የሰው ልጆች እና የአገራትን የእድገት ደረጃ ከሚያመላክቱ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ኢኮኖሚ ነው፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን የኢኮኖሚ አቅም ለሁለንተናዊ ብልጽግና የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው፡፡ የአንድን አገር ሉኣላዊነት ለማረጋገጥ ጭምር የኢኮኖሚ አቅም ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዓለም ህዝቦች መካከል የሃብታሞች ቁጥር ከሰባት በመቶ የዘለለ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት አብዛኞቹ የህብረሰተብ ክፍሎች አንድም መካከለኛ ገቢ አልያም በድህነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በድህነት ከሚታወቁ የዓለም አገራት ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ናቸው፡፡ ህዝቦቻቸውም በድህነትና ከድህነት ወለል በታች በመሆን የድህነት ተምሳሌት እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
ኢትዮጵያም በዓለም ላይ ስማቸው በድህነት ከሚነሱ አገራት አንዷ ናት፡፡ በተለይ ካለፈው ግማሽ ምዕተ አመት ወዲህ ባጋጠሟት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተነሳ ለድርቅና ለረሃብ በተጋለጠችባቸው ወቅቶች በኦክስፎርድ መዝገብ ቃላት የረሃብ ምሳሌ ተደርጋ እስከመገለፅም ደርሳ ነበር፡፡
በአንጻሩ በዓለም ላይ ምቹ የአየር ፀባይ፤ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶችና ለእድገት ወሳኝ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት በመሆን ስማቸው ከሚነሳ አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህ የድህነትና የበለፀገ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት ተቃርኖ ደግሞ በዋናነት በየዘመኑ ከነበሩ ገዢዎቿና የውጭ ጠላቶች ጋር የተገናኘ ሲሆን፤ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችም ትልቁ መንስኤ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
እንደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም መረጃ በየዓመቱ በጉቦና ስርቆት ብቻ የሚፈፀም ሙስና ከ3 ነጥብ 6 ትሪሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያደርሳል። ከዚህ ውስጥ ከአፍሪካ ከ50 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በህገ ወጥ መንገድ ሽሽት የሚፈፀም ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከግዢ እና ሌሎች አገልግሎት ዘርፎች ጋር ተያይዞ ከ35 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሙስና የሚባክን መሆኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው 16ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ላይ ተገልጿል።
ይህ በሙስና የባከነ ሀብት ለመሰረተ ልማት አውታሮች፣ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለጤና ተቋማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት፣ በጥቅሉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ቢውል 43 በመቶ የሚሆኑ የዓለም ደሃ ህዝቦች ህይወት ይቀየር እንደነበር ጥናቶች ያመላክታሉ።
በአገራችን ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ለአብነትም እኤአ በ2007 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከል እና መዋጋት እና የተባበሩት መንግስታት የጸረ ሙስና ስምምነትን አጽድቋል፡፡ ቀጥሎም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፌደራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 235/1993 እና የተሻሻለውን የፌደራል የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/1997 አጽድቆ ስራ ላይ አውሏል፡፡ ክልሎችም የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖቻቸውን አቋቁመዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት የተቋቋሙት የስነምግባርና የጸረ ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት የነቃና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ህብረተሰብ እንዲፈጠር ለመስራት፣ የሙስና ወንጀልን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንዲሁም የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሰራርን በማጋለጥ፣ በመመርመርና በመክሰስ በአገሪቱ ውስጥ ሃቀኛ የህዝብ አገልግሎት እንዲሰፍን ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን የተቋሙም ሆነ የሌሎች ህጎች መኖር ሙስናን መከላከል አላስቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ ችግሩ በየጊዜው እየተባባሰ ሄዶ አገሪቷን ጭምር ለከፍተኛ የውጭ እዳ፤ ህዝቦቿንም ለከፋ ድህነትና ኋላቀርነት እስከመዳረግ አድርሷል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ይፋ የተደረገውና በሜቴክ እና በስኳር ፕሮጀክቶች ላይ የተፈፀመው ብክነት ማሳያ ነው፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በየጉራንጉሩ የሚፈፀሙት ትናንሽ የሙስና ተግባራትም ህብረተሰቡን በማማረር የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከሁለት አመት በፊት በመላ አገሪቷ ለተከሰተው የህዝብ አመፅና በኋላም ለመጣው ለውጥ መንስኤ የነበረው ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ያስከተሉት የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበር ይታወቃል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስና የህዝቡን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በተለይ የአገር ኢኮኖሚን የሚያናጉ ትላልቅ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የተጠያቂነት አሰራሮችን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን አሁን የተጀመሩት አለምአቀፍ ስምምነቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን በየአካባቢው ህብረተሰቡን ለምሬትና ለእንግልት የሚዳርጉ ትናንሽ የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱበትን መንገድ ማመቻቸትና በዚህ ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012