“ጥላሁን ለምን ለምን ሞተ…ለምን?”
በ1950ዎቹ መጨረሻ የተቀጣጠለውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በመምራት ግንባር ቀደም የነበረው ጥላሁን ግዛው በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው ከ50 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታህሳስ 1962 ዓ.ም ነበር።
ያ ትውልድ ተቋም ታኅሳስ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ዝክረ ጥላሁን ግዛው በሚል ርዕስ ያሳተመው ጽሑፍ ጥላሁን ግዛው ከአባቱ ከንቡረዕድ ግዛው አበራና ከእናቱ ከወይዘሮ ደሴ አደዬ ረታ በ1933 ዓ.ም በራያና ቆቦ አጠርሻ በመባል በምትታወቅ የገጠር መንደር እንደተወለደ ይገልጻል።ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ዕድገቱን በአደረገባት በገጠሯ አጠርሻ የቤተክህነት ትምህርቱን እስከ ዳዊት ተከታትሏል።ቀጥሎም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ወልድያ ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት ጀምሯል።
ጥላሁን በአሥራዎቹ መጀመሪያ ዕድሜው ከአባቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንጦጦ ሚሽን አዳሪ ትምህርት ቤት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል።በማስከተልም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሎ በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ በ1959 ዓ.ም የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቀለ።
በኢትዮጵያ የተማሪዎች ትግል ከ1956 ዓ.ም ቀደም ብሎ የተፈጠረው የግራ ኃይሎች ስብስብ ተጠናክሮ “አዞዎች” የተሰኘ ቡድንን በመፍጠር 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል መርህ “መሬት ላራሹ” መሆኑ ይፋ ተደርጎ መጋቢት 4 ቀን 1957 ዓ.ም “መሬት ላራሹን የምትሹ ፤ ተዋጉለት አትሽሹ” እያሉ ተማሪዎች በአደባባይ ሰልፍ በወጡበት ወቅት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ጥላሁን በሰልፉ ተሳትፏል።
“አዞዎቹ” (ክሮኮዳይልስ) ተብለው የሚታወቁት ተማሪዎች ቀደም ሲል በይፋ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ማህበር አመራሮች ሳይሆኑ እንደ አዞ ድምጻቸውን አጥፍተው ውስጥ ውስጡን ተማሪውን ሲያንቀሳቅሱ የነበሩና ቀስ በቀስ ወደ አመራርነት የመጡ ናቸው።ዋነኞቹ የአዞዎቹ አመራሮች “ዘጠኙ ቅዱሳን” ተብለው የሚታወቁና በኋላ አብዛኞቹ የኢህአፓ መሪዎች የሆኑ ናቸው።ጥላሁን ግዛው የ«አዞዎቹ» ዓላማ አራማጅና በኋላም ለመሪነት ለመታጨት የበቃ ወጣት ነበር።በ1961 ዓ.ም. በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመኮንን ቢሻው ቢሸነፍም በቀጣዩ ዓመት ኅዳር 1962 ዓ.ም. በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ብልጫ አሸንፏል።ጥላሁን የፕሬዚዳንትነት ዘመኑ ቀዳሚ ሥራው የተማሪውን የመናገር ፣ የመጻፍና የመደራጀት ነጻነት ይበልጥ ማጠናከር ነበር።ለሁለት ወር ብቻ በፕሬዝዳንትነት የቆየው ጥላሁን የተለያዩ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ በማበረታታት የሚታወቅ ታጋይ ነበር።
ጥላሁን ግዛው ከባላባት ቤተሰብ ቢወለድም ዕድገቱ ከገበሬ ልጆች ጋር ነበር።በገጠር ኑሮው በአለባበሱም ሆነ በባህሪው ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ለመመሳሰል ይጥር ነበር።በተማሪነት ዘመኑም ጊዜውን የሚያሳልፈው ከመሰል ተማሪ ጓደኞቹ ጋር እንጂ ከባለስልጣንና ከከበርቴ ልጆች ጋር አልነበረም።እህቱ ልዕልት ሣራ ግዛው በ1957 ዓ.ም በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈው የአጼ ሀይለስላሴ ልጅ የልዑል መኮንን ባለቤት ነበሩ።
ታህሳስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም. ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ ከታናሽ ወንድሙ መኮንን ሲሳይ ጋር በመሆን ከስድስት ኪሎ በስተጀርባ አፍንጮ በር በሚባለው አካባቢ ፍቅረኛውን ዮዲት ታዬን ለመሸኘት ወጥተው ታርጋ በሌለው መኪና በተተኮሰ ጥይት ተገደለ።
ሱልጣን አባዋሪ የተባሉ ሰው “የተማሪው ትግልና የአብዮቱ ደመና” በሚል ርዕስ አንታዛ መጽሄት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የጠቀሷቸው ሌተናል ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ስለአሟሟቱ ሲገለጹ “ስለ ጥላሁን ግድያ የተለያዩ ነገሮች ቢወሩም … ሐቁ ግን ግድያው የተፈፀመው በንጉሠ-ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ፣ የንጉሱ የቅርብ አጃቢ ወይም አንጋች ክፍል ምክትል አዛዥ በነበሩት በኮሎኔል ጣሰው ሞጃ ትዕዛዝና ከብሔራዊ ጦር ተዛውረው እኔው ራሴ ደብረ-ብርሃን ካሰለጠንኳቸው በኋላ የአንጋች ክፍል ባልደረባ በሆኑት ሁለት ወታደሮች ነበር።ለዚሁ ድርጊታቸውም ሁለቱም የምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ የተሰጣቸው መሆኑን የድርጊቱ ፈፃሚዎች ነግረውኛል” ብለዋል።
በግድያው የተቆጡ ተማሪዎች የጥላሁንን አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (ስድስት ኪሎ) ቅጥር ግቢ በመውሰድ ከአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመጡ ተማሪዎች ጋር የሃዘኑ ተካፋይ ሆኑ።የጥላሁን ታሪክና የትግል ዓላማ በግጥምና በስድ ንባብ እየተሰማ የሃዘን መግለጫው ዝግጅት ተካሄደ።በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄን ያሳልጥ በነበረው ታገል መጽሔት ላይ ከወጡት ግጥሞች መካከል ተከታዮቹ ይገኙበታል።
እስከዛሬ ድረስ ልቤ ሲከዳኝ
ተምሮ ጥላሁን ሞት አስተማረኝ
እንግዲህ አልፈራም አልጓጓም ለነፍሴ
ቦታ አግኝቻለሁኝ ጥላ ለፈረሴ
አንተ ጋር ገስግሷል ጥላሁን መንፈሴ።
እሪ በያ አገሬ ዛሬ ገና አልቅሽ
በጣም ስታምኚበት ጥላሁን ከዳሽ።
ቀጥሎም በተማሪዎች ሰልፍ ታጅቦ በክብርና በጀግንነት በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቀብሩ ሥነ ስርዓት ይፈጸም ዘንድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያደረጉት ጥረት የንጉሡ ጸጥታ ኃይሎች የወሰዱት ጭካኔ የተሞላ እርምጃ የተጨማሪ ተማሪዎችን ሕይወት ቀጥፎ አስከሬኑን ከተማሪዎቹ ተወሰደ።
የጥላሁን ግዛው አስከሬን ከተማሪዎቹ በኃይል እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ታህሳስ 22 ቀን 1962 ዓ.ም መላው ዘመድ አዝማድ በተገኙበት በአካባቢው ተማሪዎች ሰልፍ አጃቢነት በወቅቱ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በማይጨው ሕዝባ ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄም የጥላሁንን መገደል አስመልክቶ ተከታዩን መግለጫ አወጣ።
“…. የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ንቅናቄና ነጻነት ወዳጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥላሁን ግዛውንና ሞቱን አተኩሮ ይመለከተዋል።ነጻነት ያለትግል አይገኝም።አይኑን ከፍቶ ፤ ጆሮውን አቅንቶ ፤ ልቡን አደንድኖ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ንቅናቄ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ አሰቃቂ አሟሟት ሳይበገር በደም ፍላት ይጠብቃል።ትግላችን ይጠነክራል እንጂ አይላላም።
“… ታኅሳስ 20 ቀን 1962 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ፣ የሁለተኛና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችና የሟቹ የጥላሁን ግዛው ቤተሰቦች ተገኝተው በግፍ የተገደለውን መሪያቸውንና ልጃቸውን ለመቅበር በመዘጋጀት ላይ እንደነበሩ ከፖሊስና ከክቡር ዘበኛ በተመለመሉ ወታደሮች አማካኝነት የገደሉትን ሬሳ መማረክ ስለፈለጉ ለመቅበር ተሰብስበው በነበሩት የሟች ቤተ ዘመዶችና ተማሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው ከ23 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ገድለው ከ157 በማያንሱ ተማሪዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ አደረሱ።ባዶ እጁን ተሰልፎ በነበረ ተማሪ ላይ ተኩስ ከፍቶ ይህን ያህል እልቂት ማድረስ ፋሽስት ጣሊያን የካቲት 12 ቀን 1928 ዓ.ም በኢትዮጵያን ላይ ካደረሰው ፍጅት የባሰ እንጂ ያነሰ አይደለም።… ኢትዮጵያውያን ከወራሪው ከጣሊያን አፍ ባወጧት አገራቸው ላይ በአሜሪካውያን ኢምፔሪያሊስቶችና በጥቂት ኢትዮጵያውያን በዝባዥ ቡችሎቻቸው በተቀጠሩ ወታደሮች የልጆቻቸው ደም ያለአግባብ ፈሰሰ።መንግስት ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውንና ለወደፊትም ለመፈጸም ያቀዳቸውን አሰቃቂ ድርጊቶች በመቃወም የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናቀርባልን።
1ኛ. በበዝባዥ መደብ ተልከው ጥላሁን ግዛውን የገደሉት ሰዎች ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ።በዝባዥ መደብ የጥላሁንን መገደል ከራሱ ለማውረድ ሲል ቀደም ብሎ ሊያጠፋቸው ያሰባቸውን አንዳንድ ተማሪዎችን በዚሁ ጉዳዩ መወንጀሉ ተቀባይነት የለውም ፤
2ኛ. በታኅሳስ 20 እና በተከታዮቹም ቀናት በአዲስ አበባና በየጠቅላይ ግዛቶቹ በሚገኙ ተማሪዎች ላይ ለተደረገው እልቂት በኃላፊነት የሚጠየቁት የፖሊስና የክቡር ዘበኛ አዛዦች ፍርድ ቤት ቀርበው አስፈላጊ ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ፤
3ኛ. ለሞቱት ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ተገቢው የነፍስ ዋጋ እንዲከፈላቸውና ለደረሰባቸውም ታላቅ በደል መንግስት በሬዲዮና በጋዜጣ ይቅርታ እንዲጠይቃቸው ፤
4ኛ. ሀ. በፖሊስ ሰራዊት ሆስፒታል ያሉት የቆሰሉ ወንድሞቻችን በዚህ ሆስፒታል የሚደረግባቸው በደል ከፍ ያለ ስለሆነ ወደ ሌላ ሆስፒታሎች እንዲዘዋወሩ ፤
ለ. ከምኒልክና ከሌሎችም ሆስፒታሎች በደንብ ሳይድኑ የተባረሩት ቁስለኞች እንደገና ተመልሰው አስፈላጊው ህክምና እንዲደረግላቸው ፤
5ኛ. በየሰበብ አስባቡ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁት ተማሪዎች ያለአንዳች ማመንታት እንዲለቀቁ ፤
6ኛ. በየቦታው የሚታደኑ ተማሪዎች ብሔራዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ፤
7ኛ. የዩኒቨርሲቲ መተዳደሪያ ሕግ እንዲሻሻልና እንዲከበር፤ መንግስት በመሰለው ጊዜ ሁሉ ወታደር ወደ ዩኒቨርሲቲ ግቢ መላኩን እንዲያቆም፤
“እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ጥያቄዎ ቻችን ፍጻሜ ካላገኙ ፍንክች የማንል መሆናችንን መገንዘብና ማወቅ የገዢው ክፍል ፈንታ ነው።የንጹህ ኢትዮጵያውያን ደም ፈሶ ከንቱ አይቀርም።…እኛ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፣ የዩኒቨርሲቲ የብሔራዊ አገልግሎት ተማሪዎች ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከላይ የተመለከቱት ጥያቄዎች እስከ 15 ቀን ድረስ ባይፈጸሙ ትምህርታችንንና ስራችንን የማንቀጥል መሆናችን እንዲታወቅልን።”
ጥላሁን ግዛው በማይጨው ከተማ አንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና አንድ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስሙ ተሰይመውለታል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 15/2012
የትናየት ፈሩ