ከሀገራችን አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። ከእነዚህም ወጣቶች አብዛኛው ወጣት ያለው በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነው። ባለፉት ዓመታት ከወጣቶች አንፃር የተከናወኑት ተግባራት በተለይም ሀገር ተረካቢና መልካም ስብዕናን የተላበሱ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ጥረቶች ተደርገዋል፤ በቂ ናቸው ማለት ግን አይቻልም።
እ.ኤ.አ በ1993 የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ማይክል ሲቨርን ሲናገሩ፤ “ግብረ ገብነትና ስነ- ምግባር ሰላማዊ የሆነ ማህበረሰብ ይኖረን ዘንድ የግድ የሚያስፈልጉን ተገቢና ጠቃሚ የመልካም ተግባር መርሆች ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።” ለዚህም ነው ትምህርት ቤቶች በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ የማይናቅ ድርሻ አላቸው የሚባለው።
በመሆኑም ትምህርት ቤቶች የእውቀት ምንጭ በመሆን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆኑ ታዳጊዎችን ኮትኩተው ለፍሬ የሚያደርሱ፣ በስነ-ምግባር አንጸው መልካም ስብዕና እንዲኖራቸው የሚያደርጉ መስኮች ናቸው።
ትምህርት ቤት ሁለተኛው ዓለም ነው። ትምህርት ቤት ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባርና ስብዕና የመቅረጽና የማነጽ ብሎም እውቀትን የመስጠትና የማስተመር ሚና አላቸው ይላል፤ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህር መስፍን በቀለ። እንደ መስፍን ገለጻ ትውልድን የማዳን ስራ ከምንም ነገር የበለጠ ቀዳሚ ተግባር ነው። ወጣቱ ላይ መስራት ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው። ምክንያቱም ወጣቱ ራሱንም አካባቢውን መቀየር ስለሚችል።
የዚች ሀገር ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው አሁን ላይ በትምህርት ቤት ባለው ወጣት እስከሆነ ድረስ የትምህርት ባለድርሻ አካላትና መንግስት በጋራ ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው የገለጸው መምህር ገብረመድህን ግርማይ፤ እዚህ ላይ ከምንም በላይ የመምህራን ሚና የጎላ ነው ብሏል። መምህራን በባህሪያት ቀረጻ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነም በአጽንኦት ያስረዳል።
የወጣቶችን ስብዕና ለማነፅ ትምህርት ቤቶች የሚኖራቸው ሚና ቀላል ባይባልም ማህበረሰቡ የራሱ ወግ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት ባለቤት በመሆኑ ወጣቶች ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ እነዚህን ዕሴቶች ለወጣቶቹ በትምህርት ቤት በሚገባ እንዲገነዘቡት ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ይገልጻል፣ መምህር ገብረመድህን።
ትምህርት ቤት የሀገር ባላደራም ጭምር ነው የሚለው መምህር መስፍን፤ የወጣቶች ስብዕና ከሚቀረጽባቸው ስፍራዎች ትምህርት ቤት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ያስረዳል። በትምህርት ቤቶች ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገር መልካም ስብዕናን ሊገነባ የሚችል ስራዎችን መስራት፤ በተለይም በስነ-ምግባር ትምህርቶች ላይ እየተሰሩ ያሉ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች መብትና ግዴታ ላይ ብቻ ያተኮሩ ሳይሆኑ ስነ-ምግባርን ማጉላት ላይ ትኩረት ማድረግ ከተቻለ ትልቅ አስተዋጾ ይኖራቸዋል።
ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው የግብረ ገብነት ትምህርት እስከ አሁን ድረስ ለማህበረሰቡ የነበረው ድርሻ ጉልህ ቢሆንም በስነ-ምግበርና ስነ ዜጋ ትምህርት አማካኝነት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግም ያስፈልጋል። ከዛ ባሻገርም የተጓዳኝ ክበባትም ድርሻ እንዳላቸው ነው መምህር መስፍን የገለጸው።
ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ የመልካም ስነ-ምግባር ትምህርት ማግኘት በጣም ወሳኝ ነው። በቀለም ትምህርት በቂ እውቀት አግኝቶ የስነ-ምግባር ትምህርት ባለማግኘቱ ምክንያት በግብረ ገብነት ካልጎለበተው ይልቅ በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀው ወጣት በመልካም ይራመዳል። ስለዚህ ከእውቀት ባሻገር ክህሎትን፣ አመለካከትን አስተሳሰብን ሊቀይር በሚችል መልኩ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጣቸውን በማሻሻል መልካም ስብዕናን የተላበሰ ዜጋን ማፍራት ይጠበቅባቸዋል።
የወጣቶችን ስብዕና በማጎልበት በኩል መንግስት ኃላፊነት መውስድ አለበት የሚለው መምህር መስፍን፤ ህብረተሰቡን የመምራት፣ በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች የመቅረፅ ኃላፊነት ቢኖረውም የመንግስት ኃላፊነት የሚመነጨው ከህዝብ ስለሆነ ህዝብን በማንቀሳቀስ፣ በማደራጀትና በማስተማር፣ ሁሉም የድርሻውን በሚወጣበት አግባብ የመምራት ቀዳሚው ሚናው ይሆናል። ሌሎች ባለድርሻዎች የእምነት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ማህበራት ጥሩ ዜጋን ለማፍራት በቅንጅት መስራት አለባቸው። ህብረተሰቡም በባህሉ ሰውን ይቀርጻል፣ በእምነቱ ሰውን ይቀርጻል፤ በነዚህ አማካኝነት ጥሩ ትውልድ የማነጽና የመቅረጽ ኃላፊነት የህብረተሰቡ ድርሻ ነው። ሁሉም ድርሻ አለው፣ ማህበረሰባዊ ውክልና ያለው መንግስትም ቢሆን ኃላፊነት አለው። የተማሪዎችን ስብዕና በማነጽ ረገድ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን በሚወጡበት አግባብ ወደ መሬት መውረድ መቻል አለበት፣ ጊዜ ይወስዳል፣ ትኩረት ይፈልጋል፣ ልፋትን ይጠይቃል በማለት ሃሳቡን ገልጿል። የሁሉንም ማህበረሰብ ድጋፍ የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም መረዳት ይገባል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ መምህር ገብረመድህን ገለጻ፤ ተማሪዎች ከወላጅ ጋር ያላቸው ትስስር መልካም እንዲሆን፤ ወላጆች ከትምህርት ቤት አመራር ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማጥበቅ በመማር ማስተማር ሂደት፣ በተማሪዎች ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር በትምህርት ቤቶች መስረታዊ የሆኑ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት ይገባል።
የወጣቱ ጉዳይ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ አቅም ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል። በትምህርት ገበታ ላይ በሚገኙት ወጣቶች ላይ መስራት ትውልድንም ሀገርንም መታደግ ስለሆነ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ የማይለውጥ ነገር ስለሌለ የሚስተዋለውን ማህበራዊ ቀውስ ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻልም ጉዳቱን መቀነስ ግን ይቻላል። በሂደትም የምንፈልጋትን ሀገር ዕውን ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ወንድማገኝ አሸብር