አዲሰ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ በሕገወጥ መንገድ ይነግዱ ከነበሩት ውስጥ 19 ሺህ ስድስት መቶ ነጋዴዎች ሕጋዊ መስመር ተከትለው እንዲሠሩ መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድ ሥርዓት ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሉሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ወደ ሕጋዊነት ለመመለስ የወጣው አዋጅ ተግባር ላይ ከዋለ አንድ ዓመት ሆኖታል።በመመሪያው መሰረት 58 ሺህ 600 ነጋዴዎች ተመዝግበዋል።ከተመዘገቡት ውስጥ 19 ሺህ ስድስት መቶ በሥርዓት የንግድ መለያ ቁጥር (ቲን ነምበር) አውጥተው በሥርዓት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
እንደ አቶ ዳኛቸው ገለፃ፤ መመሪያው ወደ ተግባር ከገባ በኋላ የመጀመሪያ ሥራ የነበረው የአጭር፣ የመከካለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ማዘጋጀት ነው።በአጭር ጊዜ ዕቅድ ከተካተቱት ውስጥ በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕገወጥ ነጋዴዎችን የመመዝገብ ሥራ ነበር።በሁሉም ክፍለ ከተሞች ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ይሠሩ የነበሩ ነጋዴዎች ሕጋዊ መስመር ይዘው እንዲሠሩ ተደርገዋል።
‹‹በአሁን ወቅት በጎዳናዎች ላይ ሸራ ዘርግተው እየነገዱ የሚገኙ ተመዝግበው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ይገኙበታ›ል›› የሚሉት አቶ ዳኛቸው፤ በተጨማሪም ነጋዴዎቹ ሰዓትና ቀናት ተለይቶላቸው የሚሠሩበት ቦታ ተሰጥቷቸው እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።በቀጣይ ተመዝግበው ወደ ሥራ ያልገቡ ነጋዴዎች ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አመልክተዋል።
ሕብረተሰቡ በሕጋዊ መንገድ እየነገዱ ከሚገኙት ይልቅ በሕገወጥ መንገድ ጎዳና ላይ ከሚነግዱ የመግዛት ባህሉ እስካሁን እንዳልተሻሻለ በመጥቀስ፤ በሕገወጥ መንገድ ከሚሸጡ ሰዎች መግዛት የጤንነት ችግርን፣ የፀጥታ መታወክ ሁኔታን እንዲሁም ከመንገድ መዝጋት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጉዳቶችን ስለሚያመጣ ሕብረተሰቡ ሕግ አክብረው ከሚሠሩ ነጋዴች ግብይት እንዲፈፅም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
መርድ ክፍሉ