የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ የያዘው በሞት የሚያስቀጣ ድንጋጌ ከተረቀቀው አዋጅ እንዲወጣ መጠየቃቸው በግሌ ልዩ ስሜትን አጭሮብኛል።
ዋናው ምክንያቴ ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ መብት ኮምሽን “ገለልተኛ ነው” የሚባል ግን በተግባር “ገለልተኛ” መሆን የተሳናው ሲሰራ ከነበረው በተለየ የአሠራር ጅማሮ ማየቴ ነው። የአሁኑ ኮምሽነር የተቋሙን ትክክለኛ ማንነት ሊወክል በሚችል መልክ ሲንቀሳቀሱ በዚህች አገር ላይ እየተፈጠሩ ካሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መሐል ትልቅ ተስፋን እንዳይ ስለረዳኝ ነው።
በአንድ ወቅት የቀድሞ ሰብዓዊ መብት ኮምሽነር በማረሚያ ቤቶች ጉብኝት ማድረጋቸውንና ባዩት ነገር መደሰታቸውን፣ የታራሚዎቹም አያያዝ ጥሩ መሆኑን መመስከራቸውን በመገናኛ ብዙሃን ስሰማ በሰውየው ዓይን ያወጣ ውሸት እጅግ ተከፍቼ እንደነበር አልዘነጋውም። ዛሬ ይህን የሚክስ ተቋም እያየን መሆኑ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው።
ዋና ኮምሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በቲውተር ገፃቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከልናለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ተከታዩን መልዕክት አስፍረው ነበር።
“ፓርላማው ለህዝብ ውይይት ያቀረበው በሰው የመነገድና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ አስፈላጊ ቢሆንም፤ የሞት ቅጣት ማካተቱ ግን ስህተት ነው። የሞት ፍርድ ጨካኝና ኢ- ሰብዓዊ የሆነ ሊመለስ የማይችል ቅጣት በመሆኑ በአዲሱ የለውጥ ምዕራፍ ተፈፃሚነቱ ሊታቀብ እና ለወደፊቱም ሊቀር ይገባል።”
ከረቂቅ አዋጁ ጭብጥ ጥቂት ነጥቦች
በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተዘጋጀው በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን የመከላከልና የመቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ ታህሳስ 15 ቀን 2012 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የሴቶች ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርገውበታል።
በረቂቅ አዋጁ ከሰፈሩት የቅጣት ድንጋጌዎች ውስጥ የሚከተለው ይጠቀሳል። ማንኛውም ሰው በሰው የመነገድ ወንጀልን የፈፀመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአሥር ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ የተደነገገ ሲሆን፣ በተፈፀመው ወንጀል ሒደት ውስጥ ባለፈ ሰው ላይ ብዝበዛ የተፈፀመ ወይም መፈፀሙ ተጀምሮ እንደሆነ በሒደቱ የተሳተፈ፣ እንዲሁም ብዝበዛውን የፈፀመው ሰው ከሰባት ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺህ ብር እስከ 70 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል።
በሰው የመነገድ ወንጀል ድርጊት ውስጥ የመመልመል፣ የማጓጓዝ፣ ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ፣ የማስጠለል ወይም የመቀበል ተግባር የተፈፀመ ባይሆንም፣ በሌላ ሰው ላይ ብዝበዛ የፈፀመ ማንኛውም ሰው ከሰባት ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺህ ብር እስከ 70 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣም ያመለክታል።
በከባድ ሁኔታ ድንጋጌው የተመለከተው ማለትም የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በሕፃናት፣ በአዕምሮ ሕመምተኛ፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፣ አደንዛዥ እፅ፣ መድኃኒት፣ የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንዲሁም፣ በመንግሥት ሠራተኛ፣ ባለሥልጣን ከሆነና ወንጀሉን የፈፀመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ከሆነ፣ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ፈቃድ ባለው አካል ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ ከሆነ፣ ቅጣቱ ከአሥር ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ30 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚሆን ረቂቁ ይገልፃል።
በሌላ በኩል የተመለከተው የወንጀል ድርጊት በከፋ መንገድ ማለትም የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን፣ ቡድኑን በመምራት፣ በማስተባበር የተፈፀመ እንደሆነ፣ በተጎጂው ላይ ከባድ ከአካል ጉዳት፣ የማይድን በሽታ ያስከተለ እንደሆነ ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ50 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር እንደሚሆን በረቂቁ ተደንግጓል። የተፈፀመው ወንጀል በተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ እንደነገሩ ሁኔታ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት፣ በሞትና ከ100 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል።
በሌሎች የዝሙት አዳሪነት መጠቀምን በተመለከተ በተቀመጠው ተጨማሪ ድንጋጌ፣ ማንኛውም ሰው ሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ሒደት ለመጠቀም ሲል፣ ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ለማርካት በማሰብ ሰውን ለዝሙት ተግባር ያሰማራ፣ ያገናኘ፣ ያቀረበ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል።
በተመሳሳይ ሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ለመጠቀም ሲል ቤቱ ያስቀመጠ፣ የሥራ፣ የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለዚህ ተግባር ያዋለ፣ ያከራየ፣ በማናቸውም ሌላ መንገድ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት መጠቀሚያ አድርጎ የያዘ እንደሆነ፣ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአሥር ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል። ከላይ የተመለከተው ድርጊት የተፈፀመው ሕፃናት ላይ እንደሆነ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺህ ብር እስከ 70 ሺህ መቀጮ እንደሚያስቀጣ የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል።
ረቂቁ ኢትዮጵያውያንን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ ሒደት ውስጥ ወይም ይህንን ተገን በማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎችም አካቷል። በዚህም መሠረት ማንኛውም ሰው ፈቃድ ሳይኖረው፣ ፈቃዱ ታግዶ፣ ተሰርዞ እያለ እንዲልክ ፈቃድ ወዳልተሰጠው አገር ዜጋን ለሥራ የላከ እንደሆነ፣ ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ20 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ይደነ ግጋል።
ከላይ የተመለከተው ወንጀል የተፈፀመው የጉብኝት፣ የሕክምና፣ የትምህርት ወይም የመሰል ጉዳዮች ቪዛን ሽፋን በማድረግ እንደሆነ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ30 ሺህ ብር እስከ 70 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል።
በተመለከተው የወንጀል ድርጊት ምክንያት የተላከው ሰው በሰብዓዊ መብቱ፣ በሕይወቱ፣ በአካሉ፣ በሥነ ልቦናው ላይ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ150 ሺህ ብር እስከ 250 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል።ከላይ የተገለፁትና ሌሎች በረቂቁ የወንጀል ድርጊት መሆናቸው የተገለፁት ተግባራት የተፈፀሙት የሕግ ሰውነት በተሰጠው አካል ወይም ተቋም ከሆነ ለወንጀሉ የተቀመጠው ቅጣት ተወስዶ ማክበጃና መቅለያ ምክንያቶች ተሰልተው፣ በቀላል እሥራት ወይም እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ እስከ 500 ሺህ ብር፣ ከአምስት ዓመት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት ከሆነ ከ500 ሺህ እስከ አንድ ሚሊየን ብር፣ ከ20 ዓመት በላይ በሆነ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሆነ ከሁለት ሚሊየን ብር እስከ ሦስት ሚሊየን ብር መቀጮ እንደሚጣልበት ረቂቁ ያመለክታል።
ስለሞት ቅጣት ሕጋችን ምንይላል?
የ፲፱፻፺፮ ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራ ሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ድንጋጌ አንቀጽ ፻፲፯ መርህ የሚከተለውን ይመስላል።
የሞት ቅጣት የሚወሰነው ወንጀሉ ፍፃሜ ያገኘ ሆኖ እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑና ወንጀለኛውም በተለይ አደገኛ በመሆኑ ለወንጀሉ ቅጣት እንዲሆን በሕጉ በግልፅ ተደንግጐ በተገኘ ጊዜ እንዲሁም ለወንጀለኛው ወንጀሉን በፈፀመበት ጊዜ ዕድሜው ቢያንስ አስራ ስምንት ዓመት የሞላው ሲሆን ብቻ ነው።
የሞት ቅጣት በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፍርዱ ካልፀና በቀር ተፈፃሚ ሊሆን አይችልም። በይቅርታ ወይም በምህረት ያልተሻረ ወይም ያልተለወጠ መሆኑ አስቀድሞ ከመመርመሩና ከመታወቁ በፊት ተፈፃሚነት አይኖረውም።
የሞት ቅጣት በሕዝብ ፊት፣ በአደባባይ በስቅላት ወይም በሌላ በማናቸውም ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ አይፈፀምም። ቅጣቱ በሰብአዊ ሁኔታ በማረሚያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲፈፀም ይታዘዛል። የአፈፃፀሙ ዘዴም ጉዳዩን በሚመለከተው የፌደራል ወይም የክልል ማረሚያ ቤት አስተዳደር የበላይ ሕግ አስፈፃሚ አካል ይወሰናል። የሞት ቅጣት ከመፈፀሙ በፊት በተቀጪው ላይ ማናቸውንም የስቃይ፣ የበቀል እርምጃ ወይም የአካል ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግ የተከለከለ ነው።
የሞት ቅጣት ከተፈፀመ በኋላ አስከሬኑን ቤተሰቡ ከጠየቀ ይሰጠዋል። ጠያቂ ቤተሰብ ካልተገኘ ግን አስከሬኑ በተገቢው ሥነ ሥርዓት ይቀበራል።
አንቀጽ ፻፲፰ የሞት ቅጣት የተፈረደበት ሰው ቅጣቱ እስከሚፈፀም የሚቆይበት ሁኔታ
የሞት ቅጣት የተፈረደበት ሰው ቅጣቱ እስከሚጸናና እስከሚፈፀም ድረስ ጽኑ እሥራት የተፈረደበት እስረኛ ቅጣቱን በሚፈጽምበት ሁኔታ ታስሮ ይቆያል።
የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ለእስረኛው ደህንነት አስፈላጊ የሆነውን የጥንቃቄ ጥበቃ ያደርግለታል።
እስረኛው ሲፈልግና ከተቻለ በታሰረበት ክፍል ውስጥ ሥራ እንዲሰራ ይደረጋል።
አንቀጽ ፻፲፱ የሞት ቅጣት አፈፃፀም ታግዶ የሚቆይበት ሁኔታ
በፍፁም ኢ-ኃላፊነት ወይም ከፊል ኃላፊነት ላይ በሚገኝ ወይም በጽኑ በታመመ ሰው ወይም ባረገዘች ሴት ላይ በዚሁ ሁኔታ ላይ እስከሚገኙበት ጊዜ ድረስ የተወሰነባቸው የሞት ቅጣት ታግዶ ይቆያል።
አንቀጽ ፻፳ የሞት ቅጣትን መለወጥ
፩ ያረገዘች ሴት ሕይወት ያለው ልጅ የወለደች ስትሆንና ይህንኑም ልጅ መመገብና ማሳደግ ሲኖርባት የሞት ቅጣቱ በዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ይለወጥላታል።
፪ በዚህ ሕግ ውስጥ በተመለከቱት ድንጋጌዎች (አንቀጽ ፪፻፳፱ እና ፻፻፴) መሠረት የሞት ቅጣት በይቅርታ ወይም በምህረት ሊለወጥ ወይም ቀሪ ሊሆን ይችላል።
እንደማጠቃለያ
የሞት ቅጣት ይኑር ወይንስ ይሰረዝ የሚሉ ክርክሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁንም የመጨረሻ መቋጫ ያገኙ አይመስሉም።ከበድ ላሉ ጥፋቶች የሞት ቅጣት መፈፀም ለጥፋቱ ተመጣጣኝ እርምጃ ነው የሚሉ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል ለከባድ ጥፋትም ቢሆን የሞት ቅጣት መፈፀም “የወንጀል ሕግን የማስተማር ዓላማ መፃረር ነው፣ የሐሙራቢ ሕግን መተግበር ነው፣ ኢ- ሰብዓዊነት ነው…” በሚል የሚሞግቱ ወገኖች አሉ።
የሐሙራቢ ሕግ ተብሎ የሚታወቀው ከዛሬ 3ሺ800 ዓመታት በፊት በጥንቷ ባቢሎን (በአሁኗ ኢራቅ) ነግሶ የነበረው ንጉሥ ሐሙራቢ ለ46 ዓመታት የጥንቱን የሚሶፓታሚያ ግዛት ( ማለትም ከጤግሮስና ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ሜዲቲራንያን ባህር ጠረፍ) ድረስ ያስተዳድር ነበር። ይህ ንጉሥ ‘የአለማችን ጥንታዊው ሕግ’ ተብሎ የሚጠራውን ሕግ የአንድ ጎልማሳ ቁመት ባላቸው ሀውልቶች ላይ አስቀርፆ በከተማ አቁሞ ነበር። 282 ሕጎችን በተለያዩ የወንጀል፣ የውል፣ የጋብቻ፣ የውርስ ጉዳዮች ላይ ያካተተው የሐሙራቢ እድሜ ጠገብ ሕግ ከምዕተ ዓመታት በላይ በጥንታዊ የዓለማችን ሕግጋት ላይ የራሱን ተጽዕኖዎች ሲያሳርፍ ኖሯል። ሕጉ በአጭሩ እንደወንጀሉ አፈፃፀም ቅጣትን ማስቀመጥ ነው። እጅ ለቆረጠ – እጁን መቁረጥ፣ወግሮ ሕይወት ላጠፋ- ወግሮ መግደል፣ ዓይን ላጠፋ – ዓይኑን ማጥፋት… የሚፈቅድ ነው።
የሞት ሕግ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከመደበኛ ሕጋቸው ያላወጡና የሚተገብሩ አገራት አሉ። አምኒስቲ ኢንትርናሽናል እ.ኤ.አ በ2018 በዓለም አቀፍ ደረጃ 690 ሰዎች በ20 አገራት የሞት ፍርድ እንደተፈፀመባቸው ጠቁሞ ከ2017 ጋር ሲነፃፀር በ31 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን በይፋዊ ሪፖርቱ ጠቅሷል። የሞት ፍርድ ከሚሰጡ አገራት መካከል ደግሞ ቻይና፣ ኢራን፣ ሳዑዱ ኣረቢያ፣ ቬትናም፣ ኢራቅ…በዋንኛነት ይገኙበታል። ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ደግሞ እ.ኤ.አ በ2018 በቦትስዋና፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው 24 ሰዎች ቅጣቱ ተፈጽሞባቸዋል።
በሌላ በኩል ቡርኪናፋሶ የሞት ቅጣትን ከሕግዋ በመሰረዝ በምሳሌነት ስትጠቀስ፣ ጋምቢያ በጊዜያዊነት የሞት ቅጣትን ማገዷ ከአምኒስቲ ኢንተርናሽልና እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምስጋና አጉርፎላታል።
በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የተቀመጠው የሞት ቅጣት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንዲያስቀረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ዋና ኮምሽነር ጥቆማ የሰጡ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ተመሳሳይ አቋም እያራመዱ ነው። ፓርላማው የሞት ቅጣቱን ይሰርዘው ይሆን? በቅርቡ የምናየው ይሆናል።
(ማጣቀሻዎች፡- የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል 2018 ሪፖርት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋዊ ድረገጽ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ፣ የጀርመን ድምጽ፣
የሕግ ባለሙያ ኪዳኔ መካሻ…)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22/2012
ፍሬው አበበ