
ከመጻሕፍት ጀርባ ላይ በታዋቂ ሰዎች አስተያየት ይጻፋል፡፡ ታዋቂ ሲባል ታዲያ ዝም ብሎ በሆነ አጋጣሚ ታዋቂ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን አስተያየቱን ለመጻፍ የሚያስችል የሙያ ቅርበት ያለው ታዋቂነት ሲሆን ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ጀርባ ላይ አስተያየት የሚጽፉት በብዛት ደራሲዎች ናቸው፡፡ ታዋቂ እና ልምድ ያለው ደራሲ ሲሆን ለአዳዲስ ደራሲዎች ረቂቁን በማየት አስተያየት ይጽፋል፡፡ የሙያ መጽሐፍ ሲሆን ደግሞ ለዚያ ሙያ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ወይም ምሁራን አስተያየት ይሰጡበታል። ለምሳሌ የታሪክ መጽሐፍ ከሆነ አስተያየት የሚጽፉበት የታሪክ ምሁራን ናቸው ማለት ነው፡፡
ይህ በመጽሐፍ ጀርባ ላይ የሚሰጥ አስተያየት በአማርኛ ምን እንደሚባል በብዙዎች የተለመደና የሚታወቅ ቃል ስላላገኘሁለት ‹‹ብለርብ›› በሚለው የእንግሊዝኛ ቃል እቀጥላለሁ፤ ወይም ለዚህ ጽሑፍ ‹‹የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት›› በሚለው እንግባባለን፡፡
አዲስ መጽሐፍ ታተመ ሲባል ስንሰማ፣ ወይም ከመጽሐፍ አዟሪ ላይም ሆነ በሌላ አጋጣሚ አዲስ መጽሐፍ ስናገኝ የመጀመሪያ ዕይታችን የፊት ሽፋኑ ላይ ነው፡፡ ቀጥሎ ግን የጀርባ ሽፋኑን ማየት ነው፡፡ ምናልባት ይህ እንደየ ግለሰቦች ምርጫ ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፤ እኔ የመጽሐፍ የፊት ሽፋን ላይ ያን ያህልም ትኩረት ስለማላደርግ ቶሎ ብዬ የጀርባ ጽሑፎችን ነው የማየው፡፡ የመጽሐፉ ጀርባ ላይ እነ ማን ምን አሉ የሚለውን ለማየት ማለት ነው። ወይም ከመጽሐፉ ውስጥ የተወሰዱ ጽሑፎችን ለማየት ማለት ነው፡፡ በታዋቂ ሰዎች አስተያየት ማስጻፍ ግዴታ አይደለም፤ አንዳንዴም ላይገኙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ደራሲው አልለማመጥም ብሎ ካሰበ ከመጽሐፉ ውስጥ እነዚህ ቢሆኑ ብሎ የመረጣቸውን አንቀጾች ያስቀምጣል፡፡ ምናልባትም የታዋቂ ደራሲ አስተያየት አልፈልግም የሚል ጸሐፊም ይኖር ይሆናል፡፡
ይህ በታዋቂ ደራሲዎች የሚጻፍ የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት ታዲያ ማሻሻጫ መሆኑ አልቀረም፡፡ የምርም አዋጪ ሆኗል፡፡ ገበያ ላይ የዋለው መጽሐፍ የሚተዋወቀው ‹‹እገሌ አስተያየት ሰጥቶበታል›› በሚል ነው፡፡ ማስታወቂያው ላይ በጉልህ የሚታየውም ያ ታዋቂ ደራሲ የሰጠው አስተያየት ነው፡፡ ‹‹እሱ እንዲህ ካደነቀውማ…!›› በሚል ብዙዎች ይገዙታል ማለት ነው፡፡ በሀገራችን ልማድ ደግሞ ራስን ችሎ ማሰብ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሌሎች የወደዱትን መውደድ፣ ሌሎች የጠሉትን መጥላት ልማዳችን ሆኗል፡፡ ስለዚህ አንድ የሚያደንቁት ደራሲ ካደነቀው ያንን መጽሐፍ ለመውደድ ይገደዳሉ፡፡
ያም ሆኖ ግን ሁሉም ሰው ታዋቂው ደራሲ በሰጠው አስተያየት መጽሐፉን ያደንቃል ማለት አይደለም፡፡ ‹‹እገሌ ጉድ ሠራኝ!›› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ የዚያን ታዋቂ ሰው የተጋነነ አስተያየት አይተው መጽሐፉን ገዝተው ሲያነቡት እንደጠበቁት ስላልሆነላቸው ማለት ነው፡፡ ‹‹ገንዘቤ ቆጨኝ!›› የሚል ሰው ሰምቼ አላውቅም፤ ‹‹ጊዜዬን አባከንኩ!›› የሚሉ ግን ብዙዎች ናቸው፡፡ የሥነ ልቦና ብክነትም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ጊዜያችንን አባክነን ምንም የሚጠቅም ነገር ስናጣበት መበሳጨታችን አይቀርም። ለዚህም ነው ብዙዎች በታዋቂ ደራሲ የተጋነነ አድናቆት መጽሐፍ ገዝተው አንብበው እንደጠበቁት አልሆንላቸው ሲል ‹‹እገሌ ምን ነክቶት ነው?›› የሚሉት፡፡ ሰውዬውን የነካው ለካ ገንዘብ ነው!
የሙዚያ ባለሙያው አብርሃም ወልዴ በአንድ መድረክ ላይ ‹‹ለጥበብ ሥራዎች መበላሸት ዋናው ምክንያት ድህነት ነው!›› ሲል ሰምቸው ነበር፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ምንም ነገር ስለሚደረግ ማለት ነው፡፡
በሀገራችን ብዙ መጽሐፎችን የጻፈ፣ ስመ ጥር እና ስመ ጥሩ የሆነ፣ ማንም ይህን ያደርጋል ብሎ ሊገምተው የማይችል ሰው ‹‹የጀርባ አስተያየት የሚጽፈው በገንዘብ ነው›› ሲባል ሰማሁ፡፡ በወቅቱ አላመንኩም ነበር፡፡ በቅርቡ ግን አንድ ከሰውዬው ያረጋገጠ ሰው ነገረኝ፡፡ ገንዘብ ይቀበላል ብቻ ሳይሆን የአድናቆት ደረጃው ራሱ እንደገንዘቡ መጠን ይለያያል፡፡ የገንዘብ መጠኑ ሲጨምር የአድናቆት መጠኑም በዚያው ልክ ከፍ ይላል ማለት ነው፡፡
ሥራ ነውና ገንዘብ መቀበሉ ችግር የለውም እንበል፡፡ ይሄ ሰውዬ መጽሐፉን ሙሉ ገጹን ካነበበው የሚያነበው ጊዜውን ሰዉቶ ነው፡፡ ሌሎች ሥራዎችን ሊሠራበት የሚችለውን ጊዜ አባክኖ ነው፡፡ ስለዚህ ማስከፈሉ ችግር የለውም ብለን ማለፍ እንችል ነበር፡፡
ዳሩ ግን በዚህ ሁኔታ የተሰጠ አስተያየት የጥበብን ደረጃ አያወርድም ወይ? ይህ ሰው ‹‹ሕይወቴን ለጥበብ የሰጠሁ ነኝ!›› ማለት ይችላል ወይ? ሕይወቱን ለጥበብ ለመስጠት የግድ ድሃ መሆን የለበትም፤ ዳሩ ግን በገንዘቡ መጠን የሚሰጥ አስተያየት የጥበብን ክብር አያወርድም ወይ? ሰዎችን ማሳሳቱስ ጥፋት አይደለም ወይ? የአድናቂዎቹን ክብር ማውረድ አይሆንም ወይ? አድናቂን መናቅ የሚባለውም እኮ ይሄው ነው፡፡ እኔ አስተያየት ሰጥቸበታለሁና እንዴትም ቢሆን አንበቡት እያለ ነው። በሌላ በኩል የተሳሳተ መረጃም እያስተላለፈ ነው፡፡ መጽሐፉ በበቂ ሁኔታ ያልያዘውን ነገር ይዟል፣ እንዲህ ነው፣ ይህን ያሟላ ነው… እያለ ሲያደንቅ ለሰዎች የተሳሳተ መረጃ እየሰጠ ነው ማለት ነው፡፡ ገንዘቡን በሌላ መንገድ ያግኘው እንጂ በእንዲህ አይነት ልክ ያልሆነ መንገድ ማግኘት ልክ አይደለም፡፡
እንዲህ አይነት ነገር ዘግይቶም ቢሆን በግልጽ በታወቀ ጊዜ አደጋ አለው፤ የራሱን ሥራ ጭምር ሞገሱን ሊያወርድበት ይችላል፡፡ የተገነባውን መልካም ስም እና ዝና ማውረድም ልክ አይደለም፡፡
በእርግጥ በዚህ ዘመን ገንዘብ ከክብር እና ከዝና በልጧል፡፡ ቀም ብዬ በገነባሁት ስም ገንዘብ ላግኝበት እንጂ ማንም ምንም ቢል ጉዳዬ አይደለም ብሎ ሊሆን ይችላል። ሰዎች ከሚሰጡኝ ክብር ይልቅ ገንዘቡ ይሻለኛል ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛው ይሻላል የሚለውን እንግዲህ የባለቤቱ ውሳኔ ነው፡፡ ገንዘብ ክብርን በበለጠበት ዘመን ለምን ለገንዘብ ብለህ ልብህ ያላመነበትን ነገር ታደርጋለህ? ብሎ መውቀስ የዋህነት ሊሆን ይችላል፡፡
በመጽሐፍ ጀርባ ላይ የሚሰጥ አስተያየት አድናቆት ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ሕፀፆች የተጠቀሱበት የጀርባ አስተያየት አላጋጠመኝም፡፡ ለመሆኑ አድናቆት ብቻ ማድረግ ግዴታ ነው ወይ? መልሱ ‹‹አዎ!›› ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም የጀርባ አስተያየት የሚሰጠው መጽሐፉን ለማሻሻጥ ነው፡፡ ዳሰሳ ሲሠራበት ግን መጽሐፉ ውስጥ ያሉ ድክመቶችም ይገለጻሉ፡፡
የጀርባ አስተያየት የሚጽፍ ሰው መጀመሪያ የሚያነበው ረቂቁን ነው፡፡ ከመታተሙ በፊት ስለሚያነበው ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል ዕድል አለው፡፡ በዚህ ምክንያት የጀርባ አስተያየት(ብለርብ) ሰጪው የጠቀሳቸው ደካማ ጎኖች ተስተካክለው ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ይሄው የጀርባ አስተያየቱን የጻፈው ሰው ያንኑ መጽሐፍ ዳሰሳ ሥራበት ቢባል የጀርባ አስተያየት ላይ ከጻፈው በተቃራኒው ደካማ ጎኖችንም ሊዘረዝር ይችላል፤ ምክንያቱም የጀርባ አስተያየት የግድ አድናቆት ብቻ ነው መሆን ያለበት የሚል ያልተጻፈ ስምምነት አለ፡፡
ከምንም በላይ ግን አሳፋሪው ዳጎስ ያለ ገንዘብ እየተቀበሉ ልባቸው ያላመነበትን መጽሐፍ የሚያጋንኑ ታዋቂ ደራሲዎች ናቸው፡፡ ጊዜያቸውን አባክነው ስለሆነ የሚያነቡት ገንዘቡን ይቀበሉ፤ ዳሩ ግን ልባቸው ያላመነበትን እየጻፉ ሰው አያሳስቱ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም