የሠፈር ወግ ቁዘማ፤
እማማ ብልጫሽ የሠፈራችን ኮከብ እናት ናቸው። ኮከብነታቸው ከሠፈር ኦሪዮንነት አልርቅ ብሎ እንጂ የመጽሐፍ ገፀ ባህርይ ሆነው ቢቀረጹ ኖሮ ልክ እንደ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር መጻሕፍትና ደራሲ በአሉ ግርማ በተውሶ እንደ ወሰዳቸው ገፀ ባህርይ እንደ እትዬ አልታዬ ህያዊ የደራስያን ውላጅ ሆነው ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገሩ ነበር። እትዬ አልታዬና እማማ ብልጫሽ በተለያዩ ዘመናት ቢኖሩም መንፈሳቸውና ሥጋቸው ግን አንድና ተመሳሳይ የሆነ ይመስለኛል። ሁለቱም ጨዋታ አዋቂ ናቸው። ሁለቱም ጥርሰ ወርቅ ናቸው። ሁለቱም የዘመን መታሰቢያ፤ ግን ሟች ሐውልቶች ናቸው። የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ሸክላነት በተገለጸበት ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ተብሎ በፈጣሪ አዋጅ መደምደሙ እንጂ በየማኅበረሰቡ ውስጥ እነዚህን መሰል ሰብዓዊ ቅመሞች ሞትን ድል እየነሱ በብዛት ቢኖሩልን ኖሮ የሕይወታችንን መሪሪ ገፈቶች እየገፈፉልን ለሳቅም ሆነ ለቁምነገር የማይነጠፍ ምንጭ ይሆኑን ነበር።
የአዛውንቷ ብልጫሽ ማኅበራዊ ሂስ፤
እማማ ብልጫሽ ጨዋታ አዋቂ የሚለው መግለጫ ብቻ አይመጥናቸውም። ቁምነገራቸውም ሆነ ቀልዳቸው ከአንጀት ጠብ ይላል። ከልጅነት እስከ ዛሬው የጉልምስና ዕድሜዬ አምርረው ሲቆጡ ያየኋቻው አንድ ዕለት ብቻ ነው። ያዘኑበትን ቀን፣ ያዘኑበትን ሁኔታና አጋጣሚውን ጭምር በሚገባ አስታውሳለሁ። የነገሩ አጀማመር እንዲህ ነበር። የሠፈራችን “አድባር” ጋሽ ጎደፋይ አንድ ዕለት በእናቴ ቤት ቡና እየጠጡ ሳለ ድንገት በንግግራቸው መካከል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ስም በክፉ ሲያነሱ ሰምተዋቸው ያወረዱባቸው የስድብ ዶፍ ምን ጊዜም አይረሳኝም።
ጋሽ ጎደፋይ ገና ንግግራቸውን ሳይጨርሱ፤ እማማ ብልጫሽ እንደ አነር እመር ብለው በመቆም ወገባቸውን እያዋቁ የቃላት ውርጅብኙን አዥጎደጎዱባቸው። “ምናለ ሟቾቹን ነገሥታት አፅማቸው እንኳ በሰላም እንዲያርፍ ብንተዋቸው። ምኒልክ እንዲህ ፈየዱ፣ ኃይለ ሥላሴ ይህንን በደል ፈጸሙ፣ ደርግ እንዲህና እንዲያ አደረገ እየተባለ እስከ መቼ ሙታኖችን ከመቃብር እየጠራን እናዋርዳቸዋለን። ምናለበት አጽማቸው እንኳ አርፎ ቢተኛበት? ላጠፉት ጥፋትስ ዛሬ ጠርተን ከርቼሌ እንወርውራቸው ወይንስ ይሙት በቃ እንፍረድድባቸው? ሞኝ ጎረምሳ የእናቴን ጡት ጠግቤ አልጠባሁም ብሎ ያለቅሳል ይባላል። አሁን ከእኔ የበለጠ ጨካኙ ደርግ ጎድቷችኋል? ሞቶ የተቀበረውን የትናንት ሥርዓት ይህንን በደለኝ፣ ያንን በደለኝ ብል ልትክሱኝ ነው፤ ወይንስ ብልጫሽ እንዲህ ብላለች ለማለት ነው።” የእማማ ብልጫሽ ንግግር መንፈስን ሰርስሮ የሚዘልቅ ቅጣት ነበር።
እኒህን አስተዋይ አዛውንት በዚህ ጽሑፌ ያስታወስኳቸው አለምክንያት አይደለም። ሰሞኑን የጠየቁኝ ጥልቅ ጥያቄ እረፍት ስለነሳኝ፣ የህሊና ሙግትም ስለሆነብኝ ነው። እንደለመድኩት ቤተሰቤን ጥየቃ አልፎ አልፎ ወደ አደኩበት የቀድሞ ሠፈሬ ብቅ ማለቴ አይቀርም። እማማ ብልጫሽን ባላገኘኋቸው ቀን ቅር መሰኘቴንም ሳልገልጽ አላልፍም። ከትልቅ የመጽሐፍ ጥራዝ ይልቅ የሳቅ ጥማቴንና የማኅበረሰባችንን ጉድፎች የማስተውለው በእርሳቸው የአፍታ ፍልስፍናዊ ንግግር ውስጥ ነው። ጋዜጣ ላይ ይጽፋል ማለትን ከሰሙ ቀን ጀምሮ “ይህንን ጉዳታችንን ለመንግሥት አድርስልኝ፣ ያንንም ጉዳይ ጣፍልኝ፣ ደግሞ ምን እንደጣፍህ ሳታነብልኝ ብልጫሽ ምግባሩ ይህንንና ያንን ተናገረች ብልህ ፌርማቶሪ ዓይን ውስጥ እንዳታስገባኝ።” (ፌርማቶሪ በእማማ ብልጫሽ ገለጻ የደህንነት ሰው ወይንም በተለምዶ ጆሮ ጠቢ) የሚባለው ዓይነት ሰው ነው።
ሰሞኑን በአደራ ጭምር የሰጡኝ የቤት ሥራ ለብዙ ቀናት እረፍት ነስቶኝ ሰንብቻለሁ። አደራቸው ከባድ ስለነበርም ልሸከመው አልሸከመው በማለት በስሜት ተንገዳግጄያለሁ። ልጻፈው አልጻፈው እያልኩም ከራሴ ጋር ትግል ገጥሜያለሁ። በመጨረሻም ቃላቸው እንደ መርግ ስለከበደኝ እነሆ የእማማ ብልጫሽን አደራ እንደሚከተለው መጥኜ የዕለቱ ውይይታችን ደርዙን ሳይለቅ እንዲተላለፍ ሞክሬያለሁ። ቃሌን ጠብቄም ይህ ጽሑፍ የታተመበትን ጋዜጣ ወስጄ ልሰጣቸው ወስኛለሁ። የዕለቱ የጭውውታችን ምልልስ ከሞላ ጎደል እንደወረደ ይህንን ይመስላል።
“ልጄ! ይሄ ከአፉ ማር ጠብ የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር ምን እናት ወለደችው? ከንግግሩ ለዛው፣ ከለዛው ወዙ፣ ከወዙ ውበቱ። አይ እናት መውለድስ እንደ እርሱ እናት ነው።” ለምን እንደርሱ አሉ እማማ ብልጫሽ? በንግግራቸው መካከል ጣልቃ ገባሁኝ። “የእናንተ ትምህርት ደግሞ . . . ምን አለ ልብ ተቀልብ ሆነህ ብታስጨርሰኝ። ዓመት አላወራ። አንድ ቃል አንጠልጥላችሁ መሮጥ ባህሪያችሁ ነው።” ይቅርታ እማማ ብልጫሽ ይቀጥሉ። ቁጣቸውን አቀዝቅዤ ወደ ንግግራችው መለስኳቸው።
“አየህ ልጄ (ዛሬም የሚጠሩኝ በልጅነት ዕድሜዬ በሚጠሩኝ ቅጽል ስም ነው) ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ልቡ ገር፣ መንፈሱ ቅን ነው። አንዳንዴ ሲናገር እንባዬ ይመጣል። ምነው እርሱ እንደሚናገረው ብንኖርለት እያልኩ እቆጫለሁ። እርሱ የሚመክረን እንድንስማማ አይደል። ፍቅር ይኑራችሁ አይደል። በጋራ ተረዳድተን እንበልጽግ አይደል። ክፋቱ ምኑ ላይ ሆኖ ነው ከግራ ከቀኝ ግራ የሚያጋቡት። እስቲ ተምረናል የምትሉት እናንተ አስተምሩኝ።”
የእኛ ማስተማር ይቅርና እርስዎ አስተያየትዎን ይጨርሱ። እኔ ከምናገር ይልቅ እርሳቸውን መስማቱ ይበልጥ ትርፍ እንዳለው ስላመንኩ አስተያየት ላለመስጠት ወስኛለሁ። “ይቀጥሉ እማማ ብልጫሽ!” ንግግራቸውን ባላቋረጡ ብዬ ጓጉቻለሁ።
“እውነቱን ልንገራችሁ ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር እግዚሃር የሰጠን አዝኖልን ነው። እኔ በንጉሡም ዘመን፣ በዚያ ጨለማ የደርግ ዘመን፣ ይሄ ይሃዴግ (ኢህአዴግ ማለታቸው ነው) በሚሉት ዘመንም ኖሬያለሁ። አንዳቸውም መሪዎች እየሳቁ ሰው ከሰው ሳይመርጡ ከልባቸው አቅፈው ሲስሙ ያየሁት ዓብይን ነው። ከንግግሩ ተግባሩ። እውነትም እናት እርሱን ብቻ ትውለድ።” እማማ ብልጫሽ ሙገሳው እኮ በዛ! ይህንን ያህል ልክ እንደ መልአክ . . . ሳላውቀው ከአፌ አመለጠኝ።
እማማ ብልጫሽ እንደለመዱት ድንገት እመር ብለው በመነሳት “ምግባሩ ይሙት ተማርን ከምትሉ አንተን ከመሰሉ ሰዎች ጋር ማውራት መደናቆር ነው። መቼ ይሆን ልጄ ደግ ደጉን አውርታችሁ ደግ ደጉን እንድናወራ የምታስተምሩን። “ልጤ ርሶ መቃብሬ ተቆፍሮ፤ ሞት አፋፍ ላይ የደረስኩት አሮጊቷ እኔ በሕይወቴ ብዙ ጉድ አይቻለሁ። ንጉሡ በውነት ብዙ ጥሩ ነገር ሠርተው ነበር። የድሃ ልጆችን አስተምረዋል። ሀገሯን አበልጥገው ነበር። ሞገስ ነበራቸው። የእርሳቸው ችግር ግትር መሆናቸውና መሠሪነት አለማጣታቸው ነው። ግን ቢሆንም ከልቤ እወዳቸዋለሁ። ከእኛ እኩል ቤተ ክርስቲያን ያስቀድሱ፣ ይጦሙና ይጠልዩ ነበር። ለሕዝባቸው ትልቅ ፍቅር ነበራቸው።”
“ያንተ ታላላቆች ግን ሀገር በውርጋጥ ይመራ ይመስል ኡኡ ብለው ንጉሡን በድንጋይ ውርወራና በስድብ አዋርደው ለጨካኙ ደርግ አሳልፈው ሰጧቸው። የደርጉ ጭካኔ ምኑ ይነገራል ልጄ። አንዱን ልጄን ይያፓ ነህ ብለው (ኢህአፓ ማለታቸው ነው) እንደወጣ አስቀሩብኝ። አንዱን ልጄን ለሀገርህ ዝመት ብለው የምስራቅ አሞራ በልቶት አሸዋ ውስጥ ተቀብሮ ቀረ። ልጄን አልቅሼ እንኳ በእናት ወግ አልቀበርኩትም። አንዱ ተረፈልኝ የምለው ልጄ ይኑር ይሙት የት እንዳለ አላውቅም። የተረፉኝ ይሄው እህትህ አምሳሉና ወንድምህ ይላቅ ብቻ ናቸው።” (የልጆቻቸውን ስም ለእኔና ለአብሮ አደግ ጓደኞቼ የሚጠቅሱት ወንድሞቻችሁ እና እህታችሁ እያሉ ነው። ሁሌም ልጆቻቸውን ወንድሞችህና እህቶችህ ሲሉ አንዳች የፍቅርና የርህራሄ ስሜት ሲያናውጠኝ ይሰማኛል።) ስሜታቸውን ለማረጋጋት በማሰብ እሺ እማማ ብልጫሽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይተላለፍ ያሉት መልዕክት ምንድን ነው?
“ጎሽ እንደሱ ንግግርህን ደርዝ አሲዘው። እንደው ልጄ ይሄ ልጅ ስንቱን ጉድ ችሏል (ልጅ የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነው)። እንዲያው ይሄ ቦለቲካ (ፖለቲካ ማለታቸው ነው) የሚሉት ክፉ ነገር ከየት ሀገር ነው የመጣብን?” አይ እማማ ብልጫሽ በማለት እንዴት ወደ ንግግራችን መስመር ላስገባቸው እንደምችል እያሰብኩ እያለ ስሜታቸውን ነቃ አድርገው ያንገሸገሻቸውን ምሬት ይዘረግፉ ጀመር።
“ለመሆኑ ይሄ ቅን መሪያችን በየቀበሌያችን ምን እንደሚሰራ ያውቀው ይሆን። ምናለ አንድ ቀን እዚህ እኛ ቀበሌ መጥቶ የሚሠራውን ግፍ ቢመለከትልን? ይህቺን አንድ ቅጠል የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት ያየሁት አሳር! በዚያ ላይ ማመናጨቃቸው። እዚያ የጎለቷቸው ጨብራራ ጎረምሶች ሰው ጤፉ፣ አባትና እናት የማያከብሩ ምንትስ ናቸው። እርሱ ነጋ ጠባ ለሀገሩ ይደክማል፣ እታች የተጎለቱት ኃላፊ ተብዬና ጨብራራ ጎረምሶች ደግሞ እኛን ያስለቅሳሉ። አደራህን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠንክረህ የምትነግርልኝ፤ ይህንን ቀበሌ የሚባል የሰነፎች ስብስብ አስወግድልን በልልኝ።” ሳቄ መጥቶ ቡፍ ማለት ስጀምር እርሳቸውም ያለወትሯቸው የወርቅ ጥርሳቸውን ብልጭ አድርገው በራሳቸው ንግግር በመገረም ፈገግ በማለት “አጠፋሁ መሰለኝ፤ ሆ! ሆ! የሠፈራችን ፌርማቶሪዎች እንዳይሰሙኝ” ብለው የጨዋታ ርዕሳቸውን በጨዋ ቋንቋ እየቃኙ ብዙ ጉዳዮችን ነካኩልኝ። ከዚህ በኋላ የእኔና የእርሳቸውን ቀጥታ ዲስኩር እዚህ ላይ ገታ አድርጌ የጠቃቀሷቸውን ማኅበራዊ ሂሶች በእኔ ቋንቋ ዋና ዋና ሃሳቦችን እነካካለሁ።
እማማ ብልጫሽ ስለ ቀበሌ መታወቂያ ጉዳይ ያነሱት ምሬት የአብዛኛውን ሕዝብ ብሶት የሚወክል ነው። በተለይም በቅርብ ወራት በምን መስፈርትና የትምህርት ደረጃ እንደተመለመሉ የማይታወቁ ስራ ጠል ወጣቶች በየቀበሌው ሲያዛጉ መዋል የተለመደ ሆኗል። የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት ያለው ሠልፍና ሕዝብን ለማገልገል የተቀመጡት የአንዳንድ ኃላፊዎች ባህርይ በእጅጉ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን የሾሟቸውን ሹማምንትም ግምት ላይ የሚጥል ነው – ይህንን በነጥብ አንድ እንያዝላቸው።
ነጥብ ሁለት። ሁሉም የመንግሥት ሹማምንት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁኑ ማለት ያዳግት ይሆናል። ነገር ግን ዋና ዋናዎቹ ሹማምንት ዝቅታን ቢለምዱ፣ ብሶተኛውን እህ ብለው ቢያዳምጡ፣ ስልጣን ኃላፊ መሆኑን ተረድተው ባለጉዳዮችን በአክብሮት ተቀብለው ችግሩን ቢፈቱ። ስብዕናቸውን እንደ ጥዋ ግምጃ አልብሰው ራሳቸውን ከፍታ ላይ ከመስቀል ዝቅ ብለው ቢያገለግሉና በተገልጋዩ ደስታ ቢረኩ ምን ይቸግራል?
ነጥብ ሦስት። እማማ ብልጫሽ እንደ ዋዛ ጠቀስ አድርገው ያለፉት አንዱ ጉዳይ ቀዳሚ መሪዎችን በመተቸት ከአጽም ጋር እንዳንጣላ የመከሩን ምክር ነው። ጀግና ትውልድ ያለፉ አባቶቹ ስህተት ሰሩ እንኳን ቢባል ነውራቸውንና በደላቸውን በተሻለ ተግባር አርሞ ያስተምራል እንጂ አወቅን እንደሚሉት ምሁራንና ፖለቲከኞች መቃብር ካልቆፈርንና አጽማቸውን አውጥተን ካላዋረድን ብሎ አይፎክርም። ይህንን ሃሳብ አስተዋይዋ እናት ከእኔ በተሻላ ቋንቋ ገልጸውታል።
ነጥብ አራት። የእኔን የእማማ ብልጫሽ የጋራ ሃሳብ በእኔ ገለጻ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕይና ፍልስፍና እታች ድረስ ወርዶ ሥር እየሰደደ ነው ለማለት አልደፍርም። በከፍታ ሥፍራ ላይ ያሉት መሪዎች የሚወስኑትና የሚሰጡት መመሪያ ውጤታማ እንዳይሆን ምድር ላይ የተቀመጠው የታችኛው የቢሮክራሲ አካል መሰናክል እያኖረ ጠቅላዩ ከሕዝብ ጋር እንዲጋጩ እየሰራ ይመስለኛል። እንዲያውም ደፈር ብለን እንነጋገር ከተባለ የላይኛው መዋቅር ሰንሰለት ከታችኛው ቢሮክራሲ ጋር ስለመናበቡ እንጠራጠራለን። ሙሉ ለሙሉ የተበጠሰ የመዋቅር ሰንሰለት ነው ባይባልም ሰልሎ ሊበጠስ የደረሰ መሆኑን ግን በድፍረት መናገር ይቻላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ፣ በየትኛውም መንግሥታዊ ተቋም ቢሆን በሙሉ ኃይል የመንግሥት ሥራ እየተሠራ ነው ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ይመስላል። ተሰራ እየተባለ የሚቀርበው የኃላፊዎች ሪፖርት በሚገባ ቢመረመር ውጤቱ የተገላቢጦሽ እንደሚሆን በተግባር አረጋግጫለሁ። ትልልቆቹ ሹማምንት በከፍታ ሥፍራ ተቀምጠዋል፤ የታችኛው ቢሮክራሲ ደግሞ በእንቅልፍና በምንቸገረኝ ቆፈን ተይዞ የእለት ውሏችንና እንጀራችን የእለት ፖለቲካ ከሆነ ሰነባብቷል። ንግዱ ቀዝቅዟል። የመንግሥት ስራ ተቆራምዷል። ኑሮ ሕዝቡን እየዳሸቀ፣ የፖለቲካው ኢንፍሉዌንዛ ሕዝብን እያጋጨ፣ የመካሪ፣ የተዘካሪና የዘካሪ ሚና ተደበላልቆ ፅንፈኞች ከፍ ብለው ቀኙን የያዙ ይመስላል። ሰላም፣ ፍቅር፣ መከባበር በሀገራችን ታሪክ እንደዘንድሮ ተወርቶላቸው አያውቁም። እንደዘንድሮም ቀለው አያውቁም። ዘመናችንና ዘመነኞቹ እኛ መልካችን ይህንን ይመስላል። “ሁሉም እንደየፊናው ወደ ህሊናው ተመልሶ ራሱን ይይ” የእማማ ብልጫሽና የእኔ ነፃ ሃሳብ ማጠቃለያ ይህ ነው። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com