ሮበርት ሞሰስ ይባላል።በቅፅል ስሙም ‹‹ዘ ማስተር ቢልደር›› በሚል ይታወቃል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን ካየቻቸው እጅግ ተፅዕኗቸው ጎልቶ ከሚታይ የከተማ መሀንዲሶች (ፕላነሮች) አንዱ ለመሆኑም በርካቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል።እኤአ በ1888 የተወለደው ይህ ሰው አንድ ከተማ በርካታ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ከመደርደር ይልቅ በዛፍ የታጀቡ ምቹ ጎዳናዎች እንዲሁም ፓርኮች ሊኖሯት እንደሚገባ በማመንና በማሳመን የአሜሪካዋን ኒውዮርክ ከተማ በሐሳብ እና በራዕዩ ልክ ገልብጦ እንደሰራት ይገለጻል፡፡
ሞሰስ፣ ኒውዮርክ ከተማን የግል ሐሳቡንና ፍልስፍናውን በሚያንፀባርቅ መንገድ እንደገነባት ሁሉ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከዓለም የአየር ሙቀት ጋር ተያይዞ አገራት ለከተሞቻቸው ውበትና ለነዋሪዎች ምቾት ሲሉ በርካታ የመናፈሻ ፓርኮችን እየገነቡና ለአገልግሎት እያበቁ ይገኛሉ።
130 ዓመታት አካባቢ ዕድሜ ያላት አዲስ አበባ በአንፃሩ በስፋት እንጂ በውበት ብዙም እንዳላደገች ይነገራል።የአፍሪካ መዲና እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ጭምር የሆነችውና በርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችን የምታስተናግደው ከተማ ስሟን፣ ዝናዋንና የዕድሜ ባለጸጋነቷን በሚመጥን መልኩ ውብ መናፈሻዎች እና አረንጓዴ ስፍራዎች አላት ከማለት የላትም ማለት ይቀላል።ስሟ ብቻ አዲስ ሆኖ አንድ ምዕተ ዓመትን የዘለቀችው ይህች መዲና ተወዳዳሪ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ እንዲሁም ለጎብኚዎች አማላይ ከተማ ለማድረግም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት «ሸገርን የማስዋብ» ፕሮጀክት በተግባር ላይ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አለም ግዛው፣ አዲስ አበባ ነዋሪዎቿም ሆኑ እንግዶቿ ውስጣዊ ስሜታቸውን የሚያዳምጡባቸው እና አዕምሯዊ ዕረፍት የሚያገኙባቸው ብሎም የሚዝናኑባቸው ውብና ንፁሕ መናፈሻዎችና አረንጓዴ ስፍራዎች ሳይኖሯት ረጅም ዓመታትን ማስቆጠሯ ከሚያሳዝናቸው መካከል አንደኛዋ ናቸው።
መናፈሻ ፓርኮችና አረንጋዴ ስፍራዎች በከተሞች መኖራቸው ነዋሪዎች ንጹህ አየር እየተነፈሱ አልያም በለምለም ዛፎች መካከል በፍፁም ምቾት እየተንሸራሸሩ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ እንደሚያደርግ የሚጠቁሙት ወይዘሮ አለም፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ግላዊነት የጎላበትን የማህበራዊ ግንኙነት ፈር በማስያዝ የጋራ ማህበራዊ እሴትን እንደሚያጠናክር ይገልፃሉ፡፡
‹‹ከሕፃን እስከ አዛውንት ለሁሉም ክፍት እንደመሆናቸውም በአጠቃላይ ‹‹ጤናማ እና ደስተኛ ህዝብ ለመፍጠር ሁነኛ አስተዋፆኦ ያበረክታሉ፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ አለም፣ በኢኮኖሚ ረገድ በአግባቡ ከተሰራባቸውም የገቢ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉና በስራ ፈጠራውም ወቅታዊውን የአገሪቱን ራስ ምታት የማቃለል አቅማቸው ግዙፍ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡
በከተማ መሃል የሚገኙ መናፈሻ ፓርኮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች መስተጋብርን ከማጠናከር ባሻገር የተለያዩ ጥበባዊ የሆኑ አውደ ርዕዮችን፣ ኮንሰርቶች እና የቲዓትር ዝግጅቶችን ማካሄድ እንደሚቻል የሚጠቁሙት ወይዘሮ አለም፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጥን አዲስ አበባም እነዚህን ትሩፋቶች ለመቋደስ መንደርደር መጀመሯ ደስታ እንደፈጠረባቸውና ተግባሩም የሚደነቅ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማት ምህንድስና ኮሌጅ ዲንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ዳንኤል ሊሬቦ፣ የወይዘሮ አለምን ሃሳብ ይጋራሉ።ከሁሉም በላይ የአፍሪካ መዲና የሆነችውና በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የምታስተናግደው አዲስ አበባ ውብና ፅዱ በሆነ መልኩ ለነዋሪዎችም ሆኑ ለእንግዶች በሚመች መልኩ የማልማት ፕሮጀክት እስካሁን ሳይታሰብበት መቅረቱም እንደሚያስቆጭ ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹ግሪካውያን ለአለም ያበረከቷቸውን በርካታ የፍልስፍና እና ሌሎች እውቀቶች ያፈለቁት በአረንጓዴ ክፍት ስፍራና መናፈሻዎች ተሰባስበው በመወያየትና በመማማራቸው ነው፡፡›› የሚሉት ዶክተር ዳንኤል፣ የከተማ መናፈሻና ክፍት ስፍራዎች የመዝናኛ አማራጭ ብቻ ሳይሆኑ የሁለንተናዊ ሃሳብ መነሾ እንደሚሆኑም ያስገነዝባሉ።እነዚህ ደህንነታቸው የተጠበቀ መናፈሻ ፓርኮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች ጎብኚዎችን እየሳቡ በመሄድ ከተማነትን እንደሚያሳልጡና እንደሚያደምቁም ያስገነዝባሉ፡፡
ዶክተር ዳንኤል ፣ ከተማ መሃል የሚገኙ መናፈሻ ፓርኮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች ከሚሸፍኑት ግዙፍ መሬት አንፃር በተለይ የመሬት ጥበት ባለባቸው አገራት መተግበር የሌለበትና ‹ቅንጦት ነው› በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎችም መልስ አላቸው።
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት አለም፣ ጥግግቱ ከፍ ያለው ወደ ጎን ከማስፋት ይልቅ ወደ ላይ የሚሰፋ ከተማን በማዋቀር በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሕዝብ ማስፈር አማራጭ አድርጋለች።ይህ አማራጭ ደግሞ ከተሞች ለመናፈሻ፣ ፓርኮች እና አረንጓዴ ቦታዎች ሰፊ ቦታ ቢሰጡም እንዳይጨናነቁ አድርጓቸዋል።ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ልትሆን የምትችለው ኒውዮርክ ነች።
‹‹አለም ላይ ኒውዮርክ ከተማ በጥግግት ከሚታወቁ ከተሞች ግንባር ቀደም ሆና ትጠቀሳለች፡፡›› ያሉት ዶክተር ዳንኤል፣ በአለማችን ትልቁ ሴንትራል ፓርክና 341 ሄክታር የሚሆን ክፍት ስፍራ የሚገኘው በዚህችው ከተማ ነው፡፡›› ሲሉም ያብራራሉ።ይህ መሆኑም ከተማዋ የጎብኚዎች መናሃሪያ እንድትሆን አንዱ ምክንያት እንድትሆን አርጓታል ነው የሚሉት።መናፈሻ ፓርኮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች ከሚሸፍኑት ግዙፍ መሬት አንፃር ፋይዳቸውን መመልከት ስህተት መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፋሰስና አካባቢ አረንጓዴ አከባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር አቶ ይርዳው ገረመው፣ ከተሞችን ተወዳዳሪ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ እንዲሁም ለጎብኚዎች አማላይ ከሚያደርጓቸው መካከል ውበትና መናፈሻ ቀዳሚ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡
አቶ ይርዳው፣ ፕሮጀክቱ የአገሪቷንና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ገጽታ እና እድገት ባሻገር ለነዋሪዎቿ ምቹ አካባቢ በመፍጠር እንዲሁም ጤናማና አምራች ዜጎች ከመፍጠር ባለፈ ቱሪዝምንም ከማጐልበት አኳያ ትሩፋቱ ከፍ ያለ መሆኑን ይጠቅሳሉ።ኤጀንሲውም ይህን አስደሳች ተግባር ዳር ለማድረስ አስፈላጊ በሆነው ሁሉ በቁርጠኝነት ለመተባበር ዝግጁ ስለመሆኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም
ታምራት ተስፋዬ