ወይዘሮ ሚሚ ተስፋዬ፣ አቧራማ ከሆኑት የአምቦ ከተማ የጉልት ገበያዎች በአንዱ ድንች፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርትና ሌሎችም አትክልቶችን ከሚሸጡ እናቶች መካከል አንዷ ናቸው። ከዚህ የጉልት ገበያ በሚያገኙት ገቢም ከራሳቸውና ከልጆቻቸው አልፈው፤ ታማሚ እናታቸውን፣ እህትና ወንድሞቻቸውን ደጉሞ የማስተዳደር ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። በአምቦ ከተማ 06 ቀበሌ ተወልደው ያደጉ ተድረውም የወለዱ ቢሆንም፤ ህይወት ሁሌም ቀና አትሆንምና ከባለቤታቸው ከተለያዩ በኋላ የሚረዳቸው ባለመኖሩ እጅ ያጥራቸዋል። ቀን በገፋ ቁጥር ደግሞ ችግራቸው እየበዛ ራሳቸውን መቻል ተስኗቸው በእናታቸው ቤት ሳሉ ‹‹ኡቡንቱ ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ ማህበር›› ሊደግፋቸው፤ መጣ። ደረሰላቸውም። ወይዘሮ ሚሚ በተደረገላቸው ድጋፍም ዛሬ ላይ ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ለመደገፍ በቅተዋል።
‹‹ኡቡንቱ ለእኔ ከምንም በላይ አስታዋሽ ሰው ባጣሁበት በችግሬ ጊዜ የደረሰልኝ ዋስትናዬ ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮ ሚሚ፤ ከባለቤታቸው ተጣልተው ከወጡ በኋላ ምንም ስላልነበራቸው ለአራት ልጆቻቸው ለትምህርትና ሌሎች ወጪዎች የሚሆን ቀርቶ በልቶ ማደር እንኳን ችግር ሆኖባቸው እንደነበር ይናገራሉ። የኡቡንቱዎችን እርዳታ ያገኙት በዚህ ውስጥ እያሉ መሆኑን በመግለጽም፤ ኡቡንቱዎች ለንግድ የሚሆን የመነሻ ብር፣ ለልጆቻቸውም ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ገዝቶላቸው እንዲማሩ በማድረጉ ‹‹ማህበሩ ከሰው እኩል እንድሰራ፤ ከሰው እኩል ወጥቼ እንድገባና ከሰው ጋር የነበረኝ የተረሳ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲታደስ አድርጎኛል›› ይላሉ።
ወይዘሮ ሚሚ እንደሚሉት፤ በማጣታቸው ጊዜ በተለያዩ ጥሪዎች ሳይቀር ሰዎች ረስተዋቸው ቆይተዋል። አሁን ኡቡንቱ ባደረገላቸው ድጋፍ መስራት በመቻላቸው ግን ልጆቼን ምን ላብላ፣ ምን ላልብስ ሳይሉ ለማስተማር በመብቃታቸው ዛሬ ላይ አንዷ ልጃቸው አምስተኛ፣ ሁለተኛዋ ሶስተኛ፣ ሌሎች ሁለት ልጆቻቸው ደግሞ ሁለተኛ ክፍል ደርሰዋል። በኡቡንቱ ቤተሰቦች ጋር በየሳምንቱ ከሚጥሉት የ50 ብር እቁብ ባለፈም በተከፈተላቸው የባንክ ደብተር መቆጠብ ጀምረዋል።
‹‹በእስካሁን የኡቡንቱ ድጋፍ ራሴን፣ ልጆቼን፣ ታማሚ እናቴንና እህቴን ጨምሮ ስምንት ቤተሰቦች እያስተዳደርኩ እገኛለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ ሚሚ፤ ይሁን እንጂ የሚኖሩት ልጆቻቸውን ይዘው በቀበሌ ቤት ከእናታቸውና እህት ወንዶሞቻቸው ጋር በመሆኑ ‹‹የመኖሪያ ቤት ጉዳይ እጅጉን እየፈተነኝ ነው ይላሉ፤ በመሆኑም ኡቡንቱ መጠለያ ቤት የማገኝበትንና ከጥገኝነት ተላቅቄ ልጆቼን ያለሰቀቀን ከጎኔ አድርጌ የማስተምርበትን እድል ቢያመቻችችልኝ ደስተኛ ነኝ›› ሲሉ ጠይቀዋል።
እንደ ወይዘሮ ሚሚ ሁሉ ‹‹ኡቡንቱዎች በወደኩበት ሰዓት ነው ያነሱኝ፤›› የሚሉት ወይዘሮ የኔነሽ መኮንን፣ በሌላኛው የአምቦ ከተማ የጉልት ስፍራ ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎችም አትክልትና ፍራፍሬን ይዘው ተቀምጠው ያገኘናቸው እናት ናቸው። ወይዘሮ የኔነሽ፣ ‹‹ኡቡንቱዎች ሲያገኙኝ የሚደግፈኝ ባለመኖሩ የምበላው የምጠጣው አጥቼ በህመም አልጋ ላይ ወድቄ፤ የአልጋ ቁራኝነትም ከመድሃኒት ተጠቃሚነት ጋር ተዳምሮ እጅጉን ኑሮዬን አጎሳቁሎት ነበር፤›› ይላሉ። ኡቡንቱዎች ቀርበው በማነጋገር በመምከር ስራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን ገንዘብ፣ ለልጃቸውም ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ሰጥተው ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንድትገባ እንዳደረጉላቸው ይናገራሉ። እርሳቸውም ባገኙት ገንዘብና በተደረገላቸው ድጋፍ ንግድ በመጀመራቸው በስራቸው ውጤታማ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ።
እንደ ወይዘሮ የኔነሽ ገለጻ፤ ጉልት ውለው በሚያገኙት ገንዘብ ምግብና ልብስ ከመቻል አልፈው በባንክ መቆጠብ ጀምረዋል፤ ቀድሞ ሊወድቅ የነበረ መኖሪያ ቤታቸውንም ቀጥለው መስራት ችለዋል። በቀጣይም የቤት እቃዎችን ለማሟላት አስበዋል። ልጃቸውንም ምን አበላለሁ፤ ምን አለብሳለሁ ከሚል ጭንቀት ተላቅቀው ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ ሰው ሆነዋል። አሁንም ግን የተወሰነ መደጎሚያ ቢያገኙ ከዚህ በላይ ለመስራትና ለመለወጥ ዓላማ አላቸው። ሆኖም ‹‹ሌሎች እርዳታ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው እንደ ኡቡንቱ ሁሉ ሌሎችም ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል›› ይላሉ።
የነባሮቹን የወይዘሮ ሚሚ እና የወይዘሮ የኔነሽ መስመርን በመከተል በኡቡንቱን ድጋፍ ሰርቶ የመለወጥ ተስፋን ሰንቀው ከሰሞኑ የኡቡንቱን ቤተሰብ ከተቀላቀሉ 50 አዲስ እናቶች መካከል ወይዘሮ በቀሉ አዱኛ አንዷ ናቸው። ወይዘሮ በቀሉ እንደሚሉት፤ ባለቤታቸው እንጨት እየፈለጡ በሚያገኟት ገቢ አምስት ቤተሰብ ማስተዳደር እጅጉን ፈትኗቸው፤ የልጆች የትምህርት ወጪ፣ የጤናና ሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች የማይሞከሩ ሆነውባቸው ቆይተዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የኡቡንቱን ድጋፍ ማግኘታቸው ደስታ ብቻ ሳይሆን ሰርቶ የመለወጥ ተስፋና ሞራልን ፈጥሮላቸዋል። ባገኙት ድጋፍም የበግ እርባታ ለመጀመር ያቀዱ ሲሆን፤ በዚህ ስራቸውም ቀደም ሲል ሲደገፉ እንደነበሩት የኡቡንቱ ቤተሰቦች ሁሉ በቀጣይ ውጤታማ ሆነው በአደባባይ ለመናገር እንደምበቃ ተስፋ አለኝ ሲሉም ቃል ገብተዋል።
ኡቡንቱ የቃሉ መነሻ ደቡብ አፍሪካ ቢሆንም የአፍሪካ ፍልስፍና ተብሎ እየተወሰደ ያለ እሳቤ መሆኑን የሚናገሩት ዕጩ ዶክተር ሰለሞን ዓለሙ፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የኡቡንቱ ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኡቡንቱ በትርጉሙም መተባበርን፣ በጋራ መኖርን፣ እኔ ዛሬ የሆንኩትን ነገር የሆንኩት በሌሎች ሰዎች ምክንያት ነው የሚል ቀና ሃሳብን የያዘ ነው። ይህ ደግሞ አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን በሙሉ የሚገልጽ እሳቤ፤ በተግባርም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም አፍሪካውያን ዘንድ የሚንጸባረቅ ነው።
ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ያለውን እድር ሰዎች ላይ ጉዳት በደረሰ ጊዜ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ለማጽናናትና ለመደገፍ የሚጠቀሙበት አገር በቀል ባህላዊ ተቋም ነው። ይህ ደግሞ ከኡቡንቱ ጋር የሚሄድ እሳቤ ሲሆን፤ በዚህም በግል ማድረግ የሚቻልን ጥቂት ነገር በጋራ በመሆን ችግሮችን ለማለፍ የሚያስችል ነው። ይሄም ‹‹የእኔ ጉዳት ያንተ/ቺ ጉዳት ነው፤ ያንተ/ቺ ደስታ የእኔም ደስታ ነው፤ ያንተ/ቺ ጥቃት የእኔም ጥቃት ነው፤ አንተ/ቺ ከፍ ስትል/ዪ እኔም ደስ ይለኛል፤›› የሚል አጠቃላይ እሳቤን የያዘ ነው።
ኡቡንቱን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ለመመስረት ያበቃውም እርሳቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ዎርክ የሶስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒ.ኤች.ዲ) ሲማሩ ህጻናትን የሚረዳ ድርጅት ፕሮግራም ኢቫሉዬሽን ስራን በሚያከናውኑበት ወቅት የተመለከቱት ጉዳይ ነበር። ይሄም በድርጅቱ ይረዱ የነበሩ 30 ልጆች በየወሩ ይሰጣቸው የነበረው 50 ብር ለልጆቹ ለመማር ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክት የነበረ መሆኑ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ይህን 50 ብር ለመውሰድ እስከ ሁለት ሰዓት በእግራቸው ተጉዘው ከገጠር ይመጡ ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዴ ይሄን ያክል በእግራቸው ተጉዘው ያንን 50 ብር የማያገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው በመስማታቸው ‹‹እኛ በራሳችን ብንደራጅ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ለምን አንችልም›› የሚል ጥያቄ ያድርባቸዋል። ይሄንንም ፎቶ ሲያነሳላቸው ለነበረ ሰው ሲያጋሩት እሱም ስሜቱ ተነክቶ ስለነበር ሁለቱ በየግል ቢያንስ አንዳንድ ልጅ ለመርዳት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ።
ይህንኑ ሃሳብ 12 የስራ ባልደረቦቻቸው ተጋርተው የውጭ እርዳታን በመፈለግ መርዳትን ሳይሆን በውስጥ ያለ ሀብትና አቅምን ተጠቅሞ የመደገፍ አካሄድን ተከትለው በነፍስ ወከፍ በወር 100 ብር እያዋጡ እአአ በጥቅምት 2014 የማህበሩን ህጋዊ ሰውነት በማረጋገጥ ወደ ስራ ገቡ። በዚህ መልኩ በ12 ሰዎች የ100 ብር መዋጮ የተጀመረው ኡቡንቱ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎች ሃሳቡን ስለወደዱትና እየተሳተፉበት ስለመጡ አሁን ላይ ወደ 460 አባላት ያሉት ቤተሰብ ተኮር የልጆች የበጎ አድራጎት ማህበር ሆኗል። በራስ አቅም መስራት በመቻላቸውም የማህበሩን ህልውና ቀጣይ ያደረገው ሲሆን፤ በዚህም እነርሱ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ እስካሉ ድረስ ብቻም ሳይሆን ዩኒቨርሲቲው እስካለ ድረስ ኡቡንቱ ይቀጥላል የሚል ጽኑ እምነት አላቸው።
ማህበሩም ለመደገፍ በሚያደርገው ሂደት በተቻለ መጠን ሊደገፉ የሚገባቸው ሰዎች እንዲመረጡ ተደርጓል። ለዚህም ከከተማው የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት እንዲሁም ከቀበሌዎች ጋር በቅንጅት እየተሰሩ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ በመጀመሪያ ዙር ለይተው ከሰጧቸው 40 ቤተሰቦች ውስጥ ቤት ለቤት ሄደው ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት 26ቱን ተቀብለዋል። በወቅቱ ለመለያ የተጠቀሙት መስፈርትም አንድም የሚማሩና ለትምህርት የደረሱ ልጆች ያሏቸው መሆኑ፤ ሁለተኛም በእናት ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰብ መሆናቸው ነበር።
ይህ ድጋፍ ልጆችን ማገዝ ቢሆንም፤ ሂደቱ ግን ልጆችን በቀጥታ ከመደገፍ ቤተሰብ አቅም ፈጥሮ የራሱን ልጆች እንዲንከባከብ ማስቻል ላይ የተመሰረተ ነው። ምክንያቱም ቤተሰብ ኡቡንቱ አስተማረልኝ ሳይሆን እኔ አስተማርኩ፤ የሚል እሳቤን በውስጡ መያዝ ስላለበት ነው። የትኛውም ቤተሰብ ደግሞ ከተደገፈና አቅም እንዲፈጥር ከተደረገ ልጁን ለመንከባከብና ለማስተማር አያንስም። ማህበሩን ቤተሰብ ተኮር የልጆች ድጋፍ የተባለበት ምክንያትም ልጅን ነጥሎ ከመደገፍ ይልቅ ሙሉ ቤተሰብን ደግፎ ማብቃት ላይ ስለሚያተኩር ነው።
ይሄን እውን ለማድረግ ደግሞ በርካታ ድጋፎች የሚደረጉ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ መረጣ እንደተካሄደ ስለ ኡቡንቱ ዓላማና ኡቡንቱ ከእነርሱ ምን እንደሚጠብቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ይሰራል። የመነሻ ገንዘብ ቢያገኙ ምን መስራት እንደሚፈልጉ በመጠየቅም ስለስራው በቤተሰብም በቡድንም ያማክራል። በንግድ ስራ፣ በቁጠባና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ስልጠና ይሰጣቸዋል። ከዚህ በኋላ በትንሹ ስራ መጀመር የሚያስችላቸውን ገንዘብ (በነፍስ ወከፍ እስከ አምስት ሺህ ብር) በስማቸው የባንክ ደብተር ከፍቶ ይሰጣቸዋል።
ይሄን ገንዘብ ለልጆች ደብተርና ዩኒፎርም በሚል እንዳያባክኑ ለአንድ ጊዜ የተማሪዎች ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ይገዛላቸዋል። በሁለተኛው ዓመት ግን ደብተርና እርሳስ በራሳቸው እንዲገዙ ነው የሚፈለገው። ምክንያቱም ልጆቻችንን አስተማርን እንጂ ኡቡንቱ ረዳን እንዲሉ አንፈልግም። ከዚህ ባለፈ እንደ ብርድልብስ፣ አንሶላ፣ ፍራሽና ሌሎችም ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረግላቸዋል። የህክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን ሲባልም ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ከነቤተሰቦቻቸው ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።
በዚህ መልኩ የሚደገፉ ቤተሰቦች ለሶስት ዓመታት የሚቆዩ ሲሆን፤ ከሶስት ዓመት በኋላ ተመርቀው ይወጣሉ። ከተመረቁ በኋላ የቁሳቁስና ገንዘብ ድጋፉ የሚቋረጥ ቢሆንም፤ የማማከርና የህክምና አገልግሎቱ ግን ይቀጥላል። በዚህ መልኩ አዳዲሶች ሲተኩ፤ የቆዩት ተመርቀው ሲወጡ አሁን ላይ የድጋፍ ሂደቱ አምስተኛ ዙር ላይ ደርሷል። በዚህ ወቅት በድምሩ ከ860 በላይ የቤተሰብ አባል ያላቸው 180 ያህል ቤተሰቦች በማህበሩ እየተደገፉ ይገኛል።
በተሰጣቸው ድጋፍ በተለያየ ምክንያት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን ያልቻሉ ቤተሰቦች ካሉም ተጨማሪ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል። ለምሳሌ በመጀመሪያው ዙር አራት ሰዎች (በህመምና ወሊድ ምክንያት) ውጤታማ አልነበሩም። ለእነዚህ ተጨማሪ ድጋፍ ሲደረግ፤ ውጤታማ ለሆኑት ደግሞ ለበለጠ ውጤት እንዲበቁ ማበረታቻ ይደረግላቸዋል። በዚህም ምንም እንኳን የስኬታማነታቸው ደረጃ ቢለያይም 20ዎቹ የማህበሩን ድጋፍ የማይፈልጉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ባንክ ተጠቅመው የማያውቁት ጭምር በባንክ ገንዘብ ማስቀመጥ፤ የቤት እቃዎቻቸውን ማሟላት፤ ማህበራዊ ትስስራቸውን ማጠናከር እና ገቢያቸውንም ማሳደግ ችለዋል።
ዕጩ ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ብዙ ችግር መኖሩ ቢታወቅም፤ አሁን መርጠው በማህበሩ እየረዱ ያሉት ቤተሰብና ልጆችን ነው። በቀጣይ አቅመ ደካሞችንና አዛውንቶችን ለመደገፍ፤ የህጻናት መንከባከቢያ ማዕከል ለማቋቋምም እያሰቡ ነው። አቅመደካሞችና አዛውንቶች ደግሞ አነስተኛ ቢዝነስ ጀምረው ራሳቸውን ያሻሽላሉ የሚባሉ ሳይሆን፤ ከድጋፍ ባለፈ ማረፊያም ይፈልጋሉ። ይሄን ታሳቢ በማድረግም አረጋውያንን መንከባከብ የሚያስችል ‹‹ኡቡንቱ መንደር›› በሚል የተለያየ ሙያ ያላቸውን አባላት በማንቀሳቀስ 100 ያክል በዝቅተኛ ወጪ የሚገነቡ ቤቶችን ለመስራት አስበዋል።
በዚህም ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ጋርም እየተነጋገሩ ቢሆንም በመሬት አቅርቦት ላይ ችግር እየገጠማቸው ነው። በመሆኑም ስራው የከተማ አስተዳደሩን ጫና የሚቀንስ መሆኑን በመረዳት የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ጉዳይን እንዲፈታላቸው ይፈልጋሉ። ምክንያቱም እነዚህ ቤቶች አንድም አቅማቸው የደከመ ሰዎች በህይወት እስካሉ የሚያርፉበት እንዲሆን፤ ሁለተኛም መንደሩ ለቤት እድሳትና መሰል ጉዳዮች ራሱን በራሱ እንዲችል አነስተኛ የንግድ ማዕከላት (ዳቦ ቤትን የመሳሰሉ) እንዲኖሩና ሌሎች ተደጋፊዎች ራሳቸውን እንዲዶጉሙ የሚደረግበት ነው።
‹‹ስራችን የብርጭቆን ግማሽ ሙሉ የማየትና ስራዎችን ማበረታታት ላይ ያተኮረ፤ ድጋፉም በዛው ልክ ጠንክረው እንዲሰሩ የማስቻል ነው፤›› የሚሉት ዕጩ ዶክተር ሰለሞን፤ በዚህም ተረጂዎቹ እየደገፋቸው ያለው መንግስት ወይም የውጭ ረጂ ድርጅት አለመሆኑንና ህብረተሰቡ ራሱ መሆኑን ሲረዱ የሚደረግላቸውን ድጋፍ ከማጥፋት ይልቅ ለውጤት ለማብቃት የሚተጉ፤ በዛው ልክም እየተለወጡና ውጤት እያመጡ፤ ቃላቸውን ጠብቀውም የተሰጣቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እየተጉ መሆኑን መገንዘብ መቻሉን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ዜጎች የበለጠ ዜጎችን እንዲረዱ ያነሳሳ፤ ከተናጥል ይልቅ ሰብሰብ ብሎ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣትም ያስቻለ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ባለው ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ባለፈ ከ15 የዘለሉ የአምቦ ከተማ ማህበረሰብ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ በአባልነት እየተሳተፉ ሲሆን፤ በቀጣይም ይሄው ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደመሆኑ አባል ያልሆኑ ስታፎችና አቅም ያለው የከተማው ህብረተሰብ አባል ሆነው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ይሄን ስራ በአግባቡ መምራት ከተቻለ በየትኛውም ዩኒቨርሲቲ አካባቢ መሰል ማህበረሰብ በመኖሩ ልምዱ ሊሰፋ የማይችልበት ምክንያት የለም። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ያለው የቁሳቁስ፣ የአስተዳደር ቢሮና ሌሎች በርካታ ድጋፎችም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሊለመድ፤ በተለይም በየዩኒቨርሲቲዎች ተበላሽተው የሚቀሩ እና በትንሽ ገንዘብ የሚሸጡ ንብረቶችን እንደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ለመልካም ተግባር/ለድጋፍ ማዋል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 24/2012
ወንድወሰን ሽመልስ