
ወቅቱ የፈረንጆቹ ድቅድቅ ክረምት አልፎ የፀደይ ጊዜ የሚገባበት መሆኑን ተከትሎ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በርካታ የጎዳና ላይ እና የመም የሩጫ ውድድሮች የሚካሄዱበት ነው።
አዲሱ የግራንድ ስላም የመም ውድድርና ዝነኛው የዳይመንድ ሊግ ፉክክሮች እንዲሁም የተለያየ ደረጃ የተሰጣቸው ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች የሚከናወኑት በዚሁ ወር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ወቅት ምርጥ የዓለም አትሌቶች በዝግጅትና በውድድሮች የሚጠመዱበት ይሆናል።
በእነዚህ ታላላቅና ስመ ጥር የአትሌቲክስ መድረኮች ተሳታፊ የሚሆኑ ክዋክብት የዓለማችን አትሌቶች በሚያደርጓቸው ፉክክሮች ሁሌም አዲስ ወይም ፈጣን ሰዓት ይመዘገባል የሚል ግምት ይኖራል። አትሌቶችም ክብረወሰኖችን ለመሰባበር በልምምድ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ በተለያዩ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ሊታገዙ ይችላሉ።
ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች አንዱ ደግሞ የመሮጫ ጫማ ነው። የመሮጫ ጫማዎች በተለይም በረጅም ርቀት ለሚወዳደሩ አትሌቶች ውጤታማ እንዲሆኑና ፈጣን ሰዓቶችን እንዲያስመዘግቡ አትሌቶች በግላቸው ከሚያደርጉት ዝግጅት ባለፈ ዘመኑን የዋጁ የመሮጫ ጫማዎች የራሳቸውን አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህን እንደ አበረታች መድኃኒት ወይም ተፈጥሯዊ ያልሆነ እገዛ በመመልከት ተገቢ አይደለም ብለው የሚቃወሙት ቢኖሩም በዓለም አትሌቲክስ ተቀባይነት በማግኘት ከዓመት ዓመት እየተሻሻለና እየረቀቀ መጥቷል፡፡
የመሮጫ ጫማዎች እየዘመኑ መጥተው በዚህ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ የዘመናት ሂደት አስፈልጓቸዋል። አትሌቶች በባዶ እግራቸው ይሮጡ እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። የእኛው ጀግና አበበ ቢቂላም ቢሆን ምንም እንኳን የመሮጫ ጫማ በነበረበት ዘመን በባዶ እግሩ በኦሊምፒክ ማራቶን ቢያሸንፍም የተለየ ታሪክ ባለቤት ያደረገው አጋጣሚ ሩቅ ዓመት የሚሻገር አይደለም።
የመሮጫ ጫማ ከታወቀና ከተለመደ በኋላ እግርን ከጉዳት ለመጠበቅ ከቆዳ እና ከዕፅዋት የሚሠሩ መጫሚያዎች ለሩጫም ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ተጽፏል። በ19ኛው ክፍለዘመን አትሌቲክስ ተወዳጅ ስፖርት መሆኑን ተከትሎ ግን ‹‹ስፓይክ›› የሚባሉት የመም መሮጫ ጫማዎች በስፋት ሊተዋወቁ ችሏል፡፡ ይህ ጫማ የላይኛው ክፍል ከስስ ቆዳ የሚሠራ ሲሆን፤ ሶሉ ደግሞ የብረት ጡት ያለውና የመሮጫ መምን ቆንጥጦ እንዲይዝ ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ነው። አሁንም ድረስ ይህን ዓይነቱ ጫማ ጥራትና ምቾቱ በየጊዜው እየተሻሻለና እየዘመነ ጥቅም ላይ ይውላል። እነዚህ የመሮጫ ጫማ ዓይነቶች የተዋወቁት በእንግሊዝ ሲሆን እንደ ኦሊምፒክ ባሉ ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች አስቀድመው በመጠቀም የታዩትም እንግሊዛውያን አትሌቶች ናቸው፡፡
እአአ 1960ዎቹ አትሌቲክስ ይበልጥ ተወዳጅ እየሆነ በመምጣቱ በመሮጫ ጫማዎች ላይ መሠረታዊ ለውጥ እየታየ የመጣበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅቶች የሚጠቀሙትን ቴክኖሎጂ በማሳደግና እንደየሩጫ ዓይነቱና የእግር ቅርጽ ጫማዎችን ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል፡፡ በቀጣይ አስርት ዓመታት ደግሞ ይኸው ሁኔታ ይበልጥ በማሻሻልና አጥኚዎችም እየተሳተፉበት የመሮጫ ጫማዎች ከመሮጫነታቸው ብቻ ባለፈ ብቃትን የሚጨምሩ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአትሌቲክስ ስፖርት ትኩረቱን ፍጥነት ላይ እያደረገ በመምጣቱ አትሌቶች ከግል ብቃታቸው ተጨማሪ አቅምን የሚሰጥ ነገር በመፈለጋቸው ነው፡፡ ፑማ እና አዲዳስ የተሰኙት የስፖርት ትጥቅ አምራቾች የተመሠረቱትም በዚሁ ጊዜ ሲሆን፤ የመሮጫ ጫማ በማምረት የተጀመረው ሥራ አሁን በዓለም ላይ እጅግ ተወዳዳሪና ስመጥር ለመሆን አብቅቷቸዋል፡፡
በ2000ዎቹ ደግሞ የመሮጫ ጫማዎች ከጊዜው የቴክኖሎጂ ደረጃ ጋር እያደጉና እየዘመኑ መጥተዋል። በቅርጻቸው ቀድሞ ከሚታወቀው የተለዩ ሲሆኑ አቅምን ከማሳደግ አልፈው ጉዳትንም እስከመቀነስ ደርሰዋል። የመሮጫ ጫማዎችን ማምረትም በስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁስ አምራቾች ዘንድ ትልቅ የንግድ ዘርፍ ለመሆን ከመብቃቱም ባለፈ እንደ ናይኪ ኤር ያሉ ምርቶች በእውቅናቸው በመላው ዓለም ለመናኘት በቅተዋል፡፡
በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄደው ይህ የመሮጫ ጫማ ፈጠራ በዋናነት ምቾትን የሚጠብቅ፣ ብቃትን የሚያሳድግ እና የሯጮችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ ነው። በዚህ ከቀጠለም መጪው ጊዜ አጓጊ ሲሆን፣ ስማርት ቴክኖሎጂ በይበልጥ የሚታይበት እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ በአንጻሩ ግን የመሮጫ ጫማን ታሪክ 200 ዓመታትን ወደኋላ የሚመልስ የባዶ እግር ሩጫ በአዲስ መልክ በማንሰራራት ላይ ይገኛል፡፡ በባዶ እግር መሮጥ ለእግር ጥቅም አለው መባሉንና ከተፈጥሮ ጋር ይበልጥ መቀራረብን ይፈጥራል የሚል እምነት በሰዎች ዘንድ ማደሩን ተከትሎም በባዶ እግር መሮጥ ዳግም ፋሽን እየሆነ ይገኛል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም