ኢትዮጵያ ያለ የሌለ ሀብቷን መድባ ልጆቿን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየመደበች የምታስተምረው በቀጣይ የሚያስፈልጋትን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ነው።እነዚህ ሀገር ተረካቢ ዜጎች የሚመራመሩ እና በራሳቸው ስራ የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ለማድረግም ነው።በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠንካራ ፣ አስተዋይ እና ሩቅ አሳቢ ሊሆኑ ይገባል።
የሚሰሟቸውን፣ የሚያነቧቸውን፣ ወዘተ መረጃዎች እንዳለ ተቀብለው የሚተግብሩ ሳይሆኑ፣ ከተለያዩ መረጃዎች ጋር እያመሳከሩ ክፉውን ከደጉ እየለዩ የሚጠቀሙ እንዲሆኑ ይጠበቃል።መረጃዎች በማን እንደተሰራጩ ፣ ለምን አላማ እንደተሰራጩ መመልከትም ይኖርባቸዋል።በእነዚህ መረጃዎች ላይ በመመስረት የሚወስዷቸው እርምጃዎች ራሳቸውን፣ ሌሎች ሰዎችን፣ አካባቢያቸውን፣ ሀገራቸውን የሚጎዱ እንዳይሆኑ መጠንቀቅም ይኖርባቸዋል።ከምንም በላይ ስስ መሆን የለባቸውም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በለውጡ ተቃዋሚዎች ማማለያዎች በመታለል እንዲሁም ከንቱ ወሬ በመነዳት ማመዛዘናቸውን እየተቀሙ ይገኛሉ።የተሰጣቸውን መረጃ አንጠልጥለው እርምጃ እየወሰዱ የሚገኙም አሉ።በዚህ የተነሳም ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አመለካከት በነጻነት የሚራመድባት ሆና ሳለ በዩኒቨርሲቲዎች ሁከት ቤቱን እየሰራባቸው ነው።ለእዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጸሙት ግድያዎች እና እየደረሱ ያሉት ጉዳቶች ማሳያዎች ናቸው።
በዚህ አይነቱ እርምጃ የሰጉትም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤተሰቦቻቸው የተመለሱበት ሁኔታ ታይቷል።ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉትም በርካታ ናቸው።መንግስት ችግሩ በጣም አሳሳቢ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ዩኒቨርሲቲዎችን እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ ‹‹ሀዘንሽ ቅጣ አጣ ከቤትም አልወጣ›› አይነት እርምጃ ገዳይም ሟችም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየሆኑ ናቸው።የተማሪዎች ምክንያታዊ አለመሆን ለእነዚህ ሃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል።ይህ አሳዛኝ ድርጊት የሀገራችንን ዩኒቨርሲቲ ገጽታም እያበላሸው ይገኛል።
በመሆኑም ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ከንቱ መረጃዎች ላይ በመመስረት እንዲሁም መረጃዎቹን ለሚለቁ እኩይ ሃይሎች ቅጥረኛ በመሆን ጭምር እርስ በርሳቸው እየተባሉ ያሉበት ሁኔታ የተማሪዎቻችንን ውድ ህይወት እያጠፋ ነው፤ ጊዜና ስነ ልቦና በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ መቀጠል የለበትም።
ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት ፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ይህን ችግር ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
በየዩኒቨርሲቲዎቹ በርካታ ውይይቶች እየተደረጉም ናቸው።እነዚህ ጥረቶች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት የሚያግዙ እንደመሆናቸው የተማሪዎችን የማመዛዘን አቅም በማሳደግ ላይ በማተኮር ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
መንግስት የዩኒቨርሲቲዎችን የጥበቃ ክፍል በፌዴራል ፖሊስ እንዲያዝ እስከ ማድረግ ደርሷል።እርምጃው በዩኒቨርሲቲዎቹ ሰላምና መረጋጋትን ለመመለስ ታስቦ የተደረገ እንደመሆኑ በጠንካራ ጎኑ ሊታይ ይገባል።ፌዴራል ፖሊስ ህዝባዊ ወገንተኝነት በተሞላበት መልኩ በመስራት በዩኒቨርሲቲዎች ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ የራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍ ይታመናል።
የዩኒቨርሲቲዎች ማህበረሰቦች እንዲሁም የየአካባቢው ህዝብ ለእዚህ የጸጥታ ሀይል ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋታቸው በፍጥነት እንዲመለሱ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ አዳዲሶቹ አጥር እንደሌላቸው ይገለጻል።ይህ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲዎቹን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ ይታመናል።በመሆኑም አጥር በተወሰነ መልኩም ቢሆን ችግሩን ሊፈታ ይችላልና አጥር እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።
አጥር ሊያስቀር የሚችለው የተወሰነውን ችግር ብቻ መሆኑን መረዳት ግን ይገባል።ዋናው መሆን ያለበት በተማሪዎች መካከል መተማመን እንዲኖር በማድረግ ለውጡን ወደኋላ መመለስ ለሚፈልጉ ሃይሎች ምንም አይነት ቀዳዳ እንዳይፈጠር መስራት ነው።በዚህ በኩል ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች የትኛውንም አይነት ቅሬታ ሊያስነሱ የሚችሉ አሰራሮችን ለማስተካከልና ግልጽነትን ለማስፈን ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
መንግስት ካለፈው የኢህአዴግ ዘመን በተለየ መልኩ ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ አቋም ማራመጃ መሆን እንደሌለባቸው በጽኑ ያምናል።የፖለቲካ ሃይሎችም ሆኑ የእነሱ ተላላኪ የሆኑ ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲዎችን የፖለቲካ አመለካከት ማራመጃ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።አሁን እየተፈጸመ ያለው ግን ለውጡን ለማደናቀፍ በሚል በቀቢጸ ተስፋ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች ስውር ሴራ ነው፡፡
እነዚህ ሃይሎች በዩኒቨርሲቲዎች ቢሮ ከፍተው ባይሰሩም፣ ያለ የሌለ ጥሪታቸውን እያፈሰሱ ዘመን በፈቀደላቸው መንገድ የፖለቲካ ስራቸውን እየሰሩ የተማሪዎችን ደካማ ጎን እየተጠቀሙ ናቸው።ችግሩ ሀገሪቱን ክፉኛ እየፈተነ ቢሆንም ፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያለውን ችግር መመከት እንዲሁም ማስወገድ የሚቻለው ተማሪዎች በእነዚህ ሃይሎች ላይ ሲነቁ ብቻ ነው።
ተማሪዎችን ይህን በማድረግ ከእነዚህ ወገኖች የሚለቀቀውን ትንሹንም ትልቁንም መረጃ ይዞ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።ለከንቱ ፖለቲከኞች መሳሪያ እየሆናችሁ የምትገኙ ተማሪዎች እባካችሁ ክፉና ደጉን በመለየት ለለውጡ አደናቃፊዎች መሳሪያ ከመሆን ራሳችሁን ጠብቁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2012