
የኢትዮጵያ ብርቅዬ እንስሳ ከመሆን አልፎ ብሔራዊ ዓርማ እስከመሆን የደረሰው ዋሊያ አይቤክስ በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የሕልውና አደጋ እንደተጋረጠበት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህን አደጋ ለመቀልበስ እና ዘላቂ የደኅንነት ዋስትናውን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡
ለትግበራ ከተሰናዱት የመፍትሔ አቅጣጫዎች መሐል ብሔራዊ ስትራቴጂ እቅድ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም ላይ ሰሞኑም በጎንደር ከተማ በተካሄደ መድረክ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ መገኘታቸውን ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ አመላክቷል።
ሚኒስትር ዴኤታው በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ‹የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እጅግ ውብ በሆኑ ተፈጥሮዎች የበለፀገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የብሔራዊ ፓርኩን ሥነ ምሕዳር ጨምሮ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የፓርኩ የዱር እንስሳት ሕይወት ከተጠበቀ ለቱሪዝሙ እንቅስቃሴ የጎላ አስተዋፅዖ እንዳለውም ገልጸው፣ የፓርኩን ደኅንነት ለመጠበቅ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንዳሉት፤ የዋሊያ አይቤክስ የሕልውና አደጋን ለመቀልበስ በጋራ መሥራት ወሳኝነት አለው። እየተመናመነ የመጣውን የዋሊያ አይቤክስ ቁጥር ለማሳደግ እና ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት በጥናት ላይ የተመረኮዘ ‹የዋሊያ አይቤክስ ጥበቃ ብሔራዊ ስትራቴጂካዊ እቅድ› ተዘጋጅቷል።
እቅዱ ማን ምን ኃላፊነት እንዳለበት የሚገልጽ የአብሮ መሥራት ዓላማን ያነገበ መሆኑን በማንሳት በቀጣይ በተቀናጀ አሠራር የዋሊያ አይቤክስን የሕልውና ስጋት መቆጣጠር እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲ/ን ሸጋው ውቤ በብሔራዊ ፓርኩ ላይ የተጋረጡ እና የሚጋረጡ አደጋዎችን ከመቅረፍ አኳያ ከብሔራዊ ፓርኩ አዋሳኝ ወረዳዎች ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀርብንላቸው በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንሰሳት ምርምርና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፈቀደ ረጋሳ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ ምልክት የሆነው ዋሊያ አይቤክስ የተጋረጠበት አደጋ ምን እንደሆነ በጥናት ተለይቶ ታውቋል።
የኮቪድ 19 እና በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በተፈጠሩ ክፍተቶች ቁጥጥር ሳይደረግ መቅረቱን አስታውሰው፣ ይህን ተከትሎ ሕገ ወጥ አደን በመስፋፋቱ ለዋሊያ አይቤክስ የሕልውና አደጋ በር ከፋች ክስተት ተፈጥሯል ብለዋል። ሌሎች እንደ ሕገወጥ እርሻ እና ሕገ ወጥ አደን የመሳሰሉት ክስተቶችም ለአደጋው ተጨማሪ ስጋት መሆናቸውን አመልክተዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ በኮቪድ ጊዜ ዓለም አቀፍ ክልከላ በመኖሩ ባለሙያዎች ገብተው መሥራት አልቻሉም፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም ተመሳሳይ ችግር በመኖሩ ሕገ ወጦች ፓርኩ ውስጥ ገብተው ያሻቸውን እንዲያደርጉ ዕድል ሰጥቷቸዋል።
አሁናዊው በዋሊያ ላይ የተፈጠረው የሕልውና አደጋ በቀጥታ ከእነዚያ ተግዳሮቶች ጋር እንደሚያያዝ ገልጸው፣ ችግሩን ከመቅረፍ እና የደኅንነት ዋስትና ከመስጠት አኳያ በቂ ጥናት እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡
የጥናቱ ውጤቱ ለዋሊያ አይቤክስ የሕልውና አደጋ ምክንያት በመሆን ሁለት ሦስተኛውን እጅ የሚይዘው ሕገ ወጥ አደን እንደሆነ ማመላከቱን አስታውቀዋል። ሕገ ወጥ አዳኞች ብርቅዬ እንስሳቱን ለማደን የሚነሱበት ዋና ምክንያት ለምግብነት ለመጠቀም እና ለባህላዊ መድኃኒት ተፈላጊ ናቸው በሚል እንደሆነም ገልጸዋል።
የሰሜኑ ጦርነት በሰላም መቋጨቱን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ሁለት ዓይነት ማለትም የርጥበት ወቅት እና የደረቅ ወቅት ጥናቶች ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ጥናቱ ወደ ስትራቴጂክ እቅድ ተለውጦ መፅደቁንም አስታውቀዋል፡፡
ቆጠራን እና ችግሮችን ለይቶ በማውጣት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የተጀመረው ጥናት፣ የሕልውና ስጋት ለወደቀበት ዋሊያ አይቤክስ ጥበቃ ዋስትና እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ጥናቱ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት እና ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም ከጂአይ ዜድ በተወጣጡ ባለሙያዎች የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችም የተቀመጡለት ነው ብለዋል፡፡
ዋሊያ አይቤክስን ይታደጋል የተባለው ስትራቴጂክ እቅድ በቀጣይ ምን አይነት የመፍትሔ አማራጮችን እንደያዘ ፈቀደ ረጋሳ (ዶ/ር) ሲያብራሩ እንዳሉት፤ የጥናት እቅዱ ሰፊ እና ጥልቅ የጥናት ዳሰሳዎችን የያዘ፣ ተልዕኮ እና ራዕይ ያለው የቀጣዮቹን አምስት ዓመታት ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ከመቶ በሚበልጡ ተግባራት የተቃኙ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ ዓላማዎችን ይዟል።
አሁን ያለውን የዋሊያ አይቤክስ የሕልውና ስጋት ለመቅረፍ እንደ ዋነኛ መፍትሔ ከተቀመጡት ውስጥ የመጀመሪያው የሕግ ማስከበር ሥራን ማጠናከር እንደሆነ መሪ ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል። የአካባቢውን ስካውቶች በማሠልጠን፣ በማንቃት ለሕግ ማስከበር እንቅስቃሴው ብቁ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደተደረገ ተናግረዋል።
ስትራቴጂክ እቅዱ ዝርያ ተኮር በመሆኑ እንደበፊቱ በጥቅሉ ሳይሆን ዋሊያን መሠረት አድርጎ የሚሠራ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ለዛም እንደ ዋልያ አምባሳደር ባሉ ከቀበሌ እስከወረዳ ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ለዓላማው ወሳኝ የሆኑ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ለእቅዱ ተፈጻሚነት የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያዎችን ጨምሮ ዋሊያ ላይ የሚሠሩ ሬንጀሮችም ዝግጁ ተደርገዋል። ሌላው ከዚህ ጋር እንደ መፍትሔ የተነሳው በውልደት ጊዜ ጨቅላ ዋሊያዎችን በመከታተል እስኪያድጉ ድረስ አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግላቸው የሚያግዝ አሠራርም ይዘረጋል። ብሔራዊ ፓርኮችን በተመለከተ የማኅበረሰቡ ኃላፊነት ወሳኝ ይሆናል።
ከተጠቀሱት የአደጋ ምክንያቶች ባለፈ በአካባቢው ባሉት ነብሮችና ጅቦች ሳቢያ አደጋው የመከሰት ዕድል እንዳለ ጠቁመው፣ ለእዚህም ማኅበረሰቡን ማንቃት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ጥብቅ የተፈጥሮ ሀብቶችንም ሆነ ብሔራዊ ፓርኮችን በተመለከተ ከማንም በላይ በባለቤትነት ሊይዝ የሚገባው የዚያ አካባቢ ማኅበረሰብ እንደሆነ አስታውቀው፣ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ አዲስ አበባ ካለው የዱር እንስሳ ባለሥልጣን እንዲሁም በአካባቢው ካለው የጥበቃ ቢሮ በላይ ወሳኝ እንደሆነ በማንሳት የያገባኛል ስሜት መሰል ችግሮች ቀጣይነት እንዳይኖራቸው መፍትሔ በመሆን እንደሚያገለግሉ አስታውቀዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው ብሔራዊ ፓርኩ በአካባቢው እንደመገኘቱ በዚህ ስትራቴጂካዊ እቅድ ላይ የአማራ ክልል መንግሥት ምን አይነት ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል። የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ለብሔራዊ ፓርኩ ከመንግሥት በላይ ባለቤቶች ናቸው።
ከመንግሥት የሚደረጉለት ቴክኒካል ድጋፎች እንዳሉ ሆነው ክልሉ የራሱን የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ሥነምሕዳር መጠበቅ ይኖርበታል። ከክልሉ መንግሥት በላይ ብሔራዊ ፓርኩን በመጠበቅ ረገድ የአካባቢው ማኅበረሰብ ድርሻ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለሕግ ተገዢ በመሆን፣ ሕገ ወጥ አደንን በመከላከል፣ ከብቶችን ለግጦሽ ከማሰማራት እና ከመሰል ድርጊቶች በመቆጠብ እንዲሁም ሕግን የተላለፉ ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ አጋርነታቸውን ማሳየት አለባቸው ብለዋል። ለዚህም የክልሉ መንግሥት ማኅበረሰቡን በማንቃት፣ የግንዛቤ ሥራ በመሥራት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ዋሊያ አይቤክስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ያሉት ፈቀደ ረጋሳ (ዶ/ር)፣ በሀገራችን ብቻ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ የሀገር ሀብት፣ ምልክት፣ ብራንድ እስከመሆን የደረሰ ነው ሲሉም ገልጸውታል። ካለው የሀገር በጎ ስም የተነሳ ለብሔራዊ ቡድናችን መጠሪያ፣ ለዋሊያ ቢራ፣ ለዋሊያ ቆርቆሮ እንዲሁም ሌሎች ስያሜነት እያገለገለ ይገኛል ብለዋል። ዋሊያ አይቤክስ ከሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ውጪ በሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች እንደማይገኝ ጠቅሰው፣ ልዩ ጥበቃ እና ክትትል እንደሚደረግለት አስታውቀዋል፡፡
‹‹ዋልያ ከብዙ ነገራችን ጋር የተያያዘ ነው፤ ይሄ ብርቅዬ እንስሳ ጠፋ ማለት ብዙ ነገራችንን እናጣለን። በትላልቅ ሀገራት እንዳሉ ገላጭ ምልክቶች ሁሉ የሀገራችን ዓርማ በመሆኑ ሁሉም አይነት የጥበቃ ሥራ ሊሠራለት ይገባል‹‹ ሲሉም አስገንዝበዋል።
ዋሊያ የሚኖርበት ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የተመዘገበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዩኔስኮ በጉዳዩ ላይ ያለው ስለመኖሩ ተጠይቀው ሲመልሱም፤ ‹‹ላለፉት ስድስት ዓመታት ጥናት በማካሄድ አሁን ያለንበት የመፍትሔ ሃሳብ ላይ ደርሰናል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ዩኔስኮ ያለው ነገር ባይኖርም እኛ ችግሩን ተረድተን አንድ ርምጃ ወደፊት ሄደናል›› ብለዋል። ያን ባናደርግ እና ለችግሩ ምንም ዓይነት ርምጃ ባንወስድ ዩኔስኮ ጣልቃ በመግባት የሰሜን ብሔራዊ ፓርክን እስከ መሰረዝ ሊደርስ ይችል እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ፈቀደ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ የዋልያ አይቤክስ ቁጥር በመቀነሱ መሰል የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠው በዛ መንገድ ቁጥሩ እንዲስተካከል የሆነበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ይሄን ስትራቴጂካዊ እቅድ ባንተገብር እና ዝም ብለን ብናይ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ዩኔስኮ ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ ይኖር ነበር ብለዋል።
‹‹በመረጃ ደረጃ ብሔራዊ ፓርኩ ያለበትን ሁኔታ አሳውቀናል። የአይዩሴ ሬድ ሊስትም በፊት ‹‹ዳንጀር›› እንደነበር፣ አሁን የበለጠ ‹‹ክሪቲካል ዳንጀር›› ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተረድቷል። በእኛ በኩል እየተሠራ ያለውንም ሥራ ስለሚያውቁ ምንም ያሉት ነገር የለም ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ እውቅና ሲያገኝ ራሱን በቻለ ሕግና ደንብ ነው። እነዚህ ሕግና ደንቦች ከተጣሱ እውቅና የሰጠውም አካል ከመዝገብ ላይ ሊፍቅ ይችላል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ፓርኩ ውስጥ ማደንን፣ ማረስን የመሳሰሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶች እየታዩ ነው። ይሄ ሁኔታ ብርቅዬ እንስሳቱን አደጋ ላይ ከመጣል እኩል ብሔራዊ ፓርኩንም እውቅና እንዲነፈገው ሊያደርግ ይችላል። በዚህ ላይ ከተለያዩ አቋሞች አንዱ ይሄን መሳዩን ሕገ ወጥ ልምምድ በማስቀረት ረገድ የማኅበረሰቡ ድርሻ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ኅብረተሰቡ ሀብቱን በንቃት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ተገቢው ሥራ ከተሠራ የዱር እንስሳት ቁጥርን መጨመር ቀላል እንደሆነ ያነሱት ፈቀደ (ዶ/ር)፣ ዋሊያ በተፈጥሮው በደንብ የሚራባ እንስሳ መሆኑንም ገልጸዋል። የተወለዱትን በደንብ መንከባከብ ከተቻለ ወደሚፈለገው ቁጥር ለመምጣት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ላይፈጅ እንደሚችልም ጠቁመው፣ ወሳኙ ነገር ሥራው እና የምንወስደው ርምጃ ነው ሲሉ ተስፋ ሰጪነቱን ገልጸዋል፡፡
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፤ አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ የቱሪዝም ዘርፍ የኢኮኖሚ ሴክተር ውስጥ ገብቷል። እንደ ሀገር የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠቀም ከጥበቃ ጀምሮ ሁሉን ዓይነት እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል።
ኬንያ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷ (ጂዲፒዋ) 18 በመቶ የሚሆነውን ገቢዋን ከቱሪዝም ነው የምታገኘው ሲሉ ጠቅሰው፣ እኛ ሰፊና በብዙ የታደለች ሀገር አለን፤ ግን እየተጠቀምንበት አይደለም ብለዋል።
በተለይ የዱር እንስሳ ጥበቃ ትኩረት አልተሰጠውም። እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ሁሉም ሊሳተፍበት የሚገባ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚያስፈልገው የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን አስገንዝበው፣ በቀጣይ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚኮንበት አማራጭ እንዲታይም ጠይቀዋል፡፡
ቱሪዝም የተፈጥሮ ሀብትና የባህል እሴት የተጠራቀሙበት ዘርፍ መሆኑን አመልክተው፣ ይሄን ገልጠን ለተጨማሪ የሀገር ኢኮኖሚ ማዋል ላይ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል። አሁን በተያዘው ስትራቴጂካዊ እቅድ መሠረት በቀጣይ የዋልያ አይቤክስ ቁጥር ወደነበረበት እንደሚመለስ አስታውቀው፣ መሰል ስጋቶች እንዳይፈጠሩ የመፍትሔ አማራጮች እየታዩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም