አዲስ አበባ:- በደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ ለሚገኘው የኦቶና ዓይነሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ መስጠቱ ትምህርት ቤቱን ከመዘጋት እንዳተረፈው ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ወሰን ዓለሙ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ዓይነሥውራን ተማሪዎች አገልግሎት በመስጠት ብቸኛ ነው::
ትምህርት ቤቱ የሚተዳደረው በኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማህበር ቢሆንም ማህበሩ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት ትምህርት ቤቱ ከሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ዓይነሥውራን ተማሪዎች ቀርቶ በክልሉ ዙርያ ለሚገኙ ዓይነሥውራን ተማሪዎችም በቂ አገልግሎት መስጠት አልቻለም።
ፕሬዚዳንቱ እንደገለፁት፤ ትምህርት ቤት በበጀት እጥረት ምክንያት ሊዘጋ ከተቃረበ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፤ በተያዘው የትምህርት ዘመን የፌዴራል ገቢዎችና ጉመሩክ ባለሥልጣን ባደረገው ድጋፍ ከመዘጋት ተርፏል:: ባለሥልጣኑ በትምህርት ቤቱ ለሚገኙ 60 ዓይነሥውራን ተማሪዎች 500 ኪሎ ግራም ስኳር፣ 500 ሊትር ዘይትና 200 ኪሎ ግራም የሚመዝን የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግሮች ያሉባቸውን እንዲሁም ለሴቶች ቅድሚያ በመስጠት ያስተምር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ወሰን፤ የትምህርት ቤቱ የቅበላ አቅም ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ የመጣና በአሁን ወቅት ደግሞ አስታዋሽ አጥቶ ሊዘጋ መቃረቡን ተናግረዋል።
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም የኢትዮጵያ መድን ኢንሹራንስ ባደረጉት ድጋፍ የዓመቱን ትምህርት መቀጠል እንደተቻለ ገልፀው፤ ይሁን እንጂ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ካላገኘ በቀጣዩ ዓመት የመቀጠሉ ዕድል አሁንም የጠበበ መሆኑን አመልክተዋል።
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት አላገኘም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት አንድ ብር ለአንድ ወገን የሚለው የገቢ ማሰባሰቢያ ሲጠየቅ በዋናነት አካል ጉዳተኞችን ትኩረት አድርጎ የነበር ቢሆንም ትረስት ፈንዱ ለአካል ጉዳተኞች ምንም አይነት ድጋፍ አለማድረጉንም ተናግረዋል።
በተያዘው የትምህርት ዘመንም ለጋሽ መሥሪያ ቤቶች ድጋፍ አድርገው ትምህርት ቤቱ ማስተማር የቀጠለ ቢሆንም፤ ሌሎች ሃላፊነት ይሰማናን የሚሉ ድርጅቶችም የተቋማቱን ፈለግ በመከተል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ ለመዘጋት አፋፍ ላይ ደረሰ የተባለውን የወላይታ ሶዶ ኦቶና የዓይነሥውራን ትምህርት ቤት የገጠመው ችግር ምንድነው ሲል ለወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ትምህርት ቤቱ በበጀት እጥረት ሊዘጋ መቃረቡን አናውቅም ማለቱ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
ፍሬህይወት አወቀ