‹‹የአብዬን ለእምዬ›› እንደሚባለው ለአገር ጥቅም የተሟገቱ እንደ ጥፋተኛ፤ ተቆጥረው በሕገወጥ መንገድ አገሪቱን ለውድቀት የሚዳርጉ ኃላፊዎች ደግሞ በሹመት ላይ ሹመት እየተደረበላቸው የፍትሕን ሚዛን የሚያዛቡ ኩነቶች መከወን ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥሯል። በዚህ ሁኔታም ሰሞኑን ወደ ቢሯችን የመጣ ጉዳይ ተመልክተናል። ለዓመታት ከሠሩበት በቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በአሁኑ ደግሞ የገቢዎች ሚኒስቴር ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞች ቅሬታቸውን እንዲህ አቅርበዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የተቋሙ የበላይ የሥራ ኃላፊዎች እኩይ ተግባራቸውን የሚረዳ ደንብ ቁጥር 155/2000 የተሰኘ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት አገርን ለኪሳራ፤ ዜጎችን ለእንግልት እንደዳረጉ ይናገራሉ። በደንቡ እንደተቀመጠው፤ ማንኛውም የሥራ ኃላፊ በሕገወጥ ሥራ ላይ ተሰማርቷል በሚል የጠረጠረውን ባለሙያ ማባረር እንደሚችልና ሠራተኛውም በሕግ ፊት ቀርቦ መከራከርም ሆነ በየትኛውም ተቋም ዳግም ተቀጥሮ መሥራት እንደማይችል ማስፈሩን ይጠቁማሉ። ይህም የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት የሚፃረር እንደሆነ ብሎም በዚህ ደንብ የደረሰባቸውን ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ያብራራሉ። እኛም የዛሬው የፍረዱኝ ባለጉዳዮቻችንን አቤቱታ፣ የሰነድ ማስረጃዎች፣ የሕግ ማዕቀፎችና የሚመለከተውን አካል ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።
የቅሬታው መነሻ
አቶ ደረጀ ታደሰ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን በኋላም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኛ እንደነበሩ ይናገራሉ። በተቋሙ በአሰብ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ በኋላም ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ መጠቀም ስትጀምር የጅቡቲ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ለረጅም ዓመታት ማገልገላቸውን ያስታውሳሉ። በኋላ ላይም ቡሬ ቅርንጫፍ ላይ የጽሕፈት ቤቱ አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል።
ከ1995 ዓ.ም በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተቀይረው ይመጣሉ። የተቋሙ አሠራር ወደብ ላይ ከነበረው የተለየ ሆኖ በማግኘታቸው ቅያሬያቸው የፈጠረላቸው ደስታ ብዙም አልቆየም። በወቅቱ ለተቋሙ በሐቅ መሥራት ለአገሪቱ በሐቅ መሥራት ውንጀላን ያስከትል እንደነበርም ነው የሚገልፁት። እንደ ጥፋተኛም ያስቆጥር ነበር። በዚህ የተነሳ ብዙ መከራና ስቃይ እንዲሁም እንግልትን ለማስተናገድ ተገድደዋል። በተለያየ ጊዜ በሥራ ኃላፊዎች ልዩ ልዩ ጫናዎች ደርሶባቸዋል፤ ከሥራ የመባረር ጽዋንም ተጎንጭተዋል።
አቶ ደረጀ ችግሮቹን ሁሉ ተቋቁመው ለመውጣት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርተዋል። ጫናዎቹ ከደንብና መመሪያ ውጭ ሥራዎች እንዲፈፀሙ ማስገደድ፤ በዚህም የመንግሥት፣ የሕዝብና የአገር ጥቅም እንዳይገኝ ማድረግ፤ ግለሰቦችን ለመርዳት ሲባል ብቻ የተቋሙ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የሚያሳድሩ ተግባራትን እንዲፈፅሙ ይገደዱ እንደነበርም ነው አቤቱታ አቅራቢው የሚናገሩት። በ2006 ዓ.ም ከነበሩበት የቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲባረሩ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያትም ይኸው እንደሆነ ያስረዳሉ።
በነበሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ይሠሩ የነበሩበት ቦታ በመንግሥት የተሰጧቸው መብቶች የሥራ ሂደት ሥር የኮንስትራክሽን ቡድን አስተባባሪ ነበሩ። ይኼ ዘርፍ ደግሞ የበርካቶችን ትኩረትና ቀልብ የሚስብ፤ በብዙ የከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት እርከኖች ላይ የተቀመጡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ዘርፉ በአገሪቱ ውስጥ ከግንባታ ጋር ተያይዞ ከባሕር ማዶ የሚገቡ ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ በመሆኑ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሕጋዊ መንገድ መንግሥት የሠጣቸውን ማበረታቻ ተጠቅመው የሚገቡ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች ደግሞ የሕጋዊ ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ ሕገወጥ ነገሮችን ወደ አገሪቱ ለማስገባት ጥረት ያደርጋሉ። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ደንብና መመሪያ የማይፈቅድላቸው ‹‹አይቻልም›› ተብሎ ሲከለከል የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች እጃቸውን በማስገባት ሕገወጥ ድርጊቱን በመተባበር ጫና ያሳድሩ እንደነበር ይገልፃሉ።
የተለያዩ ሰዎችን ለመጥቀም ከመመሪያ ውጭ ይሠሩና ያሠሩ ነበር። ለአብነት በ2005 ዓ.ም ደንብ ቁጥር 270/05 የሚል ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ ለገቡ ማሽኖች ማበረታቻ የሚሆን ፒክ አፕ ተሽከርካሪ ለኮንትራክተሮች የሚፈቅድ ደንብ ወጥቶ ነበር። ነገር ግን ይህን በሚፃረር መልኩ መመሪያው የማይፈቅድላቸውና ደረጃ አንድ ላይ በሕንፃ ግንባታ ሥራ የተሠማሩ ኮንትራክተር በሕጉ ከተፈቀደላቸው ሁለት ፒክ አፕ በተጨማሪ ሌላ ሁለት ተሽከርካሪ ያስገባሉ።
ለኮንትራክተሩ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሁለቱን ብቻ ማስገባት እንደሚችሉ ምላሽ ተሰጥቷቸው ለቀሪ ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ቀረጥና ታክስ ለመክፈል መስማማታቸውን የሚያስታውሱት አቶ ደረጀ፣ የባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ አመራሮች በጉዳዩ ላይ እጃቸውን ማስገባታቸውን ይናገራሉ። ኃላፊዎቹ የደረጃ አንድ ባለሙያው አራቱንም ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ ማስገባት እንደሚችሉ የሰጡት ውሳኔ ውዝግብ ያስነሳል። ይህም ተገቢ እንዳልሆነ ሙግት ውስጥ በመግባታቸው የበላይ ኃላፊዎቹ ጫና ያሳድሩባቸው ጀመር።
አራቱንም ከቀረጥ ነፃ ማስገባ እንደማይቻል ለኃላፊዎቹ ለማስረዳትና ሕገወጥ ድርጊቱ እንዲቆም የተቻላቸውን ሁሉ እንደጣሩ የሚናገሩት አቶ ደረጀ፤ ከእርሳቸው አቅም በላይ ሆኖ ጉዳዩ ውሳኔ ተሰጥቶበት አገርን ጥቅም በሚያሳጣ መልኩ ግለሰቡ ተሽከርካሪዎቹን እንዳስገቡ ነው የሚያስታውሱት። በጉዳዩ ጥርስ የተነከሰባቸው የመጀመሪያ አጋጣሚ ይሁን እንጂ መሠል ድርጊቶች ድግግሞሽ ሐዘንን ይፈጥርባቸውና ከዝምታ ይልቅ ፊት ለፊት መታገልን አማራጭ እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። ለአገር ጥቅም መሟገታቸውም ከሥራ እስከ መሰናበት እንዳደረሳቸው ይገልፃሉ።
የተጣለባቸውን የሕዝብና የመንግሥት ኃላፊነት ወደጎን በማለት በአገር ላይ ክህደት በእርሳቸውም ላይ ግፍ የፈፀሙት የሥራ ኃላፊዎች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሥልጣን እርከን ላይ ካባቸውን ቀይረው መታየታቸው ሐዘን እንደሚፈጥርባቸውም አቶ ደረጄ ይናገራሉ። ከሥራ ያሰናበታቸውን ዋነኛው ጉዳይ ሲያስታውሱም፤ በ2005 ዓ.ም በተቋሙ ሠራተኞች ‹‹የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነትና ፀረ አደርባይነት›› በሚል አገራዊ ንቅናቄ የሥልጠና ሰነድ እንዲዘጋጅ ከፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽንና የተቋሙ የሥነ ምግባር ዳይሬክቶሬት የሥራ አቅጣጫ ይሰጣቸዋል። በዚህም የተቋሙን አሠራር ለማሻሻል በዋና ዋና ሥራዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለሥልጠናው በሚጠቅም መልኩ ሠነዱን እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል።
እንዲያዘጋጁ የተነገራቸው ሠነድ ብዙዎችን ያስኮረፈ ነገር ግን ደግሞ በእርሳቸው ሚዛን ዕውነታነት እንደነበረው አቶ ደረጀ ያስታውሳሉ። በኋላም በአዳማ ከተማ የተቋሙ መላ ሠራተኛው በተገኘበት ውይይት ይደረጋል። በውይይቱ የተቋሙ ዋና ችግርና የሠራተኞች ብሶት ምን እንደነበር በግልጽ ተንትነው በሠነዱ ማስፈራቸው ያልተዋጠላቸው የሥራ ኃላፊዎች ከሥልጠናው መልስ የሥነ ምግባር ችግር አለባቸው በሚል አለአግባብ ይባረራሉ። ከእርሳቸው ጋር የተመሳሳይ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑ ሠራተኞችም ብዙሐኑ በግለሰብ ጥላቻ ሕግን ለማስከበር በመጣራቸው ብቻ ሳይሆን እንደሚቀርም ከራሳቸው ሁኔታ መነሻ ይናገራሉ።
ፊት ለፊት ትግል ማድረጋቸው ለረጅም ዓመታት ከነበሩበት የሥራ መደብ አለ አግበብ ዝቅ እንዲሉ ተደርገው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ቅርንጫፎች እንዲዘዋወሩ ብሎም እንዲታገዱ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ በተቋሙ ጠንካራ ሠራተኛ ስለመሆናቸውና ከሥነ ምግባር ችግር የፀዱ ስለመሆናቸው በተቋሙ የበላይ ኃላፊ ምስጉን ሠራተኛ ስለመሆናቸው የተሠጡ የምስክር ወረቀቶች እንዳሉም ይናገራሉ። ይህም ደግሞ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ኃላፊዎችን በመታገላቸው ከሥራ እስከመሰናበት ለደረሰ ችግር ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በአዳማ በተደረገ ውይይት ያኮረፉ የበላይ ኃላፊዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው ከተመለሱ በኋላ ትንኮሳዎችን ያደርሱባቸው ጀመር። አቶ ደረጀ ‹‹በመድረኩ ተቃውሞውን አስተባብረሐል›› በሚል ቂም በቀልና ጥላቻ ግምት ውስጥ የማይገቡ ሥራን ማዕከል ያላደረጉ ተራ ውንጀላዎች ተነስቶባቸው እንደነበር ይናገራሉ። እርሳቸውም ማሳያ የሚሆኑ የተፈፀሙ ሕገወጥ ድርጊቶችንና የጠፉ ሠነዶችን እያነሱ ማጋለጣቸውንና የሠራተኞችን ድጋፍ ማግኘታቸውን መግለፃቸውና መሞገታቸው እያደረሰባቸው የነበረውን ጫናና ትንኮሳ በመግለጽ፤ ለፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ለተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት ከለላ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀርባሉ።
ጥያቄያቸውን የተቀበለው ዋናው መሥሪያ ቤትም ጠንካራ ሠራተኛ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ጥቃት እንደማይደርስባቸው ያረጋግጥላቸዋል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ የመባረራቸው ዜና በተባራሪ ወሬ ይደርሳቸዋል። የወሬውን እውነታነት ለማረጋገጥ የስንብት ደብዳቤያቸውን ሲጠይቁ በአንድ በኩል ባለሥልጣኑ ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ እንደሚገኝ ይገለጽላቸዋል። ነገር ግን ስማቸው ከወርሐዊ ደመወዝ መክፈያ ሰነድ ወጥቶ ደመወዛቸው ተቋረጠ። የስንብት ደብዳቤውም በዚህ መልኩ ሳይሰጣቸው ስድስት ዓመታት ይነጉዳሉ።
ከሕዳር ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ መባረራቸው ቢነገራቸውም የስንብት ደብዳቤ ግን በእጃቸው ሳይደርስ ይቆይና በ2010 ዓ.ም መገባደጃ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አቤቱታውን እንዳሰሙ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የተባረሩበት ደብዳቤ ሲጠየቁ ሊያቀርቡ አልቻሉም። ይህንን መነሻ በማድረግ አጣሪ ወርዶ ጉዳዩን ለመመርመር ቢሞከርም ማህደራቸውን ግን በተቋሙ ማግኘት እንዳልተቻለ ይገልፃሉ። በወቅቱ እርሳውን ጨምሮ ሌሎች ከ30 ያላነሱ ሠራኞች እንደተባረሩና ይህም የተፈፀመው አለአግባብ ተጠቃሚ ሆኖ የበላይ ኃላፊዎቹን የጥቅም ተጋሪ ያላደረገ አካል የመባረር ዕጣ ፈንታ እንደሚደርስበት ነው የሚናገሩት።
በዚህ መልኩ የበላይ የሥራ ኃላፊዎች ሕገወጥ ተግባርን ተባባሪ ያልሆኑ ሠራተኞችን ለማባረር የሚጠቀሙበት ደንብ አዘጋጅተው እንደነበርም ያስረዳሉ። ደንብ ቁጥር 155/2000 ማንኛውም ኃላፊ የጠረጠረውን ሠራተኛ ከሥራ የማሰናበት ሥልጣን ሰጥቷል። በዚህም የተባረረ ሠራተኛ በአገሪቱ በየትኛውም የፍትሕ አካል ቀርቦ ተቋሙን መሞገትም ሆነ ዳግም ተቀጥሮ መሥራት እንደማይችል በደንቡ አንቀጽ 37 ላይ አስፍሯል።
ማንኛውም አገር ላይ ጉዳት የሚያደርስ ድርጊት የፈፀመ አካል ተጠያቂ ሊደረግ እንደሚገባው ባያጠራጥርም በሕግ የተወሰነበትን የእርምት ጊዜ አጠናቅቆ ሲወጣ ግን እንደማንኛውም ዜጋ ዳግም እንዲኖሩ ይፈቀድላቸዋል። ነገር ግን ደንቡ ከዚህ በተቃራኒው ዜጎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን መብት የሚፃረር ነው ይላሉ። በዚህ ሳቢያም በርካቶች በሥነ ምግባር ችግር ውስጥ በተዘፈቁ አመራሮች ከሥራ የተሰናበቱ ሲሆን፣ ሕሊናቸውን ሽጠው ማደር የከበዳቸው ሥራ እንዲቀይሩ ሌሎች ደግሞ ሳይወዱ በግድ ወደ ሌብነት እንዲገቡ ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነም ይጠቁማሉ።
ደንብና መመሪያው ዜጎች በአገራቸው ሠርተው የመለወጥ ተስፋቸውን የከለከለ በመሆኑ ተምረው እንዳልተማሩና አገራቸውን እንዳያገለግሉ ሆነው ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ከብዷቸው ሕይወታቸውን እንደሚገፉ ይናገራሉ። መንግሥትም ይህንን ተመልክቶ ጉዳዩን እንዲመረምር ይጠይቃሉ።
በዚሁ ተቋም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሥራ እንደተሰናበቱ ቅሬታቸውን ለተቋማችን ያቀረቡት ሌላኛው የቀድሞ የተቋሙ ሠራተኛ አቶ ጌታሁን ቱጂ ናቸው። እርሳቸውም በተመሳሳይ በአገሪቱ የተለያዩ ቅርንጫፎች በተቋሙ ሲሠሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ። በሥራቸው የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸውንና በውጤታማነታቸው ተመስክሮላቸው ማረጋገጫ የተሰጣቸው ሠራተኛ እንደነበሩም ነው የሚገልፁት። በተለይም ከሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ ስኬታማ መሆናቸው በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እየተዟዟሩ የአመራር ተሞክሯቸውን እንዲያሰፉ ይሠሩ እንደነበር ጠቁመዋል።
በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት ባላሰቡት ሁኔታና የሥልጣን ወሰናቸው በማይፈቅድላቸው የባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት በዘርፍ ኃላፊ ከሥራ እንደተነሱ ይናገራሉ። በዚህም የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ.ም በደብዳቤ መዝገብ ቁጥር ኢጂ 179/104 ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዝቅ ተደርገው የመመደባቸውን ዜና እንደደረሳቸው አቶ ጌታሁን ያስታውሳሉ። ምላሽ ለማግኘትና መፍትሔ ለማምጣት ቢጥሩም ድካማቸው ከንቱ እንደቀረና በደንብ 155/200 መሠረት እንደተቀጡና ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው ይገልፃሉ። በቆይታም ግንቦት 9 ቀን የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተርና ምክትሎች በሙስና ተጠርጥረው ሲታሠሩ እርሳቸውም ለእሥር ይዳረጋሉ።
በማዕከላዊ እሥር ቤት ለሦስት ወራት እንደታሰሩና በኋላም ጉዳያቸው በሕግ ሲታይ ቆይቶ አቶ ጌታሁን ነፃ መሆናቸው ይረጋገጣል። በዚህም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ የወንጀል ችሎት የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ከክሱ ሙሉ ለሙሉ በነፃ እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ነፃ መሆናቸው በሕግ ቢረጋገጥላቸውም ወደ ሥራ ገበታቸው ሊመለሱ አለመቻላቸውን ብሎም በየትኛውም ቦታ ባላቸው የሞያ ፈቃድ ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸውን በሐዘን ይናገራሉ። ይህም በአንድ በኩል ሕገወጦች እንዲፈረጥሙና ለአገራቸው የሚሠሩ ዜጎች ደግሞ ተጎጂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ሲሉ ሁኔታውን ይተቻሉ። በአሁኑ ወቅትም የደረሰባቸው ተያያዥ የሆነ ችግር ከፍተኛ እንደሆነ በማንሳት የሚመለከተው አካል ጉዳዩን እንዲመረምርና የተዛባባቸውን ፍትሕ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
ሠነዶች
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ በተገኙ ሠነዶች ላይ መመልከት እንደቻልነው በተለያዩ ወቅቶች በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ውሳኔ የተሰጠባቸው ደብዳቤዎች ይገኛሉ። በተጨማሪም ሠራተኞቹ ምስጉን መሆናቸውን የሚያሳዩ ብሎም ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተዘዋወሩባቸውና ከታገዱ በኋላም በየደረጃው በሚገኙ የፌደራሉ ፍርድ ቤቶች የነበሩ መዝገብ ግልባጮችን ተመልክተናል። በተያያዘ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር በመጽሐፋቸው ይህንኑ ቅሬታ የቀረበበትን ደንብ አንቀጽ 37 ተችተው ማውጣታቸውን ተገንዝበናል።
አንቀጽ 25 እና 37
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25 የእኩልነት መብት ተደንግጓል። በዚህም ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፣ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል ይላል። በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 ፍትሕ የማግኘት መብት ተደንግጓል። በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 በግልጽ እንደተቀመጠው፤ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይንም ፍርድ የማግኘት መብት አለው። ውሳኔውን ወይንም ፍርዱንም ማንኛውም ማኅበር የአባላቱን የጋራ ወይንም የግል ጥቅም በመወከል፣ ማንኛውም ቡድን ወይንም ተመሳሳይ ጥቅም ያላቸውን ሰዎች የሚወክል ግለሰብ ወይም የቡድን አባል የመጠየቅና የማግኘት መብት እንዳለው አስፍሯል።
ፌዴሬሽን ምክር ቤት
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ፊርማ በቀን 23/11/2011 ዓ.ም በቁጥር ፌደም/ አግ/5/393 ወጪ ተደርጎ የተላከው ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ጉዳይ ጋር በተመሳሳይ ከሥራ በተሰናበቱ ግለሰብ ላይ የተሰጠ ሌላ ውሳኔ የሰፈረበት ደብዳቤ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል ይገኝበታል። ደብዳቤው ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በቀድሞ አጠራሩ ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር እንዲሁም ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ደብዳቤው የምክር ቤቱን ውሳኔ እንዲያውቁት የተደረገበት እንደሆነም ያትታል። በዚህም ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ አንድ እና አንቀጽ 83 ንዑስ አንቀጽ አንድ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን ተመልክቶ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ውሳኔ እንደሚሰጥ አብራርቷል።
ሰኔ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በአምስተኛ የፓርላማ ዘመን አራተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት ምክር ቤቱ ባቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ ከፌደራል ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ተመልክቶ የሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ መላኩን በደብዳቤው ያብራራል። በሰነዱ በተያያዘ የመዝገብ ቁጥሩ 72/11 ደብዳቤ ላይ አመልካች የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት እንዲሁም ተጠሪዎች ደግሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በባለሥልጣኑ የሞያሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደሆኑ ያሳያል። በዚህ ላይም ምክር ቤቱ አመልካች ያቀረበውን የሕገ መንግሥት የትርጉም ጥያቄ መርምሮ ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔ መስጠቱን አስፍሯል።
ምክር ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ በሰጠው ውሳኔ ላይ እንደተመላከተው፤ ጉዳዩ ለሕገ መንግሥት ትርጉም ምርመራ ሊቀርብ የቻለው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት በ5/7/2009 ዓ.ም ለጉባዔው በላከው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መነሻነት መሆኑን አብራርቷል። ጉዳዩ በአቶ ቁምላቸው አበረ (ስማቸው የተለወጠ) በይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤቱ በአመልካችና በተጠሪዎች መካከል የነበረውን ክርክር ከተመለከተ በኋላ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚስፈልገው ነው በማለት ለጉባዔው መላኩንም አስታውሷል።
የጉዳዩ ይዘትም በፍርድ ቤቱ ይግባኝ ባይ የሆኑት ግለሰብና ተጠሪዎች በጋራ በመሆን ያስተላለፉት የዲሲፕሊን የጥፋተኝነትና የሥራ ስንብት ቅጣት ውሳኔ ምንም ዓይነት ክስ ያልቀረበበትና በጉዳዩ ያልተከራከሩበት መሆኑን በመግለጽ፤ በተጠሪዎች የተላለፈው ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (4) ጋር ይጋጫል በማለት ክርክር አቅርበዋል። በአዋጅ ቁጥር 515/99፣ በደንብ ቁጥር 77/94 አንቀጽ ስምንት፣ አንቀጽ 13፣ አንቀጽ 17 (1) እና (5) በተዘረዘሩት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት አመልካች ለቅጣት ውሳኔ ያበቃውን ክስ የመመልከት፣ የመከራከር፣ በጉዳዩ ላይ ማስረጃዎች ቀርበውም ከሆነ ማስረጃዎችን የማወቅ፣ የመመርመር እንዲሁም መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅና በጉዳዩ የሕግ ባለሞያዎች የማማከር መብት ሕጉ ያጎናጽፋቸዋል።
ውሣኔው ስለ ደንቡ
ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች ካጎናፀፈው መብቶች በተቃራኒው ተጠሪዎች በጋራ በመሆን በደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 መሠረት መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም በቁጥር EA-164/2/08 በተፃፈ ደብዳቤ በአመልካች ላይ ያስተላለፉት የጥፋተኝነትና የሥራ ስንብት ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ አራት ድንጋጌ ፅንሰ ሐሳብ ጋር የሚጣረስ ስለሆነ ጉዳዩ ለሕገ መንግሥት ትርጉም ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንዲላክላቸው መከራከራቸውን ሰነዱ ያወሳል።
ተጠሪዎች በሰጡት ምላሽ አመልካች አቶ ቁምላቸው ከሥራ እንዲሰናበቱ የተደረጉት በደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 መሠረት ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በተሰጠ ልዩ ሥልጣን መሆኑን እንዲሁም ሠራተኛውም በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ የመመለስ መብት የማይኖረው መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ሊዘጋ እንደሚገባ መከራከራቸውን አስፍሯል።
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን የይግባኝ ክርክር ካደመጠ በኋላ ለአቶ ቁምላቸው የሥራ ስንብት ውሳኔ መሠረት የሆነው ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ አንድ ጋር ተገናዝቦ ትርጉም እንዲሰጥበት ለምክር ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ያመላክታል።
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በሙስና የጠረጠረውንና ዕምነት ያጣበትን ማንኛውንም ሠራተኛ መደበኛውን የዲሲፕሊን እርምጃ አፈፃፀም ሥርዓት ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት እንደሚችል ይደነግጋል። በዚህ ሁኔታ ከሥራ የተሰናበተው ሠራተኛ በተላለፈበት ውሳኔ ቅር በመሰኘት በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ የመመለስ መብት የለውም።
ይህ ድንጋጌም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 (1) እና አገሪቱ ከተቀበለቻቸው የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 14 (3) (ለ) እና (ረ) አንፃር ሲፈተሽ ማንኛውም የተከሰሰ ሰው የቀረበበትን ክስ የመመልከት፣ የመከራከር፣ የመከላከል፣ በጉዳዩ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች የማወቅና ብሎም የመመርመር መብት አለው ከሚለው ድንጋጌ ጋር የማይጣጣም ስለሆነ ጉዳዩ በሕገ መንግሥት ትርጉም የሚሻ መሆኑን በማመን ለጉባዔው ልኳል። ጉባዔውም ጥያቄውን መርምሮታል።
ጉባኤው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 (1) መሠረት የፍርድ ወይንም የክርክር ሂደቱን ሳይከተል የሚሰጥ ውሳኔ ወይንም ፍርድ ወይንም ይህንኑ የክርክር ሂደት እንዲቀይር የሚፈቅድ ሕግ፣ መመሪያ ወይንም ደንብ ከዚሁ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ ይሆናል። በተለይም አንድ ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚችል ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይንም የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል እንዳያቀርብ የሚከለክል ወይም አቅርቦ ውሳኔ ማግኘት እንዳይችል ክልከላ የሚያደርግ ማንኛውም ሕግ፣ መመሪያ ወይንም ደንብ ከዚሁ ግልጽ ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ እንደሆነም በውሳኔው ላይ ምክር ቤቱ አስፍሯል።
በሌላ በኩል አገሪቱ የተቀበለቻቸው የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ ሦስት (ለ) እና (ረ) መሠረት ማንኛውም የተከሰሰ ሰው የቀረበበትን ክስ የመመልከት፣ የመከራከር፣ የመከላከል፣ በጉዳዩ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች የማወቅና ብሎም የመመርመር መብት እንዳለው ተደንግጓል። በተጨማሪም ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞችን የዲሲፕሊን የጥፋተኝነትና የሥራ ስንብት ቅጣት ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ የሕገ መንግሥቱ መርህ የተከተለና የዜጎችን የመከራከር መብት የጠበቀ እንደሆነ ከአዋጅ ቁጥር 515/99፣ ከደንብ ቁጥር 77/94 አንቀጽ ስምንት፣ 13፣ 17 (1) እና (አምስት) ድንጋጌዎች ላይ መረዳት እንደሚቻል ሰነዱ ያብራራል።
በመሆኑም በደንብ 155/2000 ድንጋጌ መሠረት በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሚሠራን ሠራተኛ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በሙስና የጠረጠረውን ዕምነት ያጣበት እንደሆነ መደበኛውን የዲሲፕሊን እርምጃ አፈፃፀም ሥርዓት ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት እንደሚችል መደንገጉና በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ከሥራ የተሰናበተው ሠራተኛም በተላለፈበት ውሳኔ ቅር በመሰኘት በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ የመመለስ መብት እንደሌለው መደንገጉን ይጠቅሳል።
በመሆኑም ደንቡ አገሪቱ የተቀበለቻቸውን የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት፣ የመንግሥት ሠራተኞችን የዲሲፕሊን የጥፋተኝነትና የሥራ ስንብት ቅጣት ውሳኔ አሰጣጥ አስመልክቶ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ብሎም ሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጠው ይገባል ሲል መወሰኑን ሠነዱ አብራርቷል።
ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና የቋሚ ኮሚቴውን የውሳኔ ሐሳብ በማጣመር እንደመረመረ የሚያሳየው ሰነዱ፤ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኛ አቶ ቁምላቸው ክስ ሳይቀርብባቸው፣ እራሳቸውን የመከላከል ዕድል ሳይሰጣቸውና ማስረጃ ሳያቀርቡ በዋና ዳይሬክተሩ ጥርጣሬ ብቻ ከሥራ እንዲሰናበቱ የሚፈቅደውና በየትኛውም ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ወደ ሥራ የመመለስ መብት እንደሌላቸው የሚደነግገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 25፣ 37 (1) እንዲሁም ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ይቃረናል በማለት ያረጋግጣል። በመሆኑም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እና ቋሚ ኮሚቴው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው የቀረበውን ጥያቄ ተቀባይነት እንዳለው ማመኑን ያስቀምጣል። በዚህም ደንቡ ተፈፃሚነት የለውም በማለት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ሠነዱ ያሳያል። ይህንንም መነሻ አድርጎ ተቋሙ የደንቡን አንቀጽ እንዲያሻሽል ወስኗል።
ሚኒስቴሩ
እኛም ደንቡን በተመለከተ ከፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመቀጠል የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ አንድና አንቀጽ 56 መሠረት ያሳረፋቸው ውሳኔዎች መከበር፣ የመፈፀም ግዴታ መኖሩ ተደንግጓልና በደንቡ የተባረሩ ሠራተኞችና ለተቋማችን ቅሬታ ያቀረቡትን አቤቱታ በመያዝ የሚመለከተውን አካል ለማነጋገር ሞክረናል።
በጉዳዩ ላይ የሚመለከተው የገቢዎች ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጥ በደብዳቤ ተጠይቋል። ጉዳዩም የሚመለከተው የተቋሙን የሥነ ምግባር ዳይሬክቶሬት እንደሆነ ከሰው ሀብት ዳይሬክቶሬት ባገኘነው ጥቆማ ደብዳቤውን አስገብተናል። ይሁን እንጂ ለወር ያህል ለገባው ደብዳቤ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊገኝ አልቻለም። በኋላም ደብዳቤው በመዝገብ ቤት በኩል ገቢ እንዲሆን የተነገረን ሲሆን፤ እንደተባለው ገቢ በማድረግ ተመልሰን ወደ ቢሮው ብንሄድም መዝገብ ቤቱ እስካልሰጠው ድረስ እኛ /ዝግጅት ክፍሉ/ መውሰድ እንደማንችል ነው የተገለፀልን። ይህንንም ተቀብለን ዳግም ደብዳቤውን ለመዝገብ ቤት ብንመልስም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ ለንባብ ለማብቃት የተገደድንበት ዋናው ምክንያት ከተቋሙ የጠየቅነው ምላሽ ከሚጠበቀው በላይ ጊዜ መውሰዱን ተከትሎ አቤቱታውን ለንባብ ማብቃታችንን እያስታወቅን በቀጣይ የገቢዎች ሚኒስቴር የሚሰጠን ምላሽ ካለ ለንባብ የምናቀርብ መሆኑን አስቀድመን ቃል እንገባለን።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
ፍዮሪ ተወልደ