የጥናት መጠይቆች ነገር

ብዙ አይነት ጥናቶች ቢኖሩም በአገራችን በብዛት የሚታየው ግን የትምህርት ማሟያ ጥናት ነው። በነገራችን ላይ ይህ የሚያሳየው ስንፍናችንን ነው። ጥናት የበለጠ መሠራት ያለበት ከትምህርት ደረጃ ማሟያነት ባሻገር ማሕበረሰባዊ ችግር ፈቺ ለመሆን ነበር። በእርግጥ ለትምህርት ማሟያ የሚሰሩ ጥናቶችም ማሕበረሰባዊ ችግር ፈቺ መሆን ይችላሉ፤ በተለይም ለሦስተኛ ዲግሪ (ፒ.ኤች.ዲ) የሚሰሩ ጥናቶች ከትምህርት ማሟያነት ያለፉ መሆን አለባቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ በመጽሐፍ መልክ ታትመው ለብዙ ሰዎች ማጣቀሻ ሲሆኑም አይተናል፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው።

ያም ሆነ ይህ የዛሬው ትዝብታችን ግን የመጠይቆች (Questioners) ጥያቄ ላይ ነው። ጥያቄዎቹ ምን ያህል እውነታውን ለማወቅ ያስችላሉ? የሚለውን ነው። በብዛት የሚስተዋሉትም በትምህርት ማሟያ ጥናቶች ላይ ነው። በእርግጥ መጠይቅ አንዱ ዘዴ እንጂ የግድ የጥናቱ ትንታኔ በመጠይቁ ብቻ ይሆናል ማለት አይደለም።

ብዙ ጊዜ የሥራ ቦታዬ ላይ እያለሁ መጠይቆች ይሰጡኛል፤ በትዕዛዞቻቸው መሠረት እሞላለሁ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ግን መጠይቆችን ምን ያህል እውነታውን ለማወቅ ያስችላሉ? እያልኩ አስባለሁ።

ብዙ ጊዜ መጠይቆች በምርጫ የሚሞሉ ናቸው። በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የምርጫ ብቻ መጠይቆች ሲመጡ ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም ለስንፍና ያመቹኛል፤ ማለቴ መጻፍና ማብራራት ሳያስፈልግ ዝም ብሎ ማክበብ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ ሲሆን ምን ያህል ከልብ እንደማይሰሩ ልብ በሉ!

አንዳንዱ መጠይቅ ደግሞ ያናድዳል፤ እንደትምህርት ቤት ፈተና ‹‹ኮሬክሽን›› ለመጠየቅ ያስገድዳል። ችግሩ የመጠይቁ ባለቤት ሰጥተው ወጣ ይላሉ። በዚያ ላይ ያሉት አማራጮች የተሰጡት ብቻ ናቸው የሚሆኑት፤ ሌላ ቅጽ ሞልተው ሊሰጡ አይችሉም።

በአንዳንድ መጠይቆች ላይ የሚጠየቀው ጥያቄና የተሰጠው አማራጭ ሀሳብ አይገናኙም፤ ይሄ ማለት አማራጮች ጥያቄውን በተገቢው መንገድ ለመመለስ ምቹ አይደሉም። እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲኖር ማብራሪያ መኖር ነበረበት። መልሱን የሚሞላው ሰው ያለበትን ምክንያት ግልጽ የሚያደርግበት አማራጭ መኖር አለበት። ጥናቱ ላይ ያለውን ጥያቄ ላለመግለጽ ሀሳቡን የሚገልጽ ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ፈጥሬ ልጠይቃችሁ። ጥያቄውና አማራጮች እነዚህ ናቸው እንበል።

እሳት ይጎዳል ብለው ያስባሉ?

ሀ/ በጣም እስማማለሁ ለ/ እስማማለሁ ሐ/ አልስማማም መ/ በጣም አልስማማም

እስኪ ይሄ ጥያቄ እንዴት ነው የሚሞላው? እርግጥ ነው እስማማለሁ (ይጎዳል ማለት ነው) ብሎ መመለስ ይቻላል፤ ወይም አልስማማም (አይጎዳም ማለት ነው) ብሎ መመለስ ይቻላል። ይሄ መልስ ግን የተጠያቂውን ሀሳብ አይገልጽም። የእሳት መጉዳት አለመጉዳት ‹‹እስማማለሁ›› ወይም ‹‹አልስማማም›› በሚል የሚገለጽ አይደለም። ምክንያቱም ለጉዳቱም ሆነ ለጥቅሙም ምክንያት አለው። ቢያንስ እኮ ምርጫው በከፊል እንኳን የሚል መኖር ነበረበት፤ ይሻል ነበር ለማለት እንጂ ይሄም ቢሆን አይገልጸውም።

በዚህ ጥናት ውጤት እንግዲህ ይህን ያህል ሰው እሳት ይጎዳል አለ፤ ይህን ያህል ሰው ደግሞ እሳት አይጎዳም አለ ተብሎ ይገለጻል ማለት ነው። ዳሩ ግን የተጠኚዎች ስሜት አልተገለጸም፤ ምክንያቱም ለአንድ ሰው ሁለቱም መልስ ሊሆነው ይችላል። መቼም ሁለት መልስ ለመሙላት ‹‹እስማማለሁ›› እና ‹‹አልስማማም›› የሚለውን አልሞላም። ሀሳቤ ግን እሳት እንደሚጎዳም እንደሚጠቅምም ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱም መልስ መሆን ይችላል፤ እሳት ይጎዳልም ይጠቅማልም።

አንዳንዶቹ መጠይቆች ደግሞ ተመሳሳይ ጥያቄ ሊጠይቁ ይችላሉ። የተራ ቁጥር አንድ ጥያቄ ጠቅሎ የሚመልሰውን መልስ ተራ ቁጥር ሁለት ላይም ሊደግሙት ይችላሉ። ይሄንኑ የእሳቱን ምሳሌ እንድገመውና፤ አስከትሎ ‹‹እሳት ይጠቅማል ብለው ያስባሉ?›› ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፤ ያሉት አማራጮችም እነዚያው ናቸው። የመጀመሪያው ጥያቄ እኮ ለሁለተኛው ጥያቄ መልስ ይሆናል። እሳት ይጎዳል የሚለው ላይ እስማማለሁ ብዬ ከሞላሁ በእኔ እምነት እሳት አይጠየቅምም ማለት ነው፤ ስለዚህ ሁለተኛው ጥያቄ አያስፈልግም ማለት ነው! እንዲህ አይነት መጠይቅ በማብራሪያ እንጂ በእስማማለሁ አልስማማም የሚሞላ አይደለም። ብዙ መጠይቆች ላይ የምንታዘበው ግን የዚህ አይነት ችግር ነው።

የእንዲህ አይነት ጥናቶች ችግር ይሄ ብቻ አይደለም። መጠይቁን የሚሞሉት ሰዎችም ችግር አለ። በተረጋጋ ቀልብ አንብበው አይሞሉትም (ኧረ ጭራሽ ሳያነብ የሚሞላም አይጠፋም)። በተለይ የሚጻፍ ነገር ካለው በጥሞና አንብቦ በጥሞና አይጽፍም፤ ለጥናቱ ጠቃሚው ደግሞ የሚጻፈው ነገር ነበር።

አጥኚዎች ደግሞ ሰው የተሰባሰበበት ቦታ ሄደው ነው የሚያስሞሉት፤ ሰው የተሰባሰበበት ቦታ ላይ ደግሞ የተረጋጋ ቀልብ አይኖርም። እዚህ ላይ ግን በአጥኚዎች የማንፈርድበት አንድ ነገር አለ። ሰዎች የተሰበሰቡበት ቦታ የሚሄዱት ጥናቱ ለሚመለከታቸው ሰዎች መሰጠት ስላለበት ነው። የሚመለከታቸውን ሰዎች ለማግኘት የግድ የሚሰሩበት ቦታ ነው መሄድ ያለባቸው። ለምሳሌ ጥናቱ የባንክ ሰዎችን የሚመለከት ከሆነ የባንክ ሰዎች የሚገኙት የግድ ባንክ ቤት ነው። መናፈሻ ውስጥ ተረጋግቶ ቁጭ ያለን ሰው ‹‹የባንክ ሰራተኛ ነህ?›› ተብሎ አይጠየቅም። እርግጥ ነው መጠየቁ ችግር የለውም፤ ግን አይደለሁም ቢል የባንክ ሰራተኛ ከየት ይገኛል? እንዲህ እንዲህ እያሉ የሚመለከተውን ሰው ማግኘት ደግሞ ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ ይፈጃል።

አሁን ደግሞ አንድ የሕክምና ዶክተር የነገረኝን ላካፍላችሁ። የደም አይነቴ የሚፈልጋቸውን የምግብ አይነቶች ኢንተርኔት ላይ እያነበብኩ ነበር። አስፈላጊ ናቸው ብሎ የሚዘረዝራቸው ምግቦች እኔ ብዙም የማልወዳቸው ናቸው፤ የምወዳቸውን ደግሞ እንደማይመከሩ አስቀምጧል። የሕክምና ዶክተሩ ጓደኛዬ ስለነበር አንድ ዕለት በጨዋታ መሃል አነሳሁለትና ጠየቅኩት። እንዲህ አይነት ጥናቶች ብዙም አስተማማኝ እንዳልሆኑ ነበር የነገረኝ። ምክንያቱም በተወሰነ ሰው ላይ የሚሰሩ ናቸው።

ጥናት ሁሉ ውሸት ነው ባይባልም፤ ችግሩ ግን የሚሰሩበት መንገድ ቀደም ሲል የጠቀስኩት አይነት ነው። በተለይም በእኛ አገር ደግሞ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ነው፤ ምክንያቱም የገንዘብና የጊዜ ችግር አለ። ለሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ጥናት የሚሰሩ ሰዎች ከመደበኛ ሥራቸው ጋር ነው የሚሰሩት፤ ስለዚህ ጥናቱ የሚሰራው የይድረስ ይድረስ ይሆናል ማለት ነው።

መጠይቆቹም የሚዘጋጁት የይድረስ ይድረስ ነው። እስማማለሁ፣ አልስማማም፣ በጣም እስማማለሁ፣ በጣም አልስማማም… አይነት ነገር ናቸው። ስለዚህ የሚዘጋጁ መጠይቆች ለመመለስ የሚያመቹ መሆን አለባቸው፤ መጠይቅ የሚሞሉ ሰዎችም በሚገባ ሳያነቡ ዝም ብሎ ማክበብ ብቻ መሆን የለበትም። በአጠቃላይ ጥናቶች ከልብ ይሁኑ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You