አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን የፌዴራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያስጠናው ጥናት አመለከተ::
ኮሚሽኑ ለስድስት ወራት የተካሄደውን የዚህን ጥናት ውጤት አስመልክቶ ትናንት በፍሬንድሺፕ ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ ላይ የጥናቱ አማካሪ አቶ ጌዲዮን ገሞራ እንደገለፁት፤ በጥናቱ የዘርፉን እሴት ሰንሰለት ተከትለው ለሙስና ያጋልጣሉ ተብለው ከተለዩ አስራ ስምንት አመላካቾች ውስጥ አስራ ሶስት የሚሆኑት ዘርፉን ለሙስና በከፍተኛ ደረጃ የሚያጋልጡ ናቸው::
ጥናቱ በተካሄደባቸው አማራ፣ ቤንሻንጉልጉሙዝ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና አፋር ክልሎች ከላይ ጀምሮ እስከታችኛው የማዕድን ዘርፉ እሴት ሰንሰለት ድረስ ችግሮች መኖራቸውንም አማካሪው አስታውቀዋል::መንግስት የዘርፉ ዋነኛ ተቆጣጣሪ አካል ከመሆኑ አኳያ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባው አመልክተው፣ ይህን ማድረግ ካልቻለ ዘርፉ ለሙስና ያለው ተጋላጭነት ይበልጥ ከፍ እያለ እንደሚሄድ አስገንዝበዋል::
ባለፉት አመታት ወዲህ በሀገሪቱ የታዩ አለመረጋጋቶች፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የኮንትሮባንድ ንግድ ለዘርፉ በሙስና መጋለጥ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አማካሪው ጠቅሰው፤ ዘርፉ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እያበረከተ አለመሆኑን ጥናቱ ማመለክቱን ተናግረዋል:: መንግስት እነዚህን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ካልፈታ ዘርፉን ለመለወጥ የሚያደርገውን ጥረት እጅግ ፈታኝ እንደሚያደርገውም አስታውቀዋል::
የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ምክንያት የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እየቀነሰ መምጣቱን ጥናቱ እንዳሳየም ጠቁመዋል:: ሙስናና ብልሹ አሰራሮችም ለዘርፉ ማሽቆልቆል የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸውን አብራርተዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ኮሚሽኑ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በጥናት ላይ ተመርኩዞ ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፤ይሁንና እስካሁን ድረስ በማዕድን ዘርፍ የጎላ ስራ አልሰራም:: በዚህ መነሻነትም ካለፈው አንድ አመት ወዲህ በዚህ ዘርፍ ላይ ሰፊ ትኩረት ያደረገ ሀገር አቀፍ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል::
የማዕድን ዘርፉን እሴት ሰንሰለት ተከትሎ ዘርፉን ለሙስና የሚያጋልጡ አመላካቾች በጥናቱ መለየታቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ በቀጣይ ኮሚሽኑም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥናቱ የጠቆማቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች በመያዝ ወደተግባር እንዲቀየሩ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩ አመልክተዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2012
አስናቀ ፀጋዬ