የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የንግድ ቤቶች ኪራይ ማሻሻያን ተከትሎ ከተከራይ ነጋዴዎች የተነሳውን ቅሬታ አስመልክቶ የደረሰበትን ውሳኔ ለማሳወቅ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለመገኘት ትናንት ረፋድ ላይ በስፍራው ደርሰናል፡፡ ለገሀር የሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት የፊት ለፊት መግቢው ቁጥራቸው ከሁለት መቶ በሚልቅ ተከራይ ነጋዴዎች ተሞልቷል፡፡
እንደምንም እየተጋፋን አልፈን መግለጫ ከሚሰጥበት አዳራሽ ደረስን፡፡ በውሳኔው ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር ሲመክሩ የቆዩ ከሃያ የሚልቁ የነጋዴዎቹ ተወካዮች ደግሞ ቦታውን ለጋዜጠኞች እንዲለቅቁ ቢጠየቁም፣ «አይሆንም፣ መግለጫው መሰጠት ያለበት እኛ ባለንበት ካልሆነ የተሳሳተ መረጃ ይነገራል» በሚል ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡
ጋዜጠኛው ቆሞ እንኳ መግለጫውን የሚከታተልበት ቦታ በመጥፋቱ መግለጫ ከሚሰጥበት አዳራሽ ወደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢሮ በማምራት መረጃውን ለህዝብ ለማድረስ የጓጓው ጋዜጠኛ በቢሮው ባሉ ጥቂት ወንበሮችና በቢሮው ወለል ላይ በመቀመጥ መግለጫው እንዲሰጥ ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለህዝብ እንዲደርስ የተፈለገውን መረጃ ለጋዜጠኞች የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ የንግድ ቤቶች ዋጋ ማሻሻያን ተከትሎ የቀረቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አዋቅሮ በየደረጃው ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ጉዳዩንም በጥልቀት በመመልከትና ጥልቅ ምርመራ በማድረግ ለቦርድ ቀርቧል፡፡ ቦርዱም ውሳኔዎችን ወደኋላ ሄዶ በማየትና በመገምገም ወስኗል፡፡ እንደ አቶ ረሻድ ገለጻ፤ ከተከራይ ነጋዴዎች የቀረቡ ቅሬታዎች ሦስት ገጽታ አላቸው፡ ፡ የመጀመሪያውና አብዛኛውን ቁጥር የያዘው ማሻሻያው ተገቢ ቢሆንም የተደረገው ማሻሻያ የተጋነነ ነው፤ ወቅቱንና ሁኔታዎችን ያላገናዘበና የቤቶቹን ሁኔታ ብሎም ቦታውን ያላማከለ ነው፡፡ እናም መታየት አለበት የሚል በቀና ሀሳብ የቀረበ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 397 ቅሬታዎችን ያቀፈውና ከቦታ ልኬት ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ይሄም በተገቢው መልኩ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡
ሦስተኛውና በጥቂት ግለሰቦች የቀረበው ግን በፍጹም ማሻሻያው ሊደረግ አይገባውም፤ እናም እንዳታስቡት የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ሲልም በ1997፣ በ2004 እና በ2007 ዓ.ም ለማሻሻል ተሞክሮ በጥቂት ግለሰቦች ጫና እንደቀረው ሁሉ፤ አሁንም ያንኑ ለመድገም ያሰበና በማስፈራሪያዎች ጭምር የታጀበ ነው፡፡ እነዚህን ቅሬታዎች መነሻ በማድረግም የተደረገውን ማሻሻያ በሦስት ዓመት ውስጥ እንዲደርሱበት የተወሰነ ሲሆን፤ አከፋፈሉን በተመለከተ ግን የንግድ ቤቶች፣ የንግድ ያልሆኑ ቤቶችና በዶላር የሚከራዩ ቤቶች በሚል በሦስት መልኩ በመክፈል ተመልክቷቸዋል፡፡
በዚህም የንግድ ቤቶች በመጀመሪያው ዓመት ላይ አሁን እየከፈሉ ያሉትንና የአዲሱን ጭማሪ 35 በመቶ፣ በሁለተኛው ዓመት ተጨማሪ 35 በመቶ በመክፈል በሦስተኛው ዓመት ላይ 30 በመቶ በመጨመር 100 በመቶ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡ በተመሳሳይ የንግድ ያልሆኑ ለቢሮ አገልግሎት፣ ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካል ጉዳተኞች፣ ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለፖለቲካ ድርጅት፣ ለሙያ ማህበራት፣ ለሸማቾች ማህበር፣ ለአነስተኛና ጥቃቅን እና መሰል ለትርፍ ላልተቋቋሙ ድርጅት ቤቶችን በተመለከተ ቀደም ሲል ከተወሰነው የ339 ብር ወደ 140 ብር እንዲወርድና በሦስት ዓመት ውስጥ እንዲደርሱበት ተወስኗል፡፡
በውጭ ምንዛሪ የሚከራዩ ቤቶችን በተመለከተም ከ92 ዶላር ወደ 50 ዶላር እንዲቀንስና በሦስት ዓመት እንዲደርሱበት ተወስኗል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ እንደ አራተኛ የሚቀመጠው፣ በልዩ ሁኔታ የሚታዩ ካሉ ውል ከፈጸሙ በኋላ በመመሪያው መሰረት በኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራር ታይቶ እልባት እንዲሰጠው የሚለው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህ ስር የሚወድቁት ደግሞ ቀደም ሲል በአንደኛ ደረጃ ተይዘው ነገር ግን በባቡርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ ምክንያት ገበያቸው የተቀዛቀዘባቸውና ሌሎች አካሎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ውል ከፈጸሙ በኋላ ሊያዋጣቸው ወደሚችል መስክ እንዲሰማሩ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ውሳኔ የንግድ ቤት ቁልፍ የገዙ በአዲሱ ተመን መሰረት እንዲከፍሉና ስሙንም በራሳቸው እንዲያደርጉ፤ ለውል እድሳት ይከፈል የነበረው 500 ብር እንዲሁም ለንግድ ዘርፍ ለውጥ ይከፈል የነበረውን ብር 7ሺ ክፍያ፤ ውል ሲፈጸም የነበረ የሦስት ወር ዋጋ ክምችት ለአንድ ጊዜ እንዲቀርና በነጻ እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡ አዲሱ የኪራይ ተመን ትግበራም በአንድ ወር ተራዝሞ ከየካቲት 1ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
እነዚህን የውሳኔ መግለጫዎች በውጭ ካለው የነጋዴዎች የተቃውሞ ድምጽ ጋር ታጅቦ ካደመጥን በኋላ የተከራዮችን ሀሳብ ለማድመጥ አመራን፡ ፡ “ድምጻችን ይሰማ” በሚል ከፍተኛ ድምጽ የታጀበው የተከራይ ነጋዴዎች ምላሽም የዋጋ ማሻሻያው በተገቢው ጥናት ላይ ያልተመሰረተና ወቅቱን ያልጠበቀ፤ ብሎም በአሁን ወቅት ሊደረግ የማይገባው ከጥቅሙ ይልቅም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናው የጎላ ስለሆነ ተቀባይነት የሌለው ነው የሚል ነበር፡፡
አቶ ተስፋዬ ነጋሽ የቀጣና ሦስት ተከራዮች ተወካይ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተሰማው ነገር ጊዜ ከማራዘም ባለፈ ጥያቄያቸውን የመለሰ አይደለም፡፡ የዕቃዎች ዋጋ በናረበት፣ የብር የመግዛት አቅም በወደቀበት፣ አገር ባልተረጋጋ ሁኔታ ላይ ባለችበትና ዜጎች ለውጥን በሚናፍቁበት፣ የኢኮኖሚው መዳከም በዜጎች ላይ እየታየ ባለበት ጊዜ የተከናወነው ጭማሪ ለህሊና የሚከብድና ወቅቱን ያላገናዘበ ነው፡፡ ውጤቱም ሠራተኛን የሚበትንና ሥራ አጥ ዜጋን የሚፈጥር ነው፡፡ የቀጣና አራት ተከራዮች ተወካይና የአጠቃላይ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ቀሮ ታመነ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የጊዜው መራዘም፣ የአንድ ጊዜ ክፍያዎች መቅረትና ቁልፍ ገዝተው ስም ያላዞሩትን አስመልክቶ የቀረቡት ውሳኔዎች መልካም ናቸው፡፡
ነገር ግን የንግድ ቤቶቹን በተመለከተ አጠናነው ያሉት ግን ሕጋዊነትን የተከተለ አይደለም፡፡ ጥያቄያችን ‹‹ለጭማሪው አሁን ጊዜው አይደለም›› የሚል ነው እንጂ ጊዜ አራዝሙልን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ነጋዴው ላለፉት ሶስትና አራት አመታት ስራ ሲሰራ አልነበረም፡፡ አሁን መሰራት ያለበት የቤት ኪራይ ዋጋ ማሻሻል ሳይሆን አገር ማረጋጋት ነው፡፡ እናም ውሳኔው ችግሮችን የሚያባብስ፣ ተከራይ ነጋዴውን ያላስደሰተ ብቻም ሳይሆን ከአምስት ወይም አስር ዓመት በፊት መነካት የሌለበት ዘርፍ ነው የተነካው፡፡ አቶ ረሻድ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የቀረበውን ውሳኔ ተከትሎ በአንድ በኩል አሁንም ቅናሽ መደረግ አለበት፤ በሌላ በኩል መሞከር የለባችሁም የሚሉ ሀሳቦች በተወካዮች በኩል ደርሷቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቀረበው ቅሬታ በጥንቃቄ የታየና ደንበኞችን በማይጎዳ መልኩ የተከናወነ ነው፡፡ በቦርዱ ግምገማ መሰረትም ማሻሻያው ሕጋዊ መሰረት እንዳለው፤ በጥናት ላይ ተደግፎ የተከናወነና አሳታፊም እንደነበር፤ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥና ነጻ ውድድርን ለማጎልበት እንዲሁም ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ ያለመ እንደሆነ መሆኑን በማረጋገጥ የዋጋ ክለሳው ትክክል ስለመሆኑ ወስኗል፡፡ ይልቁንም ማሻሻያው የዘገየ መሆኑን በመጥቀስ፤ ማሻሻያው ረዥም ጊዜ አስቆጥሮ የተከናወነ እንደመሆኑ የተደመጠው ድንጋጤ ተገቢ መሆኑን በማመን ነው ይህ ውሳኔ የተሰጠው፡፡
እናም ይሄንን በቀናነት ተመልክቶ መውሰዱ መልካም ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አይተውም ሰሞኑን ውል እየገቡ ያሉ አሉ፡፡ በዚህ መሰረት የማይስማሙ ከሆነ ግን ቤቱ የእነሱ የግል ንብረት ወይም የኮርፖሬሽኑ ሳይሆን የ100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት በመሆኑ በመመሪያው መሰረት ቤቱን ይለቅቁና ለኢትዮጵያውያን ጥቅም ሲባል ጨረታ ወጥቶ እንዲከራይ ይደረጋል፡፡
ምክንያቱም እነዚህን ነጋዴዎች ብዙ ተደግፈዋል፤ እስካሁንም እሹሩሩ እየተባሉ ለ300ሺ የአዲስ አበባ ነጋዴ የተነፈገውን እድል ለ40 ዓመት ይዘው ቆይተዋል፡፡ እናም ቤቶቹ ወደ ነጻ ገበያ ውድድሩ እንዲገቡና ሌላው ኢትዮጵያዊ በቤቶቹ እንዲጠቀም ይደረጋል፡፡ ዋጋው ኮርፖሬሽኑ በጨረታ ካከራያቸው ሌሎች ቤቶች ከእጥፍ በላይ ያነሰ እንደመሆኑ ተመኑ ፍትሃዊ ነው፡፡ የገበያ አለመረጋጋቱን በተመለከተም ለፖለቲካ ጥቅም ለማዋል ካልሆነ በስተቀር በአዲስ አበባ ያለን ከ300ሺ በላይ ነጋዴ ዋጋ 6ሺ ነጋዴ አይወስንም፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
በወንድወሰን ሽመለስ