በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ጫና አሳድረው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሄ እያገኙ በመምጣታቸው በዘርፉ መነቃቃት እየታየ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች ያመለክታሉ:: በ2016 የበጀት ዓመት በብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የታየውን ተስፋ ሰጭ ውጤት ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል:: ለዚህ ውጤት መመዝገብ ሚና ከነበራቸው ግብዓቶች መካከል ኮሚሽኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (Foreign Direct Investment – FDI) ለማሳደግ ያከናወናቸው ተግባራት ይጠቀሳሉ:: በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ሀገራትና በአዲስ አበባ የተካሄዱና ኮሚሽኑ የተሳተፈባቸው የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞች (Business and Investment Forums) ደግሞ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው::
የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞች የኢንቨስትመንት አቅሞችንና እድሎችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን ለመሳብ ትልቅ ሚና አላቸው:: በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በሕግ ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ባለፈው የበጀት ዓመት በ10 ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፏል:: በሲንጋፖር፣ በጀርመን፣ በሕንድ፣ በኢጣሊያ፣ በሩሲያ፣ በኔዘርላንድስ እና በቻይና በተካሄዱ የኢንቨስትመንት ፎረሞች ላይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅሞችና መልካም እድሎችን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል:: በዚህም ኢትዮጵያ ስላሏት ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ግንዛቤ ያገኙ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገሪቱ መጥተው በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተዋል:: የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ፎረሞች ያላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮ-ሩሲያ የቢዝነስ ፎረም (Ethio-Russia Business Forum) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተካሂዷል::
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በመንግሥታት መቀያየር ያልተለወጠ የረጅም ዘመናት ግንኙነትና ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል:: ሩሲያ በኢትዮጵያ የፈተና ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፈችና ወዳጅነቷንም በተግባር ያስመሰከረች ሀገር ናት:: በዓድዋ ጦርነት፣ በፋሺስት ኢጣሊያ እና በሶማሊያ ወረራ ወቅቶች እንዲሁም በሌሎች ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች::
በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የሩሲያ ነገሥታት መልዕክተኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሁም የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት መልዕክተኞች ደግሞ ወደ ሩሲያ ሄደው ጉብኝቶችን አድርገዋል፤ ስምምነቶችንም ተፈራርመዋል:: ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በ1951 ዓ.ም በሩሲያ ጉብኝት አድርገው የብድርና የድጋፍ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል:: በወታደራዊው የ‹‹ደርግ›› መንግሥት የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እጅግ ጠንካራ ነበር:: የወቅቱ የኢ.ህ.ዲ.ሪ ፕሬዚደንት ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በሶቭየት ኅብረት ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን አድርገዋል::
ከ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ወዲህም እንዲሁ በርካታ የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሁለቱ ሀገራት ይፋዊ ጉብኝቶችን አድርገዋል:: የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ1994 ዓ.ም በሩሲያ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ከሩሲያ መሪዎች ጋር የወዳጅነትና የትብብር መርህ ስምምነትን ተፈራርመዋል:: የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም በ2006 ዓ.ም በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በተካሄደው የ‹‹ቡድን 20›› አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሩሲያ-አፍሪካ እና በ‹‹ብሪክስ›› (BRICS) ጉባዔዎች ላይ ከፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ውጤታማ ውይይቶችን አድርገዋል::
የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ:: ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት፣ መንግሥት ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ያስችላሉ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል:: ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው:: የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ስራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም የንግድ (የወጭ፣ የገቢ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግዶች) እና የፋይናንስ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ ተወስኖ ውሳኔዎቹን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪም ከሦስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መግባቷ ይታወሳል::
ወደላቀ ደረጃ እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፣ ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የተተገበሩ በርካታ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲሁም ሩሲያ በአምራችና በወጭ ንግድ ዘርፍ ያላት ምርጥ ተሞክሮና አቅም የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ:: የኢትዮ-ሩሲያ የቢዝነስ ፎረም የተካሄደውም እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች መነሻ በማድረግ ነው::
ፎረሙ የተዘጋጀው በሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር አመቻች ኮሚቴ (AFROCOM)፣ በሩሲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት እና በ‹‹ሮስኮንግረስ ፋውንዴሽን›› (Roscongress Foundation) ትብብር ሲሆን፣ የሩሲያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል::
በፎረሙ በግብርና፣ በኃይል፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግንባታና በትራንስፖርት ዘርፎች የተሰማሩ ከ30 በላይ የሩሲያ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል:: በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (Ethiopian Investment Holdings)፣ ኢትዮቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ሌሎች ተቋማት በፎረሙ ላይ ተሳትፈዋል::
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ ፎረሙ በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለው የምጣኔ ሀብት ትስስር እያደገ ስለመምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ይገልፃሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ካላቸው የረጅም ዓመታት ታሪካዊ ግንኙነት እና እምቅ አቅም አንፃር ሲመዘን የሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በቂ የሚባል አይደለም:: በመሆኑም የሀገራቱን እምቅ አቅም በመጠቀም የኢኮኖሚ ትብብሩን ማጠናከር ያስፈልጋል::
የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ:: ኢትዮጵያ በወሰደቻቸው በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ምክንያት በብዙ ሀገራት በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የሩሲያ ትልልቅ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል እንደሚፈጥርም ያብራራሉ::
የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉትን በርካታ እድሎች እንዲጠቀሙ ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደር ምስጋኑ፣ ፎረሙ አዲስ አጋርነት እንደሚፈጥር እና በኢትዮጵያና በሩሲያ ሕዝቦች መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ እና ሩሲያ እንደ ‹‹ብሪክስ›› (BRICS) አባልነታቸው፤ ኢትዮጵያ የሩሲያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ መዳረሻ በመሆን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል::
በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌደሬሽን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፣ ኢትዮጵያ እና ሩስያ በብዙ ዘርፎች ጠንካራና ታሪካዊ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለረጅም ዓመታት የቆየው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት ማሳደሩን ይገልፃሉ:: የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ የለውጥ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ስትራቴጂካዊ አቋም፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷ እና በ‹‹ብሪክስ›› አባልነት መካተቷ የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረውም ያስረዳሉ።
‹‹የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊና ጠንካራ ትብብር ነው:: ግንኙነታችን በፖለቲካ መስክ ብቻ የተገደበ መሆን እንደሌለበትና የመንግሥታዊ ዲፕሎማሲ፣ የሕዝብ ለሕዝብ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ግንኙነታችን በጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር መታገዝ እንዳለበት እናምናለን›› ይላሉ::
የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር አመቻች ኮሚቴ (AFROCOM) ሊቀ መንበር ኢጎር ሞሮዞቭ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለሩሲያ ኩባንያዎች ምቹና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሆነች ይናገራሉ:: በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በብዙ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ይሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ይገልፃሉ::
ሊቀ መንበሩ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የ››ብሪክስ›› አባል መሆኗ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉት ነፃ የንግድ ቀጣናዎችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚኖረውን ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከርና ለማቀላጠፍ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያና ሩሲያ ያላቸው ታሪካዊ የዲፕሎማሲና የባሕል ትስስር ለኢኮኖሚ ትብብራቸው መጠናከር በጎ ሚና እንደሚኖረውም ያስረዳሉ::
የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሞች ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ትልቅ ሚና እንዳላቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ጥናቶችም ያስረዳሉ:: በምጣኔ ሀብታቸው ያደጉ ሀገራት ጭምር እንዲህ ዓይነት የኢንቨስትመንት አቅም ማስተዋወቂያ መድረኮችን የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን ለማሻሻል ይጠቀሙባቸዋል:: ብዙ ሀገራት የኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸውን መድረኮች በተደጋጋሚ ሲያዘጋጁ ማየት የተለመደ ነው:: ሀገራት ያላቸውን አቅም በትክክል ለማሳየት ይጠቅማሉ::
የውጭ ባለሀብቶች በተለይም ስለአፍሪካ ያላቸው ግንዛቤ በቂ ስለማይሆን መሰል የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው:: እነዚህ መድረኮች ግንዛቤ በመፍጠር ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ያመቻቻሉ:: ስለሆነም የቢዝነስ ፎረሞችን በታቀደላቸው ዓላማ መሰረት በመምራት የኢንቨስትመንት ዘርፍ አቅምን ማሳደግና ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደሚገባ ጥናቶቹ ይጠቁማሉ::
የቢዝነስ ፎረሞች ተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው ባይካድም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በዘላቂነት ለማሳደግ ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን ግን መተኪያ የማይገኝለት ወሳኝ ግብዓት ነው:: ሰላምና ፀጥታን በዘላቂነት በማስፈን፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት መጠን እና የተሳትፎ መስክ በማስፋት የዕውቀት፣ የክሕሎት፣ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ስርጸትን ማፋጠን ተገቢ ይሆናል::
በአጠቃላይ በውጭ እና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች መካከል ትስስርን በማስፋት፣ የኢንቨስትመንት ክልላዊ ስርጭትን በማሻሻል፣ እንዲሁም የውጭ ካፒታል በመጠቀም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ፤ ኢንቨስትመንቶች በአገራዊ የኢንቨስትመንት ዓላማዎች የተመለከቱ ግቦችን ማሳካታቸውን እንዲሁም በሕግ አግባብ መከናወናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም ኢንቨስትመንት የሚመራበትን ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ፣ ተገማች፣ እና ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠንና የእድገቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም