ለውጥ የሕይወት አንዱ አካል ነው። በምድራችን ሁሌም በየማይክሮ ሰከንዱ፣ በየሰዓት እና በየቀኑ የሚከሰትም ነው። በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥም በብዙ አይነት ሂደቶች ይተረጎማል፣ ይታያልም። ለዛሬ የምንነጋገረው ግን ‹‹ስለ ሰው ልጆች የአስተሳሰብ፣ የባሕሪና የድርጊት ለውጥ›› ይሆናል።
ለውጥን ቀለል አድርገን ለመረዳት ያህል ይህንን ምሳሌ እንውሰድ። የሰው ልጆች አንዳንድ ጊዜ አዲስ ምግብ መሞከር ወይም አዘውትረው ከሚሄዱበት መንገድ የተለየ አቅጣጫ መሄድ ምርጫቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አዲስ ትምህርት መጀመር፣ ወደ አዲስ ከተማ መሄድ ወይም አስተሳሰብን እና ባሕሪን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን መውሰድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ለብዙ ሰዎች ለውጥ ቀላል አይደለም። ለውጥ ለሰዎች አንዳንዴ ፍርሀት የሚፈጥር እንግዳ ስሜት ይዞ ይመጣል።
አልፎ ተርፎ በውስጣችን የሕመም ስሜት ጭምር እንዲሰማን ምክንያት ይሆናል። ነገር ግን አዎንታዊ ለውጥ ለእድገት፣ ለስኬት እና ለውስጣችን ሰላም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው በዛሬው መጋቢ አዕምሮ ዓምዳችን ላይ ይህንን ጉዳይ በቀዳሚነት መርጠን ልናወጋበት የፈለግነው። በመሆኑም በሚከተሉት ሀሳቦች በተለይ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ‹‹ለውጥን›› እንዴት መረዳት እንደሚቻልና በምን መልኩ መማር፣ መዘጋጀት እና በጠንካራ አእምሮ መቀበል እንደሚኖርብን በዝርዝር እንመለከታለን።
በመጀመሪያ ለውጥ ለምን ከባድ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው። የሰው አእምሮ ሁሌም ተደጋጋሚና ተመሳሳይ ልማዶችን በመደበኛ ተግባር ያከናውናል። አንድ ነገር ደጋግመን ስናደርግ ደግሞ ልማድ ይሆናል። ለምሳሌ ጠዋት ተነስተን ጥርሶቻችንን በተመሳሳይ መንገድ እናጸዳለን፤ ለሰዎች በተመሳሳይ መንገድ ሰላምታ እንሰጣለን፤ አስቀድመን የምናውቀውን መንገድ ተጠቅመን የሚያጋጥሙን ችግሮች እንፈታለን። በእርግጥ አንዳንድ ልማዶች መጥፎ አይደሉም። እንዲያውም ልማዶች ኃይልን ለመቆጠብ ይረዳሉ።
ልምድ ሲኖረን አዕምሯችን ስለ ተማርነው ነገር በጥልቀት ማሰብ አያስፈልገውም። አዲስ ነገር ሲመጣ ግን አዕምሮ የበለጠ መሥራት አለበት። ይሁን እንጂ ልማዳችን ለረጅም ግዜ አብሮን ሲቆይና ለውጥ ሲመጣ አዕምሯችን እንደ ስጋት ሊቆጥረው ይችላል። ለውጥን ስንገፋ በነበርንበት ሁኔታ ምቾት ሊሰማን ወይም ፍርሃት ሊሰማን ይችላል። “ይህ ለእኔ አይሆንም” ወይም “ይህን አዲስ ነገር እንዴት እንደማደርገው አላውቅም” የሚሉ የለውጥ ተቃዋሚ ኃይሎች በውስጣችን ሊመላለሱ ይችላሉ። ይህንን መሰሉ ለውጥን የመፍራት ወይም የመቃወም ስሜት የሚመጣው ከአዕምሯችን ኃይላችንን ለመቆጠብና ከሚመጡ አደጋዎች ሊጠብቀን ስለሚሞክር ነው። ይህ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪ ቢሆንም ግን በለውጥ ውስጥ የምናገኛቸውን እድሎችና ጥቅሞች በማስቀረት ከእድገታችን ይገድበናል።
የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይህንን ምላሽ “የለውጥ መቋቋም” ብለው ይጠሩታል። የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የለውጥ እውቅ ኤክስፐርት ዶክተር ጆን ኮተር የሰሩት ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ብዙ ሰዎች ለውጡን የሚቃወሙት ውድቀትን በመፍራት፣ ሊቆጣጠረው አልችልም በማለት ወይም የለውጡን ዓላማ ባለመረዳት ነው። ለውጥ በድንገት ወይም በግዳጅ ሲከሰት ይህ ስጋት የበለጠ ጠንካራ ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ትምህርት ቤት የማስተማር ስልቱን ከቀየረ ተማሪዎች ከባድ የጭንቀትና የፍርሀት ስሜት ሊያስተናግዱ ይችላሉ።
በሌላ መልኩ ብናየው አንድ ሰው በድንገት ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም ለማቆም ቢሞክር ከነበረበት ስሜት የመውጣትና ብቸኝነት ሊሰማው ይችላል። አብዛኛውን ግዜ ሰዎች የለውጥ አስፈላጊነትና ምክንያት ሳይረዱ ሲቀሩ ለውጥን የመቋቋምና ባሉበት የመርጋት ሁኔታ ያስተናግዳሉ። ይሁን እንጂ ከነበሩበት ሁኔታ በአዎንታዊ መንገድ ለውጥ ማድረግ ለራሳቸው ሕይወት መሻሻልና ለስኬታቸው ማማር እንደሆነ ሲያውቁ የመቀበል ዕድላቸው ሰፊ ነው።
ለውጥ ከስሜታችን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለውጥ በቀጥታ ስሜታችንን ይነካል። ለምሳሌ አድሜ ስንጨምር እና ስናድግ አሊያም አዳዲስ ኃላፊነቶች ሲያጋጥሙን ስሜታዊ ጫና ሊሰማን ይችላል። በአዲስ መንገድ ማሰብ ስንጀምር ወይም ከአሮጌ ልማድ ስንወጣ ግራ መጋባት ሊሰማን ይችላል። ይህ የተለመደ ነው። የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ዊሊያም ብሪጅስ እንደሚሉት፤ እያንዳንዱ ለውጥ ሦስት ደረጃዎች አሉት። በመጀመሪያ የድሮውን መንገድ ማጠናቀቅ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ውስጣችን የሚነግረን እና እርግጠኛ አለመሆናችን የሚሰማን ነው። ሦስተኛው አዲሱን መንገድ መጀመር አሊያም በለውጥ ውስጥ መቆየት ነው። ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላው ለመሸጋገር ጊዜ፣ ድጋፍ እና ራስን ማወቅ ያስፈልገናል። ብዙ ሰዎች ከለውጥ ጋር የሚመጡትን ስሜቶች እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ስለማያውቁ በሁለተኛው ደረጃ ላይ እንደተጣበቁ ይሰማቸዋል።
ለውጥ ግን ስጦታ ነው። እድል ያመጣል። አዎንታዊ ለውጦችን ስንቀበል ሕይወታችንን እናሻሽላለን። የበለጠ ብልህ፣ ጠንካራ እና የበለጠ ክፍት እንሆናለን። አዲስ ቋንቋ የሚማሩ፣ አዲስ ችሎታ የሚሞክሩ ወይም አዲስ ሥራ የሚጀምሩ ወጣቶችን እናስብ። ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ ከባድ ስሜት ቢሰማቸውም በለውጥ ውስጥ ሆነው እራሳቸውን ማሻሻላቸው የስኬት እድሎችን ይከፍትላቸዋል። ለውጥ በራስ መተማመንን ይገነባል። ዓለምን በአዲስ መንገድ እንድናይ ይረዳናል። ትልቅ ሕልም እንድናይ ያስችለናል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወጣቶች የተሻለ ሥራ፣ የተሻለ ትምህርት እና የተሻለ ኑሮ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ለመለወጥ ዝግጁ ካልሆኑ ምኞታቸው እውን ሊሆን አይችልም። አስተሳሰባችን፣ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደምንችል እና እንዴት በጋራ እንደምንሠራ ለማወቅ መጀመሪያ መለወጥ አለብን። ለምሳሌ ችግሮቻችንን እንዲያስተካክሉልን ሁልጊዜ ሌላ ሰዎች የመጠበቅን ልማድን ምርጫችን አድርገን ከቀጠልን ምንም ነገር በሕይወታችን ውስጥ በራሳችን ጥረት አናሻሽልም። ነገር ግን “አንድ ነገር ማድረግ እችላለሁ” ብለን ማሰብ ከጀመርን ስልጣኑን በእጃችን እናስገባለን። ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ ደግሞ የእድገት መጀመሪያችን ይሆናል።
ዋናው ጥያቄ ግን ለአዎንታዊ ለውጥ እንዴት እንዘጋጃለን? የሚለው ነው። ይህም ቢሆን ብዙ የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ እንደሚከተለው ራሳችንን ለለውጥ እንዴት ዝግጁ እንደምናደርግ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ለውጥ ተፈጥሯዊና አስፈላጊ መሆኑን መቀበል አለብን። በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ ይለወጣል፤ ተፈጥሮ፣ ቴክኖሎጂ እና ማኅበረሰብ የለውጥ ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ እኛም መለወጥ አለብን። ለውጥን ከተቃወምን ወደ ኋላ ልንወድቅ እንችላለን። ከተቀበልነው ግን በሕይወታችን ስኬታማ እንሆናለን። ይህ ማለት አዕምሯችን ክፍት እንዲሆን ማሰልጠን አለብን ማለት ነው። አዳዲስ ነገሮችን ለመስማት፣ ለመማር እና ለመሞከር ፈቃደኛ መሆን ይገባናል።
ሁለተኛው ጉዳይ የራሳችንን ልማዶች መረዳት ነው። ልማዶች መጥፎ አይደሉም፤ በብዙ መንገድ ይረዱናል። ነገር ግን አንዳንድ ልማዶች እንዳናድግ እና ስኬታማ እንዳንሆን ይገድቡናል። ለምሳሌ ሁልጊዜ አሉታዊ በሆነ መንገድ የምናስብ ከሆነ አዲስ ነገር ፈጽሞ ልንሞክር አንችልም። ሁልጊዜ ፍጹም የሆኑ ውጤቶችን የምንጠብቅ ከሆነ የመጀመሪያውን እርምጃ ልንወስድ አንችልም። ልማድን ለመለወጥ በመጀመሪያ ይህንን ማስተዋል አለብን። ከዚያ በተሻለ ልምድ፣ ችሎታና ባሕሪ ለመተካት መወሰን አለብን። የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ልማዶችን ለመቆጣጠርና ወደ ለውጥ ለመሄድ አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን መጥፎ ልማድን በየእለቱ በትንንሽና በአዎንታዊ እርምጃ የምንተካ ከሆነ ቀስ በቀስ ለውጥ መፍጠር እንችላለን።
በተጨማሪም ከሌሎች መማር አለብን። በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ለውጥን እንዴት መልመድ እንደሚችሉ አጥንተዋል። በቺፕ ሄዝ እና በዳን ሄዝ የተፃፈው ‹‹Switch›› የተሰኘ መጸሃፍ ለውጥ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ነገሮችን እንዴት መለወጥ እንደምንችል ያብራራል። መጸሐፉ፣ የተሳካ ለውጥ የሚመጣው በስሜት እና በምክንያት ስንመራ ነው ይላል። በመሆኑም ለውጥን ለማምጣት መለወጥን ማመን እና በርምጃዎቻችን ሁሉ የሚከሰቱ ውጤቶችን ደረጃ በደረጃ በግልፅ ማየት ስንችል ነው። አንድ ነገር ትርጉም ሲሰጠን እና ስናምንበት እሱን የመከተል እድላችን ሰፊ ነው። ከዚህ አንጻርም መፅሃፉ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማስተካከል ከመሞከር ይልቅ ቀስ በቀስ በሚመጣ ትንንሽ ስኬት መጀመር እንድንችል ይመክረናል።
ሌላው የለውጥ መሰረቱ ከወዳጅ ዘመድ ጠንካራ ድጋፍ ማግኘት ነው። ብቻችንን ካልሆንን እና ድጋፍ ካገኘን ለውጥ ቀላል ይሆንልናል። ከጓደኞች፣ አስተማሪዎች፣ ቤተሰብ ወይም አማካሪዎች ጋር መነጋገር እንችላለን። ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ ፍርሃታችንን ማካፈል እና ከተሞክሯቸው መማር እንችላለን። የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከሌሎች ተመሳሳይ ስሜት ከሚያስተናግዱ ሰዎች የሚማሩና ድጋፍ የሚያገኙ የበለጠ ስኬታማ ናቸው። በመሆኑም በአዎንታዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ ስንሆን እርዳታ ለመጠየቅ ዓይናፋር መሆን አይገባም፤ ይልቁኑ እርዳታ መጠየቅ የጥንካሬ ምልክት ነው።
ከወዳጅ ዘመድ ድጋፍ በተጨማሪ የአዕምሮ ጥንካሬን መገንባት ያስፈልገናልም። ይህ ማለት በራሳችን ማመን መቻል አለብን። አንድ ነገር አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ “መማር እችላለሁ” የሚለውን አዎንታዊ አስተሳሰብ መገንባት ይኖርብናል። ስለ ራሳችን ቀና አስተሳሰብ አለን ማለት ደግሞ ችግሮችን ችላ እንላለን ማለት አይደለም፤ ይልቁኑ እነሱን መጋፈጥ እንደምንችል እናምናለን ማለት ነው። ይህንን ጥንካሬ ለመገንባት አንዱ መንገድ ትናንሽ ግቦችን ማውጣት ነው።
ለለውጥ ለመዘጋጀት ሌላው አስፈላጊ ነገር የማወቅ ጉጉት ነው። ጉጉ ስንሆን ጥያቄዎችን እንጠይቃለን፤ መልሶችን እንፈልጋለን፤ ውድቀትን አንፈራም። የማወቅ ጉጉት አዕምሯችንን ይከፍታል። መማርን አስደሳች ያደርግልናል። ወጣቶች አዳዲስ ነገሮችን እንዲያነቡ፣ እንዲመራመሩ እና እንዲሞክሩ ሊበረታቱ ይገባል። ዓለም በአያሌ ሀሳቦችና እነሱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እና እድሎች የተሞላች ነች። ይህንን እድል ለራስ አቅም መጠቀም ይገባል። አዎንታዊ ለውጥና ስኬት የሚመጣው ንቁ ለሚሆኑ እንጂ ተቀምጠው ለሚጠብቁ አይደለምና።
ሌላው ዋናው ቁምነገር ለውጥ ጊዜ የሚወስድ መሆኑንም ማስታወስ ነው። ለውጥ ዛፍ የመትከል ያህል ነው። በመጀመሪያ ዘሩን እንዘራለን፤ ከዚያም እንዲያድግ ውሀ እናጠጣዋለን፤ ልዩ እንክብካቤ እናደርግለታለን፤ ቀስ ብሎ ያድጋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሕይወታችን ወይም በማኅበረሰባችን ውስጥ አዎንታዊ ለውጥ ጊዜ ይወስዳል። ውጤቱን በፍጥነት ካላየን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፤ ትዕግስት የሂደቱ አካል ነው።
አንዳንድ ጊዜ በለውጥ ወቅት ስህተት ልንሠራ እንችላለን። ሆኖም ልንደነግጥና ከሂደቱ ልንስተጓጎል አይገባም። ስህተቶች የመማር አንዱ አካል ናቸው፤ ውድቀትን መፍራት የለብንም። ዋናው ነገር እንደገና መሞከራችን ነው። ሁሉም ስኬታማ ሰው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ወድቋል። ዳግም ተነስተው ስኬታማ ያደረጋቸው ግን ደጋግመው መሞከራቸው ነው።
የአዎንታዊ ለውጥ ጥቅሞች
ለውጥ በሕይወት ውስጥ የተሻልን ስኬታማ ሰዎች እንድንሆን ይረዳናል። ግንኙነቶቻችንን፣ ጤናችንን፣ ትምህርትን እና ሥራችንን ያሻሽላል። የበለጠ ተለዋዋጭ እና የፈጠራ ክህሎት ያለን ያደርገናል። በፍጥነት በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ መላመድ የሚችሉ ሰዎች ስኬታማ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው። ለምሳሌ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ብዙ ሰዎች እንዴት እንደሚሠሩ፣ እንደሚማሩ እና እንደሚገናኙ አዲስ ነገር መፍጠር ነበረባቸው። በግዜው ለውጡን በፍጥነት የተቀበሉ ሰዎች አዲስ የሕይወት መንገድ አግኝተዋል። ከችግሩ ብዙ ትምህርቶችን ወስደው በፈጠራ ብዙ ስኬቶች ላይ ደርሰዋል። ወረርሽኙ ያስከተለውን ጫና መቋቋም ቸለዋልም።
በተመሳሳይ መልኩ የዲጂታሉ ዓለም በፍጥነት እየተቀየረ ነው። ሥራዎች፣ ችሎታዎች እና የመገናኛ ዘዴዎች ልክ እንደበፊቱ አይደሉም። የኢትዮጵያ ወጣቶች ዲጂታል መሳሪያዎችን፤ አዲስ ቋንቋዎችን እና አዲስ የአስተሳሰብ መንገዶችን ለመማር ዝግጁ መሆን አለባቸው። ካልተለወጥን የወደፊቱን ጊዜ ልናጣው እንችላለን።
ለለውጥ ዝግጁ ከሆንን እና ራሳችንን ክፍት ካደረግን ግን የአፍሪካም ሆነ የዓለም መሪዎች መሆን እንችላለን። በመሆኑም ወላጆች፣ አስተማሪዎች፣ መሪዎች እና ሚዲያዎች ስለ አዎንታዊ ለውጥ አስፈላጊነት መወያየትና ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው። ለውጥ የሚፈራ ሳይሆን ልንቀበለው የምንችለው የስኬታችን ምንጭ መሆኑን ማሳየት ይገባናልም።
በጥሩ ሁኔታ ስንለወጥ የተሻልን ሰዎች እንሆናለን፤ የተሻለች ሀገር እንገነባለን። ለውጥ ወደፊት ይመጣል ብለን የምንጠብቀው ነገር አይደለም። እኛ ራሳችን የምንፈጥረው ነገር ነው። እናም ሁሌም በለውጥና በመሻሻል ውስጥ እንሁን። ሰላም !!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም