የተደበቀው ወረርሽኝ
የሰውን ልጅ ለተለያዩ የጤና ችግሮች የሚያጋልጡና ለሞት የሚዳርጉ በሽታዎች ሁሉ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ እና የማይተላለፉ በሚል በሁለት ዋና ዋና ምድቦች ይጠቃለላሉ። ከዚህ ውስጥ በገዳይነታቸው የሚታወቁትና በዓለማችን ላይ ለሚከሰተው ለአብዛኛው ሞት ምክንያት የሆኑት “የማይተላለፉ” በሚለው ምድብ ውስጥ የሚገኙ በሽታዎች ናቸው። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የማይተላለፉ በሽታዎች በያመቱ የ41 ሚሊዮን ህዝብ ህይወትን ይቀጥፋሉ።
በያመቱ ይህን ያህል ህዝብ የሚያልቀው ከአራት በማይበልጡ የዓለማችን ቁጥር ገዳይ አንድ የማይተላላፉ በሽታዎች ነው። የልብና ከልብ ደም ቧንቧ ጋር የተያያዙ በሽታዎች በያመቱ የ17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት በመቅጠፍ የገዳይነቱን ደረጃ በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን፣ ካንሰር 9 ሚሊዮን፣ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን እንዲሁም ስኳር በሽታ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎችን በያመቱ በመግደል ይከተላሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በዓለማችን ላይ 422 ሚሊዮን በስኳር፣ 42 ሚሊዮን በካንሰር እንዲሁም 36 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ጋር የሚኖር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል በዓለም ላይ የስኳርን እጥፍ፣ የካንሰርን እና የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ህመመትኞችን ሃያ እጥፍ የሚሆኑ ከ850 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ በተለያየ ደረጃ በኩላሊት በሽታ የተጠቁ ሰዎች መኖራቸውን ዓለም አቀፉ የኩላሊት ማህበር በሰኔ 2018 ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ይህም ብቻ አይደለም ከዓለም ህዝብ 10 ነጥብ 4 በመቶ ወንዶችና 11 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ(ሦስት ወርና ከዚያ በላይ የቆየ የኩላሊት ችግር ማለት ነው) ያለባቸው ናቸው። በየአመቱ የኩላሊት እጥበትና ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ከ5 ነጥብ 3 እስከ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ቢኖሩም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ህክምናውን ማግኘት ባለመቻላቸው ብዙዎቹ ይሞታሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በያመቱ 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች በወቅቱ ካልታከመ ስር ወደ ሰደደ የኩላሊት በሽታ ሊለወጥ የሚችል የኩላሊት ችግር ያጋጥማቸዋል። ይሁን እንጂ የኩላሊት በሽታ ከማይተላለፉ በሽታዎች የሚመደብና በዚህ ደረጃ የዓለምን ህዝብ በስፋት እያጠቃ የሚገኝ አሳሳቢ የሆነ የጤና ችግር ቢሆንም ዓለም ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም።
“እናም አራቱ ዋና ዋና የማይተላለፉ በሽታዎች የሚባሉት አንድ ላይ ተደምረው ከያዙት በላይ በዓለም ላይ 850 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ በኩላሊት በሽታ እየተሰቃየ ባለበት ሁኔታ ለበሽታው ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ሊሆን የማይችል ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ አካሄድ ነው” ይላሉ የዓለም አቀፉ የኩላሊት ማህበር የአሁኑና የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ፕሮፌሰር ዳቪስ ሀሪስ እና ፕሮፌሰር አዲይራ። የአሁኑ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሌቪን አክለውም ”ቁጥሩ ያለምንም ጥርጥር ወረርሽኝ ነው። የተደበቀ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ”። “ዓለም የኩላሊት ወረርሽኝን ዓለም አቀፋዊ ስርጭት ለመቆጣጠር የዓለም መሪዎች አሁኑኑ ለበሽታው ትኩረት መስጠት አለባቸው”።
የጤናን ጉዳይ በበላይነት የሚመራው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም የጤና ድርጅትም ችግሩን አልካደም። ድርጅቱ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 2018 ባሳተመው አንድ ጥናት ከላይ ተጠቀሱትን አራቱን ዋና ዋና ኢ ተላላፊ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጠጠር በ2013 ጀምሮ ዓለም አቀፍ የትግበራ ዕቅድ መዘጋጀቱን ጠቅሶ፤ “ነገር ግን ሌላውን ወሳኝ ኢ ተላላፊ በሽታ ሳይካትት በመቅረቱ ዕቅዱን በከፍተኛ ደረጃ ለትችት የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል” ይላል። ይህም በሽታው ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝና የሚያስከትለው ጉዳትም እንዲጨምር ከማድረጉ ባሻገር የኩላሊት በሽታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከበርካታ ዋና ዋና ተላላፊና የማይተላለፉ ገዳይ በሽታዎች ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ አጠቃላይ በዘርፉ በተቀመጠው የዘላቂ ልማት ዕቅድ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ይሆናል።
ፈርጀ ብዙ ችግሮችና ማህበራዊ ቀውስ
በእኛም ሀገር እየተከሰተ ያለው ከዓለም አቀፉ ሁኔታ የተለየ አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዱ ወይም ሁለቱ ኩላሊታቸው ከጥቅም ውጪ መሆኑን ድንገት በሚያደርጉት የሃኪም ምርመራ የሚሰሙና የህክምናው ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የድረሱልኝ የእርዳታ ጥሪ የሚያሰሙ ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም። የሩቁን ትተን ለሃምሳ ዓመታት ያህል በሙያው ህዝብን ያገለገለውና ከኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለውለታዎች መካከል አንዱ የሆነው ታዋቂው የጥበብ ሰው አንጋፋውና ተወዳጁ ከያኔ ጋሽ ፍቃዱ ተክለማርያም በድንገት ባደረገው ምርመራ “ሁለቱም ኩላሊቶችህ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል” የሚለው ብዙዎችን ያነጋገረ ልብ ሰባሪ ዜና የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። የኋላ ኋላም በህዝብ ትብብርና መዋጮ ህይወቱን ለማቆየት ከፍተኛ ርብርብ ቢደረግም ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ የግማሽ ክፍለ ዘመን የጥበብ ባለውለታችንን በዚህ ክፉ በሽታ ምክንያት እስከ ወዲያኛው ማጣታችን አንረሳውም።
በሰራው ሥራ ከራሱ አልፎ የህዝብ መሆን በመቻሉ ቢያልፍም በብዙሃኑ ልብ ውስጥ ህያው ሆኖ የሚኖር በመሆኑ ብዙዎቻችን ስለምናውቀው ለአብነት ጋሽ ፍቃዱ ተክለማርያምን አነሳን እንጂ በየጊዜው በኩላሊት በሽታ ምክንያት ውድ ህይወታቸውን የሚያጡ ሌሎችም በርካታ ዜጎች መኖራቸውን መገመት አያዳግትም። መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በትልልቅ የሃገራችን ከተሞች በየቀኑ የሚሰማው “እገሌ የተባለ ግለሰብ ኩላሊቱ/ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ በመሆናቸውና ህክምናውን ለማግኘት የተጠየቀው ወጪ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ የወገናችንን ህይወት ለመታደግ ያላችሁን እንድትተባበሩን በፈጣሪ ሥም እንለምናችኋለን” ከሚሉ የድረሱልኝ ጥሪዎች(“ቢዝነስ የሚሰሩትን” አይጨምርም) የምንታዘበውም ይህንኑ ነው።
የኩላሊት በሽታ ዕድሜ፣ ጾታና የሀብት ደረጃ ሳይለይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እያጠቃ የሚገኝ በአንጻሩ ለህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ለብዙዎች ከአቅም በላይ በመሆኑ ከጤና ችግርነት አልፎ ውስብስብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን እያስከተለ የሚገኝ በሽታ ነው። በእንግሊዝኛው Chronic Kidney Disease” የሚባለው ከኢንፌክሽን ደረጃ ያለፈ በተለይም በድሃ አገራት ችግሩን የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ህክምና እጅግ ውድ በመሆኑ ወጪው ለህመምተኞች ከአቅማቸው በላይ ስለሚሆን ነው።
ኩላሊት በሽታን ለማከም ሁለት አማራጮች ነው ያሉት። እነዚህም አንደኛው ተከታታይ የኩላሊት እጥበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በከፍተኛ ቀዶ ህክምና አማካኝነት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ ነው። ሁለተኛው አማራጭ የተሻለ መፍትሔ ቢሆንም የህክምና ወጪው እጅግ ውድ በመሆኑ በአብዛኞቹ ድሃ አገራት በኩላሊት በሽታ የተለከፉ ዜጎች ከህመማቸው ለመዳን ሁለተኛውን አማራጭ ይከተላሉ። ይህም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ሰዎች ሁለተኛው አማራጭም ቢሆን ከአቅም በላይ ነው። በመሆኑም ከአባላቱ ውስጥ አንዱ በኩላሊት በሽታ የታመመበት ቤተሰብ ህመምተኛውን በሞት ላለማጣት ሲል ያለውን ሁሉ ለመሸጥ ይገደዳል።
ከዕለት ወይም ከወር ገቢው ባሻገር ዕቃውን፣ ቤቱን፣ መሬት ያለው መሬቱን…ሃብት ንብረቱን ሁሉ እየሸጠ በየጊዜው የሚደረገውን የህክምና ወጪ ይሸፍናል። በመጨረሻም የሚከፈል ሲታጣ ህክምናው ይቋረጣል፣ ህመምተኛው ከበሽታው ሳይድን መላ ቤተሰቡ ለችግርና ለድህነት ይጋለጣል። ቤተሰብ ይበተናል፣ ልጆች ጎዳና ይወጣሉ፣ ችግሩ ከግለሰብ አልፎ በሃገር ላይ ይሆናል፤ ማህበራዊ ቀውስ ይፈጠራል።
በዚህም ህመምተኞችን በቋሚነት ለመደገፍና በነጻ ህክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በቅርቡ ከኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት የተላለፈው ጥሪም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ጥሪው የተላለፈበት ምክንያት ለኩላሊት ህሙማኑ የሚያስፈልገው የህክምና ዋጋ ወጪ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል። አገራዊ ጥሪው የቀረበው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለሁሉም ሥራ አስኪያጆች ሲሆን ድርጅቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠትና የሚሰጠውን ህክምና በገንዘብ በመደገፍ ህመምተኞችን ለመርዳት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል። በቅርቡም ከባንኮች ጋር በመተባበር በዘውዲቱና በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሆስፒታሎች ዘጠና የሚደርሱ የኩላሊት ህሙማን ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚታከሙበትን ዕድል አመቻችቷል።
“ሆኖም…” ይላሉ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ባስተላለፉት ሃገራዊ ጥሪ “ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለህሙማኑ ህክምና የሚያስፈልገው ወጪ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱና ከዚህ ቀደም በወር አስራ ስምንት ሺህ ብር የነበረው የኩላሊት እጥበት ወጪ በአሁኑ ሰዓት እስከ ሃያ ሁለት ሺህ ብር በመድረሱ ወጪው በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ብቻ የማይቻል በመሆኑ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ሥራ አስኪያጆች በሥራቸው የሚገኙ ሠራተኞቻቸውን በማስተባበር ሠራተኛው ከደመወዙ ላይ በየወሩ ሊያስቆረጥ የሚችለውን ያህል ድጋፍ የሚያደርግበትንና ፔሮል ላይ ተተክሎ ህሙማኑ በቋሚነት የሚደገፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው ለሁሉም ሥራ አስኪያጆች አገራዊና ወገናዊ ጥሪያችንን ያስተላለፍነው”።
ድሃው ላይ የባሱት “የሀብታም በሽታዎች”
ቴክኖሎጂ ነገሮች ከመጠን በላይ እንዲቀሉ በማድረጉ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤም በእጅጉ ተቀይሯል። ይህም ሰዎች እረፍት እንዲያበዙና ከአካላዊ እንቅስቃሴ እንዲርቁ መንስኤ ሆኗል። በብዙ አገራት የቴክኖሎጂውን ዕድገት ተከትሎ የሚመጣው የኢኮኖሚ ዕድገትም ሰዎች ከተፈጥሯዊ እህሎችና ጥራጥሬዎች ከሚመረቱ ምግቦች ይልቅ ወደ ጣፋጭና ቅባት የሚበዛባቸው ስጋ ነክ ምግቦች እንዲያዘነብሉ አድርጓል። ይህም በኢኮኖሚ በበለጸጉ ሃገራት ሰዎች ለክብደት መጨመር፣ ለደም ቧንቧ መጥበብና ለከፍተኛ ደም ግፊት እንዲሁም ለስኳርና ለልብ ለመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዲጋለጥ ያደርጋል።
ለኩላሊት በሽታ መንስኤ ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ ምክንያቶች መካከል ስድሳ በመቶ የሚሆነውን አብላጫውን ድርሻ የሚይዙትም እነኝሁ ከአመጋገብና ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ። በመሆኑም ኩላሊትም ሆነ እንደ ልብና ካንሰርን የመሳሰሉ በከፍተኛ ደረጃ ዓለምን እያጠቁ የሚገኙ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ገዳይ በሽታዎች በቴክኖሎጂና በዘመናዊ ስልጣኔ መስፋፋት ምክንያት ከአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በመሆናቸው በአብዛኛው የሚከሰቱት በበለጸጉት አገራት ነው። በዚህ የተነሳም “የሃብታም በሽታዎች” በሚል ቅጽል ስም እስከ መታወቅ ደረጃ ደርሰዋል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነገሩ ሁሉ ተገለባብጦ “ያ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ” በሚለው አባባል እየተቃኘ ያለ ይመስላል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ማህበር በአውሮፓውያኑ 2012 ያሳተመው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በዓለም ላይ ከሚከሰተው ጠቅላላ የሞት መጠን ውስጥ ስድሳ በመቶ የሚሆነውን የሚይዙት እነዚያ “የሃብታም በሽታዎች” ከነባራዊው እውነታ በራቀ መልኩ ዛሬ ላይ በድሃው ብሰዋል። በሽታም ቢሆን “የሃብታሞች” የሚለው ባለቤትነት ለድሆች እንዲሰጥ ሃብታሞቹ አገራት አልፈለጉም ይሆናል እንጂ እንዲያውም “የድሃ በሽታዎች” ተብለው መቀየር ነበረባቸው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም “የሃብታም በሽታ” ይባሉ የነበሩት እነ ኩላሊት፣ ልብና ካንሰር በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከሚያስከትሉት ጠቅላላ የሞት መጠን ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸውና በዕድገት ወደ ኋላ በቀሩ ታዳጊ አገሮች ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለማችን ፈተና እየሆኑ የመጡት እንደ ልብና የልብ ቧንቧ፣ ስኳር፣ ካንሰርና ከፍተኛ ደም ግፊትና ኩላሊት የመሳሰሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በቀጣይ አስር ዓመታትም እየጨመሩ እንደሚሄዱ ጥናቱ የተነበየ ሲሆን ከፍተኛው(27 በመቶ የሚሆነው) ጭማሪ የሚከሰተው በድሃዋ የዓላማችን አህጉር በእኛዋ ማማ አፍሪካ መሆኑ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል። ታሪክ ዳቦ አይሆንም ቢባልም ዜጎቿ ታሪክ እንጂ ዳቦ ባልጠገቡባት የእኛዋ ምስኪኗ እምዬ ኢትዮጵያም በሽታው በከፍተኛ ደረጃ ይከሰትበታል ተብሎ በተተነበየውና በዓለም ላይ ሥር በሰደደ ድህነቱ በሚታወቀው የከሰሃራ በታች የአፍሪካ ክልል የምትገኝ መሆኗ ሁላችንም ያሳስበናል። ለበሽታዎቹ ህክምናና ምርመራ ከሚያስፈልገው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አኳያ ችግሩን እጥፍ ድርብ ስለሚያደርገው ትኩረት ሰጥታ መስራት እንደሚገባት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሰራው ጥናት በአጽንኦት ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ያመላክታል።
መፍትሔ፡- “ህዝብና መንግስት ቢያብር
ችግሩን ያስር”
በእርግጥ በእኛም አገር ያለው ከዓለም አቀፉ ሁኔታ የተለየ ባለመሆኑ የህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ኩላሊትን ጨምሮ ሌሎችም የማይተላለፉ በሽታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው የሚጠበቅ ነው። ሆኖም እስካሁን ባለው ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ የኩላሊት በሽታ ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ፣ የተጠቂዎችን ቁጥር፣ በሽታው እያስከተለ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር፣ እየፈጠረ ያለውን ማህበራዊ ቀውስ የሚያሳይ የተደራጀ መረጃ አለመኖሩን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህም መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳይኖራቸውና ለችግሩም ተገቢውን ትኩረት እንዳይሰጡ አድርጓል። እናም እንደ ሃገር የበሽታው ስርጭት ያለበት ደረጃና የጉዳት መጠን ለማወቅና ለችግሩ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን ነው እንላለን።
እንዲሁም ህብረተሰቡ ራሱን ከዚህ አስከፊ በሽታ አስቀድሞ እንዲከላከል ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎንም ህመምተኞች በቂ ድጋፍ የሚያገኙበትና በዘላቂነት ከህመማቸው የሚፈወሱበትን መንገድ ማመቻቸትም እንደ ሃገር ችግሩን ለመፍታት ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ውጤታማ ያደርጋል። ለዚህም መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጎች የድርሻቸውን መወጣት የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋትና ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ መንግስትና ህብረተሰቡ እጅና ጓንት ሆኖ አንድ ላይ ተባብሮ መሥራት ከቻለ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እንደጀመረው የኩላሊት ህሙማን በነጻ ህክምና የሚያገኙበት እንዲሁም የህሙማኑን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻል መሆኑን የበርካታ የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ያሳያል። በእኛም ሃገር ሁላችንም ከተባበርን የምንችለውን ካደረግን ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በሚለው ወርቃማ ዕሴታችን መንግስትም ህዝብም ሁሉም አንድ ላይ ቢያብር የማይቻል የሚመስልን ችግር ማሰር እንችላለን። ችግሩን በዘላቂነት መፍታትና አገራችንን ከማህበራዊ ምስቅልቅል መታደግ እንችላለን።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
ይበል ካሳ