው ቀውስ ዳፋው እልፍ ነው።
“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲል ብሂሉ አስቀድሞ ሳያስቡ መረጃ መልቀቅ በአገራችን ሰላም ላይ የሚኖረው ጉዳት ከቃላት በላይ ይሆናል። ይህንን መረዳትና ስራዎቻችንን በህግና በሙያው መርህ ብቻ መሰረት መስራት የውዴታ ግዴታችን ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012