በኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥር በርከት ያሉ የመንግሥትና የግል የሚዲያ ተቋማት ይገኛሉ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለንን ግንዛቤ በማሳደግና ንቃተ ህሊናችንን ከፍ በማድረግ በኩልም የማይተካ ሚና ይጫወታሉ። ሁሉም የሚዲያ ተቋማት ህብረተሰቡን ማሳወቅ፣ ማስተማርና ማዝናናትን ዋነኛ ግባቸው አድርገው ይሰራሉ። ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት እና በህዝብ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ። የህዝብን ብሶትና እሮሮ በመፈተሽ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እልባት እንዲያገኙ ማድረግም ሌላኛው ተልዕኳቸው ነው።
ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የአገራችን ሚዲያዎች ሥራዎችን የሚሰሩት በወረት ነው የሚል ወቀሳ ይቀርብባቸዋል። ወረተኝነት በተለያየ አውድ የተለያዬ ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል። በዚህ ጽሑፍ ላይ ማንሳት የተፈለገው ግን አንድን ጉዳይ ለተወሰነ ጊዜ እየተቀባበሉ ካስጮሁ በኋላ ያጉዳይ የደረሰበትን ፍጻሜ ሳያሳውቁ አጀንዳውን እርግፍ አድርጎ መተውን ነው። ይህን ሀሳብ ያጠናክሩልኛል ብዬ ያሰብኳቸውን ጥቂት ነጥቦች በሚከተለው መልኩ አቅርቤያለሁ፤መልካም ንባብ።
ኤች አይ ቪ/ኤድስ
ከጥቂት ዓመታት በፊት ሬዲዮው፣ ቴሌቪዥኑ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶችም ሳይቀሩ የሚያወሩት ስለ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ነበር። በተደረገው ርብርብም ስለበሽታው በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል። የህዝቡ ግንዛቤ በማደጉም በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ላይ ይደርስ የነበረውን አድሎና መገለል በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሽታው ከአገራችን የጠፋ እስኪመስል ድረስ ትኩረት ተነፍጎታል። ይህም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሲገለጽ ሰምተናል። በበሽታው ስርጭት መጨመር ሚዲያዎችን በቀጥታ ተጠያቂ ማድረግ አይቻል ይሆናል። ቀጣይነት ባለው መልኩ የማሳወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሥራት የድርሻቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው ግን ከወቀሳ ሊያመልጡ አይችሉም።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዩ ትዝታን ጥሎ አልፏል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ መጀመር ይፋ የተደረገበት ቀን ነውና። ይህንም ተከትሎ በሁሉም ሚዲያዎች ግድቡን የተመለከቱ ተከታታይ ዘገባዎች ወደ ህዝብ ሲደርሱ ነበር። የግድቡ መጠናቀቂያ ጊዜ፣ የሚያስፈልገው የብር መጠን የሚጠናቀቅበት ጊዜ ተደጋግሞ ተነግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ህብረተሰቡ እያደረገው ስላለውና ሊያደርገውም ስለሚገባው አስተዋጽኦም ብዙ ብለዋል። ከቆይታ በኋላ ግን ለረጅም ጊዜ ግድቡ እየተሰራ ይሁን፣ ሥራው ይቁም ይጠናቀቅ ምንም መረጃ አልነበረንም። ሲጀመር ስለሚጠናቀቅበት ጊዜ ደጋግመው ሲለፍፉ የነበሩት ሚዲያዎች ሁሉ ይጠናቀቃል የተባለበት ጊዜ አልፎ እንኳን ለምን ብለው ለመጠየቅ አልደፈሩም። ግድቡ ስላለበት ደረጃና በቀጣይነት ስለሚወሰዱ ርምጃዎች ያወቅነውም ከለውጡ በኋላ መንግሥት በሰጠው መግለጫ ነው። ሚዲያዎችም ይህን ከእኛ እኩል የሰሙ ይመስለኛል።ጠንካራና ከአንድ ሰሞን ሞቅታ የተላቀቁ ሚዲያዎች ቢኖሩን ኖሮ የግድቡ ሥራ ያለበትን ደረጃ በየወቅቱ ያሳውቁን ነበር፤ እኛም በቂ መረጃ ስለሚኖረን ግድቡ ያለበት ደረጃ ሲገለጽ በጥፊ የተመታን ያህል ባልደነገጥን ነበር።
ችግኝ ተከላ
ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ዓመታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ ሲካሄድ ቆይቷል። ሚዲያዎቻችንም የችግኝ ተከላ የሚከናወኑባቸውን ዘመቻዎች በመከተል የዘገባ ሽፋን ሲሰጡ ነበር። ከተከላው በኋላ የት እንደደረሱ ግን ምንም አልነገሩንም። የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንመለከት በ2011 በጀት ዓመት ወደ 4 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን ተተክለዋል፡፡ በተለይ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ይሁን እንጂ የተከልናቸው ችግኖች ምን ያህሉ እንክብካቤ እየተደረገለት እንደሆነና ምን ያህሉ እንደጸደቀ ግን መረጃ የለንም። ሚዲያዎቻችንም ሽፋን አልሰጡትም፤ ምክንያቱ ዘመቻው አልፏልና።
የህዝቦች አብሮነትና የሀገር አንድነት
ዶክተር ዓብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ንግግሮችን አድርገዋል። በበዓለ ሲመታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግር ጨምሮ የሁሉም ንግግሮቻቸው ማጠንጠኛ ኢትዮጵያዊነትና የህዝቦች አብሮነት ነው። በዚህ ወቅት ብዙዎቹ ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው ኢትዮጵያዊነትና የህዝቦች አብሮነትን ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩበት ነበር። ታዲያ ይህ መሆኑ መልካም አይደለም ወይ? ሚዲያዎችስ ሊመሰገኑ አይገባቸውም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መልሱ አጭርና ቀላል ነው። ሚዲያዎች ኢትዮጵያዊነትና የህዝቦች አብሮነት ላይ መስራታቸው የሚያስመሰግናቸው እና ግዴታቸውም ነው። ለዚህም ብዙዎቻችን ለዘመናት ጆሮ ነፍገናቸው የነበሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ለበርካታ ሰዓታት በማየት ምስጋናችንን ለግሰናቸዋል። ትልቁ ችግር ግን ሥራው ከጥቂት ጊዜ ሞቅታ በላይ ሊዘልቅ አለመቻሉ ነው።
የተወሰኑትን ለማሳያነት አነሳን እንጂ ሌሎችም በርካታ ነገሮችን መዘርዘር ይቻላል። የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሙስና፣ የሴቶች እኩልነትና ተጠቃሚነት፣ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት…ወዘተ በተለያየ ጊዜ በብዙ ሆይ ሆይታ ያለፍናቸውና በአሁኑ ወቅት ግን ፊታችንን ካዞርንባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።
አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ግን የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሚዲያዎች ለምን ለወቅታዊ ጉዳዮች ትኩረት ሰጡ የሚል ትችት ማቅረብ አይደለም። ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃ ማቅረብ የአንድ ሚዲያ ዓብይ ሥራ መሆኑ የታወቀ ነውና። የተሰሩ መልካም ሥራዎችን ለማጠልሸት ያለመም አይደለም፤ ተከታታይ ክትትል እና ሽፋን ለሚሹ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰብ እንጂ።
በአጠቃላይ እንደአራተኛ መንግሥት የሚቆጠረው ሚዲያ ከእስካሁኑ በበለጠ የዜጎች ድምፅ መሆን ይገባዋል። ተከታታይነት ያላቸው የምርመራ ዘገባዎች በመስራት ለህዝብ ምሬት ምንጭ የሆኑ ችግሮች መልስ እንዲያገኙ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ፣ የገጠማቸውን ተግዳሮትና የተቀመጡ የመፍትሔ ሀሳቦችን በወቅቱ ለህዝብ ማድረስ ቢችሉ መልካም ነው።
በተለይ ከለውጡ በኋላ ሚዲያዎች ከቀድሞው የተሻለ ነጻነት አግኝተዋል። ይህን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተጀመሩ ስራዎችን በወረት ከመዘገብ ተላቀው ስራዎቹ የት እንደደረሱ፤ምን ችግር እንዳጋጠማቸውና ችግሮቹንስ በምን መልኩ መፍታት ይቻላል የሚሉ ነጥቦችን እያነሱ ለህብረተሰቡ መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ሲሰሩ ነው ትክክለኛ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ተወጡ ሊባል የሚችለው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ፋንታነሽ ክንዴ