ኢትዮጵያ ሰፊ ሀብት አላት። በዓለም ማህበረሰብ ጭምር እውቅና የተቸራቸው የቱሪስት መስህቦች፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች፣ ለበርካታ ዓመታት የዘለቁ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች፣ ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። ነገር ግን እነዚህን ሀብቶች የምንጠቀምበት መንገድና የሀብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ አለመሆን በርካታ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች እንዲኖሩ አስገድዷል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች አገራት የምንሰማቸው የራስ ወዳድነትና ግለኝነት ባህርያት ተዛምቶብን ከመረዳዳት ይልቅ ለራስ ከልክ ያለፈ ህይወት እስከመኖር የደረስንባቸው አጋጣሚዎችን እንመለከታለን። ለዚህም አንዱ ማሳያ በድህነት በምትታወቀው አገራችን ውስጥ የምናያቸው ከልክ ያለፉ የቅንጦት እቃዎችና የአኗኗር ዘይቤዎች ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ።
ለምሳሌ የሚላስ የሚቀመስ ያጡ በርካታ ህጻናትና አረጋውያን እንዲሁም ከ80 ሺህ የሚልቁ የጎዳና ተዳዳሪዎች ባሉባት አገራችን አንድ ውስኪ እስከ 85 ሺህ ብር የሚሸጥበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ስንሰማ ምን ያህል በህይወት ተቃርኖ ውስጥ እንደምንኖር ያመላክታል።
በዓለም ላይ በስልጣኔያቸው ቀዳሚ የነበሩት ግሪኮች በዘመናቸው ከሚመሩባቸው የህይወት መርሆዎቻቸው ውስጥ ግንባር ቀደሙ “በልክ መኖር” የሚል ነበር። ይህ ማለት ሀብት ማፍራትን ወይም ባለፀግነትን መከልከል አይደለም። ይልቁንም ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠቀምን፣ ከተረፈም ለሌላቸው ማካፈልንና ለመዝናናትም ሆነ ለደስታ ከልክ በላይ እንዳንሄድ የሚያሳስብ ነው። የእምነት መፅሃፎችም እነዚህን በልክ የመኖርና ሌሎችን የመርዳት ተግባራትን ይደግፋሉ።
በአገራችን እነዚህ የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት አልፎ አልፎም ቢሆን አልጠፉም። ለዚህም የምንመለከታቸው የመረዳዳት ባህሎች ማሳያዎች ናቸው። በዚህ ሰብአዊ ድርጊት ከተሰማሩ ማህበራት ኡቡንቱን ማንሳት ይቻላል።
ኡቡንቶ በአምቦ የሚገኝ ልጆችን ማዕከል ያደረገ ግብረሰናይ ማህበር ነው። ማህበሩ በአካባቢው ያሉ ለችግር የተዳረጉ እናቶችና አረጋውያንን በመርዳትና ልጆቻቸውን ማስተማር እንዲችሉ አቅም እየፈጠረ ያለ ተቋም ነው። ይህን ማህበር ለየት የሚያደርገው
ደግሞ ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ከሚያገኟት ጥቂት ገቢ ላይ በማካፈል በጎነትን ሰብእናቸው ባደረጉ፣ ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው ሌሎችን ለማሳደግ በተዘጋጁ የበጎ ተምሳሌቶች የተመሰረተ መሆኑ ነው።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች የተመሰረተው ይህ ማህበር በተለይ ልጆቻቸውን ያለ እናት የሚያሳድጉ እናቶችን በመርዳት በራሳቸው አቅም እንዲያስተምሩ አቅም እየፈጠረ ያለ ማህበር ሲሆን 460 አባላት ያሉት ነው። እንዲህ አይነት ማህበራት በአንድ በኩል ኢትዮጵያውያን ከተረዳዱና ለበጎነት የልባቸውን በር ከከፈቱ ምን ያህል ለሌሎች እንደሚተርፉ የሚያሳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ለእኛ መቆም እንዳለብን የሚያስተምር ትልቅ ተምሳሌት ነው።
የልደት በዓላቸውን በማክበር ሰበብ ውስኪ የሚያወርዱ፣ ትላልቅ ድግሶችን የሚደግሱ እና ለደስታና ፌሽታ የተመሰረቱ ማህበራት በተበራከቱበት በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ማህበራት መኖራቸው ተስፋን የሚሰጥ ነው።
ከዚህም ባሻገር በእነዚህ በጎ አድራጊ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ለእለት ጉርስ ብቻ ሳይሆን ነገን ያለመና ታዳጊዎች የተረጂነት ስሜት ሳይሰማቸው በነፃነት እንዲማሩና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ በማድረግ ጠንካራ አገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ተግባር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከነዚህ በጎ አድራጊ ማህበራት ጎን በመቆሙ ሊመሰገን ይገባል።
አሁን አገራችን እንዲህ አይነት መልካም ሰብእና ያላቸው ዜጎች በየዘርፉ ያስፈልጓታል። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ቁም ነገር መስራት የሚችሉ ዜጎችን በተለይ ወጣቶችን ትሻለች። አሁን ካለንበት አገራዊ ችግር በዘላቂነት ለመላቀቅ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል መሆኑን አምኖ የሚቀበሉና በመደጋገፍ ወደተሻለ ብልፅግና ለማደግ የሚጥሩ ዜጎችን መፍጠር የግድ ነው።
አንተ የዚህ አካባቢ አይደለህምና ውጣ ሳይሆን ተከባብሮና ተደጋግፎ ለማደግ የሚጥር ማህበረሰብ፣ ከአቅም በላይ በልቶ በቁንጣን የሚጨናነቅ ሳይሆን ካለው ላይ ቀንሶ ሌሎችን ለመደገፍ የሚተጋ፣ በወሬ ሳይሆን በስራ የሚያምን፣ ነገን አሻግሮ የሚያይና ሌሎችንም አቅፎ ለመሻገር የሚጥር ራዕይ የሰነቀ ዜጋ ለብልጽግናችን ወሳኝ በመሆኑ በመደጋገፍ ችግሮቻችንን መፍታት አለብን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012