አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ባላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና በተለያዩ አማራጮቿ ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭነቷ እጅግ መጨመሩ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሃይሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ሲመጡ መንግሥት ፍቃድ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን ያደርግላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ገበያ በጣም ቅርብ መሆኗ፣ የአሜሪካ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ መሆኗ እንዲሁም በገበያ ተደራሽነቷ የተለያዩ ካምፓኒዎች እየመረጧት ይገኛሉ።
‹‹አንድ ካምፓኒ በኢትዮጵያ የተለያዩ ምርቶችን ቢያመርት የገበያው ጉዳይ ሊያሳስበው አይችልም።›› ካሉ በኋላ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት አገር በመሆኗ በምሥራቅ አፍሪካም ሰፊ ህዝብ በመኖሩ የተለያዩ ካምፓኒዎች የቱንም ያህል ምርት ቢያመርቱ ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥም ሆነ ለምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ተደራሽ ማድረግ እንደሚችሉ አመልክተዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ በተለይም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት አገሪቷ ያላትን ዕምቅ ሀብት እንዲሁም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር እያስተዋወቀ ይገኛል። በዚህም በተለያዩ አገራት ማለትም አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና ሌሎች አገሮችም ኢንቨስት ለማድረግ ኢትዮጵያን ተመራጭ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰው ሃይል በቀላሉ ሰልጥኖ ወደ ሥራ መሰማራት የሚችል በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ብቁ የሆነ የአየር መንገድ አገልግሎት ማቅረብን ጨምሮ ከሌሎች አገራት በተሻለ መልኩ እንደ መብራት፣ መንገድና ስልክ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በመኖራቸው ተወዳዳሪ አድርጓታል። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት መካከል ግንባር ቀደም በመሆኗና በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በራሱ ለባለ ሀብቱ ትልቅ ተስፋ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት ሊያደርጉና ሊሰሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችም አሏቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች ብቻ ሰባት መቶ ሚሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል።
ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ኮሚሽኑ፤ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ከማስተዋወቅ ባለፈ ለባለሀብቶቹ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ይሠራል።
ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ፤ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ የኦን ላይን አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ በርካታ ባለሀብቶች መካከል ቻይና አንዷ ስትሆን ቻይናውያን ባለሀብቶች የቋንቋ ችግር እንዳይገጥማቸው በቻይንኛ ቋንቋ ዌብሳይት ተገንብቷል። ይህም ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጋት ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ መሆኑን አቶ መኮንን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳድራ የውጭ ኢንቨሰትመነትን በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን፤ ከአፍሪካ ደግሞ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮንጎና ሞሮኮን በመከተል በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አቶ መኮንን አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
ፍሬህይወት አወቀ