• በሃይማኖትና በትምህርት ተቋማት ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ቡድኖች ላይ እርምጃ ይወሰዳል
• የዘንድሮው ምርጫ የለውጡ አዎንታዊ ተፅእኖ የሚታይበት ነው
• ፍኖተ ብልጽግና የተሰኘ የፓርቲው የአስር ዓመት ዕቅድ ይፋ ይደረጋል
አዲስ አበባ፦ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ አቅጣጫ ማስቀመጡን የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ስራ አስፈፃሚው በሃይማኖትና በትምህርት ተቋማት ጥቃት ዙሪያ እንዲሁም በዘንድሮው ምርጫ ላይ መክሮ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ውይይት ማድረጉን ተከትሎ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሰላም እና የፀጥታ እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ጥልቅ ውይይት ተደርጓል። በሃይማኖትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በቡድንና በተናጠል በተደራጀ መልኩ ጥቃት የማድረሱ ዘመቻ እየተባባሰ መጥቷል።
ይህ እኩይ ተግባር የኅብረተሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ እንደሚከት ስራ አስፈፃሚው ገምግሟል። በወንጀሉ የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድም አቅጣጫ ተቀምጧል።
‹‹በወንጀሉ በተሰማሩ አካላት በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት እና የፍትህ ተቋማት እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ ተላልፏል›› ያሉት የዋና ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ፤ የአገሪቷንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የዘንድሮውን ምርጫ እና በብልጽግና ፓርቲ የ10 ዓመት እቅድ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታውቀዋል።
እንደ ዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊው ገለፃ፤ የዘንድሮው ምርጫ አገሪቱ ትልቅ የፖለቲካ ሪፎርም እያደረገች ባለችበት ወቅት መደረጉ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ለየት ያደርገዋል። በዚህም የለውጡ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚታይበት ይሆናል።
ከዚህ ባሻገር ስራ አስፈፃሚው ባደረገው ውይይት ከአዎንታዊ ተፅዕኖው ባሻገር ስጋት የሚታይበት ምርጫ እንደሚሆን ታሳቢ መደረግ አለበት የሚል አቋምም ይዟል። በዚህ መነሻ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋቱን ታሳቢ በማድረግ ምርጫው ይራዘም ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃሉ። የብልፅግና ፓርቲ ምርጫውን በተያዘለት
የጊዜ ገደብ ማድረጉ ህገመንግስታዊ ኃላፊነትን የመወጣት አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለው። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫው አሸናፊ ሆኖ የመውጣት እቅድም አስቀምጧል። ለዚህም ለኢትዮጵያ ብልጽግና ይጠቅማሉ ያላቸው ሃሳቦችን ይዞ ይቀርባል። ሂደቱም በሃሳብ ትግል ላይ የተመሰረተ፤ ሰላማዊ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አባላቱን ጨምሮ ደጋፊዎቹ ሊሰሩ እንደሚገባም ወስኗል።
ስራ አስፈፃሚው ከተወያየባቸው ወቅታዊ አጀንዳዎች መካከል ሌላኛው ‹‹ፍኖተ ብልጽግና›› የብልጽግና የ10 ዓመት እቅድ እንደነበርም የዋናው ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ ተናግረዋል። በዚህም በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ተምሳሌት እንድትሆን ይሰራል።
የዕቅዱ ዋና ማጠንጠኛም ‹‹ማምረት፣ ማምረት፣ ማምረት›› የሚል ሲሆን በምግብ፣ መድኃኒት እና ልብስ ምርቶች ላይ በቀዳሚነት ተሳታፊ መሆን እንደሚገባም ታሳቢ መደረጉን ገልፀዋል። በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ምግብና ምግብ ነክ ጉዳዮች በማቀነባበር የተትረፈረፈ አቅርቦት እንዲኖር ይሰራል። ለዚህም ቴክኖሎጂ፣ የሰው ሃይል እንዲሁም የፋይናንስ አቅምን የመገንባት ስራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
ዳግም ከበደ