የበጋው መብረቅ እና የደመናው ሠዓሊ

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ሁለት ጀግኖችን እናያለን። አንዱ የጦር ጀግና፤ ሌላው የጥበብ ጀግና! ከጦር ጀግናው እንጀምር

የበጋው መብረቅ ጃጋማ ኬሎ

ከመቃብር በላይ የሚውል ስም ከመቃብር በታች የሆነውን ሥጋ ሕያው ያደርገዋል። ‹‹ጀግና አይሞትም!›› የሚባለው ለዚህ ነው። ጀግና አይሞትም ሲባል በሥጋ ቢያርፍም በሥራው ሕያው መሆኑን ለመግለጽ ነው። ሕያው ነው ማለት በሠራው ሥራ ሌሎችን ያሠራል ማለት ነው። የዓድዋ ጀግኖቻችን ዛሬ በሕይወት የሉም። ሥራዎቻቸው ግን ዛሬም የጀግንነት ወኔ እንዲኖር አድርገዋል። ከእነዚህ አንዱ ሌተናንት ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ ናቸው።

የበጋው መብረቅ የሚል ቅጽል ስም አላቸው፤ የበጋ መብረቅ ልዩ ክስተት እንደማለት ነው። ያረፉት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ነው።

ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ የተወለዱት ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም በቀድሞው አጠራር በጅባትና ሜጫ አውራጃ፣ በደንዲ ወረዳ ዮብዶ በተባለ ሥፍራ ነው። አባታቸው ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ) የሕፃኑ ጃጋማ መወለድ እጅግ ከፍ ያለ ደስታ አሳደረባቸው። ‹‹ … ለሰባ ዓመታት ሙሉ የጠበቅሁት አንበሳ ይህ ነው … የፈረሴን ስም ሰጥቸዋለሁ›› ብለው ‹‹ጃገማ›› ብለው ስም እንዳወጡለት ይነገራል።

ሕጻኑ ጃጋማ በተወለደ በዓመቱ እናቱ ወይዘሮ ደላንዱ በአካባቢው ተከስቶ በነበረ በሽታ ምክንያት በመሞታቸው በአክስቱና በሞግዚት እንዲያድግ አባቱ ወሰኑ። አክስቱም ጃገማን ከወንድሙ ጋር ፀበል አስጠምቀው፤ ቄስ ቀጥረው ዳዊት እንዲማር አደረጉ። በ1923 ዓ.ም ደግሞ አባቱ ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ) አረፉ።

ጃገማ ገና በለጋ እድሜው ‹‹አባቱ የመረጠው›› እየተባለ ለዳኝነት መቀመጥን፣ ፈረስ ግልቢያን፣ ጦር ውርወራን፣ ምክክቶሽን፣ ጋሻ አነጋገብን፣ ረሃብንና ውሃ ጥምን መቋቋምን፣ ውሃ ዋናን … እየተማረ በጥሩ ሥነ ምግባር አደገ። በልጅነት ዘመኑ ስለቅድመ አያቱ ጎዳና ነሞ የጀግንነት ታሪክ በተደጋጋሚ ስለሰማ እርሱም እንደቅድመ አያቱ ጀግና መሆንን ያልም ነበር፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ጃገማ ገና በ15 ዓመቱ አርበኛ ሆኖ የፋሺስትን ጦር ለመፋለም ወሰነ። ከአጎቱ ልጅ አሰፋ አባ ዶዮ ጋር ወደ ጫካ ገቡ። እህቱና ወንድሞቹም ተከተሉት። ገበሬዎች፣ ወታደሮች፣ ሾፌሮች … ከጃገማ ጋር ተቀላቀሉ። አሰፋ አባ ዶዮን ጨምሮ መጀመሪያ ከጃገማ ጋር ለአርበኝነት የወጡ ብዙ ወጣቶች በቤተሰቦቻቸው ተግሳፅ አማካኝነት ከጫካ ወጥተው ወደ መንደራቸው ቢመለሱም ጃገማ ከእርሱ በእድሜም ሆነ በሌሎች ነገሮች የሚበልጡ በርካታ ሰዎችን በስሩ ማሰለፍ ቻለ፡፡

የጃጋማ አባት በአካባቢው ዘንድ ይወደዱና ይከበሩ ስለነበር የአካባቢው ሕዝብ በታዳጊው ጃገማ የሚመሩትን አርበኞች በልዩ ልዩ መንገዶች ያግዝ ነበር። አርበኞቹም በፋሺስት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር ጦሩን መፈተን ጀመሩ። ፋሺስቶች ጥይት የሚጭኑባቸውን እንስሳት በመምታት ፋሺስቶችና ባንዳዎች ሲሸሹ አርበኞቹ መሣሪያና ጥይት እየሰበሰቡ ማከማቸት ቀጠሉ። ጣሊያኖችም ጃገማንና ተከታዮቹን ለመደምሰስ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።

አርበኞቹ በጊንጪና አካባቢው በነበረው የፋሺስት ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘራቸው ጣሊያኖች በጊንጪና በአካባቢው ጠንካራ ምሽግ ሠርተውና ጦራቸውን ጠምደው ተቀመጡ። ሐሮታና ጀልዱ የነበረው የጠላት ጦር ግንኙነት ፈጥሮ ስለነበር አርበኞቹ መተላለፊያ መስመሩን ለመቁረጥ ጥቃት ሰነዘሩ። ከጥቃቱ ባገኙት መሣሪያም ትጥቃቸውን አጠናከሩ። የጃገማ ተከታዮች ቁጥራቸው ጨመረ። ፋሺስቶች ተጨማሪ ምሽጎችን ለመገንባት ቢያስቡም ቀድመው በገነቧቸው ምሽጎች ውስጥም እንደልባቸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀሩ። አርበኞቹ በሚያዝያ ወር 1931 ዓ.ም ሐሮታና ጀልዱ የነበረውን የጠላት ጦር ግንኙነት ለመበጣጠስ የወሰዷቸው ርምጃዎች አዲስ አበባ ድረስ ተሰሙ፤ ብዙ የነፃነት ተዋጊዎችም እነጃገማ ያሉበት ድረስ ሄደው ተቀላቀሉ፡፡

በጃገማ የሚመራው የአርበኞች ጦር ምዕራብ ሸዋ በነበረው የኢጣሊያ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ብዙ ጉዳቶችን አደረሰበት። አርበኞቹ ድንገተኛ ጥቃቶችን ሰንዝሮ በፍጥነት ከአካባቢው በመሰወር የጠላት ጦር ጥይት እንዲያባክን በማድረግ፣ የአካባቢው ሰው ከፋሺስት ወታደሮችና ከባንዳዎች ላይ ጥይት እንዲገዛ በማስተባበርና ጥይት በጫኑ እንስሳት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ጥይቱን በመውሰድ የመሣሪያ ክምችታቸውን ያጠናክሩ ነበር።

በጥቅምት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማን ለማጥቃት ወደ ሰንጎታ ተራራ የሄደው 350 የፋሺስት ጦር ጃገማ በሚመራቸው 17 አርበኞች ተሸነፈ። የጃገማ አርበኞች ብዙ የጠላት ወታደሮችን ገደሉ፤ ባንዳዎች የዘረፉትን ንብረት አስመለሱ፤ ወታደሮችንና መሣሪያ ማረኩ። የጃገማ ጀግንነትም እየገዘፈ ሄደ። የአካባቢው ሕዝብም የጃገማን ጀግንነት ከቅድመ አያቱ ጀግንነት ጋር እያነፃፀረ በማውራት በጠላት ጦር ካምፕ ውስጥ ፍርሃቱ እንዲጨምር አደረገ። ወደ ወሊሶ ሄዶ በአካባቢው ከፋሺስት ጦር ጋር ሲዋጉ ወደነበሩት ወደ ደጃዝማች ገረሱ ዘንድ ሄደ። የፋሺስት ጦር በደጃዝማች ገረሱ ላይ ውጊያ ከፍቶ ስለነበር ጃገማም በውጊያው ላይ ተሳትፎ የማታ ማታ ድሉ የአርበኞቹ ሆነ። ደጃዝማች ገረሱም ‹‹ … አንተን የመሰለ ጀግና የወለደች እናት ትባረክ …›› ብለው ጃገማን አመሰገኑት፡፡

ጃገማ በአንድ ውጊያ ላይ የማረከውን የኢጣሊያ ወታደር እንዳይገደል አድርጎ ስለአርበኞቹ ኃይል እንዲሁም ስለፋሺስቶች ፈሪነትና አረመኔነት ከነገረው በኋላ ‹‹ከምርኮኝነት ነፃ የምትወጣው ለጥይት መግዣ የሚሆነኝን 10 ሺህ ሊሬ ከከፈላችሁኝ ብቻ ነው›› አለው። በአንድ ኢጣሊያዊ መልዕክተኛ አማካኝነት ጃገማ 10 ሺህ ሊሬ ተቀብሎ ምርኮኛውን ፈታው። ምርኮኛውም ወደ ጦር ሠፈሩ ሄዶ ስለጃገማ ጀግንነት ለአለቆቹ ሲነግራቸው ደስ ባለመሰኘታቸው ወደ ሌላ ሥፍራ አዛውረውታል።

ጃገማ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም። ጃገማ ደጃዝማች ገረሱን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት ‹‹ … ጃገማ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሠራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና …›› የሚል መልዕክት ከስመ ጥሩዋ የውስጥ አርበኛ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ደረሰው። ጃገማም በፍጥነት ወደ አዲስ ዓለም አቅንቶ የምሽግ ሰበራው የጦር አዝማች ሆነ። ጥቃቱን አፈፃፀም የሚያሳይ መመሪያ ለባልደረቦቹ አስረድቶ የስምሪት ትዕዛዞችን ሰጠ። ራሱ ምሽጉ ውስጥ ገብቶ ቦምብና ሌሎች መሣሪያዎችን ይዘው የነበሩ የፋሺስት ጦር ባለሥልጣናትን ገድሎ የመሣሪያ ዝርፊያው እንዲፈጸም አደረገ፤ እስረኞችንም አስፈታ። በዘመቻው ላይ ከአርበኞቹ ወገን የሞቱት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከጠላት ወገን ግን ከ100 በላይ ጣሊያናውያንና ጠባቂዎቻቸው ተገድለዋል።

በመጋቢት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማ የጭልሞን ምሽግ ከቦ በፋሺስት ጦር ላይ ተኩስ ከፈተ። ‹‹እጃችሁን ካልሰጣችሁ አንላቀቅም!›› የሚል መልዕክትም አስተላለፈ። ‹‹እንደራደርና እጅ እንሰጣለን›› ካሉ በኋላ አዘናግተው ሊያመልጡ ሲሉ ከአርበኞቹ ተኩስ ተከፈተባቸውና 13 የኢጣሊያ ወታደሮችና አንድ ሺህ 500 ባንዳዎች ተማረኩ። ጊንጪ በጃገማ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለች። ወዲያውኑም ጃገማ የኢጣሊያ ጦር የሚተማመንበት የሐሮታ ምሽግ ላይ ጥቃት እንዲከፈት አዘዘ። የጠላት ጦር አንድ ጊዜ እየሸሸ፤ ሌላ ጊዜ እያጠቃ መፋለሙን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ ጃገማ ብቻውን ሆኖ ቦታ እየቀያየረ መድፍ ሲተኩስ የፋሺስት ጦር ተስፋ ቆርጦ ለመጨረሻ ጊዜ ሸሸ፤ ከሞት የተረፈውም ተማረከ። የጃገማ ጦር በድል አዲስ ዓለም ገባ። ሆለታንም በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡

ከግንቦት 1934 ዓ.ም ጀምሮ ሆለታ ገነት ጦር ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመግባት የውትድርና ሥልጠና አጠናቆ የሻለቃነት ማዕረግ አገኘ። ከዚያም ለጥቂት ጊዜያት ያህል በአምቦና በቢሾፍቱ ተመድቦ አገልግሏል። ከዚያም በአምባላጌና በራያ አዘቦ በግዳጅ አፈፃፀም ላይ ባሳየው ብቃት በሜጀር ጀኔራል አበበ ዳምጠው ተመስክሮለት ሻለቃ ጃገማ የብርጌድ አዛዥ ሆኖ ተሾመ።

በ1947 ዓ.ም የሌተናንት ኮሎኔልነት ማዕረግን አገኘ። የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ማርሻል ቲቶ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የተደረገላቸውን የክብር ሰልፍ የመሩት ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ ነበሩ።

በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ለማክሸፍ ለጥቃት የተንቀሳቀሰው ኃይል አዛዥ ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ ኬሎ ነበሩ። በ1958 ዓ.ም የሜጀር ጀኔራልነት ማዕረግን አግኝተዋል። በ1965 ዓ.ም ደግሞ የብሔራዊ ጦር አዛዥ ሆነው ተሹመዋል።

በፈረስ ስማቸው ‹‹አባ ዳማ›› የሚባሉት፣ ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። ጀግናው ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው በዕለተ እሑድ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

የደመናው ሠዓሊ

ሌላው በዚህ ሳምንት የሚታወሱት ሰው ደግሞ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ናቸው። አርቲስቱ ያረፉት ከአሥራ ሦስት ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ነው።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፤ በአሁኑ ሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንኮበር ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ. ም ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ነው።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ ሀገር በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ በሥነ ሥዕል በቅርፃ ቅርጽና በሥነ ሕንፃ ዲዛይን ተከታትለዋል፡፡

በነበራቸው የሥነ ሥዕል ዝንባሌ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን፤ በወጣትነት ዘመናቸው በ1957 ዓ.ም ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ጋር ከኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እጅ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል። ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች አባል ሲሆኑ በተሰማሩበት የሥነ ሥዕል ጥበብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ታላላቅ ሰዎች የሚሰጠውን ‹‹የዓለም ሎሬት›› የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል። ከዘጠና ሰባት በላይ የዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡

በሥዕሎቻቸውም፤ ሥርዓተ አምልኮን፣ ማኅበራዊ አኗኗር የማኅበረሰቡን ደስታና ኀዘንና ጀግንነቱን ሥልጣኔውንና ሀገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን አበርክተዋል። በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና እምነት በመነጨ ለተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በስቱዲዮአቸውና በጸሎት ቤታቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ሥዕላትን አበርክተዋል። ከሠሯቸው መካከልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በግድግዳ ላይ የተሠሩ መንፈሳዊ ሥዕላትን በቀለም ቅብ፣ በባለቀለም ጠጠሮች፣ በክርክም መስታወቶችና በሞዛይክ ከታወቁትና ስመ ጥር ከሆኑት ሠዓሊ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ጋር ሠርተዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ውስጥም ሥዕሎታቸው በክብር ተቀምጠውላቸው በጎብኚዎች እየታዩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም በሥዕሎታቸውና በቅርፃ ቅርጾቻቸው አማካይነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን ‹‹ቪላ አልፋ›› የተሰኘው ባለ 22 ክፍሎች መኖሪያ ቤታቸውና የግል ስቱዲዮአቸው ውስጥ ይህንኑ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርገዋል፡፡

በቪላ አልፋ ስቱዲዮ ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት ሥዕላት፣ የተወለዱበት አንኮበር የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሚያስደንቁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ እሴቶችን አካቶ የያዘ ነው። ቪላ አልፋ ዛሬም በሥዕል ማሳያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ በልጅነታቸው የሰማይ ደመናን አንጋጠው በመመልከት ይመሰጡ ነበር። ደመናው የተለያየ አይነት ቅርጽ ሲሠራ በተፈጥሮ ይደመማሉ። ማነው እንዲህ በተለያየ ቅርጽ የሚሠራው እያሉ በልጅነት አዕምሯቸው ይጠይቃሉ፤ ይፈላሰፋሉ። ይህን የሰማይ ደመና መመሰጥ ወደ መሬት አውርደው እርሳቸው ደግሞ የሥዕል ሸራ ላይ መመሰጥ ጀመሩ። እነሆ የዓለም ሠዓሊም ሆኑ።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አፈወርቅ ተክሌ እነሆ በእነዚህ ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡

በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ሥዕል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የመጀመሪያውን የ‹‹ዳግም ቀረበው›› ፍርድ ሥዕል፣ በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት፣ በአዲግራት የ‹‹ዳግም ምጽዓት›› ፍርድ ሥዕል፣ በለንደን ‹‹ታወር ኦፍ ለንደን›› የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል፣ በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን ላይ የቀረበው ‹‹የመስቀል አበባ›› ሥዕል፣ ‹‹እናት ኢትዮጵያ››፣ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል እና ‹‹ደመራ›› ተጠቃሾች ናቸው።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You