
በዜጎች ላይ በዘፈቀደ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎችን የመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝም እንዲታረሙ ማድረግን የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1142/2011 ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊነት ጥሎበታል፡፡ የመልካም አስተዳደር በአገሪቱ እንዲሰፍን የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር እንዳለበትም ደንግጓል፡፡የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በክፍል ሶስት የማስተግበር ኃላፊነትንም ሰጥቶታል፡፡
ዶክተር እንዳለ ሃይሌ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በፐብሊክ ማኔጅመንት ፖሊሲ ሰርተዋል፡፡በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት እና በአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡አሁን ደግሞ በዋና ዕንባ ጠባቂነት ተሹመው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ዋና ዕንባ ጠባቂው ዶክተር እንዳለ የዛሬው የተጠየቅ እንግዳችን ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚባለው ምንድን ነው?
ዶክተር እንዳለ፡- የዕንባ ጠባቂ ተቋም ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በስዊድን አገር የተቋቋመ ነው፡፡ ለመቋቋም ምክንያት የሆነው ፍርድ ቤቶች የሚያዩት ይበልጥ የደረቅ ወንጀልን ስለነበር በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚደርሱ ተጽዕኖዎች ወይም በደሎችን የሚያየው ማንነው? የሚል ክርክር ዘወትር ይነሳ ነበር፡፡ በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት ገለልተኛ ተቋም መቋቋም እንዳለበት ታምኖበት የእንባ ጠባቂ ተቋማት መቋቋም ጀመሩ፡፡ በየሀገራቱም እነዚህ ተቋማት ተቋቁመው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ የአስተዳደር በደሎችን የሚያዩ በተለያየ አገር የተለያየ ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ አንዱ ዕንባ ጠባቂ ሲሆን፤ አንዳንዶች public protector፣ ሌሎች ደግሞ administrative justice ይሏቸዋል፡፡ በጥቅሉ አስተዳደራዊ ፍትህን መስጠት ዋነኛው ተግባራቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለተቋሙ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎችን የመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝም እንዲታረም ማድረግ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ የተቋሙ ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ የአስተዳደር በደል የሚባለው ምን ማለት እንደሆነ ቢገልጹልኝ?
ዶክተር እንዳለ፡- አስተዳደራዊ በደል ስንል በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚሰጧቸው ውሳኔዎች አሉ፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚያወጧቸው አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች በህገ መንግሥት ከተሰጣቸው መብቶች ጋር ይቃረናሉ ወይስ አይቃረኑም ? በወጡት ህጎች ዜጎች እየተዳኙ ነው ወይስ አይደለም ? አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦቹ በሚጣሱበት ሰዓት አስተዳደራዊ በደል ደርሷል ወይስ አልደረሰም ብለን ውሳኔ ላይ የምንደርስበት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዓለም አቀፍ ገጽታውና አተገባበሩን ከኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጋር አነጻጽረው ይንገሩኝ ?
ዶክተር እንዳለ፡- አሁን በዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ተወደደም ተጠላ አገራት ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከእዚህ በፊት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዴሞክራሲያዊ ከመሆን ይልቅ ይበልጥ አምባገነናዊ ነበሩ።ስለዚህ መንግሥታት ትላልቅ አገራት ለሚሰጡት እርዳታ በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ አለ ወይስ የለም? መልካም አስተዳደር አለ ወይስ የለም? የሚለውን እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡ ስለዚህ አገራት ሳይወዱ በግዳቸው ወደ ዴሞክራሲ ባህሪይ የመቀየር አስገዳጅ ሁኔታ ይጣልባቸዋል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ስለመኖሩ ሲመዘን የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት ስለመኖራቸው እንደመስፈርት ይታያል። የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፀረ ሙስናና ስነምግባር ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ናቸው፡፡
የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች፣ ኮሚሽኖች ወይም በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚያቀርቡ ናቸው። እነዚህ ተቋማት የሚያቀርቡት አገልግሎት ባግባቡ ስለመቅረቡ፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከሆነ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚያይበት፣ የአስተዳደራዊ በደል ከሆነ ደግሞ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያይበት ነው፡፡ ስለዚህ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ፣ የዴሞክራሲ ጉዳይና የሙስና ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቋማት እንዲኖሩ የሚያስገድድ ሁኔታ አለ፡፡ ግን እንደየአገራቱ ሁኔታና የዕድገት ደረጃ የተቋማቱ አቅምና ብቃት ይወሰናል፡፡ በትላልቅ አገራት የተቋቋሙ ዕንባ ጠባቂ ተቋማት በጣም ትላልቅ ጉዳዮችን የሚሰሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ አሁን እኛ ከምንሰራው ሥራ አንጻር ሲመዘን እነርሱ አልፈው ሄደው እናገኛቸዋለን፡፡ ለምሳሌ ካናዳን ብንመለከት መንግሥት ወይም ሌሎች ማህበራት ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡት ወተት አለ፡፡ ወተቱ የሚቀርበው በበቂ ሁኔታ ስለመሆኑ፣ ስለይዞታው የሚጠይቁበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ እንጂ አስፈጻሚው አካል ይበድለዋል ወይስ አይበድለውም የሚለው ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ ወይም ብዙ የአፍሪካ አገራትን ስንመለከት ደግሞ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ወይም መንግሥታት የበለጠ ዴሞክራት ባለመሆናቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በደሎች ስለሚደርሱ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም ሆኑ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት አስፈላጊ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር ያላቸው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው?
ዶክተር እንዳለ፡- የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስተዳደራዊ በደሎችን ያያል፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ያያል፡፡ ሰብዓዊ መብት ሲባል አንድ ዜጋ በተፈጥሮ የሚያገኘው መብት ማለት ነው፡፡ በማረሚያ ቤቶች፣ በፍርድ ቤቶች ወዘተ ሰብዓዊ መብት ስለመከበሩ ይመለከታል፡፡ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ደግሞ መንግሥት የሚያቀርበውን አገልግሎት ህብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ መቅረቡን ያጣራል። በተለያየ መንገድ ዜጎች ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን ይመለከታል፡፡ ግን አስተዳደራዊ በደሎቹ እየከፉና እያደጉ ሲሄዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚደርሱበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንዴም ሁለቱ ሊደራረቡ ይችላሉ፡፡ በአስተዳደራዊ በደልና በሰብዓዊ በደል መሃል ላይ በሚሆንበት ጊዜ እንዴት መፈታት እንዳለበት በአዋጃችን በግልጽ እንደተቀመጠው አመልካቹ ቀድሞ ያመለከተበት ተቋም ጉዳዩን በባለቤትነት ይይዘዋል፡፡ ለምሳሌ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀድሞ አመልክቶ ከሆነ ጉዳዩን ኮሚሽኑ ይመለከታል፡፡ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቀድሞ ቀርቦ ከሆነ ተቋሙ ይመለከተዋል፡፡ እንደገናም ዕንባ ጠባቂ ተቋም የቀረበለት ይበልጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይልካል፡፡ ሰብዓዊ መብት የቀረበለት ጉዳይም የበለጠ አስተዳደራዊ ጥሰት ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ ጉዳዩን ለኮሚሽኑ ያስተላልፍልናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ከተሰጡት ስልጣንና ኃላፊነት አኳያ በእስካሁን አተገባበሩ ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል ይላሉ?
ዶክተር እንዳለ፡- አጠቃላይ ህብረተሰቡ ከሚፈልገው እና አሁን ካለው አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር ሲመዘን ተቋሙ የሚፈለግበትን ውጤት አምጥቷል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከህግ የበላይነት ያለመከበር ጋር ተያይዞ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች አሉ፡፡ እነዚህ የመብት ጥሰቶች በሚደርሱበት ሰዓት ተወደደም ተጠላ የአስተዳደር በደል የሚደርስበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ስለዚህም ህብረተሰቡ ከሚፈልገው አንጻር ተደራሽ ሆነናል ለማለት ያስቸግራል። ግን በየዓመቱ ከምናቅደው አንጻር ግን በተለይ ዶክተር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ብዙ ለውጦች ታይተዋል። ተቋሙ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን፡፡
ለምሳሌ ባለፈው ዓመት 3,485 የአቤቱታ መዝገቦች ቀርበውልናል፡፡ መዝገቦቹ 155 ሺ 119 አቤት ባዮች የያዙ ሲሆን፤ ከእነዚህ አቤቱታዎች ውስጥ 1 ሺ 490 መዝገቦች ዕልባት አግኝተዋል፡፡ የቀረበው አቤቱታ አስተዳደራዊ በደል ስለመድረሱ ወይም አለመድረሱ ተጣርቶ እልባት ሰጥተናል ማለት ነው፡፡
እልባት ካገኙት አንድ ሺ 653 መዝገቦች መካከል 41 ነጥብ ስምንት በመቶ የሚሆነው ታርሟል፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ጊዜ የሚጠይቁ አሉ፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች በስድስት ወራት አንዳንዶች ደግሞ በሶስት ወራት እንደሚፈጸሙ የምንጠብቃቸው ጉዳዮች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምርመራ ተደርጎባቸው የመፍትሄ ሃሳብ የሰጣችሁባቸውን ጉዳዮች ስለመፈጸማቸው የምትከታተሉበት አሰራር ዘርግታችኋል?
ዶክተር እንዳለ፡- በተቋሙ የተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች አሉ። ከእነዚህ መካከልም አንዱ የምርመራ ሥራ የሚሰራ ሲሆን፤ ሌላው የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውን ክፍል ነው፡፡ የምርመራ ሥራ የምንለው አንድ ግለሰብ አቤቱታ ይዞ ወደ ተቋማችን ሲመጣ ያንን ጉዳይ መርምሮ የመፍትሄ ሃሳብ የሚሰጥ ነው፡፡ የመፍትሄ ሃሳብ የተሰጣቸው መዝገቦች ለመፍትሄ ሃሳብ ክትትል ቡድን ይላካሉ፡፡ ክፍሉ የአቤት ባዮቹን ውሳኔ ይዞ ስለመፈጸሙ ክትትል ያደርጋል፡፡ በፊት የነበረው አንዱ ችግር የመፍትሄ ሃሳብ ከተሰጠ በኋላ ስለመፈጸሙ ክትትል የሚደረግበት አሰራር አለመኖሩ ነበር። አሁን ይህንን ችግር ቀርፈናል ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምርመራ አድርጋችሁ ጥፋት መሆኑ ታምኖበት ወይም በተጨባጭ አውቃችሁት እንዲታረም አቅርባችሁ እርምጃ ባለመወሰዱ የደረሰ ጉዳት ካለ ቢነግሩኝ ?
ዶክተር እንዳለ፡- የመፍትሄ ሃሳብ ተሰጥቷቸው የማይፈጸሙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ አምና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በልዩ ሪፖርት አቅርበናል፡፡ የምንሰጠው የውሳኔ ጉዳይ ፍጻሜ ካላገኘ ለብዙሃን መገናኛ የተቋሙን ስም ጠቅሰን ለሕዝብ እናጋልጣለን፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በልዩ ሪፖርት እናቀርባለን፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ የሃዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተሰጡ ውሳኔዎችን ባለመተግበር በልዩ ሪፖርታችን አሳውቀናል፡፡
ባለፈው ዓመት ሪፖርት ካቀረብንና ያልፈጸሙ ተቋ ማትን ስም ዝርዝር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላክን በኋላ ብዙ ተቋማት ትብብር አሳይተዋል፣ የመፈጸም ዝንባሌያቸውም የተሻለ ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በትግበራ ሂደት የአስፈጻሚ አካላት ትብብርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ ምን ይመስላል ?
ዶክተር እንዳለ፡- በፊት ምክር ቤት አካባቢ ለዴሞክራሲ ተቋማት የሚሰጡት ትኩረት፣ ድጋፍና ክትትል ደካማ ነበር፡፡ አሁን ግን ራሱን የቻለ የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በየጊዜው በአካል በመገኘት ይከታተላል፡፡ ሪፖርታችንን በመመልከት ድጋፍ በመስጠት በኩል የተሻለ ነው፡፡ ግን ተቋሙ የበለጠ መስራት እንዲችል የፋይናንስ፣ የግብዓት፣ የሰው ኃይል ድጋፍ ያስፈልገዋል። በእዚህ በኩል አሁንም ውስንነቶች አሉ፡፡ በቂ ተሽከርካሪ ባለመኖሩ፣ የሰው ኃይል ባለመሟላቱ፣ ለሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ በተለይ የተቋማችን ዋና አላማ አስፈጻሚ የህግ ባለሙያዎችን ፍልሰት ማስቆም አልቻልንም፡፡ ከእኛ ጋር ሲነጻጸር አንድ አቃቤ ህግና አንድ ዳኛ የሚከፈላቸው የደመወዝ መጠን እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ያሉ ተቋማት ለተመሳሳይ ሙያ፣ ተመሳሳይ ትምህርት ደረጃና ተመሳሳይ ልምድ የሚከፍሉት ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ባለሙያን ማቆየት እና በተገቢው መንገድ ተቋሙን እንዲያገለግሉ ማድረግ የሚቻለው በበቂ የደመወዝ ክፍያ አሊያም የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ እኛ ያንን ማድረግ ስላልቻልን ባለሙያዎቹ ሁለት ዓመት የሥራ ልምድ ከያዙ በኋላ ጥለውን ወደእነዚህ ተቋማት ይኮበልላሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ለመንግሥት አካላትም ሆነ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳስበናል፡፡ ሆኖም በሚፈለገው ልክ እየደገፉን አይደለም፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ለአስተዳደር በደል መነሻ ምክንያቶች ናቸው ብላችሁ የለያችኋቸው ጉዳዮች ካሉ ቢነግሩኝ?
ዶክተር እንዳለ፡- የአስተዳደር በደል የሚያደርሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ተለይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል መሬት አንዱ ነው። ህገ መንግሥቱ ላይ መሬት የመንግሥትና የህዝብ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ ግን መንግሥት መሬትን ለአንድ ፕሮጀክት ፈልጎ በሚወስድበት ጊዜ ተገቢ ካሳ ከፍሎበት መሆን አለበት። መንግሥት ተገቢ ካሳ እየከፈለ አይደለም። በተለያዩ ክልሎች የተለያየ አይነት የካሳ ክፍያ ተቀምጧል። ይህንን ክፍተት የፌዴራል መንግሥት ግምት ውስጥ አስገብቶ መንግሥት ለሚያሰራቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች የተሻለ ክፍያ ይከፍላል። ክልሎች ጋር ግን ሲታይ አንድ ከተማ ላይ የካሳ ክፍያ የሚከፍለው የከተማ አስተዳደሩ ሲሆን አፈጻጸሙም ክልሉ በሚያወጣው የሊዝ ዋጋ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡
በብዛት በአስተዳደር በደል አቤቱታ የሚቀርበውም ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ሌላው መንግሥት ከሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ የሚፈጸም በደል አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጡረታ፣ ከትምህርት፣ ከ ገቢዎችና ጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ በብዛት በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ጥያቄም ይቀርባል፡፡ የቀበሌ ቤቶች ላይ መንግሥት ያስቀመጠው መስፈርት አለ፡፡ ሆኖም አስፈጻሚ አካላት እየተስተናገዱ ያለው በመስፈርቱ መሰረት አይደለም፡፡ ‹‹ተራዬ ደርሶ ለሌላ ተሰጠብኝ›› የሚሉ አቤቱታዎችም ይመጣሉ፡፡
አሁን አሁን እየቀረበ ያለው የአስተዳደር በደል ደግሞ የህዝብ መፈናቀል ነው፡፡ በማንነታቸው ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ በስፋት በሚፈናቀሉበት ሰዓት መንግሥትም ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡ ግን አንድ አካባቢ ላይ አምስትና ስድስት ሰዎች ተጽእኖ መፍጠር ስለማይችሉ መንግሥት ትኩረት አይሰጣቸውም፡፡ ስለዚህም ይህ ቅሬታ ሆኖ ለእኛ ይቀርባል። አካል ጉዳተኞችን መንግሥት በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ሆኖም እነርሱን
የማያስተናግዱ ክፍለ ከተሞችና የከተማ አስተዳደሮች አሉ። መረጃ ክልከላም ላይ የሚነሳ ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ወደአንዳንድ ተቋማት ዘንድ ሄደው መረጃ ጠይቀው ተከለከልን የሚሉ አስተዳደራዊ በደሎች ወይም ጉዳዮች ይታያሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለተቋማችሁ ከተሰጠው ኃላፊነት አንዱ የመረጃ ነጻነት አዋጁን ማስፈጸም ነው፡፡ ከእዚህ አንጻር ምን እየተገበራችሁ ነው ?
ዶክተር እንዳለ፡- የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በክፍል ሶስት ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን የማስተግበር ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡ ከእዚህ አንጻር ብዙዎቹ ዓይን ባወጣ መልኩ መረጃ የመከልከል ችግሮች ባይኖሩም ተቋማዊ በሆነ መንገድ መረጃ ተደራጅቶ የሚገኝበት ማንኛውም ዜጋ ተቋሙ ከሚሰራው ሥራ አኳያ ሪፖርቶች፣ ዕቅዶች፣ የሚያወጣቸው መመሪያዎችን የመረጃ ማዕከል አዘጋጅቶ አደራጅተው ያላስቀመጡና በዌብ ሳይት የመጫን ሁኔታ ክፍተት አለው። ዌብ ሳይቶቹ ቢታዩ በብዛት ከሁለት ሶስት ዓመታት በፊት የተጫኑ ሆነው የሚገኙበት ሁኔታ አለ፡፡
ሚዲያዎች ጋር እያጋጠመ ያለው ከመረጃ ጋር ተያይዞ ከእዚህ በፊት በኮሙኒክሽን ጉዳዮች በሚኒስቴር ደረጃ ተዋቅሮ ሲሰራ የነበረው አሰራር መቅረቱ ችግር እየፈጠረ መጥቷል፡፡ ማንኛውም ሚዲያ ስለፈለገው አካባቢ ተቋሙን ጠይቆ መረጃ የሚያገኝበት ሁኔታ ነበር፡፡ ተቋሙ በመፍረሱ ብዙ ብዙሃን መገናኛ መረጃ የሚገኝበት ማዕከል አለመኖሩን እንደችግር ያነሳሉ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት መረጃ ሊሰጥ የሚችለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ነው፡፡ ከእዛ ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ጋዜጠኛ መረጃ ቢፈልግ የሚያገኝበት መንገድ የለም፡፡ አንዱ ችግር የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት መፍረስ ነው የሚል ግምገማ አለን፡፡ ጽህፈት ቤቱ የሚፈርስ ከሆነ ሊተካው የሚችል፣ ፕሬስ ሴክሬታሪያትም ከሆነ ቀድሞ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሲሰራ የነበረውን ወክሎ መስራት አለበት፡፡ አንዳንዶች ደግሞ መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው ግንዛቤ በመፍጠርም ክፍተት አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ጋዜጠኛነቴ ከግል ተሞክሮዬ ልነሳና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ኃላፊዎች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ የእዚህ አንዱ ችግር የመረጃ ነጻነት አዋጁ ኃላፊዎች መረጃ ባይሰጡ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ድንጋጌ አለመኖሩ እንደክፍተት ይነሳልና ምን ይላሉ ?
ዶክተር እንዳለ፡- አዋጁ ላይ የአስገዳጅነት ባህሪ አለመኖሩ አንድ ክፍተት ነው፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን አንድ ተቋም ላይ አንድ ሰው ኃላፊ ተብሎ ሲሾም የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ እንደመሆኑ ስለተቋም መረጃ የመስጠት ሚና ይኖረዋል፡፡ ተቋሙን ወክሎ የሚያስፈልገውን መረጃ የመስጠት ግዴታም አለበት፡፡ እንደገናም የተቋሙ ወኪል ነው፡፡ ለምሳሌ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ሲል ተቋሙን ወክዬ የምገኘው እኔ ነኝ፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የተቋም ኃላፊ መረጃ የመስጠት ግዴታዬ ነው ብሎ አያስብም።ብዙ አስፈጻሚ አካላት የሚስተዋለው መሰረታዊ ችግር በየተቋማት የሚገኙትን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ብቃታቸውን በማሳደግ የተቋማቱንና ኃላፊውን የሚመለከቱ አስፈላጊ መረጃዎች እነርሱ እንዲሰጡ አይደረግም፡፡
አሁን ያለው አጠቃላይ ተሞክሮም ሁሉም ተቋማት ላይ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ማግለል ይስተዋላል። እነርሱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ስለተቋሙ ለዜጎች መረጃ የመስጠት ኃላፊነታቸውን ብቻ እንዲወጡ የማድረግ የተቋማት ችግር አለ። እንደገናም ተቋማት ከሚዲያ ሚዲያን የማማረጥ ችግርም ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ቴሌቪዥንን መርጦ የመስጠት ዝንባሌ ይታያል፡፡ ኤፍ ኤሞች የበለጠ ለህብረተሰብ ተደራሽ ናቸው ግን ቴሌቪዥንና ሬዲዮን የሚያማርጡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አሉ፡፡ መሰረታዊ ችግሩ ግን አስፈጻሚ አካላት ለዜጎች መረጃ የመስጠት ኃላፊነት ሳይሆን ግዴታ አለብኝ ብሎ ማሰብ ላይ የግንዛቤ ችግር ይስተዋላል፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ በልዩ ልዩ መድረኮች ኃላፊዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር ኃላፊ ሆኖ የሚቀመጥ ሰው መረጃ መስጠት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ማንኛውም አካል በዓመት አንዴና ሁለቴ ወቅት ጠብቆ ሳይሆን በማንኛውም ሰዓት መረጃ የመስጠት ኃላፊነትም ግዴታም አለበት፡ግን ይህንን የሚያደርግ ተቋም ወይም ኃላፊ ጥቂት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ክፍተት ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?
ዶክተር እንዳለ፡- ዋናው የግንዛቤ ችግሩ መፈታት ይኖርበታል፡፡ አንድ መሪ ዴሞክራት ነኝ ብሎ ሲያስብ፡፡ አንድ ዴሞክራቲክ መሪ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለትም ግልጸኝነት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ተቋሙ ግልጽ አሰራር ስለመዘርጋቱ መንግሥት ከሚመድብለት በጀት አንስቶ ለህብረተሰቡ መግለጽ ይጠበቅበታል፡፡ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነትን ሊያሰፍን ይገባዋል፡፡ እነዚህን ያላሟላ መሪ ዴሞክራት ነው ለማለት አያስችልም፡፡ የሚፈለገውን አገልግሎት ስለመስጠቱ፣ በተጠያቂነት ረገድም ህብረተሰቡ ስለተቋሙ መረጃ ስለማግኘቱ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በእዚህ በኩል ተከታታይነት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሰራት ይኖርበታል። የአንድ ተቋም ሚኒስትር ስለሆነ መፈራት የለበትም፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታንም ሚዲያዎች ማጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ የሆነ መረጃ ተጠይቆ የማይሰጥ ከሆነ አልሰጠኝም ብሎ ማጋለጥ ይገባል፡፡ አንዳንዴ የሚሸፋፈንበት ሁኔታ ተገቢ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ተጠያቂነት የለም የሚሉ አሉ። አንዳንድ ተቋማትና ህዝብን እናገለግላለን ብለው ኃላፊነት የተረከቡ ሰዎች ባጠፉትና በፈጸሙት ልክ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ችግር እንዳለ ይነሳል፡፡ የመልካም አስተዳደር መርህ የሆነውን ተጠያቂነትን ዕውን ከማድረግ አኳያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን እየሰራችሁ ነው ?
ዶክተር እንዳለ፡- የተጠያቂነት መርህን ተግባራዊ ለማድረግ የአስተዳደር ሥነሥርዓት ህግ አዘጋጅተን ለጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስተላልፈናል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ኃላፊነቱን ተረክቧል፡፡ በህዝብም አስተችቷል እኛም እየተሳተፍንበት እንገኛለን፡፡ ይህ ህጉ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት እያንዳንዱ አስፈጻሚ አካል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ እስካሁን ያለው ክፍተት አንድ ሰው በሰራው ልክ ተጠያቂ አይሆንም ነበር፡፡ ከተጠያቂነት ይልቅ ወይ ከቦታው ተነስቶ ሌላ ቦታ የሚሾምበት ወይንም የሚመደብበት ሂደት ነበር። ዋነኛው ክፍተቱ ግን የአስተዳደር ሥነሥርዓት ህግ ያለመኖር ነው፡፡ በቅርቡ ጸድቆ ተግባራዊ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፡- ተቋማችሁ ከሚቀርብለት አቤቱታ ተነስቶ ምርመራ በማድረግ እርምት ከመውሰድ አንጻር ችግርና ውስንነቶች እንዳሉበት የሚተቹ አሉ። በእዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር እንዳለ፡- የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም ሆነ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ሲባል አስፈጻሚ አካላት በእነርሱ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት የለባቸውም። አሁን ባለው ሁኔታ የትኛውም የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በእኛ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህንን እርግጠኛ ሆኜ እነግርሃለሁ፡፡ ተቋሙ ነጻና ገለልተኛ ነው፡፡ ከለውጡ በፊት ግን ብሄራዊ ደህንነት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩ እንዲቋረጥ ያደርግ ነበር። ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮም ተደውሎ ይህንን ጉዳይ ተውት የሚባልበት ሁኔታ ነበር፡፡
እኔ ወደእዚህ ቦታ ከመጣሁ በኋላ በእዛ ጊዜ የተተው ጉዳዮች እንደየጉዳዮቹ ሁኔታ እንደገና ተመልሰው እንዲታዩ እየተደረጉ የተፈጸሙ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በጉዳዮቹ ሁኔታ የማናያቸው የይርጋ ጊዜ የሚያግዳቸውም አሉ ። ግን ከለውጡ በኋላ ብዙ የተፈቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማገዝ ረገድም አሁን ባለው ሁኔታ ትንሽ ልዩነት አለው። የህግ አውጭው አካል (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) እየጠነከረ ሲሄድ የዴሞክራሲ ተቋማት የዕንባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ እየጠነከረ ይሄዳል። የተሻለ ድጋፍ እየሰጡን ይገኛሉ፡፡ እኛ የምንሰጣቸውን ሪፖርት ተመልክተው መልስ ይሰጡናል፡፡ ያልፈጸሙ አስፈጻሚ አካላት ካሉም ጠርተው በማነጋገር እያገዙን ናቸው አሁን ለውጦች አሉ፡፡ ባለን የሰው ኃይልና በጀት አንጻር እየሰራን ነን፡፡ ግን እነዚህ ለውጦች አሁን ካለው የተወሳሰበ የአስተዳደር ችግርና ህብረተሰቡ ከሚፈልገው አንጻር ብዙ ይቀረናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት እንደአገር በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆኑ ግጭቶችና ሁከቶች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከእዚህ አኳያ ተቋማችሁ ሰላምን በማስከበር በኩል ምን ያህል ሚና ነበረው? አሁንስ እየተፈጸሙ ካሉ ወቅታዊ ጉዳዮች አንጻር ምን እያደረጋችሁ ትገኛላችሁ ?
ዶክተር እንዳለ፡- ከእዚህ አንጻር የእኛ ተቋም ሊሰራ የሚገባው መንግሥት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ማሳሰብ ነው፡፡ ይህንን በሚዲያም ሆነ በሪፖርቶቻችን በተደጋጋሚ መንግሥት የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የታዩትን ክፍተቶች እንዲሞላ አሳስበናል፡፡ መንግሥት ታጋሽና ሆደ ሰፊ ሊሆን የሚችለው እስከተወሰነ ገደብ ድረስ ነው፡፡ ዜጎች እየሞቱ፣ በማንነታቸውም እየተፈናቀሉ ባለበት ሰዓት መንግሥት ታጋሽና ሆደ ሰፊ መሆን የለበትም፡፡ መንግሥት ሆደ ሰፊ መሆን የሚገባው የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማስፋት አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የተለያዩ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች አገር ውስጥ የገቡበት ሁኔታ አለ፡፡ እነርሱም ዜጋ ሆነው ግን ፖለቲካውን ስለተቃወሙ ብቻ የተገደሉበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ቻይ መሆንም ያስፈልጋል፡፡
ዜጎች የመጻፍ፣ የመናገር፣ መረጃ የማግኘት፣ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ፣ በሚፈልጉት የፖለቲካ ድርጅት፣ በሚፈልጉት አመለካከት ዙሪያ የመሳተፍና የመደራጀት መብት አላቸው፤ ይህንን በማድረግ በኩል መንግሥት ሆደ ሰፊና ቻይ ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ የሌሎችን መብት በሚጥስ መንገድ የአጥፊዎች መብት ሊከበርላቸው አይገባም፡፡ የአንድ ግለሰብ ወይም ዜጋ መብት ሊከበርለት የሚገባው የሌላውን መብት እስካከበረ ጊዜ ነው፡፡ ሌላውን ሕዝብ እያፈናቀለ፣ ሌላ ሰው እየገደለ ዴሞክራቲክ ነኝ ማለትም አይቻልም፡፡ ዜጎች ከመንግሥት የሚፈልጉት አንዱ ነገር በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ፤ በሰላምም ወጥተው መግባት እንዲችሉ ነው፡፡ ዜጎች መንግሥት እንዲኖር የሚፈልጉትም ሆነ ግብር የሚከፍሉት የተለየ ፍላጎት ኖሯቸው አይደለም፡፡ የህግ የበላይነት እንዲያሰፍንላቸው እንጂ፡፡
በየትኛውም አገር መንግሥት ይኑር ሲባል ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ ጉልበተኞች ጉልበት የሌላቸውን ሰዎች እንዳይደፍሩ፣ ብዙሃኑ የአናሳውን መብት እንዳይጥስ ስለሚፈለግ ነው ፤በአንድ አገር ውስጥ መንግሥት እንዲኖር የሚፈለገው፡፡ እንጂ ሌላ ምክንያት ኖሮ አይደለም፡፡ ስለዚህ የህግ የበላይነትን በማስከበር የሚታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ ክፍተቶቹ አሁን ካለንበት የሽግግር ወቅት አንጻር ታሳቢ የምናደርጋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ነገር ግን የሽግግር ወቅት በሚሆንበት ሰዓት ሊታለፉ የማይገባቸው ቀይ መስመሮች ይኖራሉ፡፡ የእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የትኛውም አገሮች እንደኛ ሽግግር ያካሄዱ አገራት ቀይ መስመርን ያሰምሩና እንዳይጣስ ያደርጋሉ፡፡የህግ የበላይነት ካልተከበረ ህብረተሰቡ የጽንፈኝነት፣ የብሄርተኝነት ሰለባ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንድ አገር የፖለቲካ ብልሽት ወደ መንግሥት ተቋማት የማይገባበት ሁኔታም የለም፡፡ የጸጥታ አካሉም ላይ የእዛ አይነት በሽታ ሊጋባ ይችላል፡፡ ግን ከእዚህ በፊት የጸጥታ ኃይሉ የተገነባበት መንገድ መከላከያን ጨምሮ ገለልተኛ ተደርገው አይደለም፡፡ የተዋቀረውና የተደራጀው በተለያየ የጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት ነው፡፡ አሁን ለተከሰተውም ችግር የጸጥታ አካላት መከላከያን ጨምሮ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ስላልተደራጁ ነው የህግ የበላይነትን ማስከበር ያልቻሉት፡፡
ለምሳሌ ግብጽን መመልከት ይቻላል፡፡ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙሪሲ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት እስከተወሰነ ደረጃ መከላከያ ጣልቃ አልገባም። ሆኖም አገሪቱ ልትጠፋ ስትል በቀጥታ ጣልቃ ገብቷል፤ የነበረውንም ስጋት አስቁሟል፡፡ ምክንያቱም ገለልተኛ ነበር ማለት ነው።ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ እንደእነርሱ አይነት ተቋም እየገነባን አልመጣንም፡፡ እንደውም በተቃራኒው መከላከያውንም ሆነ ሌላውንም አካል በጎጥ በብሄር እየከፋፈልን ነው የመጣነው ፡፡ አሁን የሚታየውም የእዛ ውጤት ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ የተደረጉና እየተደረጉ ያሉ የህግ ማሻሻያዎች የሚደርሰውን የአስተዳደር በደል በማስከበር በኩል ምን ያህል አስቻይ ነው ይላሉ?
ዶክተር እንዳለ፡- የተለያዩ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ተቋማት የተቋቋሙበት አዋጆች አሳሪ የነበሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን አሁን ለማሻሻል ተሞክሯል፡፡ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸው ውሳኔዎችን የማይተገብሩ አካላት ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ አንቀጽ አልነበረውም፡፡ በተሻሻለው አዋጅ እያንዳንዱ አስፈጻሚ አካል ባይፈጽም መረጃችንን አደራጅተን ወደጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በመሄድ ክስ እንዲመሰረት የምናደርግት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም አንድ አስፈጻሚ አካል ባይፈጽም ወደሚዲያ ሄደን የምናጋልጥበትን አጋጣሚ (NAMING AND SHAMING) ዕድል አዋጁ ፈጥሮልናል፡፡ ከዚህ በፊት ተወካዮች ምክር ቤትን ፍቃድ የምንጠይቅበት ሁኔታ ነበር፡፡ አጠቃላይ የፖለቲካው ብልሽት በፈጠረው የህግ የበላይነትን ካለማክበር ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ላይ በስፋት አስተዳደራዊ በደል የሚፈጠርበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ከእኛ ተቋም በላይ ይሆንና አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዎ ውሳኔንም ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋማችሁ ህዝቡ የሚፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ ተግዳሮት የሆኑበት ናቸው ብላችሁ የለያችኋቸውን ቢዘረዝሩልን ?
ዶክተር እንዳለ፡- ለተቋሙ የሚያስፈልገው ሃብት አለመሟላት አንዱ ነው፡፡ ይህ ሃብት የሰው ኃይል፣ ገንዘብና አስፈላጊ ግብዓት በመመደብ በኩል ትልቅ ችግር ሆኗል። መንግሥት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተቋሙ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲመደብ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በእኛ በኩል አስፈላጊ የሥራ መደቦችን በመክፈትና በማዋቀር ሰርተን ተግብረናል፡፡ ለሠራተኞች አስፈላጊ ጥቅማ ጥቅም አጥንተን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ ልከን አፈ ጉባኤ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር። ግን ጉዳዩ አፈ ጉባኤውን የሚመለከት ነው በሚል መልሶ ለአፈ ጉባኤው መድረሱን መረጃ ደርሶናል። በመሆኑም የሠራተኛን ፍልሰት ለማስቆም የሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፈጥኖ መጽደቅ አለበት፡፡ አስፈጻሚ አካላት ላይ አሁንም መተባበር ላይ ጉድለት አለ፡፡ በጣም ቅን የሆኑ የተቋማት ኃላፊ ያሉትን ያህል በተቃራኒው የቅንነት ችግር ያለባቸው አሉ። ውሳኔያችን ከሚኒስትር እስከ ቀበሌ አስተዳደር ይደርሳል።
በእነዚህ ሁኔታ የመተባበር ችግር አለ።ግን በአንጻራዊ መልኩ መሻሻሎች አሉ፡፡
መንግሥት አሁን የህግ የበላይነትን ባለማክበሩ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ጥሩ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ክልል ጌዲኦ፣ አማራ ክልል ቅማንትና የአማራ ህብረተሰብ ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ዜጎችን በማቋቋም ጥሩ ደረጃ አለ። ሶማሌ ክልል ከኦሮሚያ የተፈናቀሉትን በማቋቋም ረገድ እጥረቶች አሉ፡፡ አገራዊ ፖለቲካው የሚፈጥራቸው ሁኔታዎች ለእኛ ተግዳሮት ናቸው፡፡ መንግሥት ዴሞክራት መሆንና የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻለ እነዚህ ተቋማት መኖራቸው ዝም ብሎ ለይስሙላ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መልዕክት ካሎት?
ዶክተር እንዳለ፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥት የጀማመራቸው የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህ የለውጥ ሥራዎች በፌዴራል ደረጃ የታጠሩ ናቸው። መንግሥት እስከ ታች መለወጥ ይኖርበታል፡፡ ለውጡ በየደረጃው እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል መድረስ አለበት፡፡ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ መንግሥት የህግ የበላይነትን በማስከበር ግዴታውን መወጣት አለበት። ማንኛውም ዜጋ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከህግ በታች ናቸው፡፡ በመሆኑም የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል መንግሥት ቁርጠኛ መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
ዶክተር እንዳለ፡-እኔም አመሰግናለሁ!
ዶክተር እንዳለ ኃይሌ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 14/2012
ዘላለም ግዛው