በተደጋጋሚ ከሚሰራጩት ዜናዎች መካከል የኮንትሮባንድ ጉዳይ አንዱ ነው። በያዝነው ወር ክብደቱ ሰባት ኪሎ ግራም የሚመዝን ወርቅና ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ አገር ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተዘግቧል። 190 ኪሎ ግራም የሆነ 9ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የብር ጌጣጌጥና 520 የሞባይል ቀፎ በኮንትሮባንድ ሲንቀሳቀስ መያዙ ከተዘገበ ብዙ አልቆየም።
በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 22 ሽጉጥ ቶጎ ጫሌ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ ተገኘ ከሚለው ዜና ባሻገር በሱልልታ እና በሌሎችም የተለያዩ ኬላዎች በተደጋጋሚ የጦር መሳሪያዎች ሲዘዋወሩ ተይዘዋል፤ በሚል ይዘገቡ የነበሩ ተደጋጋሚ ዜናዎች አይዘነጉም።
እነዚህ ዜናዎች እንደሚያመለክቱት ኮንትሮባንድ በከፍተኛ ደረጃ መኖሩ ነው። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስን በማስከተል አገሪቱን እንደሚያዳክም አመላካች ነው።
ኮንትሮባንድ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን ቀረጥ ከማሳጣት ባሻገር በህብረተሰቡ ጤና እና ደህንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ምርቶችን በማስገባትና የማህበራዊ ግንኙነትን በማበላሸት፤ እጅግ አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ጥራት የሌላቸው ወይም ቀድመው አገልግሎት የሰጡ ቁሳቁስ በአነስተኛ ዋጋ ወደ አገር በማስገባት የአምራች ኢንዱስትሪን እንደሚጎዳ እና ኢኮኖሚውን እንደሚያደቅ አያጠያይቅም።
ህጋዊ ሆነው ቀረጥ ከፍለው ምርቶችን ወደ አገር የሚያስገቡ አካላት ለገበያ ሲያቀርቡ በኮንትሮባንድ ካስገቡት ጋር በዋጋ መፎካከር የማይችሉ በመሆናቸው፤ ህጋዊ አስመጪዎች እንዲጎዱ ያደርጋቸዋል።
በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ መላክ ያለባቸው ቡና እና ስጋን እንዲሁም የቁም እንስሳትን የመሳሰሉቱ በኮንትሮባንድ ወጥተው በዓለም ገበያ ላይ ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ከማድረግ ባለፈ በዘርፉ ወደ ውጪ የሚልኩ አካላትን ለኪሳራ ይዳረጋሉ። ስለሆነም ይህ ችግር በጋራ መከላከል ይገባል።
የሽጉጥና ቦንብን የመሳሰሉ አደገኛ የጦር መሳሪያዎችን ወደ አገር በማስገባትም ሰላም እንዳይኖር፤ ፖለቲካው ግጭት እንዲበዛበትና እንዲበላሽ የሚያደርግ ነው። ይህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት የሚያስከትለውን ኮንትሮባንድ ለመቆጣጠር ከጉምሩክ ኮሚሽን ስራ ባሻገር ሁሉም ህብረተሰብ ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት።
የኮንትሮባንድ ጉዳት የእያንዳንዱን ዜጋ ቤት የሚያንኳኳ ነው። የአስመጪውንም ሆነ የላኪዎች ገቢ ላይ ከሚያደርሰው የኪሳራ መጠን ባለፈ፤ እነዚህ ወገኖች ተስፋ በመቁረጥ ከገበያ ቢወጡ፤ እንደሌሎቹ በህገወጥ ሥራ ላይ ቢሰማሩ ወይም ኮንትሮባንድ ላይ ቢሳተፉ የመንግስትን ገቢ ይቀንሳል።
ይህ ደግሞ በእያንዳንዱ ሰው ህይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ የማይቀር ነው። በኮንትሮባንድ የሚገባውን የጦር መሳሪያም የህብረተሰቡ የደህንነት ስጋት ነው። ስለሆነም በጋራ መከላከል የግድ ነው።
ህብረተሰቡ ከጥቆማ ጀምሮ ኮንትሮባንድን ለመከላከል የሚያሳየው ትብብር የጉምሩክ ኮሚሽኑን ማገዝ ብቻ ሳይሆን የአገሪቷን ኢኮኖሚ መታደግና ኮንትሮባንድ ህዝቡ ላይ የሚፈጠረውን ጫና መቀነስ መሆኑን መረዳት ይገባል። ተቋማት የኮንትሮባንድ ተግባራት የሚፈጥሩት ጫና ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት የቤት ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል።
በተለይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ሥርዓቱን በማመቻቸት ዜጎች ወደ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዳይገፋ በመጠበቅ፤ ግብርና ሚኒስቴርም በተለይ ከቁም እንስሳት ጋር ተያይዞ ሊሰራ የሚገባውን የእንስሳት ማቆያ እና ማከሚያ ማዕከላቱን በመገንባት፤ የጸጥታ መዋቅሩም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ስርዓት በማስያዝ፣ መላው ህብረተሰብ ደግሞ ከጥቆማ ጀምሮ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ተባባሪ በመሆን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012