ኪሮስን በክብር

ሥራና መልኩ ዛሬም ቢሆን ከብዙዎቻችን አዕምሮ አይጠፋም። ምክንያቱም ከብዙ ዓመታት በፊት የወደድናቸውንና ዛሬ እንደ ትዝታ የሆኑብንን ቲያትሮች በመድረክ ላይ ሲጫወት ተመልክተነዋል። ከዚህ የምንበልጠው ደግሞ፤ ሁላችንም አንዲት የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ በምንመለከትበት በዚያ ዘመን፣ በጉጉት ስንጠባበቃቸው ከነበሩ ድራማዎች ውስጥ ብቅ ሲል አይተነዋል። ሌሎቻችንም የጊዜው ምርጥ ፊልም ብለን በተመለከትናቸው ፊልሞች እናውቀዋለን።

ጊዜው የቅርብ ሩቅ እንጂ ሩቅ አይደለም። ከሀገር ፍቅር እስከ ብሔራዊ ቲያትር ቤቶች፣ ከቴሌቪዥን ሳተላይት እስከ ሬዲዮ ሞገድ በሁሉም ራሱን ያስተዋወቀን ቢሆንም፤ ከዓመታት በፊት በገጠመው የጤና እክል ሳቢያ ከሁሉም ገሸሽ ብሎ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት መኖር አለመኖሩ እንኳን የተምታታምብን ጥቂት አይደለንም።

ከወደኋላ በነበሩ 40 ዓመታት ውስጥ ከኪነ ጥበብ ሞሰቦች ላይ ማዕድን የቆረሰን ኪሮስ ኃይለሥላሴን ላለማወቅም ሆነ ላለማስታወስ አይቻለንም። እኚያን ሁሉ ያለፍንባቸውን የቲያትር፣ የፊልምና ድራማ ቅያሶችን ካስታወስን፣ ኪሮስ የቱ ጋር እንደነበረ እናስታውሰዋለን። መልኩን፣ ገጽታውን፣ የተጫወታቸውን ገጸ ባህሪያትን ሁሉ ከምናባችን ዓይኖች ፊት እንከስታቸዋለን። ምናልባትም እስከዛሬ የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ያላውቅንም፣ በእግረ መንገድ ራሳችንን እንታዘበዋለን።

በመድረክና በቴሌቪዥን መስኮቶች እየተመለ ከትናቸው ኖረን ድንገት ሲሰወሩብን፣ የት ገቡ? ምን ሆነው? ብለን ስለማንጠይቅ የአብዛኛዎቹ ትውስታችን የሚቀሰቀሰው አረፉ የሚል ዜና የሰማን ዕለት ነው። ከክፋት የሚቆጠር ባይሆንም፤ ልናራግፈው ያልቻልነው ልማዳዊ ሸክም ሆኖብናል። ከእያንዳንዱ ዝነኛ ባስተጀርባ ዳዊት የመድገም ያህል፣ ዐረፍተ ነገሩን የምንደጋግመው፣ ምናልባት እንደ ጥንቃቄ ምልክቶችና መልዕክቶች ለማስታወስ ቢሆነን በማለት ነው።

አስታዋሽ አይጥፋና ኪሮስ ግን ታወሰ። ስሙ ከቤት ከሰፈሩ ላይ እንዳይቀር፣ በአደባባይ የዘለዓለም የክብር ሽልማቱ በሚሆን ዝግጅት ለመመስገን በቅቷል። እኛንም ሁልጊዜ ያለፈውን ከመዘከር ታድጎናል። ባሳለፍነው ሳምንት፣ በመጋቢት 27 ቀን 2017ዓ.ም፣ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ የተደረገለት የምስጋናና የክብር መድረክ፣ ለአንድ ለኪሮስ ኃይለ ሥላሴ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ከባለዕዳነት የሚገላግለን ነው። ለአንጋፋው አርቲስት የሚገባውን ክብር፣ በሚገባው መድረክ ላይ ነበር ያገኘው። ታላቅ የነበሩን ታላቅነት ማየት በራሱ ትልቅ ነገር አለው። የሚያከብሩ የተከበሩ ናቸውና ትልቅነቱም ለሁሉም ነው።

የጀግንነትና የነጻነት አርማ ከሆነችው ከዓድዋ ማይ ቅንጣል ወረዳ ውስጥ በትዳር ተጣምረው፣ ከአንዲት ጎጆ ውስጥ የሚኖሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ ገብረ እዝጊ እና አቶ ኃይለ ሥላሴ ረዳ፤ የአብራካቸውን ክፋይ ለማየት ለረዥም ጊዜ እግዜሩን ሲማጸኑ ኖረዋል። ወልደው ለመሳም ስለት ተስለው በእምነትና በተስፋም የእግዜር ይሁንታ ጠበቁ። ጸሎትና ስለታቸው ከጸባኦቱ ደርሶ፣ ከጽርሃ አርያም ተበሰረላቸው። መጋቢት 27 ቀን በ1947ዓ.ም የስለት ፍሬ ልጃቸውን ታቅፈው ሳሙ። ስሙን “ኪሮስ” ብለው ሰየሙት። ጥበብና ወላጆቹም የዛሬውን ኪሮስ ኃይለ ሥላሴን (ኪያን) አገኙ።

በጊዜው አባቱ ፖሊስ ስለነበሩ፣ ገና ከጨቅላ ዕድሜው ጀምሮ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ፣ ልጅነቱን ያሳለፈው በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ነው። ከቅንጣል ወደ ውቅሮ ከተማ እንደተዘዋወሩ፣ ኪሮስ ፊደል መቁጠሪያ ዕድሜው ደርሶ ትምህርት ቤት ገባ። ወደ 3ኛ ክፍል ሲዘዋወር ግን ከውቅሮ ወደ አጽቢ ወንበርታ ቀየሩ። ብዙም ሳይቆዩ እንደገና ከአጽቢ ወደ ስንቅ አጣ ወይንም “ፍረወይኒ” እየተባለች ወደምትጠራዋ ከተማ ገቡ። ኪሮስ በዚህ ሁሉ ዞሮ ዞሮ በስተመጨረሻ ወደ ውቅሮ ሲመለስ ትምህርቱን ከ4ኛ ክፍል ጀመረ። እስከ 8ኛ ክፍል የተማረውም በዚሁ ነው።

ኪሮስ ትምህርቱን በውቅሮ በሚከታተልበት ጊዜ በክበባት ውስጥ የመሳተፍ ልምድ ነበረው። በወቅቱ ታዲያ ከኪሮስ ጋር ሌላ ኪሮስ ነበረ። እውቁና አንጋፋው የትግርኛ ሙዚቀኛ ኪሮስ ዓለማየሁ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አብሮት ይማር ነበር። በቲያትር፣ በሙዚቃና በቦይስ ስካውት ክበባት ውስጥ አብረው ይንቀሳቀሱ ነበር። ኪሮስ ኃይለ ሥላሴ ቀልዶችና መናገር የሚወድና ተማሪዎችን በየአጋጣሚዎቹ ፈገግ የሚያሰኝ ስለነበረ የብዙዎችን ቀልብ መግዛት የቻለ ተወዳጅ ነበር። ልጅነቱንና ወጣትነቱን እንዲህ ካለው የጥበብና የኑሮ ክረምት በጋ ሲያልፍና ሲያሳልፍ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥቡን ታቅፎ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደረሰ፡፡

ኪሮስ ኃይለሥላሴ ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም ብቅ ያለው በ70ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የዘመናዊ ቲያትር ጥበብን ከቀሰሙ የመጀመሪያዎቹ መካከል አንደኛው ነው። ጊዜው ቀድሞ በልምድ የነበረውን የቲያትር መልክ ውስጥ ውስጡን በተማረ ኃይል እየተተካና አብዮታዊው ሽግግር እየተካሄደበትም ይመስል ነበር። ኪሮስ በ1975ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ፣ በቀጥታ ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተመደበ። ከዘመናዊው ትምህርት የቀሰመውን ዕውቀት እያካፈለ፣ እሱ ደግሞ ከብዙ አንጋፋ የቲያትር ባለሙያዎች ልምዱን እየተቀበለ፣ በብዙ ነገሮች ራሱን ለማዳበር ቻለ። ወጣትነቱንም እያበሰለ፣ ሕይወትን ማጣጣም የጀመረው ከዚሁ ቤት ላይ ነው። ከወጣትነቱ አንስቶ እስከ ጉልምስና በነበረው የዕድሜ ጉዞና ርምጃዎች መነሻና መድረሻ ከዚሁ የተሳሰሩ ናቸው።

በአብዛኛው እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ከቲያትር ጋር የተያያዙ ነበሩ። የቬኑስ ነጋዴ፣ ሳልሳዊ ባልንጀራ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ ጣውንቶቹ፣ ባልቻ አባነፍሶ፣ ጠልፎ በኪሴ፣ አሉ እና ሌሎችም የትወና ችሎታውን የገለጡ ቲያትሮች ናቸው። ኪሮስ 18 ያህል የሙሉ ጊዜ ቲያትሮችን መሥራት ችሏል። በቲያትር መድረኮች ላይ ብቻ ሳይገታ፣ በበርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎች ውስጥም ምስሉን አኑሯል። በገመና 1 እና 2 ተከታታይ ድራማ ሠርቷል። ከሠራቸው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች መካከል “ዳና” በተሰኘው ድራማ ውስጥ ያየው ማንም ኪሮስን ላለማድነቅም ሆነ ለመርሳት አይቻለውም። በፊልሞች ውስጥም እንዲሁ የገዘፈ ዐሻራውን ማኖር የቻለ ነው። ሰማያዊ ፈረስ፣ ስላንቺ፣ ስጋ ያጣው መንፈስ፣ 15ኛ ደቂቃ ኦፕሬሽን…እኚህን ጨምሮ በ16 ፊልሞች ውስጥ የትወና ብቃቱን አሳይቶባቸዋል። ኪሮስ የሚታወቀው በአማርኛ ትወናዎቹ ውስጥ ብቻ አይደለም፤ “ፀዋር ልቢ”፣ “ሓድጊ”፣ “እዛ መሬት” እና በሌሎችም ተከታታይ የትግርኛ ድራማዎች ውስጥ ተሳትፏል፡፡

ኪሮስ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ ለረዥም ዓመታት በትወና ሙያው ከማገልገሉ ባሻገር፣ በተለያዩ የኃላፊነት ወንበሮች ላይ ተቀምጦም ቲያትር ቤቱን ለማቅናት ደፋ ቀና ብሏል። ኪሮስ በኪነ ጥበብ መሰላል ላይ ቆሞ ሲያንጽ የታየው እንደ እናቱ በሚያያት ሀገር ፍቅር ቤት ውስጥ ብቻ አይደለም። በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በሥነ ጥበባት ማስተባበሪያ ዘርፍ ውስጥ በሃላፊነት ሠርቷል። የባህል መምሪያው ኃላፊ ሆኖም አራቱን የአዲስ አበባን ቲያትር ቤቶችን በአንድ ላይ መርቷል። በእነዚህና በሌሎችም፣ በጊዜያዊና በመደበኛ ተልዕኮዎች ውስጥ ለኪነ ጥበቡ ዘርፍ፣ በተለይም ለቲያትር ዕድገት ሳያንገራግር በቆራጥነት አገልግሏል። በባህሪው በእያንዳንዱ ቦታና ጊዜ ላይ ከሁኔታዎች ጋር የመጣጣም የተለየ ችሎታ አለው። ሁሉንም እንደ አመጣጡና እንደመልኩ የማስተናገድ ጥበብን ያዳበረው ምናልባትም ካለፈባቸው መንገዶችና ካገኛቸው ልምዶች ይሆናል።

ከወጣቶች ጋር ወጣት ሆኖ ይታያል። ያለምንም የስሜት የበላይነት ያደምጣቸዋል። ስሜታቸውን ይረዳል። ከልጅ ከአዋቂው ጋር መግባባትን ያውቅበታል። ለጀማሪው ጆሮና ልቡን ሰጥቶ፣ ዕውቀትና ልምዱን ማጋራትን አይታክትም። በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኃላፊነት ሲሠራ በነበረባቸው ጊዜያቶች ውስጥ ለወጣቶች የነበረው ቦታና አገልግሎት በልዩነት ነበር። ወጣቶቹ ጀማሪያን በቲያትር ክበባትና በኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው እንዲሠሩና አዳብረው ወደ መድረክ እንዲያወጡት ያደርጋቸው ነበር። የነብስ ጥሪያቸው አድማጭ አልባ ጩኸት እንዳይሆን፣ በተቻለው ጆሮና ልብ ከሙያው ጋር እየሰጠ ይተጋላቸው ነበር።

ከእርሱ አንጋፋ የሆኑትንም ሆነ አቻዎቹን ማክበርና የሚገባቸውን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ በየትኛውም አቅጣጫ ቢበደሉና የተገባቸውን ቢነፈጉ እንደራሱ ጉዳይ አድርጎ ከመሟገት ወደኋላ አይልም። ከእነዚህ ማንነቶቹ የተነሳ፣ ኪሮስ ከማንም ለማንም የቅርብ ነው። በሁሉም ቦታ ለሁሉም መጠሪያው “ኪያ” ነው። ‹የኔ› የኔ እያሉ ይጠሩታል። “አንደበተ ርቱእ እና የተረት አባት” እያሉም ያሞካሹታል የቅርብ ጓደኞቹ። በዚሁ አንደበቱም በ166 ያህል መድረኮችን መርቷል። በሚያምረውና በሚያስገመግመው ወፍራም ድምጹ መድረክ ላይ ቆሞ ብዙውን አጋፍሯል፡፡

ኪሮስ ኃይለ ሥላሴ ከብሔራዊ ቲያትር በጡረታ የወጣው በ55 ዓመቱ ነበር። ከዚህ በኋላ ኪሮስ እንደ አብዛኛው ጡረተኛ ሰፈር ላይ አልዋለም። ከህመም ጋር ብዙ ነገሮች የማያመቹ ቢሆኑም ደፈር ብሎ ከአንድ ወዳጁ ጋር ተስማምተው ወደ ሸገር ኤፍ ኤም ሄዱ። የአየር ሰዓት ወስደው በአንድ ፕሮግራም ላይ ለሁለት ለመሥራት ነበር። የአየር ሰዓት አግኝተው የራሳቸውን ዝግጅትም ማቅረብ ጀመሩ። ነገር ግን ትልቅ ፈተና ገጠማቸው። የአየር ሰዓት ያህልን ነገር ይዞ፣ ያለ ዝግጅት አጋር (ስፖንሰር) መቀጠል ብቻ ሳይሆን መጀመሩም ከባድ ነውና በባትሪ ቢፈለግ የሚደግፍ ጠፋ።

ከወራት በፊት ኪሮስ ከአንድ ፖድካስት አዘጋጅ ዘንድ ቀርቦ ስለዚሁ ጉዳይ አነሱ። ኪሮስ ሁኔታውን ሲገልጽም፤ ለስፖንሰር በሄዱበት ድርጅት “ኮሌጅ ነው ወይ የከፈታችሁት…” መባላቸውን አነሳው። አጋርነት የተጠየቁቱ ኮሌጅ ነው ወይ የከፈታችሁት ማለታቸው፤ ዝግጅታችሁ ትምህርት የበዛበትና ፈታ የማያደርግ ነውና አድማጭ ስለማይኖረው ምርትና አገልግሎታችንን በናንተ ፕሮግራም አናስተዋውቅም ለማለት ነበር። እንግዲህ የዚህ ሽሙጥ ቅኔው ሲፈታ፣ ዛሬ ላይ አብዛኛዎቻችን የምንፈልገውን እንጂ የሚያስፈልገንን የማናውቅ መሆናችንን የሚያሳይ ነው። ከቁም ነገር መሸሽ በጀመርንበት ጊዜ ላይ ኪሮስ ቁምነገር በሬዲዮ ይዞ ብቅ ቢል፤ ካላሳቅኸን ዞር በል ተብሎ ተገፋ።

የኪሮስ ሕይወት ጣዕሟ ከሀገር ፍቅር መሆኑ በብዙ ምክንያት ነው። ሀገር ፍቅር ከሰጠችው ነገሮች አንዱ የውሃ አጣጩን ነው። ባለቤቱንና የልጆቹን እናት አርቲስት ፀዳለ ግርማን ያገኘው ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ነው። አሁንም ድረስ ከግማሽ በላይ ሕይወቱና የኑሮ አደባባዩ ሀገር ፍቅር ናት። ሃሳቡ ሁሉ እርሷ ናት።

ኪሮስ ኃይለ ሥላሴ በሕይወት ዘመኑ እንደ አደይ አበባ ፈክቶና ልምላሜን ዘርቶ፣ በጸአዳ መንፈስ ከታየባቸው ቀናት ሁሉ፣ እንደ መጋቢት 27 ቀን 2017ዓ.ም ያለች ቀን የምትኖረው አይመስለኝም። ከቅዳሜዎች ሁሉ ውብ የነበረች ቅዳሜም ያቺው ቀን ናት። የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ስለርሱ ብሩህ ፈገግታዋን ካሳየችባቸው አጋጣሚዎች ሁሉም የዚያን ዕለቷ ልዩ ናት። ኪሮስ “ሀ” ብሎ የቲያትር ጥበብን የተዋወቀባትና ያወቀባት፣ ተዋህዶ ያዋሃደባት፣ ጠረንዋ እንደ እናት ጠረን ከሚጠራው ከእቅፏ ስር ገብቶ፣ ጡቶቿን ጠብቶና ጥበብን ጠግቦ የረካው በእርሷ ነው። “ኪያ” እያሉትና እያለችው፣ እርሱም “ኪያዬ” ብሎ በፍቅር የሚጠራት ናትና በስተመጨረሻ ይህን ስትመለከት የደስታ እንባ ላለማንባት አይቻላትም፡፡

በማርሽ ባንድ ታጅቦ ከስምና ሥራው ጋር ከፍ ብሏል። ከምሰሶ ማማ በላይ ከነፋሱ ጋር እንደሚውለበለብ ሰንደቅ፣ ኪሮስ በጥበብ ኃይል ተውለበለበ። የአንጋፋው አርቲስት የዘመናት ድካም ያለ እግዜር ይስጥልኝ በከንቱ እንዳይቀር ያሰቡ ሁለት ወገኖች ያንን ግሩም ዝግጀት አሰናድተውታል። አንደኛው ተስፋ የኪነ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ ሲሆን፣ ሁለተኛዎቹ ደግሞ የራሱ የኪሮስ ልጆች ናቸው። እርሱ ለሁሉም የጥበብ ልጆች አባት ነውና በእነርሱና በወዳጅ አድናቂዎቹ፣ እንዲሁም በቤተሰቡ ስም ሁሉንም ወክለው፣ ሁሉን እያሰቡ ከልዩ ልዩ የጥበብ ማዕድ ጋር በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተገናኝተው፣ እልፉን አገናኝተዋል፡፡

ዕለቱ በመሐሪ ብራዘርስ ባንድና በሌሎችም ታዋቂ ድምጻውያን የመድረክ ሥራዎች ደማምቆ አልፏል። ዕውቅ ተዋንያን የተሳተፉበት አጭር ጊዜ የመድረክ ድራማም ሌላኛው የዝግጅቱ ፍካት ነበር። ኪሮስ ከትናንት እስከ ዛሬ ያሳለፈባቸውን የሕይወት መንገድ ውጣውረዶችና ስኬቶችን የሚዳስሰው ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ የኪሮስ ሥራና ሕይወት ተቃኝቶበታል።

ኪሮስ ከዚህ ቀደም በርካታ ሽልማቶችን ከበርካቶች እጅ ላይ ተቀብሏል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንኳ “ከፍተኛ የኪነ ጥበብ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ” በሚል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅ ሽልማት ተቀብሏል። “ስላንቺ” በሚለው ፊልም በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ፊልም አዋርድ አግኝቷል። በ “ሰማያዊ ፈረስ” ፊልም ከራክማኖቭ የቲያትር ኮሌጅ ሽልማት ተበርክቶለታል። እንዲሁም በጉማ አዋርድ “የሕይወት ዘመን ተዋናይ” በሚል ለዘመናት ድካሙ ማመስገኛ ተችሮታል።

ሕይወት የክፉና ደጋ ምስቅልቅል ናት። አንዳንድ ጊዜ የማይወጡትና የማያልፉት የሚመስልን ተራራ ከፊት ትደነቅራለች። ኪሮስ እንዲሁ ይመስል ነበር። ከዓመታት በፊት መውጣትና መግባት፣ ማየትና መተያየት የናፈቀው ጊዜ ነበር። ሁሉም ነገር ለዓይኖቹ ጭልምልም ብለው ማየት ተሳነው። ብርሃኑን አጣ። እጁን ተይዞ እየተመራ የሚሄድ ሆነ። ከሚወደው ሙያ ከሚናፍቃቸው ነገሮች ተራራቀ። ደረጃ መውጣት መውረድ፣ እንዳሻው መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ነገሮች ከፉበት።

የዚያኔ ከአንድ ጋዜጠኛ ፊት ተቀምጦ አንድ ነገር ተናገረ፤ እንዲህ ሲል “ሚስቴ ቆንጆ ነች። ቆንጆ መሆኗን አይቼ፣ መርጬ ነው ያገባኋት። ሀገሬን አውቃታለሁ። ያላየሁት የኢትዮጵያ ምድር የለም። አፍሪካ ውስጥም አልጄሪያ፣ ዙምባብዌን፣ ቦትስዋናን ሩዋንዳን…አይቻለሁ። ከዓለም ፈረንሳይን፣ ቤልጂየምን፣ ስዊዘርላንድን፣ ዓይኔ ደህና ሳለ አሜሪካንም አይቻለሁ። …የምችለውን ያህል አንብቤያለሁ። ልጆቼንም አውቃቸዋለሁ መልካቸውን። ዓይኔን 60 ዓመት አይቼበታለሁ። የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር…መጽሐፍ ቅዱስን በኋላ ስረጋጋ በተመስጦ፣ ረጋ ብዬ አነበዋለሁ ብዬ አስቀምጬው፤ አሁን እሱን ማንበብ አለመቻሌ ይቆጨኛል” ብሎ ነበር።

እንግዲህ ሁሉም ነገር ለመልካም ይሆናል። አንዲት መልካም የመሰለች ቀንም ብልጭ ብላ ታየች። ከብዙ የሕክምና ድካም በኋላ፤ የሞራ ግርዶሹ በቀዶ ጥገና ተገፎለት ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ማየት ቻለ። 70ኛ ዓመት የልደት በዓሉን፣ ከ40 ዓመታት የመድረክ ቆይታው ጋር በመጋቢት 27 ቀን 2017ዓ.ም፣ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት፣ ለዘመናት ከዳከረባት መድረክ ላይ በክብር ወጥቶ፤ ኪሮስ ተከብሮ፣ አክብሮና ከምስጋና ጋር ከብሮ ወርዷል። አሁንም ረዥም ዕድሜና ጤናውን ከጸባኦቱ ያድልልን!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You