በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ»!! እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሰን። «ነገር በምሳሌ…» ይሉትን ብሂል ያወረሱን የቀደሙቱ ኢትዮጵያውያን፤ ምሳሌንም በየነገሩ ውስጥ እያካተቱ በጎ ያሉትን ሁሉ ያመላክቱን ነበር። በእነዚህ ስንኞችም ውስጥ የገና በዓሉ ሰውን የፈጠረ አምላክ ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም መወለዱን የሚያስብና የሚያስታውስ ነውና፤ የትህትና መሆኑን ለማጠየቅ፤ «የለም ሎሌ ጌታ» ሲሉ በልጆች ጨዋታ መካከል እንዲታወስ አኑረውታል።
ስለገና በዓል አንስቶ ይህን አለማለት የማይቻል ሆኖ እንጂ፤ ነገራችን ከገና ስጦታ ጋር የተገናኘ ነው። በመግቢያ በመውጫችን፤ በመመላለሳችን እንደምናየው በየመንገዱና በየንግድ ማዕከላቱ የስጦታ ዕቃዎችና መጠቅለያዎች፣ ቤት ማድመቂያ ጌጣጌጥና የባህል አልባሳትን ጨምሮ ለውጪ ድምቀት ለውስጥ ሙቀትና ጉልበት የሚሆኑ ምርቶች በብዛት እናያለን።
ብዙ ሰዎች ታድያ ሸመታቸው ከስጦታዎች ተርታ ነው። ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ፣ ለፍቅረኛ፣ ለትዳር አጋር፣ ለልጅ ወዘተ ስጦታዎችን ይገዛሉ፤ እርስ በእርስም ይሰጣጣሉ። ይህን የሚያውቁ በንግዱ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችም ተፈላጊ ይሆናል የሚሉትን ምርት በብዛት ይዘው ይቀርባሉ። የንግድ ቤቶቻቸውን ያስውባሉ፣ ደጃቸውን በቀለማት ያደማምቃሉ።
ታድያ የከተማው ድባብ ሰሞኑ የገና በአል ያለበት እንደሆነ ያስታውቅ እንጂ አገርኛ መልኩን የተነጠቅን ይመስላል። የነጮቹ «የገና አባት» አልባሳትና በቀለማቱ የተዘጋጁ ጌጣጌጦች እንዲሁም የገና ዛፎች በርክተው ይታያሉ። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች መካከል በአንዱ የተዘፈነ ዘፈኖች ከመሰማቱና ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያውያን ከመሆናቸው በቀር አብዛኛው የገጽታው አካል የሆኑ ስርዓቶች ከባህርማዶ በውሰት የተገኙ መሆናቸው ያስታውቃል።
ይህም ይቆየንና፤ የገና በዓል እና ስጦታ ምን ያገናኛቸዋል? በአገራችን የስጦታ መሰጣጠት ባህሉ እንዴት ነው? የአገር ባህል ሥራ የሆኑ ወይም የእደ ጥበብ ውጤቶችስ ከስጦታው ተርታ ተሰልፈዋል ወይ? ወይስ ከባህር ማዶ ተገዝተው የመጡትን ነው ስጦታ የምንለዋወጠው? የሚሉት ጉዳዮች ላይ የተወሰነ እንበል።
የገና ስጦታ
የህክምና ባለሙያ እንዲሁም የዳረጎት ዘተዋህዶ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዲያቆን ዶክተር አቤል ኃይሉ ስለገና በዓል እንዲሁም በዓሉ ከስጦታ ጋር ስላለው ግንኙነት በእምነትና በሃይማኖት መነጽር እንዲህ አመላከቱን። መጀመሪያ «ገና» ለሚለው የበዓሉ ስያሜ ሁለት ዓይነት የትርጓሜ እይታ አለ። አንዱ ምንጩን ከግሪክ ያደረገ ሲሆን ልደት የሚል ትርጉምን ይሰጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ነብያት የጌታችንን መወለድ እየተጠባበቁና ዘመን እየቆጠሩ «ገና ይህን ያህል ጊዜ ቀረ» ይሉ ነበርና፤ በዛ ስም ተጠራ የሚሉም አሉ።
ታድያ በየትኛውም ትርጓሜ የገና በዓል የእግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም መወለድ የሚታሰብበት መሆኑ ግልጽ ነው። «እንግዲህ የልደት በዓልን እና ስጦታን ምን አዛመዳቸው?» ስንል፤ ዲያቆን ዶክተር አቤል የገና በዓል በራሱ ስጦታ መሆኑን ነገሩን። እንደምን ቢባል እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወልድን የሰጠበት ቀን ነውና።
ቅዱሱ መጽሐፍም በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንዲህ ማለቱም ዲያቆን ዶክተር አቤል ይጠቅሳሉ፤ «በእርሱ የሚያመን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና» የበዓሉ መሠረታዊ ትርጓሜም ይኸው፤ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ውድ ስጦታ ያገኘ መሆኑ ነው። በተጓዳኝ ጌታችን በተዋህዶ ሰው የሆነው ዓለምን እንዲያድንና እንዲፈውስ በመሆኑ በተጨማሪ በዓሉ የስጦታ ቀን ለመሆኑ ማሳያ ይሆናል።
ከዚህ ባሻገር ያለው ደግሞ ጌታችን በተወለደበት በረት ውስጥ የተከሰቱት ሁሉ ከስጦታ ጋር የሚገናኙ መሆናቸው ነው። ይህም ደግሞ እንደሚከተለው ይገለጣል፤ «በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ፤ ቤተልሔም ከተማ ያላትን በረት ሰጥታለች፤ አበርክታለች። በበረቱ የነበሩት እንስሳት ደግሞ እስትንፋሳቸውን ገብረዋል። «ስብሃት ለእግዚአብሔር በሰማያት፤ ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ» እንዲል ቅዱሱ መጽሐፍ፤ መላዕክትም ዝማሬን ሰጥተዋል። እረኞቹም ከመላዕክቱ ጋር ዘምረዋል። ሰብአ ሰገል ወይም የጥበብ ሰዎች ደግሞ ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤን አቅርበዋል»
እነዚህ ስጦታዎች እያንዳንዳቸው ዋጋ ነበራቸው። የጥበብ ሰዎች ያቀረቧቸው ስጦታዎችም እያንዳንዳቸው ትርጓሜና ምስጢር ያላቸው ናቸው። ታድያ በዚህ ውስጥ በዓሉ የስጦታ መሆኑን ከመረዳት ባለፈ፤ ሁሉም በአቅሙና ባለው ስጦታ ቢሰጥ መልካም እንደሆነና ትርጉም ያለው ስጦታ መስጠት እንደሚገባ ያመላክታል።
እኛ እና ስጦታ
ታድያ በአገራችን ስጦታ የመስጠት ባህል ምን ይመስላል? ዲያቆን ዶክተር አቤል በአንድ ወቅት በሰጡን ቃለ ምልልስ አጫውተውን ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት ስጦታ መሰጣጠት በአገራችን ድሮም የነበረና የተለመደ ነው። በቀደመው ጊዜ ነገሥታት እንደ ባህላቸው ወርቅ፣ የሀር ጨርቅ፣ የዝሆን ጥርስ፣ አልባሳትና የመሳሰለውን ይሰጣጡ ነበር። «በአገራችን የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ከወዳጅ፣ ለእጮኛ፣ ለቤተሰብ፣ ለማኅበርና ለመሳሰለው ስጦታ የመስጠት ባህል ከውጪ የመጣ ነው ተብሎ መተው የለበትም። እንደው ከውጪ መጣ ቢባል እንኳ በጎ ባህል በመሆኑ መበረታታት ይኖርበታል።» ይላሉ።
በእርግጥ በአገራችን ስጦታ የመሰጣጠት ባህል ከጥንት የመጣ ነው። እንኳን ኢትዮጵያዊ ሰውና ምድሪቱም ወቅቱን ጠብቃ በምታፈራው ሁሉ ለኢትዮጵያውያን ስጦታን ትሰጣለች። ለአዲስ ዓመት አደይ አበባ፣ ለጥምቀት ቄጠማ፣ ዘመድ ጥየቃ አረቄና ዳቦ፤ ብቻ ለሀዘኑም ለደስታውም ሰው ስጦታ መሰጣጣትን ሳያውቀውም ለምዷል። ከዚህ በኋላ ጥያቄው የሚሆነው ምን ዓይነት ስጦታዎች ናቸው በብዛት የሚሰጡት ነው።
ሁሉም ባለሙያ በየዘርፉና በትኩረት በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ያተኩራል። የቤት ውስጥ እቃ፣ አልባሳት፣ ጣፋጭ ምግቦች፣ ግብዣ፣ ጌጣጌጥ ወይም መጽሐፍት፤ ሁሉም በየመንገዱ «ይህ ነገር ቢሰጥ መልካም ነው» እያለ ሃሳቡን ያካፍላል። «ይህ ትክክል ነው» የሚባልም የለም፤ ሁሉም እንደምርጫውና እንደፍላጎቱ፤ ደስ እንደሚያሰኘውና በአቅሙ የሚያደርገው በመሆኑ ነው።
ካለፉት ሳምንታት መካከል በአንዱ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የእደ ጥበብ ውጤቶች አውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ነበር። በዛ አውደ ርዕይ ላይ ከተሳተፉ ነጋዴዎች መካከል አናግረናል። በዚህ ላይ አስተያየቱን የሰጠን ወጣት ታምሩ አሸናፊ የተለያዩ በእጅ የተሰሩ የአንገትና የተለያዩ ጌጣጌጦችን ለደንበኞቹና ለፈላጊዎች ያቀርባል። በተለያየ ቅርጽ የተሰሩ የአንገት ላይ ጌጦችን፤ የእጅ አንባሮችን፣ በተለያዩ ቀለማት የተሠሩ የሸማ ውጤት የሆኑ ሻርፖችና ኮፍያዎች፤ ሌሎችም ብዙ እቃዎችን ይዟል።
ታድያ ገበያው ጥሩ ቢሆንም ሰዎች ለስጦታ እነዚህን የእጅ ሥራዎች ብብዛት እንደማይመርጡ ይጠቅሳል። «ጌጣጌጦችን ለመግዛት የሚፈልጉ ሰዎች በብዛት ከውጪ የሚገቡ ብልጭልጭ የበዛባቸው ቁሳቁሶችን ነው የሚመርጡት። በአገራችን ለስጦታነት ሊበረከቱ የሚችሉ እቃዎች በብዛት ላይገኙ ይችላሉ፤ ቢሆንም ግን ያሉትን ብንገለገል የአገራችንን ነገር ማስተዋወቅ በመሆኑ የተሻለ ነው» ብሏል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንዱ ሥራ በዚህ የእደ ጥበብ ውጤቶች ላይ መሆኑን የሚኒስቴሩ ዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ ነግረውን ነበር። እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ የኪነጥበበ ዘርፍ የሚባሉትን ሆነ እንደ እደ ጥበብ ያሉ ባህላዊ እንዲሁም አገር በቀል እውቀቶች ሁሉ ኢኮኖሚውን መጥቀም አለባቸው።
ይህን ከማድረግ አንጻር ሚኒስቴሩ በእቅድ ከያዘው ሥራ ጎን ለጎን ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የእደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ሕዝብን ሊጠቅም የሚገባ ሥራዎችን እንዲሠሩ በማድረግ በኩልም የታሰበ መኖሩን ጠቅሰዋል። ይህም በሚፈለገው ደረጃ ለሥነ ምጣኔው ድጋፈ እያደረገ አለመሆኑ ያስነሳው ጉዳይ ነው። ታድያ እዚህ ላይ በዋናነት በምሳሌ የጠቀሱት የስጦታ እቃዎችን ነው።
እንዲህ አሉ፤ «ለምሳሌ የስጦታ እቃዎችን ስናይ፤ በብዙ ቦታዎች የሚሸጡት የእኛን ሰንደቅ ዓላማ ቀለም የያዙ ይሁኑ እንጂ ከቅርብ አገራት እንደ ኬንያ ካሉት እንዲሁም ተሻግሮ ከቻይና እና ሌሎች የሚመጣ ነው።» ብለዋል። ሲታዩ ኢትዮጵያን የሚገልጹ ብዙ የእደ ጥበብ ውጤቶች በአገር ውስጥ የተመረቱ ሳይሆን ከቻይና የመጡ መሆናቸውን ማሰብ በእርግጥ ሊቆጭ የሚገባም ነው።
እዚህ ላይ አቶ ገዛኸኝ አያይዘው፤ አንድ ሰሞን ርዕስ የነበሩትና ከቻይና ታትመው ሲመጡ የቆዩትን ጨርቆች አንስተዋል። «ይህን ሁሉ ወደ ኢኮኖሚው እንዴት እናምጣው ነው ጥያቄው? ለዚህም ምላሽ ለመስጠት እነዚህንና ሌሎች በርካታ አገርን ሊጠቅም የሚችል ነገሮች ላይ በስፋት እየሠራንበት ነው።» ብለዋል፤ አቶ ገዛኸኝ።
የስጦታችን ነገር ጋር ስንመለስ፤ ስጦታ የመቀባበል ባህል መልካም ሆኖ ብሎም በአቅም ሊሆን መገባቱ ሳይዘነጋ፤ ዐይንን ወደ አገርኛው ነገር ጣል ማድረግም መልካም ይሆናል። በእርግጥ ስጦታ ሰጪ ለዓይኑ መልካም የሆነ ነገርን ካየ፤ ሊሰጠው ለመረጠው ሰውም ጥቅም ይኖረዋል ብሎ ካመነ፤ የትኛውንም ነገር ስጦታ ብሎ ሊያቀርብ ይችላል።
ወደ ባህር ማዶ ለሚሄድ ሰው የአገር ባህልን የሚገልጽ ስጦታ ለመስጠት እግራቸው የሚኳትን ሰዎች ያጋጥሙናል። «ምን ልስጥ?» ብለው የሚጨናነቁም አሉ። ይሄኔ የፍቅር፣ የክብርና የምስጋና መገላለጫ የሆነውን ስጦታ፤ በአቅምና በምርጫ ሲሰጡ፤ ለአማራጭ የሚሆነውን ማቅረብም ከአቅራቢው ይጠበቃል።
እንደ ቀደሙት አበውና እመው ስርዓት፤ ሁሉም በእማሬው ባይሆን እንኳ ፍካሬው በዙ የሚል፤ ከሰሙ ይልቅ በወርቁ የሚናገር ምሳሌአዊ ፈጠራ የታከለበት እደ ጥበብ ሥራን ማቅረብ ይቻላል። ለዚህ ስጦታውና ችሎታው ያላቸውን ሰዎች ወደፊት አውጥቶ ማስተዋወቅም አስፈላጊ ነው። ከላይ እንዳነሳነው ወጣት ታምሩ ያሉ ለዐይን ግቡ የሆኑና ብዙ ምርጫን የሚሰጡ ምርቶችን ለሚያቀርቡም ማበረታቻ ሳያስፈልግ አይቀርም።
ዘንድሮ ምን እንስጥ/ እንሰጣጥ?
ከዲያቆን ዶክተር አቤል ጋር በነበረን ቆይታ ተከታዩን መልዕክት በመዝገቢያቸው አስተላለፈው ነበር። በዛም ላይ በአንድ በኩል የሰው ልጅ ለአምላኩ ልቡን ሊሰጥ እንደሚገባ ያነሳሉ። አያይዘውም አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ሰላም እየጠፋ ነውና፤ «ሰው ሰላምን ሊሰጥ ይገባል» ይላሉ። ሰላም በልብ የሚገኝ ነገር ነውና፤ ሁሉም በአቅሙ ሰላምን ቢሰጥ ሲሉም ጠይቀዋል።
እንግዲህ የገና በዓል በክርስትና እምነት የሰው ልጅ ከአምላኩ ከየትም የማይገኝ ስጦታን ያገኘበት ጊዜ ነው። ደግሞም ሕይወት ለእያንዳንዳችን አንድ ጊዜ የምትሰጠ ውድ ስጦታ መሆኗን ሁላችን እናውቃለን። ከዛም ከፍ ስንል፤ ኢትዮጵያ ለሁላችን የተሰጠች እናታችን አገራችን፤ እኛም ለእርሷ የተሰጠን ልጆችዋ ሕዝቧ ነንና፤ ስጦታችንን እናክብር። ዘንድሮ ስጦታችንን ሰላም እናድርገውና ሰላም ሰጥተን ሰላም እንቀበል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
ዳግም ከበደ