እፍኝ ማስታወሻ ስለ ኤክሳይዝ ታክስ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የኤክሳይዝ ታክስ ከተጨማሪ እሴትና ከተርን ኦቨር ታክስ ጎራ የሚሰለፍ የሽያጭ ታክስ ዓይነት ነው፡፡ ከሁለቱ ታክሶች የሚለየው በሁሉም የሚሸጡ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚጣል ሳይሆን በተመረጡት ላይ ብቻ የሚሰበሰብ በመሆኑ ነው፡፡ ታክሱ የሚጣለው ደግሞ ዕቃዎቹ ከውጭ ወደ አገር ቤት ሲገቡ ወይም በአገር ውስጥ ሲመረቱ ነው፡፡
የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣለው በዋናነት በቅንጦት ዕቃዎች ላይ ነው፡፡ እናም ኪሳቸው ዳጎስ ካለ ሰዎች ላይ ገንዘብ በመሰብሰብ ለድሆች የሚቀርቡ አገልግሎቶችን የመደጎሚያ መንገድ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል አንዳንዶች ኤክሳይዝ ታክስ ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “በቅንጦት ዕቃዎች ላይ የሚጣል ታክስ” የሚል የአማርኛ አቻ ሲሰጡት የሚደመጡት፤ ስህተት ቢሆንም ቅሉ፡፡
መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይም ይጣላል ኤክሳይዝ፡፡ የሕብረተሰቡን ጤና በሚጎዱና የማህበራዊ ችግር በሚያስከትሉ እንዲሁም በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ዕቃዎች ላይም የሚጣል ነው። የሚሰበሰበው የታክስ ገንዘብም ለህብረተሰብ ጤናና ለአካባቢ እንክብካቤ ሥራዎች መደጎሚያ ይውላል፡፡
የዚህ ታክስ ዋና ዓላማው ከፍተኛ የታክስ ጫና በመጣል የእነዚህን ዕቃዎች አጠቃቀም መቀነስ ነው፡፡ መቼም ግብር መሰብሰብ ጥንትም ቢሆን የመንግስታት ሁነኛ ሥልጣን ስለሆነ በየዘመኑ የተለያዩ የታክስ ዓይነቶችን ወደታክስ ሥርዓታቸው በማካተት ተጨማሪ ገቢ የመሰብሰቢያ መንገድን ይዘረጋሉ፡፡
ኤክሳይዝም እንዲሁ በአገራችን ከኢጣሊያ ወረራ በፊት ከ1924 ዓ.ም. ጀምሮ በአልኮል መጠጦች፣ በዕጣን፣ በሲጋራ፣ በምንጣፍና በአልባሳት ላይ ይጣል እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ መውጣት ተከትሎ የታክስ ሥርዓቱን በመቀላቀል ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የመሰብሰቢያ መሳሪያው ሆኖለታል፡፡
የአዲሱ አዋጅ መሰረቶች
በሥራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/1995 ወትሮም ቢሆን የተለያዩ ሳንካዎች ነበሩበት፡፡ በተለይም የዘመን መለዋወጥንና የቴክኖሎጂ መሻሻልን በሚዋጅ መልኩ የቅንጦት ዕቃዎች እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤና የሚጎዱና የማህበራዊ ችግርን የሚያስከትሉ እቃዎችን በዝርዝርና አሟጦ አላካተተም። መሰረታዊ በመሆናቸው የገበያ ተፈላጊነታቸው የማይቀንሱ እቃዎችንም እንዲሁ፡፡
ከሁሉም በላይ አዋጁ የኤክሳይዝ ታክስ የማይጣልባቸውን ዕቃዎች ባለማካተቱ በአፈጻጸም ረገድ እንቅፋቶች ሲገጥሙት ቆይተዋል፡፡ ይልቁንም ኤክሳይዝ የሚጣለው በዕቃዎች ላይ ብቻ በሚመስል ሥሁት መሰረተ-ሀሳብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ታክሱ ሊጣልባቸው የሚገቡ አገልግሎቶችን ከታክስ ሥርዓቱ ውጪ አድርጓቸው ኖሯል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን የኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላበትን ዋጋ ሲያስቀምጥ በአገር ውስጥ ለተመረቱ ዕቃዎች የማምረቻ ወጪን (Cost of Productionን) ታክስ የሚሰላበት ዋጋ አድርጎ በመነሳቱ ምክንያት ግብር ከፋዮቹ ሊከፈሉ የሚገባቸውን ትክክለኛ የታክስ መጠን አስቀድመው እንዳያውቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ተገማችነት የተባለውን የሸጋ የታክስ ሥርዓት መገለጫ እንዳይላበስ አድርጎታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የታክስ ባለሥልጣኑ ባለሙያዎች አንዳንድ ጊዜ የማምረቻ ወጪ ሊባሉ የሚችሉትን ወጪዎች ከማምረቻ ወጪ ውስጥ በማውጣት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ የማምረቻ ወጪ ያልሆኑትን በማካተት የግብር ውሳኔ የሚሰጡ በመሆኑ ታክስ ከፋዮች ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ መንግስትም ቢሆን ተገቢውን ታክስ እንዳይሰበስብ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡
በተጨማሪም በነባሩ አዋጅ የተዘረጋው የኤክሳይዝ ታክስ አሰባሰብ ሥርዓት በቀላሉ ለሚፈፀም የታክስ ማጭበርበር ወንጀል የተጋለጠ መሆኑን ነው መንግስት ሲገልጽ የሚደመጠው፡፡ በዚህም የሚፈለገውን ያክል ታክስ ለመሰብሰብ አለመቻሉንም ይጠቅሳል፡፡
ከአገራችን በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች በኤክሳይዝ ታክስ የሚሰበሰቡት ገቢ ከጠቅላላ ምርታቸው 1 ነጥብ 4 በመቶ ሆኖ ሳለ በአገራችን የሚሰበሰበው መጠን ግን 0 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ መሆኑ ሲታይ ደግሞ የመንግስትን ሃሳብ ያጠናክረዋል፡፡ በዚህ መነሻ ነው እንግዲህ እነዚህን የነባሩን ሕግ ጉድለቶች የሚያርምና አዳዲስ ጉዳዮችንም ያካተተ ነው ያለውን ረቂቅ ሕግ ያሰናዳው፡፡
የኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላበት ዋጋና አከፋፈሉ
በነባሩ አዋጅ መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ የስሌት መሰረት (የሚሰላበት ዋጋ) በአገር ውስጥ ለተመረቱ ዕቃዎች የማምረቻ ወጪ ሲሆን፤ ወደአገር ውስጥ ለሚገባ ዕቃ ደግሞ የዕቃው ዋጋ፣ የመድን አረቦን እና የማጓጓዣ ወጪ ነው፡፡
አዲሱ አዋጅ ደግሞ ከነባሩ ሕግ በተሻለ የኤክሳይዝ ታክስ የስሌት መሰረትን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በአገር ውስጥ ለተመረቱ ዕቃዎች ኤክሳይዝ የሚሰላበትን ዋጋ የማምረቻ ወጪ የሚለውን በማስቀረት የዕቃዎቹ የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም ግብር ከፋዮቹ ሊከፈሉ የሚገባቸውን ትክክለኛ የታክስ መጠን አስቀድመው እንዲያውቁ ስለሚያደርግ የታክስ ተገማችነትን ያጎለብታል፡፡
የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ የሚባለው ደግሞ አምራቹ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸውን ዕቃዎች የሸጠው ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች መካከል (በሁለት ሰዎች መካከል በትክክለኛ የገበያ ዋጋ) በሚደረግ ግብይት ለገዥው የሆነ እንደሆነ ገዥው የከፈለው ዋጋ መሆኑን ሕጉ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ሌላ በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ዕቃው ከአምራቹ ፋብሪካ በወጣበት ጊዜ ያለው ትክክለኛ የገበያ ዋጋም የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ነው ይላል ሕጉ፡፡
እዚህ ላይ የፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ በዕቃ አቅርቦት ላይ የተጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ቴምብር (ካለ) ወጪውንና የተመላሽ ዕቃ መያዣዎችን ወጪ እንደማይጨምር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎች የኤክሳይዝ ታክስ ማስከፈያ ዋጋ ደግሞ በዕቃው ላይ የጉምሩክ ቀረጥ የሚከፈል ቢሆንም ባይሆንም በጉምሩክ አዋጅ መሠረት የሚሠላው የዕቃው ዋጋ እና ሊከፈል የሚገባው የጉምሩክ ቀረጥ ድምር ነው፡፡
በአገልግሎት ላይ የኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላበትን መሰረትም ሕጉ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት አገልግሎቱን ለመስጠት የተመዘገበው ሰው የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን አገልግሎቶች የሸጠው ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች መካከል በተደረገ ግብይት ከሆነ ተከፋይ የሆነው የአገልግሎቱ ዋጋ (የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያውን ሳይጨምር) ወይም ኮሚሽን ወይም ሌላ ክፍያ ነው፡፡ በሌላ ማናቸውም ሁኔታ ደግሞ የአገልግሎቱ ትክክለኛ የገበያ ዋጋ የኤክሳይዝ ታክሱ የሚሰላበት ዋጋ ሆኖ ይወሰዳል፡፡
ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ የተደረጉ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በወፍ በረር
የአዲሱ ረቂቅ ሕግ በጎ ጎኖች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ የተደረጉ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ራሱን በቻለ ሰንጠረዥ ዘርዝሮ ማስቀመጡ ነው። በሰንጠረዡ መሰረት ዕቃዎቹ ወይም አገልግሎቶቹ በመሰረቱ የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣልባቸው ቢሆንም ቅሉ፤ መንግስት በፖሊሲ፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ዕቃዎቹና አገልግሎቶቹ ጥቅም ላይ ከሚውሉበት ልዩ ሁኔታ መነሻ ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ አድርጓቸዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የአካል ጉዳተኞች ወደ አገር እንዲያስገቡት የተፈቀደ ለአካል ጉዳተኞች እንዲያገለግል ሆኖ የተሠራ አንድ የግል ልዩ ተሽከርካሪ ከታክስ ነጻ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ “ለአካል ጉዳተኞች እንዲያገለግል ሆኖ የተሠራ…ልዩ ተሽከርካሪ” የሚለው አገላለጽ ብዥታ የሚፈጥርና ለትርጉም የተጋለጠ ነው፡፡
በተለይም አካል ጉዳተኞች እንደየጉዳታቸው ዓይነት ሊያገለግላቸው የሚችል የተለየ ተሽከርካሪ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ የድንጋጌው ዓላማ ደግሞ ከታክስ ነጻ ማድረግ እስከሆነ ድረስ በፍላጎታቸው ልክ የትኛውንም ዓይነት ተሽከርካሪ ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ ሆነው እንዲያስገቡ በግልጽ መፍቀድ አለበት፡፡
ከዚህ ውጭ ግን እንዲህ ዓይነት ድንጋጌ ማስቀመጥ ግልጽነት የጎደለው ከመሆኑም በላይ ለአካል ጉዳተኞች ተብለው በልዩ ሁኔታ የሚፈበረኩ ተሽከርካሪዎች በዓለም ገበያ ዋጋቸው ከፍተኛ በመሆኑ አካል ጉዳተኞች እንደጉዳታቸው ዓይነት በራሳቸውም ሆነ በሌላ ድጋፍ አድራጊ የሚያሽከረክሩትን ማናቸውንም ዓይነት ተሽከርካሪ አስገብተው እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ “እንካ” ብሎ ግን ከልካይ ሥርዓትን ይዘረጋል፡፡
በአደጋ የተጐዱ ሰዎችን ለመርጃ እንዲውሉ የኢት ዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ወደ አገር የሚያስገባቸው ዕቃዎች እንዲሁም ወደ አገር የሚገቡ መንገደኞች ይዘዋቸው የሚመጡ አግባብ ባለው ሕግ የተፈቀዱ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎችም ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ ተደርገዋል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪም አውሮፕላን በበረራ ባለበት ጊዜ ተሳፋሪ መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በጉዞ ወቅት የሚጠቀሙባቸው በነፃ የሚሰጡ ዕቃዎች ከታክስ ነጻ ናቸው፡፡ የዲፕሎማቲክ ወይም ኮንሱለር ሚሲዮኖች ወይም ዲፕሎማቶችና ቆንስላዎች ወይም በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ የዲፕሎማቱና የቆንስላው ቤተሰቦች ወደ አገር የሚያስገቧቸው ወይም ከአገር ውስጥ የሚገዟቸው በዲፕሎማቶች መብትና ጥቅም ደንብ የተፈቀዱ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎችና አገልግሎቶችም ነጻ ከተደረጉት ውስጥ ተካተዋል፡፡
በተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ኤክሳይዝ ሊፈተሽ ይገባዋል
በነባሩ አዋጅ በአገር ውስጥ በሚመረቱና ወደአገር በሚገቡ 19 ዕቃዎች ላይ ታክስ ተጥሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውሉ የሣህንና የልብስ ማጠቢያ መሣሪያዎች፣ የቪዲዮ ዴክ፣ የጠረጴዛ፣ የግድግዳና የእጅ ሰዓቶች፣ አሻንጉሊቶችና መጫወቻዎች ላይ ሲሰበሰብ የቆየው የኤክሳይዝ ታክስ አነስተኛ መሆኑን ነው መንግስት የሚገልጸው፡፡ ከዚህም ሌላ እነዚህ ዕቃዎች አሁን በደረስንበት ደረጃ የቅንጦት ናቸው ያልሆኑና ለሕብረተሰቡም አስፈላጊ በመሆናቸው ከዝርዝሩ ወጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተመሳሳይ ዕቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎ ሳለ በዝርዝሩ ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩ አሉ፡፡ እንዲሁም አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የምታፈስባቸው ሆነው ሳለ አስፈላጊ ያልሆኑና አጠቃቀማቸው ሊገደብ የሚገባ እንደ ቸኮላት፣ ሰው-ሰራሽ ፀጉር የመሳሰሉ ዕቃዎች በአዲሱ ሕግ ተካተው የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው ተደርጓል፡፡
በአካባቢ ላይ ጉዳት ከሚያስከትሉ ዕቃዎች ውስጥ ዋነኛው ተሽከርካሪዎች የሚያመነጩት ካርቦን ነው፡፡ በተለይም አሮጌ ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ካርቦን ስለሚያመነጩ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ የመለዋወጫና የነዳጅ ፍጆታቸውም ከፍተኛ በመሆኑ ለሚጠቀሙበት ነዳጅና መለዋወጫ አገሪቱ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ነው፡፡ በሕይወትና በንብረት ላይ ለሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ያላቸው አስተዋጽኦም እንዲሁ፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ ነው እንግዲህ መንግስት በተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ መከለስ ያስፈለገው፡፡ ይህ የተሽከርካሪዎች ጉዳይ ታዲያ ግንባር ቀደሙ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በነባሩ አዋጅ ሁሉም ዓይነት ተሽከርካሪዎች የስሪት ዘመናቸው ግምት ውስጥ ሳይገባ በአንድ ዓይነት ቋት ውስጥ ተካትተው ያላቸውን ሲሲ ብቻ መሰረት በማድረግ ከ30 እስከ 100 ፐርሰንት ታክስ ነው የሚጣልባቸው፡፡
በአዲሱ አዋጅ ግን ተሽከርካሪዎቹ በዓይነት፣ በስሪት ዘመን፣ በሚሰጡት አገልግሎት (የሰው፣ የዕቃ፣ የመወዳደሪያ፣ የኮንስትራክሽን፣ የክሬን ወዘተ)፣ ሰውና ዕቃ በመጫን አቅማቸው እንዲሁም ኪሎ ዋታቸውና ሲሲያቸው ብሎም በነዳጅ/በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆኑ ተለይቶ፤ ሁለት እግር፣ ሶስት እግርና ከዚያ በላይ ተለይተው ነው ታክስ የተቆረጠላቸው፡፡
እርግጥ ነው አገራችን በስልጡን አገራት ጎዳናዎች ላይ አይናችሁን ላፈር የተባሉ ተሽከርካሪዎች መጣያ እንዳትሆን ተሽከርካሪዎቹ እንዳይገቡ የሚከለክል ሕግ ማውጣት ትችላለች፡፡ ይሁንና ይህ በራሱ በዓለም የንግድ ድርጅት ስምምነቶች የተከለከለ በመሆኑ የድርጅቱ አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡
ለዚህም ይመስላል መንግስት በአዲሱ አዋጅ በተካተተው መልኩ ከፍተኛ የኤክሳይዝ ታክስ መጣሉን የመረጠው፡፡ ያም ሆኖ የተጣለው ከፍተኛ የኤክሳይዝ መጠን ያረጁ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ የመከልከል ያህል ውጤት ያለው በመሆኑ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለይም በአገር ቤት ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠምና የማምረት ኢንደስትሪው ባላደረገበት ሁኔታ ሕጉ ከፍተኛ የታክስ መጠን ይዞ የመውጣቱ ነገር ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተም ከገቡ በኋላ የአገልግሎት ዘመናቸው ሲጨምር የበካይነት ደረጃቸውም የሚጨምር በመሆኑ ከወዲሁ በኤክሳይዝ ታክስ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው ቅቡልነት ያለው ነው፡፡ ይሁንና የተጣለው ከፍተኛ የታክስ መጠን በድጋሚ ሊፈተሽና ማስተካከያም ሊደረግበት ይገባል፡፡
ከሁሉም በላይ በግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ የሰፋፊ መስኖ እርሻ ልማት፤ የሜካናይዝድ ግብርና እና የኩታ ገጠም ማሳዎችን ድንበር በማጥፋት በጋራ የማልማት ስትራቴጂዎች እየተተገበሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት በትራክተሮች ላይ ከ100 እስከ 400 ፐርሰንት ታክስ መጣሉ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡
የአልኮልና የሲጋራ ኤክሳይዝ ኮንትሮባንድን እንዳያስፋፋ
አልኮልና ሲጋራን በመሳሰሉ የህብረተሰብ ጤና አዋኪዎችና ቦዘኔነትን በማስፋፋት የጊዜና የአምራች ጉልበት ብክነትን በሚያመጡ ምርቶች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ መደረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁንና አንዳንዶች ታክሱን ተከትሎ በሚመጣው የዋጋ ንረት ምክንያት ገበያው በኮንትሮባንድ በሚገቡ ዕቃዎች እንዳይጥለቀለቅ ስጋት አላቸው፡፡
ስጋቱ ምክንያታዊ ቢሆንም የዓለም ባንክ ጥናትንና የአገራት ልምዶችን የቀመሩ ጽሁፎች እንደሚያሳዩት የኤክሳይዝ ታክስ መጨመር ለኮንትሮባንድ መስፋፋት ዓይነተኛ መነሾ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሸማቾች ስልጡን አለመሆን፤ ልል የንግድ ቁጥጥር ሥርዓትና ደካማ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ድምር ውጤት ነው ኮንትሮባንድን የሚያስፋፋው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንኑ በቅጡ የተገነዘበው ይመስላል፡፡ የኤክሳይዝ ታክስን በተገቢው መጠን ለመሰብሰብ የሚያስችል ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚዘረጋና የኤክሳይዝ ቴምብርን (ምልክትን) ሥራ ላይ እንደሚያውል ነው ረቂቅ አዋጁን ለፓርላማው ባቀረበበት ወቅት የገለጸው፡፡
በዚህም መሠረት የኤክሳይዝ ታክስ በተከፈለባቸው የአልኮል መጠጦችና ሲጋራዎች ላይ ታክሱ የተከፈ ለባቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ የኤክሳይዝ ቴምብር ይለጠፍባቸዋል፡፡ እንዲሁም ከቀረጥና ታክስ ነፃ መብት ላላቸው በሚሸጡ ዕቃዎች ላይ ከቀረጥና ታክስ ነፃ ሆነው የተሸጡ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ይደረግባቸዋል፡፡
በመሆኑም ቴምብር ያልለጠፉ (ምልክት ያልተደረገባቸው) ዕቃዎች በገበያ ላይ ሲውሉ በቀላሉ በመከታተል እርምጃ ለመውሰድ የሚያስቻል ሥርዓት በአዲሱ አዋጅ በመዘርጋቱ የአፈጻጸም እንከኖች እንደተጠበቁ ሆነው በሕጉ ምክንያት ኮንትሮባንድ ይስፋፋል የሚለው ሥጋት በመጠኑም ቢሆን የሚቀንስ ይመስላል፡፡
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 14/2012
በገብረ ክርስቶስ