አዲስ አበባ፡- በክልሎች ግንኙነት ላይ ያተኮረ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመወያየት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥሪ ቢያቀርብም የአንድም ክልል ተወካይ አልተገኘም።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሎች ከክልሎች ጋር እንዲገናኙ ሲሠራ የሕግ መሠረት አለመኖሩ፤ ፈቃደኛ ያልሆኑ ክልሎችን ማገናኘት እንዳይቻል ማድረጉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፍትህ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አበበ ጉዴቦ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የክልል መንግሥታት እና ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ ያተኮረ ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴው ከተመራ ስድስት ወራትን አስቆጥሯል።
የሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል ተወካዮች በረቂቅ አዋጁ ላይ እንዲመክሩ ጥሪ ቢተላለፍላቸውም ታህሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለመገኘታቸው የተዘጋጀው መድረክ ተሠርዟል።
ለሁሉም ክልሎች እና ለከተማ አስተዳደሮች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፤ ለክልል ምክር ቤት አፈጉባኤዎች ሳይቀር በልዩ ሁኔታ ለሁሉም ደብዳቤ የተላከ መሆኑን ተናግረዋል።በተጨማሪም ደብዳቤው ደርሷችኋል? በሚል የማረጋገጫ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው አንዳንዶቹ እንዳልደረሳቸው ቢናገሩም፤ ደብዳቤው መላኩ ተነግሯቸው እንዲመጡ ተጠይቀዋል።
ረቂቅ አዋጁን አንብበውና ተዘጋጅተው እንዲገኙ ኮፒ ተደርጎ የተላከ መሆኑን እና ሁሉም ይመጣሉ ተብሎ ታስቦ እንደነበር ያመለከቱት አቶ አበበ፤ ነገር ግን በዕለቱ ከሰላም ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጭ ማንም አለመገኘቱን አመልክተዋል።ግብርና እና ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጥሪ ቢቀርብላቸውም አለመገኘታቸውን ተናግረዋል።
እነደ አቶ አበበ ገለፃ፤ ረቂቅ አዋጁ ሰፊ የህዝብ ውይይትን የሚጠይቅ ሁሉንም ክልሎች የሚመለከት ነው፡፡
ህዝቡን ያሳተፈና የበሰለ አዋጅ ለማውጣትም የግድ ውይይት መደረግ አለበት።ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑም መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
የሕግ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ሃዱሽ አዛናውም ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የመንግሥታት ግንኙነት ረቂቅ አዋጅን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል::
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አዋጁ ላይ ተወያይቶበት ለዝርዝር እይታ ለሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው መሆኑን አስታውሰው፤ ቋሚ ኮሚቴው በራሱም ሆነ በምክር ቤት አባላቱ የተነሱ ጥያቄዎችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል ብለዋል።
ከፌዴሬሽን አስረጂዎች ቀርበው ለጥያቄዎች መልስ በመስጠት ያብራሩ ሲሆን፤ አዋጁ በቀጣይም የክልል መንግሥታት እና ከፌዴራል ተቋማት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ጨምሮ የህዝብ ውይይት የሚካሄድበት መሆኑን እና በእነርሱ በኩል አስፈላጊው ሥራ በሙሉ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ለክልሎች ግንኙነት ሥርዓት ይበጅለት የሚል ጥያቄው ለስድስት ዓመታት ሲቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል።ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ፌዴሬሽኑ ችግሮችን ለማቃለል ክልሎች ከክልሎች ጋር ለማነጋገር ቢያቅድምና ምንም እንኳ ብዙሃኑ ፈቃደኛ ሆነው ቢገናኙም አንዳንዶቹን ለማገናኘት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ አስቸግሯቸው እንደነበር ጠቁመዋል።
ሌሎች የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚከተሉ አገራት የክልል መንግሥታት ግንኙነት ሕግ ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፤ አዋጁ መዘጋጀቱ ክልሎች በመካከላቸው ያለው ግንኙነት በሕግ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እና መግባባት እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
ምህረት ሞገስ