የኦቲዝም መንስኤን በአምስት ወራት ውስጥ ለማወቅ ጥናት ሊደረግ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር እየተስፋፋ ያለውን የኦቲዝምን መንስኤ በአምስት ወራት ውስጥ ለማወቅ “መጠነ ሰፊ ምርመራ እና ጥናት” እንደሚደረግ ተናገሩ። ለአስርት ዓመታት ጥናት ሲደረግበት የቆየውን እና ውስብስብ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያዎች የኦቲዝምን መንስኤ መረዳት ሚኒስትሩ እንደሚሉት በወራት ውስጥ የሚደረስበት ቀላል ጉዳይ አይሆንም በማለት ሙከራውን የተሳሳተ እና ተጨባጭ ያልሆነ ሲሉ ተችተዋል።

በቅርቡ በትራምፕ የተሾሙት የአሜሪካ የጤና ሚኒስትሩ ኬኔዲ ኦቲዝም ከክትባት ጋር የተገናኘ ነው የሚል ንድፈ ሃሳቦችን የሚያራምዱ ሲሆን፣ ሐሙስ ዕለት በተካሄደው የካቢኔው ስብሰባ ላይ በቀጣይ ወራት የሚደረገው ምርምር “ከዓለም ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶችን ያሳትፋል” ብለዋል ።

“በመጪው መስከረም እየተስፋፋ ያለው ኦቲዝም መንስኤው ምን እንደሆነ እናውቃለን፣ ይህም አጋላጭ የሆኑትን ምክንያቶች ለማስወገድ ያስችለናል” ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የመንግሥት መረጃ እንደሚያመለክተው ከአው ሮፓውያኑ 2000 ወዲህ በአሜሪካ ውስጥ የኦቲዝም መጠን በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። እኤአ በ2020 ከስምንት ዓመት ታዳጊዎች መካከል የኦቲዝም ክስተት መጠን 2 ነጥብ 77 በመቶ መድረሱን የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል አስታውቋል።

ሳይንቲስቶች ለቁጥሩ መጨመር ስለኦቲዝም ያለው ግንዛቤ መጨመር እንዲሁም የኦቲዝም ትርጉም እና የሚያካትታቸው ሁኔታዎች መስፋት በከፊል ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችል አመልክተዋል። ተመራማሪዎች ለኦቲዝም ምክንያት የሚሆኑ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

መንግሥታዊው የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም በየዓመቱ በኦቲዝም ላይ ለሚደረጉ ጥናቶች ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያወጣል።

ተቋሙ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥሙ የኬሚካል ተጋላጭነት፣ የአየር ብክለት፣ ያለ ጊዜው የሚከሰት ወሊድ፣ በወሊድ ጊዜ ዝቅተኛ ክብደት እና ዕድሜ ከገፋ በኋላ የሚያጋጥም እርግዝናን ጨምሮ ሌሎች ለኦቲዝም ምክንያት ይሆናሉ ብሎ ዘርዝሯል።

ኬኔዲ ውጤቱ መስከረም ላይ ይታወቃል ስላሉት የምርምር ፕሮጀክት ዝርዝር እና ምን ያህል ገንዘብ እንደተመደበለት ያሉት ነገር የለም። “በጥናቱ የክትባቶችን ተፅዕኖ የምንመረምር ሲሆን፣ ለኦቲዝም ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉንም ጉዳዮችን እንመለከታለን” ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

“የምግብ ሥርዓታችን፣ ውሃችን፣ አየራችን፣ የተለያዩ የልጆች አስተዳደጋችን እንዲሁም ሌሎች ለኦቲዝም መስፋፋት ምክንያት የሆኑ ለውጦችን ጨምሮ ሁሉም ነገር ላይ ጥናቱ ይደረጋል። “ነገር ግን የጤና ሚኒስትሩ በኦቲዝም ምክንያት ላይ የሚደረገው ጥናት መጀመርን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የኦቲዝም ማኅበር ባወጣው መግለጫ ዕቅዱን “ጎጂ፣ አሳሳች እና ተጨባጭ ያልሆነ” ሲል ተችቶታል።

ጨምሮም ኦቲዝም “ከአደገኛ እና ከተላላፊ በሽታዎች ጋር የሚመደብ አይደለም” ሲል የኬኔዲ መሥሪያ ቤት አቋምን የተቃወመ ሲሆን፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኦቲዝም በዋናነት በአካባቢያዊ ምክንያቶች የሚከሰት ነው መባሉ “አሳሳች ከመሆኑ በተጨማሪ መገለልን የሚያስከትል ነው” በማለት ችግሩ ያለባቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዳያገኙ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትሩ በክትባቶች ላይ ባላቸው ጥርጣሬ እና ተቃውሞ የተነሳ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሲሆን፣ በኦቲዝም ላይ የሚደረገውን ጥናት ላይ እንዲሳተፉ ተመሳሳይ አቋም ያላቸውን ግለሰብ መሾማቸው መነጋገሪያ ሆኗል። ተቀባይነት ያላገኘው ኦቲዝም እና በልጅነት የሚሰጡ ክትባቶች ተያያዥነት አላቸው የሚለው ሃሳብ ትኩረት ያገኘው አንድ ብሪታኒያዊ ዶክተር በአውሮፓውያኑ 1998 ላንሴት በተባለው የሕክምና መጽሔት ላይ ጽሑፋቸው ከወጣ በኋላ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ዶክተሩ ለጥናቱ የተጠቀመባቸው መረጃዎች ሐሰተኛ ሆነው በመገኘታቸው ጽሑፉ ውድቅ መደረጉን ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You