የቡና ማሽን የሠራው ታዳጊ

ተማሪ ቴዎድሮስ ታደሰ ይባላል። በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ የእድገት በሥራ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ቡና በቀላሉ በአጭር ጊዜ ማፍላት የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ሰርቷል። የፈጠራ ሥራውም ‹‹አጠቃላይ የቡና ማሽን (ኮፊ ፕሮሰሲንግ ማሽን)›› ይሰኛል። ይህን የፈጠራ ሥራ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው ዘጠነኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሳይንስና ምህንድስና ቀን አውደ ርዕይ ላይ አቅርቧል።

ተማሪ ቴዎድሮስ ገና በልጅነት እድሜው ይህን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ካነሳሱት ምክንያቶች ዋንኛው በየቀኑ ቡና ሲፈላ የሚመለከተው አሰልቺ(ረጅም) ሂደት ነው። ቡና አጥቦ፣ ቆልቶ፣ ፈጭቶ እስከ ማፍላት ድረስ ባሉት ሂደቶችን ማሳጠርና ጊዜ መቆጠብ የሚቻልበትን ሁኔታ አሰላስሏል። በተለይ ኮንዶሚንየም ቤት መብራት ሲጠፋ ከፎቅ ወደ መሬት ወርደው ቡና ለመውቀጥ ብዙዎች ሲሰላቹም ተመልክቷል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ብዙዎች ቡና ማፍላት ሥራ ሆኖባቸው መጠጣት እየፈለጉ ሲተውትም አስተውሏል።

ተማሪ ቴዎድሮስ ይህን ሁሉ አስተውሎ በቸልታ ማለፍ አልፈለገም፤ ይልቁንም ለችግሩ መፍትሔ ያለውን ሲያሰብና ሲያሰላስል ይቆያል። ቆይታው ከንቱ አልሆነም፤ ቡናን እየተዝናኑ በቀላሉ ማፍላት ቢቻል ሰዎች ቡና እያማራቸው አይቀርም በሚል ቡና በቀላሉ ማፍላት የሚችል የቡና ማሽን መሥራት ችሏል።

የቡና ማሽኑ ቡናውን አፍልቶ እስኪጨርስ ቆሞ መጠበቅ አያስፈልግም። ተቆልቶ ለመጠጣት እስከሚደርስ ድረስ ያሉትን ሂደቶች በቅደም ተከተል ካከናወነ በኋላ መጨረሱን በስልክ ደውሎ ማሳወቅ የሚችልም ነው። ተማሪ ቴዎድሮስ አንድ ሊትር ቡና እንዲያፈላ ታሰቦ የተሠራ መሆኑን ገልጾ ‹‹ቡና አጥቦ እስከ ማፍላት ድረስ ያለውን ሂደት በሙሉ በ15 ደቂቃ ውስጥ አከናውኖ ይጨርሳል›› ይላል።

ተማሪ ቴዎድሮስ እንዳብራረው፤ ማሽኑ በሀገር ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ሌሎች የቡና ማሽኖች ለየት ከሚያደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋንኛው በጠባብ ቦታ ላይ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን የቡና አፈላል ሂደት አንድ ላይ አጠቃሎ መጨረሱ ነው። በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑ ሌላኛው ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ማሽኑ ቡና እንዲያፈላ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሳይፈጽም ቢቀር እንኳ በሞባይል ስልክ ላይ ደውሎ በማሳወቅ ማስታወስ መቻሉ ከሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ለየት እንዲል ያደርገዋል።

ማሽኑ ቡናውን ለማፍላት ቡና በቤት ውስጥ ሲፈላ የሚከተለውን ሂደት መሠረት ያደረገ ቅደም ተከተል አለው። ማሽኑ አንድ ሊትር ቡና ለማፍላት ታሰቦ የተሠራ ሲሆን በቅደም ተከተሉ መሠረት በቅድሚያ አንድ ሊትር ቡና ለማፍላት የሚያስፈልገው 250 ግራም ቡና ወደ ማሽኑ እንዲገባ ይደረጋል። ይህ አካሄድ ቡናው እንዳይወፍር ወይም እንዳይቀጥን ያደርገዋል። ከዚህ በበለጠ ወይም ባነሰ መጠን የምንጠቀም ከሆነ ግን ቡናው ሊወፍር አልያም ሊቀጥን ይችላል።

የመጀመሪያ ሂደት ላይ ቡናው ወደ ማሽኑ ከገባ በኋላ ማሽኑ ቡናውን አጥቦ እጣቢውን ወደ ተዘጋጀለት ቦታ በማስገባት ያስወግዳል። በመቀጠልም ቡናውን ወደ የሚቆላበት ቦታ እንዲሄድ ይደረጋል። ቡናው በሚገባ ከተቆላ በኋላ ወደ መፍጫው ከመግባቱ በፊት እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል፤ ከዚያም ወደሚፈጭበት ቦታ ይገባል። ከተፈጨ በኋላም ወደሚፈላበት ቦታ ገብቶ እንዲፈላ ያደርጋል። ከዚያም ቡናውን በአንድ በኩል፤ አተላውን በሌላ በኩል እንዲወጣ ያደርጋል ሲል ተማሪ ቴዎድሮስ ያብራራል።

ማሽኑ ቡናውን አፍልቶ እስኪጨርስ መጠበቅ የሚፈልግ ሰው አጠገቡ ሆኖ መጠበቅ ይችላል፤ ለመጠበቅ የማይችልና ቡናውን እስኪፈላ ድረስ ሌሎች ሥራዎች መሥራት የሚፈልግ ደግሞ ወደ ሥራው መሄድ እንደሚችልም ያስረዳል። ማሽኑ ልክ ቡናውን ስለመፍላቱ እንዲያሳውቅ በተሰጠው ስልክ መሠረት ደውሎ እንደሚጠቁም አመልክቷል።

ማሽኑ ቡናውን አፍልቶ ሲጨርስና ቡና ጠጪው ወደ ማሽኑ ሲጠጋ ማሽኑ የስኒ ማስቀመጫውን ከማሽኑ ወጥቶ ስኒ በማስቀመጥ ለመቅዳት ዝግጁ እንደሆን ይገልጻል። ማሽኑ ቡናውን አፍልቶ ከጨረሰ በኋላ የሰጠነውን ትዕዛዝ ረስተን ሄደን ከሆነም ስልካችን ላይ ደውሎ ያስታወሰናል። ከአካባቢው ርቀን ሄደንም ከሆነ በአካባቢው ያለው ሰው ቡናውን ሳይቀዘቅዝ እንዲጠቀምበት የሚያስችል ሁኔታ እንዳለውም ይናገራል።

እንደ እርሱ ማብራሪያ፤ ማሽኑን ተንቀሳቃሽና ተሽከርካሪ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ሊጠቀመው የሚችልና ጊዜ የሚቆጥብ ነው፤ በተለይ በየቤታችን እንደተለመደው ዓይነት የቡና አፈላል ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈላ የሚፈልጉ፣ ነገር ግን የማይችሉ ሰዎች ካሉ ማሽኑን ተጠቅመው ቡና መጠጣት ይችላሉ።

ብዙ ሰዎች ጊዜ ስለሌላቸው ቡና መጠጣት እያማራቸው ሳይጠጡ የሚወሉባቸው አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ይናገራል። በተለይ አቅመ ደካሞች ቡና ፊታቸው ታጥቦና ተቆልቶ መጠጣት ቢፈልጉም፣ ይህንን ለማድረግ አቅም ስለሌላቸው ሲቸገሩ ይታያል ሲል ጠቅሶ፣ ይህ ማሽን ግን ይህን ሁሉ ችግር እንደሚቀርፍ ያመለክታል።

ማሽኑ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ሲሆን፤ ከወዳደቁና በቀላሉ አካባቢው ላይ ከሚገኙ ቁሳቁስ የተሰራ ነው። ለአብነት ማንቆርቆሪያ እንደ ቡና መቁያ፣ ሽንኩርት መፍጫን እንደ ቡና ማጠቢያ አድርጎ ተጠቅሞበታል፣ የቡና ማሽን ዲናሞን በመቀየር፣ የቡና ማቀዝቀዣ ማሽን እና የኤሌክትሪክ ማብሪያና ማጥፊያዎች መጠቀሙን ይናገራል።

ማሽኑ በአንድ ጊዜ የሚያፈላው አንድ ሊትር ቡና 15 ስኒ ያህል ቡና ሊወጣው እንደሚችል አስታውቆ፣ ‹‹ይህ ማለት ደግሞ አስራ አምስት ሰዎችን በአንድ ጊዜ ቡና ማጠጣት ይችላል ማለት ነው›› ሲልም ያብራራል። በ15 ደቂቃ ውስጥ አስራ አምስት ሰዎች ቡና ማጠጣት እንደሚችል ተናግሮ፣ ማሽኑ በተለይ ቡና በማፍላት ሥራ ለተሰማሩ ሰዎች በጣም አዋጭ እንደሆነ ይጠቁማል። ለሆቴሎች፣ ለካፌዎችና ለመሳሳሉትም ቡናን በቀላሉና ፈጣን በሆነ ዘዴ ለማፍላት ያስችላል ሲል ያብራራል።

ይህንን የቡና ማሽን ለመሥራት ሲነሳ በሀገር ውስጥ የተሠሩ የተለያዩ የቡና ማሽኖች መመልከቱን የሚናገረው ተማሪ ቴዎድሮስ፤ ከተመለከታቸው ማሽኖች አብዛኛዎቹ የተቆላ ቡና ጨምቀው የሚያፈሉ መሆናቸውን ይገልፃል። አዲሱ ማሽን ግን በቤታችን ውስጥ እንደሚፈላው ቡና ዓይነት ሂደት ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንደሚያፈላም ይገልጻል።

ተማሪ ቴዎድሮስ እነዚህን የቡና ማሽኖች ካየ በኋላ የተለያዩ ሂደቶችን በአንድ ላይ አጠቃሎ ቡና ማፍላት የሚያስችል ማሽን መፍጠር እችላለሁ ብሎ መነሳቱንም ይገልጻል። ቡና ቤት ውስጥ የሚፈላበትን ባሕላዊ የአፈላል ሂደት የተከተለ የአፈላል ሥርዓት ተከትሎ የሚያፈላ የቡና ማሽን መሥራት እንደሚችል አምኖ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደቻለም ያመለክታል። ማሽኑ ቡና የማፍላት ቅደም ተከተሉን ጠብቆ የሚያፈላ ስለመሆኑም በመኖሪያ ቤትም በትምህርት ቤትም ተፈትሾ መረጋገጡን ይናገራል።

‹‹ለዚህ ማሽን ብዙ አውጥቼበታለሁ ብዬ አላስብም፤ ያወጣኋቸው ነገሮች በጣም ጥቂት ናቸው፤ ለማድመቂያ ቀለሞች፣ ለኤሌክትሪክ ገመዶች ፣ ለቻርጅ ቦርዶች እና ለብሬከሮች ብቻ ጥቂት ወጪ አውጥቼለሁ እንጂ ሌሎቹ ከቤት ውስጥ ያገኘኋቸው እቃዎች ናቸው›› የሚለው ተማሪ ቴዎድሮስ፤ ማሽኑ እንደሚሰራበት ቁስና እንደሚፈለገው መጠን ዋጋውን መተመን እንደሚቻልም አስታውቋል። ብዙ ወጪ የማያስወጣ መሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ እንደሚቻል ያስረዳል።

እንደ ተማሪ ቴዎድሮስ ማብራሪያ፤ አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ ሆኖ ዋጋ ለማውጣት ይከብዳል። ምክንያቱም ከዚህ በተሻለ መልኩ መሥራት ይቻላል። ይህ ማሽን ለ15 ሰዎችን ቡና እንዲያጠጣ ታስቦ የተሠራ ነው። ከዚህ በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚፈለግ ከሆነ በዚያ ልክ ለመሥራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዋጋ ማውጣት ይቻላል።

ይህን በማሽን ላይ የሚጨመርበት ካለ ጨምሮ፣ የሚቀነሰውም ካለ ቀንሶ በተሻለ መልኩ ለመሥራት ሃሳብ አለው። ማሽኑ በሀገር ውስጥ በስፋት ተመርቶ ሁሉም ሰው ሊጠቀምበት እንዲችል ለማድረግ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ይናገራል። በተለይ በቡና መፍላት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሰዎች ድካማቸውን በማቅለልና ጊዜያቸውን በመቆጠብ በቀላሉ ቡና ማፍላት የሚችሉበት መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህ የፈጠራ ሥራ በሚሰራበት ወቅት አንዳንድ ቁሳቁስን ለማሟላት ብዙ ጥረት ማድረጉን አስታውሶ፣ ትምህርት ቤቱ አንዳንድ ወጪዎችን በመሸፈን ድጋፍ እንዳደረገለትም ነው ያመለከተው።

የፈጠራ ሥራን ከልጅነቱ አንስቶ እንደጀመረው አስታውሶ፤ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች መሥራቱንም ይናገራል። የፈጠራ ሥራዎቹን ለውድድር አቅርቦ ማበረታቻዎች እንዳገኘባቸውም ይገልጻል። ይህም በፈጠራው እንዲገፋ ብርታትና ጉልበት እንደሆነው ያስረዳል። የቡና ማሽን ሥራው ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ደረጃ የቀረበ መሆኑ ይጠቁማል።

በፈጠራ ሥራ የመቀጠል አላማ ያነገበው ተማሪ ቴዎድሮስ፤ የወደፊት እቅዱም ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች በመሥራት የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ መቻል መሆኑን ይገልጻል። ይህንን ማሽን ለሁሉም ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ብዙ እቅድ እንዳለው አመልክቶ፣ ‹‹ይህ ማሽን ትልቁ ሥራዬ ነው። እድሉን ካገኘሁ ገና ብዙ በውስጤ ያሰበኳቸውና ብሰራቸው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፈጠራ ሥራዎች አሉኝ። እነዚህን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥረት አደርጋለሁ›› ይላል።

‹‹ማሽኑን በትምህርት ቤት ያዩ ሁሉ በእጅጉ አድንቀውታል፤ ተገርመውበታልም፤ ይህም ይበልጥ እንድበረታታ ትልቅ ሞራል ሆኖኛል›› የሚለው ተማሪ ቴዎድሮስ፣ በቀጣይም ለአሰባቸው ሥራዎች መሠረት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆነው ይገልጻል። የፈጠራ ሥራን አሃዱ ብሎ ሲጀምር አካባቢ ተስፋ ያስቆረጡትና ወደኋላ እንዲመለስ ያደረጉት ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር አስታውሶ፣ የጀመራቸውን ሥራዎች ባሰበው መልኩ ማስኬድ ሲያዳግተው ተስፋ እየቆረጠ መልሶ እየሞከረ እንደሚቀጥል ይናገራል።

እንደ እርሱ ወደ ፈጠራው ዓለም ለመግባት የሚፈልጉ እምቅ ችሎታ ያላቸው በርካታ ልጆች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሶ፣ እውቀታቸውን ማውጣት እንዳለባቸውም ያስገነዝባል። ይህንን እንዲያደርጉ የሚደግፋቸው ባይኖር እንኳ ሠርተው ማሳየት እንዳለባቸው ያመለክታል። ወደኋላ ሳይመለሱ ደጋግመው በመሞከር የተሻለ እንደሚሰሩ ጠቁሞ፤ ይህ ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት እየፈጠረ ይመጣል ብሏል። ሥራቸው ዛሬ ላይ ተቀባይነት የሌለው ቢመስላቸው ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ ሳይመለሱ እንዲሰሩ አመልክቶ፣ ‹‹ሥራቸው የሚፈለግበት የራሱ ጊዜና ወቅት እንዳለው በማሰብ በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል›› ሲልም ይመክራል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ህዳር 17/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You