የፍረዱኝ ገጽ በዛሬው አምዱ የአራት ኪሎ ከባሻ ወልዴ ችሎት ቁጥር ሁለት የግል ባለይዞታ የልማት ተነሺዎች እነምስጋናው ከበደ (56) ሰዎች በደል ደርሶብናል የሚለውን ጉዳይ ይመለከታል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በ2006 ዓ.ም ቤቱን አግኝተን በምትክነት ሲሰጠን የከፈልነው ዋጋና ከእኛ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ተነስተው ቤት አለ ተብሎ በ2005 ዓ.ም ቤት የተሰጣቸው ሰዎች ከከፈሉት ዋጋ የ100 ሺ ብርና በላይ ልዩነት አለው ይላሉ፡፡ ከአንድ ቦታ ተነስተን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ ቤት እያለ የለም ብሎ አቆይቶን ጭማሪ እንድንከፍል መደረጉ ተገቢነት የለውም የሚል ቅሬታንና በጉዳዩ ላይ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠን የመፍትሄ ሃሳብ አለመፈጸሙ የፈጠረውን ቅሬታ አስመልክቶ የቀረበን አቤቱታ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡
የቅሬታው ምንጭ
ከባሻ ወልዴ ችሎት ቁጥር ሁለት የግል ባለይዞታ የልማት ተነሺ የሆኑት አቶ ምስጋናው ከበደ ከጎረቤቶቻቸው ጋር 56 ባለ ግል ይዞታዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ሌሎች ነዋሪዎች ከአካባቢው ሲነሱ 56 የሚሆኑትን የግል ባለይዞታዎች ቆርጠው እንዳስቀሯቸውም ይናገራሉ። አራዳ ክፍለ ከተማ እየቀረቡ ለምን እንደዘገዩ ሲያመለክቱ እንደነበረም ይጠቅሱና፤ ወደክፍለ ከተማው ደጋግመው በመመላ ለሳቸው ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም ጠርተዋቸው በወቅቱ ቤት ስለሌለ ባለ አንድ ወይንም ባለሁለት መኝታ ቤት ውሰዱ መባላቸውንም ይመሰክራሉ፡፡
ምርጫችን ከመሰረቱ ባለሶስት መኝታ ቤት ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች የግል ባለይዞታ ሆነው ከሌሎቹ ጎረቤቶቻቸው መለየታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ቤተሰቦቻችንንስ እንዴት እናደርጋቸዋለን በማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በምላሻቸው እንዳሳወቋቸውም ይገልጻሉ፡፡ በጠየቁት መሰረትና መንግስትም ባዘዘው መሰረት እንዲፈጸምላቸው መጠየቃቸውን በወቅቱም ምላሽ ሳይሰጣቸው ዝም ብለው እንደተዋቸው ነው የሚናገሩት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ ምላሽ እንዲሰጣቸው በመመላለስ ያደረጉት ጥረት ምላሽ እንደተነፈገውም አቶ ምስጋናው ይጠቅሳሉ፡፡
ታህሳስ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ለአራዳ ክፍለ ከተማ ደብዳቤ ጽፈው ምላሽ ሳያገኙ ቤቶች ኤጀንሲ ሄደው እንዲያናግሩ በቃል እንዳዘዟቸው የሚያመለክቱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከኤጀንሲው ምላሽ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ውጤት አልባ መሆኑንም ነው የገለጹት። ተመላልሰው ቢጠይቁም አለማግኘታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ እኛ በጠየቅነው መሰረት በ2005 ዓ.ም ተነስተን ቢሆን ኖሮ አሁን እየጠየቅን ያለነው ጥያቄ አይመጣም ነበረ ሲሉ አቶ ምስጋናው በምሬት ይገልጻሉ፡፡
ሰፈራቸው በተለምዶ አራት ኪሎ እየተባለ ይጠራ በነበረው አንደኛ ደረጃ ነባር ቦታ መሆኑን አቶ ምስጋናው ያስታውሳሉ፡፡ ቤታቸውን በወቅቱ ሸጠውት ቢሆን ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣላቸው እንደነበረ በቁጭት ይናገራሉ፡፡ ይህንን ትተው በ50 እና 60 ሺ ብር ግምት ቤታቸው ፈርሶ መሬቱ ተወስዶ ኮንዶሚኒየም ይሰጣችኋል ተብለው ከኖሩበት ሰፈር እንዲወጡ መደረጉን በመግለጽ፤ ይህንን ያህል የካሳ ክፍያ መሰጠቱም ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው። ይህንን ብንጠይቅም ሰሚ አጥተናል ይህ ትክክል አይደለም የሚል ወቀሳም ነው ያቀረቡት።አካባቢውን መልቀቅ የነበረባቸው በ2005 ዓ.ም እንደነበርና የተሠጣቸው ካሳም ትክክል አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ምስጋናው፤ ለዘገዩት ለ56ቱም አቤቱታ አቅራቢዎች የተሰጡት ቤቶች ቀድመው ተገንብተው የነበሩ መሆናቸውን ነው የሚያብራሩት፡፡ ከ56 ቱ መካከልም 39 ሰዎች አራተኛ ፎቅ ላይ ባለሶስት መኝታ ቤት እንደተሰጣቸው ይገልጹና፤ ይህም ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋቸውም ይናገራሉ፡፡
በኤጀንሲው ስህተት በእኛ ላይ ዕዳ ሊጫንብን አይገባም የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ቤት ተገኝቷል ተብለው እጣ ካወጡ በኋላ ውል ሲዋዋሉ የተነገራቸው የክፍያ መጠን ጭማሪ እንዳለው ማረጋገጣቸውንና የተጨመረው ክፍያ ኢ-ፍትሃዊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ቀድመዋቸው ቤት የወሰዱትንና ቅሬታ አቅራቢዎቹ የወሰዱትን በንጽጽር እንደ አብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ተመሳሳይ ካሬ፣ በአንድ ህንጻ ላይ አንደኛ ፎቅ የደረሳቸው የልማት ተነሺ 86 ካሬ አንድ ብሎክ አንድ ኮሪደር ላይ የተከፈለው 210 ሺ ብር ሲሆን አቶ ምስጋናው አራተኛ ፎቅ ተመሳሳይ ካሬ ሜትር ስፋት ወስደው 317 ሺ ብር እንዲከፍሉ እንደተወሰነባቸው ይናገራሉ፡፡ ልዩነት ያለው የገንዘብ አከፋፈል ትክክል አለመሆኑን የሚናገሩት አቤት ባዮቹ የዘገየነው በእኛ ጥፋት ባለመሆኑ በነበረው የክፍያ ተመን ልንከፍል ይገባናል ሲሉም ያመለክታሉ፡፡
እንደ ቤቱ ስፋት ከ108 ሺ እስከ 129 ሺ ብር ልዩነት እንዲከፍሉ መደረጋቸውን የሚናገሩት አቤት ባዮቹ፤ በመቀጠልም ተገቢውን ምላሽ በመነፈጋቸው አቤቱታቸውን ይዘው ወደ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ዕንባ ጠባቂውም ጉዳዩን መርምሮ ከሚመለከታቸው አካላትና ከማስረጃዎች ጋር መዝኖ ምላሽ እንደሰጣቸውም ይመሰክራሉ፡፡ በዕንባ ጠባቂው የተሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ ባለመፈጸሙም አምና በልዩ ሪፖርቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ። ጉዳያቸው በህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እጅ እንደሚገኝም ይናገራሉ። ሆኖም ግን ለመከታተል ባደረጉት ጥረት ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉና ዶክመንታቸው ጠፍቷል መባሉንም ይናገራሉ፡፡
ሌላው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ሃይሌ ዘለቀ ሰኔ ወር 2004 ዓ.ም አካባቢው ለልማት እንደሚፈለግ ተገልጾላቸው እንዲነሱ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ያስታውሳሉ፡፡ ለልማቱ ተባባሪ በመሆን ለመነሳት ፈቃደኛነታቸውን እንዳሳዩም ነው የሚገልጹት፡፡ የሚፈልጉትን ቦታ ወይንም ኮንዶሚኒየም የሚፈልገውን የመኝታ ቤት መጠን ገልጾ መሙላታቸውን ያስታውሱና፤ በ2005 ዓ.ም ለተወሰኑ የልማት ተነሺዎች ምትክ ቤቶችን መስጠት መጀመራቸውን ነው የሚያብራሩት፡፡ ይሁን እንጂ ከእነርሱ መካከልም ባለ ሶስት መኝታ ቤት የጠየቁ የተወሰኑ ሰዎችን እንዲቆዩ እንዳደረጓቸውም ነው የሚገልጹት፡፡
የተወሰኑትን እንዲነሱ በማድረግ ቀሪዎቻችንን ደግሞ እንድንቆይ ተወስኖብን ቆይተናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ‹‹የተነሱ ጎረቤቶቻችን ቤታቸው እየፈረሰ ብቻችንን በመቅረታችን ለችግር ተጋልጠን ስለነበር ቤቶች መፍረስ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2006 ዓ.ም የሚመለከታቸውን አካላት በጠየቅነው መሰረት ባለሶስት መኝታ ቤት እንዲሰጠን እያናገርን ቆይተናል›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በጊዜ መነሳት ይፈልጉ እንደነበረ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን በመጥቀስም፤ ቤት የለም የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው መቆየቱን ነው የሚገልጹት፡፡ ከአመልካቾቹ መካከል ተወክለው የተለያዩ የአስተዳደሩ የጋራ ቤቶች ህንጻ ግንባታዎች በመዘዋወር ዝግ ቤቶች መኖራቸውንና የት የት ቦታ ላይ እንዳሉም መዝግበው ማቅረባቸውን ነው ቅሬታ አቅራቢው የሚናገሩት፡፡
‹‹ይህ እናንተን አይመለከትም›› የሚል ምላሽ ከኤጀንሲው እንደደረሳቸውም አቶ ሃይሌ ይናገራሉ። የተዘጉ ቤቶች እያሉ የለም ተብለው እንዲቆዩ መደረጋቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ቤት እንዲሰጠን ስንወተ ውት የቆየነው ቤቶች እየፈረሱ የነበረበት ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ ስለነበረ ነው የሚሉት አቶ ሃይሌ፤ ይህ ሆኖም ሁለት ዓመታትን እንዲቆዩ መደረጉን ያነሳሉ፡፡ በ2006 ዓ.ም ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ለ56ቱም በተለያዩ ቦታዎች ባለሶስት መኝታ ቤቶች እንደተሰጧቸው፣ ነገር ግን በ2005 ዓ.ም ከተመደቡት ሰዎች ጭማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ መወሰኑንም ነው የነገሩን፡፡
ቤቶች እያሉ በየጊዜው እንዲሰጠን እየጠየቅን አዘግይተውን ተጨማሪ ክፍያ ክፍሉ መባላችን ተገቢነት የለውም፡፡ ችግሩ የእኛ ባለመሆኑ በተጨመረው የኮንዶሚኒየም ክፍያ ተመን መካተት የለብንም። ውሳኔው መስተካከል አለበት ባይ ናቸው አቶ ሃይሌ። መሀል አራት ኪሎ የግል ይዞታችንን ለልማት ለቀን ስናበቃ ከጎረቤቶቻችን ተነጥለን ተጨማሪ ክፍያ ክፈሉ መባሉ በፍጹም አግባብነት የሌለው መሆኑንም ነው የነገሩን፡ ፡ ቅሬታቸውን ይዘው የተለያዩ ቦታዎች መሄዳቸውን በመጥቀስም፤ መፍትሄ በማጣታቸው ወደሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በመሄድ ማስረጃቸውን ማቅረባቸውን ነው ያብራሩት፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከለውጡ በኋላ በመንግስት ምርመራ ተደርጎበት አሳማኝነቱ የተረጋገጠበት ጉዳይ ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቢደርስ መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋን ሰንቀው እንደነበረም ይናገራሉ። ወደጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጉዳዩን ባስገቡ በሳምንቱ የቤቶች ኤጀንሲ በአዳዲስ አመራሮች መመራት በመጀመሩ መፍትሄ እንደሚያገኙ ተነግሯቸው ተመልሰው ጉዳያቸውን እንዲጠይቁ መደረጉንም ይገልጻሉ፡፡ መረጃዎቻቸውን ይዘው መሄዳቸውን በመጠቆምም፤ የተለየ ምላሽ እንዳልተሰጣቸውም ይናገራሉ፡፡ ለውጥ ቢኖርም በላይኛው አመራር ብቻ የተካሄደ ብቻ እንጂ የታችኛውን እርከን ባለመዳሰሱ የቀድሞው አሰራር መቀጠሉን ያሳያል ባይ ናቸው፡፡
አቶ ምስጋናውም ‹‹ምላሽ ይገኛል በሚል ተስፋ አራዳ ክፍለ ከተማና ቤቶች ኤጀንሲ አሰቃይተውናል›› ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም ማመልከታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የጻፉት ደብዳቤ ከስድስት ወራት በኋላ ወደቤቶች ኤጀንሲ መመለሱንና እዛ ሄደው እንዲያናግሩ መታዘዛቸውን ይመሰክራሉ፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ ቤቶች ኤጀንሲ ቢሄዱም ኤጀንሲው የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን ጠቅሶ እንደ አዲስ እንዲያመለክቱ መባላቸውንና ጉዳያቸውን ባግባቡ ተመልክተው ምላሽ ሊሰጣቸው አለመቻሉን ያመለክታሉ፡፡
በመሆኑም ይላሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ቤቱን ለመውሰድ መዘግየት የተፈጠረው በእኛ ስህተት አይደለም፡፡ በኤጀንሲው ስህተት በተፈጠረው መዘግየት ምክንያትም ተጨማሪ ክፍያ በመክፈል ልንቀጣ አይገባም፡ ፡ ስለዚህ በወቅቱ ለልማት ተነሱ በተባልነው ወቅት በነበረው የዋጋ ተመን ልንከፍል ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ለዕንባ ጠባቂ የቀረበው አቤቱታ በአጭሩ
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 211/ 1992 ዜጎች ተፈጽሞብናል የሚሉትን አስተዳደራዊ በደሎች ተቀብሎ ይመረምራል፡፡ የቀረበው አቤቱታ ትክክል ሆኖ ሲያገኘው ወይም ጥፋት መሆኑን ሲያምንበትም እንዲታረም የማድረግ ስልጣንና ተግባር ተጥሎበታል። በእዚህ መሰረትም ከአራት ኪሎ የባሻ ወልዴ ችሎት ቁጥር ሁለት የልማት ተነሺዎች የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አም ኖ መርምሯል፡፡
በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ቀኘ እንደሚናገሩት፤ አመልካቾቹ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 የባሻ ወልዴ ችሎት ቁጥር ሁለት የግል ባለይዞታ የልማት ተነሺዎች እነምስጋናው ከበደ (56) ሰዎች ናቸው፡፡ በልማት ምክንያት ቤታቸው
ሲፈርስ በአካባቢው ነዋሪ ከነበሩት ባለይዞታዎች መካከል ለተወሰኑት በ2005 ዓ.ም ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤት የተሰጣቸውና ክፍያቸውን በወቅቱ ያጠናቀቁ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም 56 የሚሆኑት ቅሬታቸውን ለዕንባ ጠባቂው ያቀረቡት አመልካቾች የከተማ አስተዳደሩ ምትክ የሚሆኑ ቤቶች ተሰርተው እያለ በወቅቱ ምትክ ቤት የለም በማለት ሊሰጠን ባለመቻሉ ቅሬታ ተፈጥሮብናል ማለታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ቅሬታቸውንም በተደጋጋሚ ጊዜ አቅርበው ጉዳዩ ከታየ በኋላ ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤት በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም እንደተሰጣቸው ይገልጻሉ፡፡ የተጠየቁት ክፍያ ግን ከእነርሱ ጋር የልማት ተነሺ ሆነው በ2005 ዓ.ም ምትክ የተሰጣቸው የልማት ተነሺዎች ከከፈሉት ክፍያ ጭማሪ ያለው በመሆኑና ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤቱን ሳያገኙ የቀሩት በአስተዳደሩ ችግር ምክንያት መሆኑን በመጥቀስም የተደረገባቸው ጭማሪ ፍትሃዊ ባለመሆኑ ጉዳዩ እንዲታይላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀው መፍትሄ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ አስተዳደራዊ በደል ተፈጽሞብናል በማለት አቤቱታ ማቅረባቸውን ያብራራሉ፡፡
በዕንባ ጠባቂ ተቋም የተደረገ ምርመራ
ዕንባ ጠባቂው የቀረበውን አቤቱታ፣ ኤጀንሲው የሰጠውን ምላሽ፣ በአካል ከኤጀንሲው የሚመለከታቸው አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶች እና ተያይዘው የቀረቡ ማስረጃዎችን አገናዝቧል። ቀጥሎም አቤቱታ አቅራቢዎቹ በ2004 ዓ.ም ሲነሱ ምትክ ባለ ሶስት መኝታ ቤቶች ተገንብተው ነው የተከለከሉት ወይስ አልነበሩም? አቤት ባዮች ቤቱን ሳይረከቡ የቀሩት በራሳቸው ጥፋት ነው ወይስ አይደለም? የሚሉና በ2004 ዓ.ም የልማት ተነሺዎች እንደመሆናቸው ቤት የለም በማለት በ2006 ዓ.ም ባለው የቤት ዋጋ ማስተናገድ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? የሚሉ ጭብጦችን ለይቶ መርምሯል፡፡
በወቅቱ ቤቶች እያሉ ተከለከልን ለሚለው ቅሬታ እንደማስረጃ ከተወሰደው መካከል አቶ ጥላሁን አበበ የተባሉ ከአቤት ባዮች ጋር ይኖሩ የነበሩት ግለሰብ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ጥላሁን ከልማት ተነሺዎች መካከል በ2005 ዓ.ም ባለ ሶስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ሰሚት ቁጥር አንድ ሳይት ብሎክ ቁጥር 368 አንደኛ ፎቅ የተሰጣቸው ናቸው። እርሳቸውን ለማስረጃነት ያክል የምርመራ ቡድኑ አነጻጽሮ አቅርቧል፡፡ በወቅቱ ቤት የለም ተብለው ከተከለከሉት አቤት ባዮች ውስጥ ለአቶ ምስጋናው ከበደ አቶ ጥላሁን በወሰዱበት በዚሁ ሳይትና ብሎክ አራተኛ ፎቅ የቤት ቁጥር 368/26 በሰኔ 2006 ዓ.ም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለቤቱ የተጠየቁት ክፍያ ግን በዛው ህንጻ ላይ ካሉት የልማት ተነሺ በአንድ መቶ ሺ ብር ጭማሪ እንዳለው መርማሪ ቡድኑ አረጋግጧል።
የምርመራው ውጤት
በ2005 ዓ.ም ለአቤት ባዮች ባለ ሶስት መኝታ ምትክ ኮንዶሚኒየም የለም ወይም አልተገነባም በተባለበት ወቅት ከአቤት ባዮች ጋር እኩል በልማት ለተነሱት አቶ ጥላሁን ባለ ሶስት መኝታ ምትክ ኮንዶሚኒየም መሰጠቱን የምርመራ ቡድኑ ውጤት ይጠቅሳል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ በዚሁ ህንጻ ላይ ከአቤት ባዮች አንዱ ለሆኑት አቶ ምስጋናው ከበደ በ2006 ዓ.ም ባለ ሶስት መኝታ ምትክ ኮንዶሚኒየም ከአንድ መቶ ሺ ብር በላይ ጭማሪ በማድረግ መተላለፉን አስመልክቶ የቤቶች ኤጀንሲ ጉዳዩን የሚያስቀይር ተቃራኒ ማስረጃ አልላከም። ይልቅም በ2006 ዓ.ም የተመደቡት ቤቶች በ2005 ዓ.ም ተሰርተው ያለቁና ለሌሎች ሰዎች ዕጣ ያልወጣባቸው ስለመሆናቸው የአቤት ባዮቹ ማስረጃ የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
ከኤጀንሲው ኃላፊዎችና ከባለሙያዎቹ ጋራ በአካል ውይይቶች በተደረጉበት ወቅት ግንባታቸው ለተጠናቀቀ ግን ለተጠቃሚዎች ባልተላለፉ ክፍት ቤቶች ላይ ወለድ የሚከፈል በመሆኑ ቤቶቹ ተሰርተው ባለቁበት የግንባታ ጥሬ ዕቃ ብቻ ሳይሆን ክፍት ለቆዩበት ወለድ ጭምር ተጠቃሚዎች እንዲከፍሉ ያደርጋል የሚለውን አስመልክቶም በ2006 ዓ.ም የተላለፉት ባለ ሶስት መኝታ ቤቶች በ2005 ዓ.ም ተሰርተው ያለቁ ከሆነና አቤት ባዮች በወቅቱ መረከብ ሲኖርባቸው በራሳቸው ጥፋት ዘግይተው ካልሆነ በስተቀር በልማት ከተነሱበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለመረከብ ጥያቄ ሲያቀርቡ ለነበሩ አቤት ባዮች ተገንብተው ያለቁ ቤቶችን በአስተዳደሩ ጥፋት አዘግይቶ በ2006 ዓ.ም ባለው የመተላለፊያ ዋጋ ተረከቡ ማለት አቤት ባዮች ላላጠፉት ጥፋት እንደመቅጣት ይቆጠራል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የልማት ተነሺዎች እንደመሆናቸው ከሌሎች ቤት ፈላጊዎች ቅድሚያና ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በመሆኑም አንድ የኮንዶሚኒየም ህንጻ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፈው የህንጻ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በመሆኑ፣ አንድ ሙሉ ህንጻ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ግማሹን ፎቅ በአንድ ዙር የኮንዶሚኒየም ዋጋ ቀሪውን ፎቅ በቀጣይ ዙር በተጋነነ የዋጋ ልዩነት ከአንድ አካባቢ ለልማት በተነሱ ተጠቃሚዎች ማስተላለፍም ተገቢ አይደለም፡፡
በልማት ተነሺዎች መካከል አድልዎ የሚፈጥርና ተሰርተው ያለቁ ግን በኤጀንሲው መዘግየት ምክንያት ለልማት ተነሺዎች ያልተላለፉ ቤቶች ሳይተላለፉ ክፍት ለቆዩበት ጊዜ እንዲከፍሉ መደረጉ ተጠቃሚዎችን ተጎጂ ያደርጋል፡፡ በኤጀንሲው ያለውን አሰራርም ፍትሃዊና አሳማኝነትንም ያሳጣል። በመሆኑም የዋጋ ልዩነት በማድረግ እንዲከፍሉ ማድረጉ አግባብ ሆኖ እንዳላገኘው ዕንባ ጠባቂው አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ ምላሽ
ዕንባ ጠባቂው በጉዳዩ ላይ የሰጠውን የመፍትሄ ሃሳብ አስመልክቶ ኤጀንሲው ለዕንባ ጠባቂው ምላሹን በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሚያዝያ 09 ቀን በወቅቱ ለኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ይባል ለነበረው ተቋም በአለው አሰራር መሰረት ለልማት ተነሺዎች በጊዜው 100 ተገንብተው ከሚጠናቀቁ ቤቶች ቅድሚያ እየተሰጡ እንዲስተናገዱ መባሉን ይጠቅሳል። ከእዚህ ውጪ አመልካቾች የሚመርጡበት፣ ከእዚህ ሌላ ሊሰጠን አይገባም የሚሉት ሳይት መረጣ በከንቲባ ጽህፈት ቤት በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ተጠቅሶ እንደተጻፈላቸውና በአለው አሰራር መሰረት እንዲስተናገዱ መደረጉን ያመለክታል፡፡
በመሆኑም ባለጉዳዮች ያልተስተናገዱት ሳይት እየመረጡ በሚፈልጉት ሳይት ቤት እንዲሰጣቸው ስለሚጠይቁ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እንደገናም 100 ቤቶች እየተሰጣቸው እንዲስተናገዱ መደረጉ በወቅቱ የቤት እጥረት መኖሩን ያሳያል ሲልም ይገልጻል። በመሆኑም በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ሲስተናገዱ የልማት ተነሺዎች በየወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣው የቤት መሸጫ ዋጋ መሰረት እንዲተላለፉ መደረጉን ያስቀምጣል፡፡
በሌላ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ በወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 ክፍል ስድስት አንቀጽ 26 ነጥብ አንድ መሰረት ከግል ይዞታቸው በልማት ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች ከመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ተጣርቶ እና ተረጋግጦ በሚቀርብ የምትክ ቤት ጥያቄ መሰረት የቤት ምደባ ስራው ይከናወናል፡፡ ለሁሉም የልማት ተነሺዎች ምትክ ቤት ምደባ የሚካሄደው የቤት አቅርቦት ችግር ከሌለ በምርጫቸው መሰረት በዕጣ ይስተናገዳሉ፡፡ ግን የቤት አቅርቦት እጥረት ካጋጠመ ባለው የቤት አቅርቦት መሰረት እንዲስተናገዱ ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም በወቅቱ የነበሩት የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ የባለ ሶስት እና የባለ ሁለት መኝታ ቤት በወቅቱ እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።
መመሪያው የልማት ተነሺዎቹ ባለ ሶስትና ባለ ሁለት መኝታ ቤት በማይኖርበት ጊዜ ተነሺዎች ባለ አንድ መኝታ ቤት የመረከብ ግዴታ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ሆኖም ኤጀንሲው ባቀረበው አማራጭ ለመስተናገድ ያልፈለገ ተነሺ የአስተዳደሩን መስተንግዶ እንዳልፈለገ ተቆጥሮ የግል አማራጭ የመወሰን መብቱ የተጠበቀ ነው ስለሚል በወቅቱ ባለ ሶስት መኝታ ቤት ለማግኘት እየጠበቁ እያለ የማስተላለፊያ ዋጋው ጭማሪ ስለተደረገ እንደማንኛውም የልማት ተነሺ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ ስለሆነም የከተማ አስተዳደሩ ባጸደቀው የማስተላለፊያ የዋጋ ተመን መሰረት ተስተናግደዋል። የዋጋ ተመኑ ጸድቆ ለመስሪያ ቤቱ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ አናስተናግድም፡፡ በመሆኑም ወደ ኋላ በመመለስ ቀደም ሲል ሌሎች የልማት ተነሺዎች የቤት ሽያጭ በፈጸሙበት የዋጋ ተመን ለማስተናገድ እንቸገራለን በማለት ምላሹን አሳውቋል፡፡
የዕንባ ጠባቂ አቋም
ከኮንዶሚኒየም ቤት ድልደላ መመሪያ ጋር በተያያዘ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ጉዳዩን እንደማይፈጽም ጠቅሶ የላከውን ምላሽ አስመልክተው ሲገልጹ መመሪያው ሁለት ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ የሚሰራበት ምክንያት እንደሌለ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ቀኘ ይናገራሉ፡፡ እንደገናም ከፍትሃዊነት አንጻርም እንደዕንባ ጠባቂ ተቋም አቋም ተገቢ እንዳልሆነም ያመለክታሉ፡፡ መመሪያው የወጣው በ2008 ዓ.ም መሆኑን በመጥቀስም፤ ለሰዎቹ ቤቶቹ የተላለፉት ደግሞ በ2006 ዓ.ም መሆኑንና በወቅቱ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ለልማት ተነሺዎች ቤት ሲያስተላልፍ የነበረው ፍላጎታቸውን ጠይቆ በፍላጎታቸው መሰረት ያስተናግድ እንደነበረም ነው የሚያብራሩት፡፡ እንደ አካሄድም ሊተገበር የሚገባው ይህ አይነት አሰራር ነው ባይ ናቸው፡፡
ምክንያቱም ይላሉ ዳይሬክተሩ፤ ሰዎች በነበራቸው የግል ይዞታ ውስጥ ያላቸውን የቤተሰብ ሁኔታና አብረዋቸው የነበሩ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ሲኖሩ ቆይተዋል፡፡ ሲለቁም ሊሰጣቸው የሚገባው የቤተሰባቸውን ብዛት በመመልከት ነው፡፡ ባለ ሶስት እና ሁለት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ቤት ጠይቀው ከሌለ ባለ አንድ መኝታ ቤት እንዲወስዱ በመመሪያ የተጣለው እርሱም ከሌለ መብቱን ይተዋል በሚል መመሪያው ያስቀመጠው ከፍትሃዊነት አንጻር ችግር ነው ተብሎ ይወሰዳል፣ የዜጎችንም ህገ መንግስታዊ መብት ይቃረናል ይላሉ፡፡ ሰዎች በልማት ምክንያት ላጡት ንብረት ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብት አላቸው የሚል አቋምም ይዘዋል፡፡
ሰዎች በልማት ምክንያት ሲነሱ መንግስት ከልማቱ የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግና ልማቱን በበጎ መልኩ እንዲመለከቱት ማድረግ ይኖርበታል። የነበሩበትን ቦታ ለቅቀው በቤት ጥበትና በሌሎች ጉዳዮች ችግር ውስጥ የሚገቡበት ምክንያት መፈጠር የለበትም። በመሆኑም በእዚህ ጉዳይ መመሪያው መጠቀስ የለበትም የሚል አቋም ዕንባ ጠባቂው መውሰዱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ሌላ በምክንያትነት የተጠቀሰውን ተገንብተው ከሚጠናቀቁ ቤቶች በየጊዜው 100 ቤቶች ቅድሚያ እየተያዙ እንዲስተናገዱ ከእዛ ውጭ ያለውን ማስተናገድ አይቻልም በሚል ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተጻፈን ደብዳቤ በምክንያትነት በመጥቀስ ላለማስተናገድ በቁጥር የሚቀርበውን አስመልክቶ እንዳመለከቱትም በቁጥር ተወስኖ የሚገደብ አይደለም፡፡ ሊወሰን የሚገባው አለማዋለሁ ተብሎ በተያዘው ቦታ ልክ ሊሆን ይገባዋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ምክንያቱም 200 ሰው በልማት ተነስቶ 100 ቤት ነው የተያዘው ማለት ኢ-ፍትሃዊ ነው፡፡ መመሪያም ህግም ሊያስረው አይገባም፡፡ ሰዎቹ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ እንዳያገኙ የገደባቸው ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም ደግሞ ቤቶቹ በሚፈልጉት መሰረት ቤት እንዲደለደልላቸው የተጻፈ ደብዳቤ በዕንባ ጠባቂው እጅ አለ። በ2006 ዓ.ም የተፈጸመውም እርሱን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ማለትም ከኮንዶሚኒየም ቤት ድልደላ ጋር ተይይዞ የወጣውን መመሪያ ቁጥር 01/2008 እና ከከንቲባ ጽህፈት ቤት አዲስ ከሚሰሩ ቤቶች በየጊዜው ከሚጠናቀቁ ቅድሚያ እየተያዙ እንዲስተናገዱ ከእዛ ውጭ ያለውን ማስተናገድ አይቻልም በሚል የተጻፈውን ደብዳቤ በምክንያት ተጠቅሶ ኤጀንሲው የመፍትሄ ሃሳቡን ላለመፈጸም ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ አይደለም። ጉዳዩን ይዘን በአካል በማነጋገር የተሰጠን ምላሽም ይኸው ነው ሲሉ አቶ መንግስቱ ገልጸዋል፡፡
ከዕንባ ጠባቂው የተሰጠ የመፍትሄ ሃሳብ
ከባሻ ወልዴ ችሎት ቁጥር ሁለት የግል ባለይዞታ የልማት ተነሺዎች እነምስጋናው ከበደ (56) ሰዎች በወቅቱ ምትክ ቤቶቹን ሳያገኙ የቀሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ችግር ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም አቤት ባዮቹ ምትክ ቤት ማግኘት ይገባቸው በነበረበት ወቅት ማለትም በ2005 ዓ.ም ባለው ባለ ሶስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት በሚተላለፍበት ዋጋ በማስከፈል ከዚህ ቀደም እንዲከፍሉ የተጠየቁትን ዋጋ ማስተካከያ በማድረግ ውጤቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቁ ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ማሳሰቡንም ነው አቶ መንግስቱ የሚያብራሩት፡፡
ሆኖም የተለየ ወይም አዲስ ነገር ከኤጀንሲው አልተገኘም የሚሉት አቶ መንግስቱ፤ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሰጠው የመፍትሄ ሃሳብ የማይፈጸም ከሆነ ዕንባ ጠባቂው ተጠሪ ለሆነለት ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በልዩ ሪፖርት ማሳወቅ ይጠበቅበታል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ የእነምስጋናው ከበደ (56) ሰዎች ጉዳይን አስመልክቶም ግኝቱን ተጠሪ ተቋሙ አልፈጽምም ያለበትን ምክንያት በቂና አሳማኝ አለመሆኑን ጠቅሶ በልዩ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ነው የሚናገሩት፡፡
በመንግስት መዘግየት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን ወደ ዜጎች ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም። ጫናውም እነርሱ ላይ ሊያርፍ አይገባም ይላሉ። በመሆኑም የመፍትሄ ሃሳቡ በምክር ቤቱ በኩል ሊፈጸም ይገባዋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ በምክር ቤቱ በኩል ጉዳዩ የተመራለት የሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚሰጠው ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑንም ነው የሚጠቁሙት፡፡
የህግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
የቋሚ ኮሚቴውን እየመሩ የሚገኙት ኃላፊዎች በ2011 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የተወከሉ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። ስለጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌላቸውም ከክፍሉ ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም የባለጉዳዮቹ ተወካይ (አቶ ምስጋናው) ጋር ከትናንት በስቲያ ስልክ በመደወል እንደገና ፋይላቸውን እንዲያመጡ መደረጉንና ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ተመልክቶት ምላሽ ለመስጠት እንደወሰነ ሰምተናል፡፡
አቶ ምስጋናው ከቋሚ ኮሚቴው ተደውሎ ‹‹እባክዎ ዶክመንቱ ስለጠፋብን ኮፒውን እንደገና ያስገቡልን›› መባላቸውን፣ ዶክመንቱንም ትናንት ጠዋት አስፈርመው ማስረከባቸውን ነግረውናል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 14/2012
ዘላለም ግዛው