የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ በርካታ የውይይት መድረኮችም እየተካሄዱበት ይገኛል። ረቂቅ አዋጁ በማህበረሰቡ ውስጥ መከባበርና እኩልነት እንዲዳብር፣ ለዲሞክራሲ ስርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሀሰት መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ያለመ ነው። በዚህም ሰዎች ሃሳባቸውን በነፃነት ሲገልፁ ሰብዓዊ ክብርንና የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማድረግ የረቂቅ አዋጁ ቁልፍ ዓላማ ነው።
በረቂቅ ህጉ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ግልጽና የማያሻሙ እንደሆኑ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጠንከር ያለ አቋሙን እየገለፀ ይገኛል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ዜጎች ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ የሚኖረው አተረጓጐምና አተገባበር ላይ ስጋት አላቸው። በዚህም የህግ አተረጓጎሙ ዲሞክራሲንና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በሚጋፋ መልኩ የሚታይ ከሆነ አዋጁ የአፋኝነት ሚና ሊኖረው ይችላል ሲሉ ይገልፃሉ።
በእርግጥ ይህ ስጋት በቅርቡ እየተሻሻለ ያለው የፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ከነበረው የጠነከረ ዱላ መሰል ስጋት ጋር የሚቆራኝ እና ጠባሳውም ለዚህ ረቂቅ አዋጅ መነሻ ስጋት ሆኗል። የፀረ ሽብር አዋጁ የሰብአዊ መብትን በግልጽ የሚጋፋ እና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ሲያፍን እንደነበር በተግባር ጭምር ያየነው ጉዳይ ነው።
በአንፃሩ ፀረ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ህግ ግን ሰብዓዊ መብትን የሚጋፋ ሳይሆን የሌሎችን ክብርና ሞራል የመጠበቅ ሚና ያለው ነው። ረቂቅ ህጉ፤ “አትሳደብ፣ አታንቋሽ” ነው የሚለው።
በመሆኑም ይህ አዋጅ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከመገደብ ጋር አይገናኝም፤ ህጉ መከባበርን የሚያሰፍን ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በተለያየ መልኩ ለግጭት እና ለሰላም እጦታችን ምክንያት የሆኑትን ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመቀነስ ጉልበት ይሆናል።
የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች አስጊ በሆነ ሁኔታ እየተበራከቱ መምጣታቸው የትኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያሳስበው ጉዳይ ነው። በዚህም የተነሳ ጉዳዩ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ጭምር ትኩረት ማግኘቱ ተገቢና ትክክለኛ ነው።
በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ ትንሽ ትልቅ ሳይል ሁሉንም ለህግ ተገዥ የሚያደርግ በመሆኑ ቢያንስ ቢያንስ በጥላቻ ንግግር እና በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚመጣን አገራዊ አደጋን ማስታገስ የአዋጁ ተልዕኮ በመሆኑ ሁሉም ሊያምንበት ይገባል።
የአዋጁ አላማ አንደኛ፤ ሰዎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብአዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል፤ ሁለተኛ በማህበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጎለብት ማድረግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት መስፋፋትንና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከልና መቀነስ የሚያስችል ነው።
የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን በተመለከተም፤ የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልፅ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆን ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ የተከለከለ ነው ይላል። ይህ ረቂቅ አዋጅ ለእነዚህ ድንጋጌዎችም ልዩ ሁኔታን ያስቀምጣል።
በልዩ ሁኔታ ድንጋጌውም አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ተወስዶ የማያስጠይቀው፡- ድርጊቱ ለትምህርት ወይም ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገ እንደሆነ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባ፣ በዲሞክራሲ ስርአት ውስጥ ተቀባይነት ያለው ትችትና የፖለቲካ ንግግር፣ የማስታወቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ አካል እንደሆነ፣ በቅን ልቦና የሚደረጉ ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች ወይም አተረጓጎም ከሆነ ነው ይላል።
አንድ ዘገባ እንደ ሃሰተኛ ዘገባ ተወስዶ በህግ የሚያስጠይቀውም ንግግሩ የጥሬ ሃቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ፣ ንግግሩ ቀልድ፣ ስላቅ ወይም ልበ ወለድ መሆኑ ግልፅ ከሆነ እንዲሁም ንግግሩን ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በእሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ነው ይላል።
በአጠቃላይ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የትኛውንም የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አያፍንም። ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትንም ቢሆን በሚፈለገው ዓላማና ልክ መግለፅ የሚያስችል ሲሆን ሃሳብን በነጻነት ከመግለፅ መብት ጋር ተያይዞ ሆነ ተብለው የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በህግ አደብ ያስገዛል። ይህ ሲሆን ደግሞ የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር ከፍ በማድረግ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመንታህሳስ 23/2012