
አዲስ አበባ:– ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የግሉ ዘርፍ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ አስተዋፅዖ እያበረከተ እና ኢትዮጵያውያንም በዲጂታል መንገድ የገንዘብ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻለ እንደሚገኝ ተገለጸ።
አሪፍ ፔይ ፋይናሽያል ቴክኖሎጂ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ መስከረም ደጀኔ፤አሪፍ ፔይ ፋይናሽያል ቴክኖሎጂ ከጃሚ ዌብ አፕ ጋር በመቀናጀት በማኅበራዊ ሚዲያ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እየለቀቁ ብዙ ተከታይና አድናቂ ላላቸው ሰዎች የገንዘብ ስጦታ ሊያገኙ የሚያስችል አዲስ ሲስተም ወደ ሥራ አስገብቷል። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ወደ ሥራ የገባው ትግበራ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ፍቃድ የተሰጠው የፋይናንሽያል ተቋም ያደርገዋል ብለዋል።
ሥርዓቱ በተለይ ነጋዴዎች ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ ያስችላል። ኅብረተሰቡ ከቴክኖሎጂ ጋር ቅርብ መሆን ይጠበቅበታል ያሉት ኃላፊዋ፤ ከ32 ባንኮች፣ ከቴሌ ብር እና ከሌሎችም ጋር ግንኙነት የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ የዲጂታል ሥርዓትን በተገቢው መልኩ መልመድ ይኖርበታል። ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህን እያሰፋ ይቀጥላል። አገልግሎት አሰጣጥ በዲጂታል እየተቀየረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሲስተሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት የግሉ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ ሊወስድ ይገባል ያሉት ኃላፊዋ፤ ድርጅቱ ብሔራዊ ባንክ የግል ተቋማት እንደፋይናንስ ተቋም እንዲያገለግሉ ያወጣውን ሕግ መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ለመጀመር ውሳኔ ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
መንግሥት የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ መንገዱን መክፈቱ ምቹ ሁኔታ ተደርጎ ይታያል ያሉት ኃላፊዋ፤ በገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ ለመጀመር በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን ማኅበር ሆኖ መደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ሲስተሙ የለማው በሀገር በቀል እውቀት ነው። ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ለ200 ሠራተኞች ሥራ ዕድል በመፍጠር ጀምሯል።
አሠራሩ ኢንቨስትመንት ይኖረዋል፣ ድርሻ የሚኖራቸው ባለቤቶች አሉት። ቴክኖሎጂ ላይ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችም ያስፈልጋሉ፤ እነዚህ ተሟልተዋል ብለዋል።
የጃሚ ዌብ አፕ መሥራች ወጣት ናታን ዳምጠው በበኩሉ እንደገለጸው፤ ወደ ተግባር የገባው አዲሱ ሥራ ለመልካም አገልግሎት ስጦታ ለሚበረከትላቸው ሰዎች በዲጂታል መንገድ ጉርሻ እንዲያገኙ ታስቦ የተጀመረ ነው።
የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ስላልነበረ እንዲህ አይነት አሠራር ከሁለት ዓመታት በፊት ለመጀመር ማሰብ ከባድ ነበር። አሁን አሪፍ ፔይና የመሳሰሉ በዘርፉ መምጣታቸው ሥርዓቱ ቀላል እንዲሆን አስችለውታል።
የቲክቶክ፣ የዩቲዩበር፣ ኢንስታግራመር፣ የፌስቡክ ፀሐፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከአድናቂዎቻቸውና ከተከታዮቻቸው ከላይክና ከሼር በላይ ገንዘብ ለመላክ ለሚፈልጉ እንዲጠቀሙ ታስቦ የተዘጋጀ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ አሠራር እንደሆነ አብራርተዋል።
የውጭ አገር ተሞክሮን በመቀመር በኢትዮጵያም እንድንጀምር አስችሎናል። ተሰጥዖዋቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በነፃ በመልቀቅ ብዙ ተከታዮችና ሼሮችን ሲያገኙ የነበሩ ሰዎች ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኙ በር ይከፍታል ብለዋል።
ትግበራው ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ አስተዋፅዖ ያደርጋል። የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ እየለቀቁ ገንዘብ የሚያገኙበት፣ ሥራም የሚፈጠርበት መንገድ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም