
በየም ብሔረሰብ ተወላጆቹ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የራሳቸውን የመቀበሪያ ሳጥን እና መከፈኛቸውን (መገነዣቸውን) ቡልኮ ያዘጋጃሉ። ቀደም ብለው በማዘጋጀታቸው ልጆቻቸውም ሆኑ ዘመድ አዝማዶቻቸው እንዲሁ ዕድራቸው ለሳጥን እና ለከፈን መግዣ ብሎ የሚያወጣው ገንዘብም ሆነ የሚባከን ጊዜ አይኖርም። የለቅሶ ሥነ ሥርዓቱ ግን እንደ እድሜ ደረጃው ቢለያይም በጭፈራና ለቅሶ ሀዘንን በመግለጽ የሁሉንም የብሔረሰቡን የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ያንፀባርቃል።
ሟች በሕይወት ዘመናቸው ያዘጋጁት ሳጥን ለዚሁ ተብሎ ወደ ተቆፈረው ጉድጓድ የሚሄደው እና ለቀብር ወደተዘጋጀው ጉድጓድ የሚገባው ከአስክሬኑ ቀድሞ ነው። በብሔረሰቡ ይሄ የሚሆነው ሳጥኑ በጣም ተጠርቦ የሚዘጋጅ ትልቅና ከባድ በመሆኑ ከአስክሪኑ ጋር ሲሆን የበለጠ ስለሚከብድም እንደሆነ ይነገራል። አስክሬኑ በቃሬዛ ሄዶ ቀድሞ ጉድጓድ ውስጥ ወደ ገባው ሳጥን ይገባና ግብዓተ መሬት ይፈፀማል። አስክሬኑ ወደ መቃብር የሚሸኘው እጅግ በደመቀ ለቅሶና በጭፈራ በታጀበ ሥነ ሥርዓት ነው።
ባሕል የአንድ ብሔረሰብ አኗኗር ውጤት ስለመሆኑ ጥናቶች ያመላክታሉ። የሰው ልጅን ባሕል አስመልክቶ እ.ኤ.እ በ1900 በተደረገ ጥናት «ባሕል» የኅብረተሰቡ ቋንቋ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ጭፈራ …ሌሎችም መገለጫዎች ጎልተው የሚንጸባረቁበት ዐሻራዎች ነው።
በመምህር አካለ ወልድ የተዘጋጀው መዝገበ ቃላት እንደሚያመላክተው ባሕል የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተገኘ ነው። ይሄው መዝገበ ቃላት የባሕል ምንነትን አስመልክቶም አንድ ሰው በማኅበረሰብ አባልነቱ የሚያገኘው እውቀት፣ እምነት፣ ኪነጥበብ፣ ልምድ፣ ግብረ ገብነት (Moral) ሲሆን በአጠቃላይ የአንድ ማኅበረሰብ የማንነቱ ዐሻራ ያረፈበትና መገለጫ ማለት ስለመሆኑም ትንታኔ ይሰጣል። ከማኅበረሰብ ጋር እያደገና እየተለወጠ የሚሄድ የሰው ልጅ የተግባር ውጤት ነው ይለዋል።
እ.ኤ.አ በ1961 ፍራንሲስ ኢ ሚርል አተያይ ደግሞ ባሕል እውቀትን፣ እምነትን፣ ሥነ-ጥበብን፣ ሞራልን፣ ሕግን፣ ሀገረሰባዊ ልማድን፣ የተለያዩ ችሎታዎችና ተግባራትን የሚያጠቃልል ሥርዓት ነው። ኢትዮጵያ በዚህ በኩል የካበተ ሀብት ያላት ሀገር ስትሆን ለዛሬ የየም ብሔረሰብ ባሕላዊና እና ታሪካዊ እሴቶች ከሆኑት አንዱን የየም ብሔረሰብ የለቅሶ ሥርዓት እናስነብባለን። በመምህር አካለ ወልድ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ባሕል ከማኅበረሰብ ጋር እያደገና እየተለወጠ የሚሄድ እንዳሉት ሁሉ የየም ብሔረሰብ የለቅሶ ሥርዓት በዚሁ መንገድ እየተቃኘ የመጣ ወይም ከዚሁ ባሕል የተቀዳ ነው ማለት ይቻላል።
የም የሚለው ስያሜ የብሔረሰቡ መጠሪያ ሲሆን “የምሳ” ደግሞ የብሔረሰቡ መደበኛ ቋንቋ ነው። ብሔረሰቡ ከአስራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ታዋቂና ጠንካራ መንግሥት መስርቶ ይኖር እንደነበርም የጥናት መዛግብት ያስረዳሉ። የለቅሶ ሥነ ሥርዓቱ ታሪክ መነሻም ከዚሁ ጊዜ ጋር የተያያዘ ነው። የየም ብሔረሰብ የለቅሶ ሥርዓትን አስመልክቶ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሶሻል ሳይንስና ሂዩማኒትስ ኮሌጅ በ2011 ዓ.ም ባደረገው ጥናት ደመቀ ጀንበሬ እንዳመላከተውም የለቅሶ ሥነ ሥርዓቱ በመሠረተ ባሕል ሞዴል ንድፈ ሃሳብ የተቃኘ ነው።
ጥናቱ እንዳመላከተው፤ በየም ብሔረሰብ ሞት የፈጣሪ ቁጣ ነው ተብሎ ይታመናል። እንዲህ ተብሎ የሚታመንበት ሞት በየሞች ላይ ሲደርስም ታዲያ ራሱን የቻለ የክዋኔ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። ሥነ ሥርዓቱ በሟቹ ዕድሜ፤ ጾታ እንዲሁም በማኅበራዊ ደረጃ የተከፋፈለ ነው። ከማኅበራዊ ደረጃ አንፃር ለአብነት እንደሚጠቅሰውም ሟቹ ንጉሥ፤ የጎሳ መሪ፤ ጀግና እንዲሁም የዕድሜ ባለፀጋ ከሆነ የሚከወነው የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ይሄንኑ ግብሩን ታሳቢ ያደረገ ነው። የሟች «ዚዛ» የሚሉት እና በአማርኛ ሙሾ የሚሰኘው ሥርዓትም የሟችን ተግባርና ማንነት በብርቱ የሚያመላክቱ ናቸው።
የለቅሶ ሥነ ሥርዓቱ ከዕድሜ ወይም ከጾታ አንፃር ሲታይ የአባ ወራው ወይም የእማ ወራዋ ቀድሞ መሞት እንደ የሟቹ ቋንቋ ኪኖ እንደ አማርኛው ትርጓሜ ደግሞ ቡልኮ የሚቀመጥበትን ቦታ ይወስናል። በዚዛ (ሙሾ) ክወናውም ልዩነቶች እንደሚፈጥር በጥናቱ ተጠቁሟል።
የየም ብሔረሰብ የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ለየሞች ብዙ ነገራቸው ስለመሆኑም ጥናቱ ያነሳል። ማንነታቸውን እና ማህበራዊ ትስስራቸውን ያጠናክሩበታል፤ ይገነቡበታል። በተጨማሪም የማኅበረሰቡን ታሪክ፣ እምነትና አመለካከት የሚገልፁበት አጋጣሚ ነው፡፡
“ብሔረሰቡ ራሱን የቻለ የቀብር እና የለቅሶ ሥርዓት አለው” ያለን ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የፕሮሞሽን ባለሙያው በረከት ይገዙ ነው። በረከት እንደነገረን በብሔረሰቡ አንድ ሰው ሲሞትም ወዲያው አይናገርም። ቀድም ብሎ ለቤተዘመድ፤ ሌሎች ሌሎች ሰዎች መልእክት እንዲደርስ ይደረጋል። እነሱ ተጠርተው ከመጡና አንድ ሁለት ቀን ከቆየ በኋላ ነው ለቅሶ የሚጀመረው። ምክንያቱም ለለቅሶ ሥነ ሥርዓቱ የሚያስፈልግ ዝግጅት ማድረግ እንዲቻል ነው። የሚደረገው ዝግጅት ከምግብና መጠጥ ጀምሮ መልእክት ደርሷቸው ከቀብር በፊት እንዲሰበሰቡ የተደረጉ እንግዶችን ማስተናገድ የሚያስችል ሲሆን ዝግጅቱ በሙሉ በድብቅ ነው የሚደረገው። በተለይ ንፍሮ የሚቀቀለው ቆጮ የሚጋገረው፤ የተለያዩ መጠጦች ከቀብር መልስ ለለቀስተኛ መስተንግዶ የሚቀርቡ ዝግጅቶችም እንዲሁ በዚሁ ጊዜ በተለይም ሟቹ እንደ ነገ ሊቀበር ሲል ነው በድብቅ የሚዘጋጁት።
ሟቹ የቤቱ አባወራ ከሆነ በሕይወት ዘመኑ ሞቱን ታሳቢ አድርጎ ያዘጋጀው ቡልኮ ጎጆ ቤት ላይ ይሰቀላል። ሲሰቀለም የአጋዘን ቀንድ እላዩ ላይ ከተደረገ በኋላ ቡልኩ እላዩ ላይ ይጣላል። ይሄም የሚሆነው በብሔረሰቡ ባሕል የቤቱ ራስ አባወራ ነው ተብሎ በመታመኑ ሲሆን በዚህ መልኩ ቡልኮውና ቀንዱ የሚሰቀለውም የቤቱ አባ ወራ ወይም ትልቅ ሰው መሞቱን ለማመላከት ነው።
ሟቿ የቤቱ እማወራ ከሆነች ቡልኮው አጥር ላይ ነው የሚንጠለጠለው። ይሄ ሥነ ሥርዓት ንጋት ላይ ከተፈፀመ በኋላ የተሰባሰቡት ለቀስተኞች ለቅሷቸውን በጩኸት ያውጃሉ። ከዚህ ጀምሮም ጥሪ ተደርጎላቸው ቀደም ብለው በሟች ቤት ውስጥ ከተገኙ ዘመድ አዝማዶች በተጨማሪ የትኛውም የአካባቢው ነዋሪ እና ከሟች ጋር ትውውቅ ያለው ለቀስተኛ ወደ ለቅሶው ቤት ይጎርፋል። በባሕሉ ወንዶች ወደ ለቅሶው ቤት የሚመጡት ጫፍና ጫፉ ላይ ብረት ያለው ዱላ ወይም ጦር ይዘው ነው። ሴቶች ደግሞ ነጣላቸውን አዘቅዝቀውና ከወገብ በታች አስረው ነው። ሴቶች ጦርና ዱላቸውን ይዘው በተመሳሳይ መሬት እየነኩ እየተነሱና ወደ ኋላ እየሄዱ ያላቅሳሉ።
ይሄኔም ሀዘንተኞቹ ተነስተው ይቀበሏቸዋል፤ ይተቃቀፉና ሀዘናቸውን ይገልፃሉ። ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በዚህ መልኩ በተለይም ሴቶች ነጠላቸውን እንዳዘቀዘቁ ልዩ ትይንት ባለው መልኩ መሬት በመንካት ወደኋላ መለስ ቀለስ እያሉ ሀዘንተኞችን ያስለቅሳሉ። መጨረሻ ላይ ሀዘንተኞችን ያቅፏቸውና ይቀመጣሉ። አዲስ ለቀስተኛም ሲመጣ የሚያስተናግዱት በተመሳሳይ መልኩ ነው። ሀዘንተኞችን ያላቅሳል፡፡
ለቅሶው «ዌውዋ ቴጋና ኬስዋ » ወይም በአማርኛ (አንተ እገሌ/አንቺ እገሌ ልጥራህና ውጣ) «ካቡዋ» «… (ተነስልኝ፣ ተነስልኝ.. )» ያንዋ ካቢን አምኒዋ« (መጥቻለሁ ተነስና እንሂድ)፤ »ጉዙዋ አፊዕቴቶሶ?» (ንቃ እንጂ አንቀላፍተሃል ወይ ?) አዞዞ አኔ ግዕተፋዋ አቴሶ (ሌላ ቀን አታኮርፍም ነበር ምን ሆነሃል?) ካሳዬፊን ማኮንዋ ( ቀና በልና ልንገርህ) ኬሳ ኡጶዋ አፋኖሶ ? (ውጣና ላግኝህ የለህም ወይ?) በሚል ልዩ ለዛ ባለው ዜማ እና ትርኢታዊ እንቅስቃሴ የታጀበ ነው። ሟች በመልካምነቱ የሚታወቅ ትልቅ ሰው ከሆነ «አውኔን ኒኔን ኮኢኛ» በአማርኛው ከዛሬ ጀምሮ ሁለም ነገር በእርሶ አበቃ ይሰኝለታል።
ይሄ ዓይነቱ ልዩ ትእይንት ያለው ለቅሶ እየቀዘቀዘ ለቀስተኛውና ሀዘንተኞቹ እየደከሙ ሲመጡ ደግሞ እንደገና በብሔረሰቡ ዘንድ ዚዛ በአማርኛው ሙሾ የተሰኘው እና ሟች የሚወደስበትም በቁጭት የሚነሳበትም የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ይተካል። ጀግንነቱ በሕይወት ዘመኑ ያደረገው በጎ ነገር ሁሉ ይነገራል፡፡
አቶ በረከት እንደሚናገረው፤ በየም ብሔረሰብም ትልልቅ ሰዎች በሞት ሲለዩ ሟች የሚሸኝበትና የብሔረሰቡ የተለያዩ እሴቶች መተዋወቂያና ማስተላለፊያ ከሆኑ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ የዚዛ ክወና ነው፡፡
ሀዘንተኞችን ለማጽናናትና ለማበረታታት በተለየ አቀራረብ ታጅቦ የሚከወን ከየም ብሔረሰብ የለቅሶ ሥርዓት ገጽታዎች ውስጥ አንዱ ክፍል እንደሆነም ያነሳል፡፡
የብሔረሰቡ የሀገር ሽማግሌ አቶ ዲጋ ቦሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በዚዛው ክወና ላይ ወንዶችም ሴቶችም ይሳተፋሉ። የዚዛ ክወናው መሪ፣ አውጪ፣ ተቀባይና ታዳሚ ያለው ነው። ጋሻ፣ ጦር፣ የአጋዘንና የድኩላ ቀንድ፣ የአንበሳና የነብር ቆዳ፣ በየምኛ ቋንቋ «ሾሮዶ» ከእንሰት ተረፈ ምርት የሚሠራ የልብስ ማስቀመጫ ሳጥን የዚዛ ክወናውን የሚያጅቡ ቁሳቁሶች ናቸው።
ክወናው ካለ ወይም የቀንድ ቡድን ሲደርስ ነው የሚጀመረው። ቡድኑ በመሪው አማካኝነት የቲሻ ሥርዓቱን ካከናወነ በኋላ ትንሽ አረፍ በማለት ውሃ ማጠጫ የሚሆን ምግብ ቀምሶ ይመለስና የዚዛ ክወና ውስጥ ይገባል። ክወናው የራሱ የሆነ አዝማችና የአካል እንቅስቃሴ (ውዝዋዜ) ሥርዓት አለው። ሁለት ሴቶች ነጠላቸውን ወገባቸው ላይ በማሰር ከሟች በራፍ በኩል ከሀዘንተኞች ፊት ሆነው የሾሮድው ክዳን እንዳይወልቅ እና እጃቸውንም እንዲያሳምም በጨርቅ ማሰር ይጠበቅባቸዋል።
ወደ ቀኝ ወደ ግራ ወደፊት ወደ ኋላ ነጠር ነጠር እያለ ሾሮዳውን ከመሬት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ እያጋጩ በባለ ሁለት ምት የሙዚቃ ቅኝት ድም፣ ድም፣ ድም… በሚል ድምጽ ያጅባሉ። ጋሻ የያዙ ወንዶች በፊናቸው ፊታቸውን ሾሮድ ወደሚመቱ ሴቶች በማድረግ በጦር ዘንጋቸው ጋሻቸውን በሾሮዳው ምት ልክ እያጋጩ እንዮ የዚዛ ቅኝቱ የዜማ ባሕሪ ወደፊት ወደኋላ ሄድ መለስ በማለት እንዲሁም በክብ መስመር በመዞር ይከውናሉ። በትከሻቸው ወይም በጭንቅላታቸው ቀንድ የተሸከሙት፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ከአንገታቸው እስከ ወገባቸው የለበሱት ወንዶች ቡድንም በፊት መሪው አማካይነት በሰልፍ በመሆን መጀመሪያ ረጋ ያለ እንቅስቃሴ እያደረገ የሟችን መኖሪያ ቤት ዞሮ በመመለስ ከተመረጠው የዚዛ ክወና ዜማ ቅኝት ጋር ይዘላል።
የዚዛ ሥርዓት ለቀስተኞች የሚሳተፉት በሁለት መልኩ ሲሆን አንደኛው ሙሉ በሙሉ በዚዛ ክወናው በመግባት ሁለተኛው ዳር ሆኖ በትወናው በመመሰጥና በእንሰት ጥላ በመቀመጥ ነው። በአጠቃላይ በክወናው አቧራው ሲቦን፣ የደከመው ሲወጣ ፤ አዳዲሶች ሲቀላቀሉ እጅግ እየደራ የለቅሶ ቦታ መሆኑ ቀርቶ ወደ ጭፈራነት ይቀየራል። በዚህ ጊዜ በየምኛ ቋንቋ ካሞ፤ በአማርኛ ደግሞ የሟች ሴት ልጆች ወይም እህቶች በለቅሶ ጩኸት ዚዛውን በመበተን ወደ ሀዘን ድባብ ይቀይሩታል። እሳቸው እንደነገሩን ካሞ የሚባሉት ትዳር ይዘው የሚኖሩ የሟች ሴት ልጆች ወይም እህቶች ጋር የለቅሶ ሥርዓቱን የሚያሞምቅ ቡድን ሲሆን ለቅሶ ሲከሰት በቡድን ተደራጅተው ለቅሶ ቤት በመምጣት ለቅሶውን በጩኸት የሚያደምቁ ናቸው።
በዚህ ሁኔታ የለቅሶው ሥርዓት ሲከናወን ቆይቶ አስክሪኑ ሊሸኝ ይነሳል። አስክሪኑ ከመነሳቱ በፊት ሟቹ አባወራው ከሆነ ጎጆ ቤቱ ላይ የተሰቀለው ቡልኮ፤ ሟቹ የቤቱ እማወራ ከሆነች በአጥሩ ላይ የተንጠለጠለው ቡልኮ ይወርዳል። ዋናው ለአስክሪኑ ከፈን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የቡልኮው ጥለት ቤት ውስጥ የሟች ታላቅ ሴት ልጅ ካለች ይሰጣታል። አንገቷ ላይ ታስረዋለች። ይሄም አንድም ሀዘን መግለጫ ሁለትም የሟቹ ልጅ መሆኗን ማመላከቻ በመሆን ያገለግላል፡፤ ለቀስተኛው የሚሰናበታትና የሚያላቅሳት በዚሁ ምልክት መሠረት የሟች የበኩር ልጅ መሆኗን በማረጋገጥ ነው።
የሟች ግብዓተ መሬት ከተፈፀመ በኋላ አባቶች የሟቹን ቤተሰብ ፣ ሀዘንተኞችንና ለቀስተኞች በሙሉ በሕይወት ዘመናችሁ መቃብር አስቆፍሩ፤ ሳጥን አሠሩና አዘጋጁ የሚልና ሌላም በርካታ ምርቃት ይመርቃሉ። ምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄደው ከቀብር መልስ በዛው ቀብር በተከናወነበት ሥፍራ ነው። በስተመጨረሻም ወደ ላይ ይዘውት የነበረውን ቀንድም ሆነ ዱላና ጦር ወደ ታች በመዘቅዘቅ ወደ ቤት ይመለሳሉ። ተመልሰውም ለሀዘን ተብሎ የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ይመገባሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም