
የክርስትና አምነት ተከታዮች በዛሬው እለት የእየሱስ ክርቶስን የልደት ቀን የገናን በዓል በደማቅ ስነ ስርአት ያከብራሉ።በዓሉ በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ ስርአቶች የሚከበር መሆኑ እንዳለ ሆኖ የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ እንደየአቅማቸው እየደገሱ የተለያዩ መልኮችን በማስያዝ በአሉን በደማቅ ስነስርአት በደስታ ያከብሩታል፡፡
ለእዚህም ሰፊ ዝግጅት ይደረጋል።በዓልን ያህል ትልቅ ጉዳይ ከፊት እያለ ለእዚህም ለእዚያም በሚል ገንዘብ አይወጣም።በዓልን አስቀድሞ ያጣጣሙ ከቀደመው በበለጠ ባማረ መልኩ እንዲከበር በሚል ተጨማሪ ስራም ሰርተው ይሁን ቆጥበው ይዘጋጃሉ፤ ልጆች በጎረቤት የሚደረገውን የበዓል ዝግጅት እየተመለከቱ እንዳይጓጉ በሚል በዓል ለማክበር ብዙ ዝግጅት ባይደረግ እንኳ ለልጆቹ ሲባል ቤቱ በዓል በዓል እንዲሸት ለማድረግ ይሞከራል፡፡
በበአል ወቅቶች መደሰት የተለመደ ነው።በዓል ለብቻ ሊከበር ቢችልም ሰዎችን የሚያስተሳስርበት ሁኔታ በርካታ ነው።በዚህ የተነሳም ለበዓል የቤተሰብ አባላት ይሰባሰባሉ፤ በውጪ ሀገርም ሆነ ከቤተሰብ ራቅ ብለው በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ለመገናኛት ቀጥሮ የሚይዙት አንድም በአንዲህ አይነቱ የደስታ ቀን ነው፤ በአል የጋራ ነውም ይባላል።በቅርብ የሚገኘው ዘመድ አዝማድ እንዲሁም ጎረቤት ይጠራራል።
በአል በአንድ ጣሪያ ስር ብቻ እንዲከበብ አይፈለግም፤ ለነዳያን ይታሰባል።ከቤት መውጣት የማይችሉ፤ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሰዎች የበዓል ስሜት እንዳይለያቸውና እንዳያዝኑ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።ይህ የመተሳሰብ ባህል በወጣቶቻችን ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰፋፋ መጥቷል፡፡
ወጣቶች በዓላት ሲቃረቡ እየተሰባሰቡ ነዳያንን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን አቅመ ደካሞችን የበዓል ወግ እናሳያለን ድጋፋችሁን አርጉልን እያሉ በየቤቱ በየጎዳናው እየዞሩ ገንዘብ ያሰባስባሉ፤ በእዚህም ምግብ በማዘጋጀት እነዚህን ወገኖች አሰባሰበው በመመገብ በአልን በጋራ እያሳለፉ ይገኛሉ።
የእነዚህ ወጣቶች ተግባር በእጅጉ ሊደነቅ ይገባል።ስር በሰደደ ድህነት፣ በአሳዳጊና ጧሪ እጦት ወዘተ ሳቢያ ወደ ጎዳና የወጡ ወገኖች ጨርሶ እንዳልተረሱ ለማሳየት፣ ሌሎች ወገኖች ሊደርሱላቸው እንደሚችሉም ለማመልከት ይጠቅማል።ይህ ተግባራቸው ከተጀመረ ቆየት ቢልም አሁን አሁን እየሰፋ መጥቷል።ይህ ተግባር በግለኝነት ላይ
ብቻ በመመስረት የቆየውን የመተሳሰብ ባህል የረሱ ወገኖችን በማንቃት ወገናቸውንም እንዲያስቡ ያደርጋል።
በሀገራችን እየተፈጠረ ያለው የአኮኖሚ አቅም ልዩነት አንዱ እየተንበሸበሸ የሚያረገውን እያጣ፣ ሌላው የበይ ተመልካች እንዲሆን እያደረገ ነው።የበዓል አከባበሩም እንደዚያው መሆን ከጀመረ ቆየት ብሏል።ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተው ድፍት ብለው ሲያድሩ፣ ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ጭምር እንድንጠራጠር በሚያደርግ መልኩ በሀብት ማማ ላይ ቆመው ከስራቸው ያለውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ እየዘነጉት ይገኛሉ።
ይህ የሚቀየርበት ዘመን ሊመጣ ቢችልም እስከዚያው ድረስ ግን ያላቸው የሌላቸውን ሊደግፉ የሚችሉበት አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል።በተለይ በበዓላት ወቅት እና የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስባቸው ወቅቶች ያለው የሌለውን ሊደግፍ የሚችልበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል።ለእዚህ ደግሞ መንግስት ኃላፊነት ቢኖርበትም እንዲህ በበዓል ወቅት ችግረኞች የበዓል ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ በበጎ አድራጎት ተግባር የሚሰማሩ ወገኖች ሚና ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ለእዚህ ደግሞ በእምነት ተቋማት፣ በግል ተነሳሽነት፣ ወዘተ ህብረተሰቡ በዓሉን ችግረኞችን በመርዳት ጭምር እንዲያከብር ለማድረግ እየተከናወነ ያለው አርአያነት ያለው ተግባር እንደ እርሾ ሊያገለግል ይችላል።ህዝቡም የእነዚህ የበጎ አድራጎት ተግባር የአስተባባሪዎች ስራ ይበልጥ ጎልብቶ ለችግረኞች መድረሱን እንዲቀጥል ለማድረግ ይህን አርአያነት ያለው ተግባር አጠናከረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡
የእምነት ተቋማት መሪዎች ሁሌም በበዓላት ወቅት በአንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው እንደሚጠቅሱት፤ ምእመናን የትኛውንም መንፈሳዊ በዓል ከችግረኞች ጋር ማክበር ይጠበቅባቸዋል።በዓሉን ከችግረኞች ጋር ያከበራችሁ በሙሉ እምነቱም ሰብአዊ ተግባርም የሚጠይቀውን አድርጋችኋል፤ በቀረባላችሁ የእርዳታ ጥሪ መሰረት ድጋፍ ያደረጋችሁ ግለሰቦችም ሆናችሁ ድርጅቶች ፤ ሁላችሁም ምስጋና ይገባችኋል፡፡
እናንተ በዚህ የበአል ወቅት ነዳያን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አቅመ ደካሞች፣ ወዘተ የበዓል ስሜት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ብላችሁ የሰው ፊት እየገረፋችሁ እርዳታ ስታሰባስቡ በኋላም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች አሰባስባችሁና አብራችሁ ሆናችሁ በዓልን ያሳለፋችሁ ወገኖች በቅድሚያ እንኳን አደረሳችሁ !! ስራችሁ አኩሪ ነውና በርቱ!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012