ምዕራፍ አንድ፤
ፋሽስት ኢጣሊያ በጀግኖች አርበኞቻችን ድል በተመታ ማግሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእንግሊዝ የቃል ኪዳን ጦር ታጅበው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከስደት ወደ ሀገር ተመልሰው መንበረ ሥልጣናቸውን በዘረጉ ዕለት ኦፊሴላዊ ንግግራቸውን የጀመሩት በሚከተለው ሃሳብ መንደርደሪያነት ነበር፣ “የሰማይ መላእክት፣ የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ በዚህ በዛሬ ቀን ቸር እግዚአብሔር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና በቂ አይደለም፣ ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን የአዲስቱ ኢትዮጵያ ያዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው፤ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል፣”
ንጉሠ ነገሥቱ፤ “አይዟችሁ! የነገይቱ ኢትዮጵያ አዲስ ነች፤ ዘመኑም አዲስ ዘመን ነው፣” በማለት ለሕዝባቸው ታላቅ ተስፋ ሰጥተው በማረጋጋት የዙፋናቸውን መሠረት አጥብቀው ተከሉ፣ ዜጎችም ከዚያ በኋላ ለ33 ዓመታት ያህል፤
“አባባ ጃነሆይ የእኛ እናት አባት፤
አሳድገውናል በማር በወተት፣
ይኑሩልን ለክብራችን፣
ኃይለ ሥላሴ ድል አድራጊው ንጉሣችን፣
እያሉ በመዘመር በንጉሣዊው ፍፁማዊ ሥልጣን ሥር ተገዝተው ኖሮ፣ ውሎ ሲያድር ግን እኛ የያኔው ታዳጊዎች፤ “ዳቦ ለተራበ!” የሚል መፈክር አንግበው ዙፋኑን ከሚፋለሙ ታላላቆቻችን ኋላ ኋላ እየተከተልን 1966 ዓ.ምን አገባደድን እስከ ታሪካዊው የ1967 ዓ.ም ዋዜማ ድረስ እየጮኽንና መፈክር እያዳመቅን አብረን ተጓዝን፣ በርሃብ የረገፉትና እየተረፈረፉ የነበሩት ወገኖቻችን የጣር ጩኸትና የተፋፋመው የለውጥ ወጀብ በዳቦ ጥያቄ እየተነቃነቀ የንጉሡን ዙፋን ከግራ ከቀኝ አላጋው፣
ንጉሡ የሰሯቸውን መልካም ተግባራት በሙሉ መደምሰሱ አግባብ ባይሆንም “የጠቅላይ ሚኒስትራቸው የአክሊሉ ኃብተ ወልድን ፋታ! ፋታ! ተማጽኖ” ከቁብ ያልቆጠረው ሕዝብ የዳቦ ቅርጫት እየተባለ በተዘመረላት ሀገር የዕለት ዳቦ ብርቅ ሆኖና ርሃብ ሰልጥኖ የሥርዓተ መንግሥታቸውን መንበረ ሥልጣን ገዝግዞ ጣለው፣
የንጉሡም ሆነ የዙፋናቸው የታሪክ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘግቶ ከንግግራቸው ውስጥ ዛሬም ድረስ አትርፈን በክብር የጠበቅነው “አዲስ ዘመን” የሚለውን የዚህን ጋዜጣ ስያሜ ብቻ ነው፣ የያኔዎቹ “ዳቦ ለተራበ! ባይ አዳናቂ ታዳጊዎችም” እንኳንስ ዳቦ ልንጠግብ ቀርቶ የሚከተለውን የጸጋዬ ገ/መድኅን ግጥም በቃል እየወረድን ሥርዓቱንም ሆነ የታዳጊነታችንን ዕድሜ እንደዋዛ ተሰናበትነው፣
ስንት ቀን ትሆን የርሃብ አዋይ?
እስቲ እናንተ ተናገሩ ተርባችሁ የምታውቁ፤
ከቸነፈር አምልጣችሁ፣ ተርፋችሁ እንደሆን ሳታልቁ፤
ትንፋሽ ቀርቷችሁ እንደሆን ያስችላችሁ እንደሁ ጥቂት፣
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓልት ስንት ሌሊት፣
መልስ በሌለው ዝማሬ ጮኸን ጩኸታችንን ለቀማው ደርግ መንበረ ሥልጣኑን አሳልፈን ሰጠን፣
ምዕራፍ ሁለት፤
“ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!” የሚለውን መፈክር አንግቦ የንጉሡን መንበር የተረከበው ወታደራዊው መንግሥትም ወር ተራው ደርሶ “ዳቦ ለተራበ!” ለሚለው የሕዝብ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ፣ ማዕዳችሁንም በዳቦ አትረፈርፋለሁ ብሎ በመሃላ ጭምር እያማለለን “መንጌ! መንጌ!” አሰኝቶ በማዘመር ገና በጠዋቱ በለውጥ ፈላጊው ትውልድ መንፈስ ውስጥ ተሰነቀረ፣ ወታደራዊው ጁንታም ውሎ ሳያድር በተንበሸበሸ አዋጅ ተስፈኛውን ሕዝብ አስፈነደቀ፣ ጥቂቶችንም የደም እንባ አስነባ፣
“ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ፣
ለሀገር ብልጽግና ለወገን መከታ፣
ሀሁ ኢትዮጵያ ትቅደም፣
ተብላ እንዳልነበር የዳቦ ቅርጫት፣
እንዴት እናታችን ትባል እራባት፣
እያልን የቁጭት መዝሙር በዘመርን በወጣትነት ትኩስ ዕድሜያችን የዳቧችንን ጉዳይ ወደ ጎን ገፍተን “በቀኝና በግራ የርዕዮት ዓለም እንክርዳድ” እርስ በእርስ ተሳከርን፣ ተጠፋፋን፣ ደርግንም አፋፋን፣ የወጣትነታችንን ዕድሜም በከንቱ ዓላማ አጨነገፍን፣
ደርግም እንኳንስ በዳቦ ጥጋብ ሊያንበሸብሸን ቀርቶ የዕለት እንጀራችንን በቀበሌ ሬሽን እንድንገዛ ፈርዶብን ለዕለት ዳቦ ኮታ በሕዝብ ሱቅ ደጃፍ መሰለፍ የዘወትር ተግባራችን ሆነ፣ ይብስ ብሎም የራበው ሆዳችን እያንቋረረ በጦር ወሬ እየጠገብን አቅራራን፤ ፈከርን፣ ምድሪቱም ከምስራቅ እስከ ሰሜን፣ ከደቡብ እስከ ምእራብ በወጣቶች የደም አበላ ጨቀየች፣
ንጉሡን ከመንበረ ሥልጣን የፈነገለው የዳቦ ጥያቄ እጣ “በሠፈሩት ቁና” እንዲሉ፤ በደርጉም ላይ ደርሶ ከበረሃ ሲንደረደር በመጣው ኃይል የወታደሩ መንግሥት ተንበርክኮ የምኒልክን ቤተ መንግሥት ለማስረከብ ተገደደ፣ የወጣትነት ዕድሜያችንም “የዳቦ ያለህ ጩኸቱ!” ምላሽ ሳያገኝ እብስ ብሎ ወደ ጉልምስና ተሸጋገርን፣
ምዕራፍ ሦስት፤
ደርግን አዋርዶና ተዘባብቶበት የሀገሪቱን የስልጣን በትር በእጁ ያስገባው በረኸኛው ኢህአዴግም ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል በ“ሞኣ አንበሳና በኢትዮጵያ ትቅደም” መቃብር ላይ ተደላድሎ በመቆም ቀዳሚዎቹን መንግሥታት ለከት በሌላቸውና ለሰብዕና ክብር ደንታ በማይሰጡ ፍልፍሎቹ እየሰደበና እያላገጠባቸው ትውልዱን ጭምር የስድብ ተማሪና ግብረ ገብ ጠል አድርጎ ቀረፀው፣
“ሕዝቡ በቀን ሦስቴ ይበላል!” የሚለው “የዳቦ” ተስፋ ለብዙኃኑ ሳይሆን ለጥቂቶች በሹመት መልክ ተሰጠ፣ ኢምንቶች ሀገሪቷንም የሀገሪቷንም ሀብት ተቀራመቱ፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሁለት አሀዝ አድጓል የሚለው ተረት ተረት “በዳቦ ምትክ” የዕለት ቀለባችን ሆነ፣ “ዳቦ አምራች” ደሃው ገበሬ ከይዞታው ላይ እየተፈናቀለ የአዲስ አበባና የዋና ዋና ከተሞች መሃልና ዳር በሕንጻ ደን ተቸመቸሙ፣
“ያ ሕንጻ የማነው?” ሲባል “እንዳታስበላን የትልቁ ምንትስ ነው፣ ያኛው ደግሞ የእነ እከሊት ነው፣ ስለ እነዚያኞቹ አትጠይቀኝ ልኑርበት” እየተባለ ዝርዝሩ በወረቀት ቢያሰለች በጣት ጥቆማ ሕንጻዎቹ እየተመላከቱ ማውራቱ ባህላችን ሆነ፣ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እያልን በነገ የብልፅግና ተስፋ እኛ ዜጎች የዳቦ ርሃብተኛ ጉሮሯችንን በተረት ሸነገልነው፣ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድም በኢኮኖሚ እድገት እኛን የሚቀድም እንደሌለ በንግግር በማይሰንፉ መሪዎቻችን አንደበት አሳወጅን፤ ዓለምም በለበጣ ሳቅ እያጀበ አጨበጨበልን፣
ከዕለት እንጀራችን መሶብ ላይ ቆርሰን የምናሳድረው “የአዋይ ጉርሻ” እንኳን አጥተን ቅኔ “በሚያፈልቀው” አንደበታችን እንደለመድነው በራሳችንም፣ በእግዜሩም ሆነ በገዢዎቻችን ላይ ስለ ርሃብ መቀኘት ጀመርን፣ ርሃብ ስንት ቀን እንደሚፈጅ እንኳ ስሌቱ ጠፍቶን ግራ ተጋባን፣ “ርሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?” ለሚለው የጸጋዬ ገ/መድኅን የግጥም ጥያቄ መልሱ ስለጠፋብን “እንጃ!” ብለን መለስንለት፣ ለተራበው ሆድ ዳቦ ማቅረብ ያቃተውና የበሰበሰው ጥጋበኛው ኢህአዴግ በተራቡ የሀገሪቱ ወጣቶች ተመንግሎ ተንኮታኮተ፣ የእኛም የጉልምስና ዕድሜ ለዕለት ዳቦ እንደተቀኘ የጉልምስና ደረጃን ተሻግሮ ወደ ሁለት ፀጉር የሽምግልና ዕድሜ ዳርቻ ተቃረበ፣
ምዕራፍ አራት፤
ከሙት መንፈስ (ኤኬራ) ትግሉን ያላጠናቀቀው የአራተኛው ምዕራፍ የዘመነ ዓብይ ሥርዓትም ተስፋው በዝቶ፤ ዳቦው ርቆን “መንግሥታችን ሆይ! የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” እያልን በመማጸን ላይ ነን፣
ዛሬም ጌቶቻችን ነጋ ጠባ እንደሚደሰኩሩልን ከሆነ የዓለም መንግሥታትና ረጂዎች ድጋፍና እርጥባን ከመቼውም ዘመን ይልቅ በአሁኑ ወቅት ማካፋት ሳይሆን እንደ ዶፍ እየዘነበልን እንዳለ በአሜን እያጀብን ልብ ተቀልብ ሆነን እየሰማን ነው፣ ተስፈኛው ጠቅላይ ሚኒስትራችንም መሃላቸውን በተግባር ሊያረጋግጡ እረፍትና እንቅልፍ ሳያታልላቸው የሻገተብንን የዕለት ዳቦ መጋገሪያ ምጣድ እያሟሹ በሙልሙሎች ማዕዳችንን ሊሞሉልን ሲታትሩ እናስተውላለን፣ በጥቂት ወራት በሥልጣን የተራመዱባቸው የእግራቸው ኮቴም በርግጥም እርጥብና ለምለም እንደሆነ ባንመሰክር ፈጣሪያቸውና ፈጣሪያችን ይታዘበን ይመስለናል፣ ያደነቋቸውና ያከበሯቸው የዓለም ሕዝቦችም “ምስጋና ቢስ” ብለው ሊንቁን ይችላል፣
ችግሩ ግን የተቦካው የተስፋ ሊጥ ዳቦ ሆኖ ተጋግሮ ለመበላት ያለመድረሱ ነው፣ ኑሮ ሕዝቡን አስክሮ እያንገዳገደ አዝለፍልፎታል፣ እንደ ለመድነው ርሃባችንን ችለን ጥቅልል ብለን ተኝተን እንዳናድር እንኳ በመላ ሀገሪቱ የምንሰማቸው የሰላም እጦቶች እያባነኑን ከርሀቡ ጋር በማበር እንቅልፋችንን ነጥቀውናል፣
መንግሥታችን ሆይ! ብልፅግና ፓርቲ በመቃብሩ ላይ ያቆጠቆጠውን ሟቹን ኢህአዴግን ጨምሮ ሦስቱም ቀዳሚ የሀገራችን የመንግሥት ሥርዓቶች ከመሠረታቸው የተናዱት በሕዝቡ የዳቦ አቅርቡልን ጩኸት እንደሆነ የታዳጊነታችንን፣ የወጣትነታችንንና የጉልምስናነታችንን ሦስት የዕድሜ እርከኖች ምስክርነት አቁመን እያጣቀስን ለማሳየት ሞክረናል፣
“ዳቦ ለተራበ!” እያለ ለአራተኛ ጊዜ (ቁጥር አሳሳትኩ መሰለኝ) ሕዝቡ በነቂስ ከመንቀሳቀሱ አስቀድሞ ለሆዳችን ብቻ ሳይሆን የሕሊናችን ሰላም እንዲረጋገጥና በሕግ የበላይነት በተከበረ ማዕድ እንድንጠግብ አቤቱ መንግሥትዎ በሁለት ጆሮው ያድምጠን፣
ማታ ማታ በሰላም ውለን ወደየጎጇችን ስንሰበሰብ ልክ እርስዎ ያደርጉታል ብለን እንደምንገምተው እንደየእምነታችን ለፈጣሪ ጸሎታችንን የምናደርሰው፤ “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር!” እያልን ነው፣ ማለዳው ወገግ ሲልም “ቤተ እምነታችን በሰላም አድሮ ይሆን ወይ!” እያልን እስከመጠየቅ ደርሰናል፣ ጠዋት ያለ ቁርስ ባዶ የምሳ ሳህን ቋጥረን ለሥራ ስንሰማራ የምንጸልየው ደግሞ እንዲህ እያልን ነው፣
“ዓብይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሆይ፣
በቤተ መንግሥት የምትኖር፣
ርዕይህን ወደን፣ ፈቅደን ተከትለንሃል፤
በብልፅግና ፓርቲህም ተስፋ ጥለናል፣
የተናወጠውን ተስፋ አርግበልን፣
የሰከረውን ገበያ አብርድልን፤
የተማሪ ልጆቻችንን ነፍስ ታደግልን፣
እኩይ ምናምንቴዎችን አርምልን፣
የሴረኞችንም ስራ አክሽፍልን፣
ትምህርት ቤቶችንና ቤተ እምነቶችን አስጠብቅልን፤
አቤቱ የርሃብ ማስታገሻ ዳቧችንንም በገፍ አቅርብልን፣
ለሥራ ፈጠራውም አትስነፍብን፤
የዕለት እንጀራችንንም ዛሬ ስጠን፣”
ይህ ጸሎት የከተሜው፣ የገጠሬው፣ የሠራተኛው፣ የተማሪው፣ የአዛውንቶችና የህጻናት የጋራ ጸሎት ነው፣ ለመንግሥታችን መስሚያ ጆሮ ይስጠው፣ አሜን፣ ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ