
– አቶ ቦንሳ ባይሳ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር
መንግሥት የተስማሚነት ምዘና አካላት ብቃታቸው በአክሬዲቴሽን ተቋም እንዲረጋገጥ የጥራት ፖሊሲ ነድፎ እየሠራ ይገኛል። ለዚህም ያበረታታል ይደግፋል። የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ለማሟላት የፍተሻና የኢንስፔክሽን ሥራዎች የአክሬዲቴሽን ዕውቅና ባለው ወይም ውክልና በተሰጣቸው የተስማሚነት ምዘና አካላት ይሰጣል፤ ብሄራዊ የአክሪዲቴሽን ተቋም የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት የአክሬዲቴሽን እውቅና ይሰጣል።
የዝግጅት ክፍላችን ተቋሙ የተስማሚነት ምዘና ተቋማትን በምን መልኩ ነው አክሬዲት የሚያደርገው? ባለፉት ወራት ምን አቅዶ ምን ሠራ? በሚሉትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የ2017 በጀት ዓመት ተጠናቋልና በበጀት ዓመቱ ምን ምን አንኳር ተግባራት ተከናወኑ? ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ቦንሳ፡- ተቋማችን በዋናነት የተስማሚነት ምዘና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በተቀመጠው ዓለም አቀፍ አክሬዲቴሽን ስታንዳርድ መሠረት አክሬዲት ያደርጋል። እነዚህ አክሬዲት የምናደርግባቸው ዘርፎች የምንሰጠው የሰርተፊኬሽን አገልግሎት ነው።
እንደተባለው የበጀት ዓመቱ መጨረሻ ነው፤ በተለይ በሜዲካል ላቦራቶሪ በዓመቱ ውስጥ እንፈጽማለን ብለን ያቀድነው ወደ 23 ነበር፤ ነገር ግን ከታቀደው በላይ ወደ 31 ተቋማትን አክሬዲት ማድረግ ችለናል። በፍተሻ ላቦራቶሪ ወይም ካሊብሬሽን ውጤታማ ዓመት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
እንደሚታወቀው አክሬዲቴሽን በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው። የሚሰጠው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት በተለይ አንደኛ ንግድን ያሳልጣል። በመሆኑም እየተሠራ ያለው በዓለም አቀፍ ሥርዓት መሠረት በአንድ ስታንዳርድ በአንድ ፍተሻ ሁሉም ሀገራት ላይ ተቀባይነት እንዲኖረው ነው። ይህም ከሀገር ጋር እንዲሁም ከጥራት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ አክሬዲቴሽን የሰውን ጤና፣ የአካባቢን ጤና እና አጠቃላይ የንግድ ተወዳዳሪነትን የሚያስጠብቅ የጥራት ማረጋገጫ አሠራርና ሥርዓት ነው። እናም እየሠራን ያለነው በዚያው መሠረት ነው።
በጥቅሉ በፍተሻ ላቦራቶሪ፤ በካሊብሬሽን፣ በኢንስፔክሽን፣ በሰርተፊኬሽን እና በሜዲካል ላቦራቶሪ ዓለም አቀፍ እውቅናም አለን። እንደ አሕጉርም በአፍሪካ አክሬዲቴሽን አባል ነን። የዓለምአቀፍ አክሬዲቴሽን ፎረም (International Accreditation Forum – IAF) እና የዓለምአቀፍ የላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን ትብብር (International Laboratory Accreditation Cooperation – ILAC) አባል ነን።
አዲስ ዘመን፡- ከፍተሻ ጋር በተያያዘ ላቦራቶሪዎቹ የሚገለጹት እንዴት ነው?
አቶ ቦንሳ፡– ከፍተሻ ጋር በተያያዘ ትልልቅ የሚባሉ የምርምር ተቋማትን ለምሳሌ ከግብርና ባለስልጣን ባለፈው ወደ ውጭ የሚወጡ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶችን የተለያዩ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ እና የእንስሳት ውጤቶችን የሚፈትሽ ትልቅ ተቋም አክሬዲት አድርገናል።
እነዚህ አክሬዲት የምናደርጋቸው ውስን ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ውጤታቸው በሀገሪቷ የንግድ ተወዳዳሪነት ላይና ጤንነትን ከመጠበቅ አኳያ የሚታዩ ናቸው፤ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንደመድኃኒት፣ የግብርና ግብዓትና ሌሎች የኬሚካል አይነቶች ጭምር እኛ አክሬዲት ባደረግናቸው ላቦራቶሪዎች ሲፈተሹ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ያሟሉ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ነው። አክሬዲት የተደረገ ላቦራቶሪ ለተቆጣጣሪው፣ ለአምራቹም ሆነ ለተጠቃሚው ዋስትናን የሚፈጥር ነው።
በዓለም ላይ መግባባት የሚቻለው ትልቁ የመግባቢያ ቋንቋ ቢኖር ጥራት ነው። ምርት ሲመረት ልንግባባ የምንችለው በጥራት መሠረተ ልማት ወይም ደግሞ አክሬዲቴድ በሆነ የተስማሚነት ምዘና ተፈትሾ የተመሰከረለት ምርት በእኛም ሀገር ላይ ተቀባይት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህ እምነት ይፈጥራል። ለሻጩ፤ ለተቀባዩ እና ለአምራቹ መተማመን እንዲኖር ያደርጋል። አሁን ላይ እንደከዚህ በፊቱ ጥራት የቅንጦት ሳይሆን ወሳኝ መሆኑን ያሳያል። ንግድ ላይ ያለአክሬዲቴሽን መወዳደር እንደማይችል ማሳያ ነው።
በአህጉርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም በንግድ እየተሳሰረ ነው። ስለዚህ ይህ ትስስር በጥራት ላይ ካልተመሠረተ ወደ ሀገር የሚገቡ ባዕድ ነገሮች በሰው ላይ፣ በአካባቢ እና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን መቆጣጠር አይቻልም። የሚቻለው የጥራት መሠረተ ልማት አቅም ማጎልበት ስንችል ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ትልቁ አቅማቸውን የሚፈትሽ ነው።
የፍተሻ አገልግሎት ጥራት እናረጋግጣለን ስንል ለምሳሌ የፍተሻ አገልግሎት የሚሰጥ የምዘና ተቋማትን የሰው ኃይል ተወዳዳሪነት ብቃትን ያረጋግጣል። የአሠራር ሥርዓትንም ያረጋግጣል። በተጨማሪም እነዚህ የፍተሻ አገልግሎት ሲሰጡ በየትኛው ስታንዳርድ ነው የሚለው የዶክሜንቴሽን እንዲሁም የአመራር ሥርዓት አቅምን ያረጋግጣል። የሚጠቀሙት ላቦራቶሪ በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት በጊዜ ‹‹ካሊብሬት›› ስለመደረጉ እነዚህን በሙሉ አይቶ የሚወጣው ምርት በዚያ ሂደት ውስጥ አልፎ ጥራቱን የጠበቀና በየትኛውም ዓለም አቀፍ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንሰጣለን። እናም ይህ አጠቃላይ የአንድ ጊዜ ሥራ ብቻ ሳይሆን ጥራት ሥርዓት እንዲሆን ሥርዓትን የመትከልና የመገንባት ሥራ ይሠራል። የአደጉ ሀገራት ዛሬ ላይ ላሉበት ደረጃ የደረሱት በዚህ መልኩ ነው። ስለሆነም እኛ እንደሀገር ይህን ለማድረግ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭም እንዲሆኑ ለማስቻል በተጨባጭ የተሠራ ነገር አለ?
አቶ ቦንሳ፡- በእርግጥ እኛ ቀጥታ ምርቶቹ ዘንድ ሄደን አንሠራም። የምንሠራው ሶስተኛ ወገን (ገለልተኛ) በመሆን የምንሰጠው የጥራት ማረጋገጫ ነው። ለምሳሌ አሁን አምራቾች የራሳቸው የመጀመሪያ ደረጃ ላቦራቶሪ አላቸው። አስቀድሜ የጠቀስኩት የግብርና፤ የእንስሳት ተዋጽኦና የእንስሳት ውጤቶችን የሚያረጋግጥ ላቦራቶሪ አክሬዲት ሲደረግ በተዘዋዋሪ ወደ ውጭ የምንልካቸውን የእንስሳት ተዋጽኦዎችን፣ ሌሎች ነገሮችን እዚያው ጥራቱ የተረጋገጠ ሆኖ እንዲወጣ መጀመሪያ ላቦራቶሪውን አክሬዲት እናደርጋለን።
ይህን ስንል ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ባለሙያዎቹ ጭምር ቴክኖሎጂው በደረሰበት የእውቀት ደረጃ ስልጠና ስለመውሰዳቸው፤ ብቁ ስለመሆናቸው፤ የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጠ ስመሆኑ ባለሙያዎቹን ጭምር እናያለን። ሌላው ላቦራቶሪው ጭምር በውድ ዋጋ ስለተገዛ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት በየጊዜው ‹‹ካሊብሬት›› ስለመደረጉ የሚሰጠው ውጤት ትክክለኛና ታማኝ ስለመሆኑ በተቀመጠው አሠራር ሥርዓት መሠረት እንፈትሻለን።
ሌላው የሚጠቀሙት የጥራት ማንዋሎች አሉ። ጥራት በአጋጣሚ የሚመጣ ነገር ሳይሆን ሥርዓት ያስፈልገዋል። የጥራት ማንዋል የምንላቸው ተቋሙ በአጠቃላይ የሚመራበት የጥራት ዓላማ ማንዋል ሲሆን፣ ራሳቸውን የመዘኑበት ማንዋል ያስፈልጋል። ጥራት በባለሙያው ዘንድ ስለመታወቁ ጭምር የምናይበት ሁኔታ አለ። ይህን በሀገር ውስጥ በራሳቸው በመጀመሪያ ደረጃ የምርምር ተቋማት አክሬዲት እናደርጋለን።
በተዘዋዋሪ የሚመጡ ምርቶች አሉ። ለምሳሌ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ይመጡና የተስማሚነት ምዘና ማለትም የኢትዮጵያ ተመስማሚነት ምዘና ሊሆን ይችላል፤ አሁን ባለው ንግድ አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን አክሬዲት እናደርጋቸዋለን። እንደዚያ ማለት የሚመረቱ ምርቶች ወደ እነዚህ ተቋማት ሲመጡ እኛ አክሬዲት ባደረግነው የተስማሚነት ምዘና ተቋማት ተፈትሸው መስፈርቱን ማሟላታቸው ሰርቲፋይድ ከሆኑ በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት በእኛ አክሬዲት ተደርገው ሰርቲፋይድ ይደረጉና የትም ሀገር ሔደው ምርቶቻቸውን የሚሸጡበት አሠራር ነው። ቀጥታ አምራቹም ዘንድ አክሬዲት ለመሆን ፍላጎት ካላቸው የአምራቹ ላቦራቶሪ አክሬዲት ይደረጋል። በዋናነት እነዚህ የተስማሚነት ምዘና የሚባሉት ተቋማትን አክሬዲት ይደረጋሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ ሀገር የሚገቡ እንደ የኤሌክትሪክ የቆርቆሮና ሌሎች ምርቶች የቁጥጥር ሁኔታው እንዴት ይታያል?
አቶ ቦንሳ፡- የቁጥጥር ሥራ እኛን አይመለከትም። ይህን ስንል እኛ ተጠሪ የሆንበት ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አለ። በተቋሙ የወጭ ገቢ ምርቶችን ሁሉንም ዘርፍ የሚቆጣጠር ዘርፍ በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ የሚመራ አለ። ከውጭ የሚገቡ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ፣ የቆርቆሮ፣ በተለይ አስገዳጅ ስታንዳርድ አላቸው። ይህም ማለት ደረጃውን ሳያሟሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት አይችሉም። እነዚህን ናሙና ወስዶ የሚፈትሸው ማን ነው? ሲባል እኛ አክሬዲት ያደረግነው የተስማሚነት ምዘና ተቋም ነው።
ይህም ማለት በቀጥታ እኛ ተቋም ገቢ እና ወጭ ምርቶችን የመፈተሽ ማንዴቱ የለንም። እኛ ሶስተኛ ወገንና ገለልተኛ ነን። እነዚህን የሚፈትሹ ተስማሚነት ምዘና የምንላቸው ምርቶች የጥራት የደረጃ የምስክር ወረቀት የሚሰጡ፤ የሚመጡ ምርቶች ኢትዮጵያ ባወጣችው ሀገር አቀፍ ወይም ዓለምአቀፍ ስታንዳርድ መሠረት አሟልተው ስለመግባታቸው ፈትሾ ውጤቱን የሚሰጠውን ተቋም ብቻ አክሬዲት እናደርጋለን። ይህ ሲባል የመፈተሽ አቅሙ፣ የሰው ኃይል፣ የአሠራር ሥርዓት አለው ማለት ነው። ስለዚህ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ናሙና ይወስዱና በዚያ አግባብ ፈትሸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ተቆጣጣሪው አካል ሌላ ነው። እኛ የፍተሻ አገልግሎት የምንሰጠው ለአብነት የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና አገልግሎትን አክሬዲት እናደርጋለን። ሌሎችም የኢንስፔክሽን አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን አክሬዴት እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- አክሬዲት የምታደርጓቸውን ተቋማት የምትቆጣጠሯቸው በምን መልኩ ነው? ሥራቸውን በአግባቡ ስለመሥራታቸው ያለው ክትትል ተቋሙን ይመለከታል?
አቶ ቦንሳ፡– እኛ አክሬዲት ያደረግናቸውን የተስማሚነት ምዘና ይሁኑ ሌሎችም ለምሳሌ የሜዲካል ላቦራቶሪ ተቋማት ሊሆንም ይችላል፤ በየስድስት ወሩ የክትትል ሥራ ይሠራል።
ክትትል ሲባል በወሰዱት ሰርቲፊኬት እውቅና ልክ ነው እየሠሩ ያሉት? ሥርዓቱስ በዚያው ልክ እየቀጠለ ነው? በሚለው እና በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የክትትል ሥራ ይሠራል። ያንን የማያሟሉ እና በዚያ ልክ የማይቀጥሉ ከሆነ የሰጠነው የምስክር ወረቀት ምልክት ይደረግበትና ለሁሉም የምናሳውቅበት አሠራር አለን። ስለዚህ አንድ ጊዜ አክሬዲትድ ስለሆነ እስከ አራት ዓመት ይቆያል ማለት አይደለም። ስለዚህ የክትትል ሥራ ይሠራል። ከደንበኞች፣ ከሠራተኞች፣ ከተቆጣጣሪ አካላት ጥቆማዎች ከመጡ፤ እንዲሁም በወሰዱት አሠራር ወይም እውቅና ልክ እየሠሩ አይደለም የሚል ጥቆማም ከመጣ ወዲያውኑ የምንፈትሽበት የአሠራር ሥርዓት አለን።
አዲስ ዘመን፡- በገለጹት መንገድ ክትትል አድርጋችሁ እውቅናውን ያሳጣችሁት ተቋም ይኖር ይሆን?
አቶ ቦንሳ፡– በዚህ መልኩ እውቅናውን ያሳጣነው ተቋም የለም። እውነት ለመናገር ቅድም እንዳልኩት ወደዚህ አሠራር የሚመጡት ተገድደው አይደለም። እየመጡ ያሉት ዓለም ላይ ያለው ውድድር ታማኝነትን ወይም ደግሞ ገበያው ላይ ለመቆየት አክሬዲቴሽን ወሳኝ እንደሆነ እና ጥቅሙን የተረዱት ናቸው። ለአብነት አሁን ላይ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ከሀገር አቀፍ አልፈው ወደ አህጉር አቀፍ እየተሸጋገሩ ነው። ይህ ሲሆን መተማመን ይፈጥራል፤ ያለምንም እንግልት ከጊዜ፤ ከዋጋ አንጻር የምርቶቻቸውን ብዙ ነገር ይቆጥባሉ። ስለሆነም እስካሁን ከሰው ኃይል ጋር በተገናኘ ካልሆነ በስተቀር ሥራቸውን እውቅናቸውን የተነጠቁ የሉም።
አዲስ ዘመን፡- ቁጥጥሩ እስክታች ስላልሆነ ሸማቹ አካል እንዳይጎዳ እየተደረገ አይደለም እየተባለ ይነገራልና በእርሶ አመለካከት ከተቋሙና ተቋሙ እውቅና ከሚሰጣቸው ተቋማት ጋር ሲነጻጸሩ መከላከል ተችሏል ማለት እንችላለን?
አቶ ቦንሳ፡- አሁን ሁሉም የራሱን ድርሻ መለየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ወደሀገር የሚገቡ ምርቶች ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት የጥራታቸው ደረጃ ይፈተሻል፤ ደረጃ የማያሟላ ከሆነ ወደ መጣበት ሀገር እንዲመለስ ወይም እንዲወገድ ይደረጋል። በተለይ ይህን በሚመራው ገቢ ምርቶችን በተመለከተ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የቁጥጥር ዘርፉ የሚከታተላቸው ናቸው። በየማምረቻው ማለትም በየኢንዱስትሪው ኢንስፔክት ይደረጋል። የጥራት ደረጃቸውን ያሏሟሉት ይታሸጋሉ። በተጨማሪም ምርት እንዲሰበስቡ ከመደረጉ ባሻገር በሕግ እንዲጠየቁ የሚደረግበት ሁኔታ አለ።
ማህበረሰቡ ምርት ሲገዛ የት፤ መቼ እንደተመረተ፤ የአገልግሎት ጊዜው የሚያበቃበት መቼ ነው፤ እንዴት ነው የመጣው የሚለውን ነገር የማየት ልምዱ ብዙም የለንም። ስለዚህ ይህን ጉድለት በመሙላት እንደ ሀገር የጥራት ጉዳይ ባህል መሆን አለበት። ይህን ልምድ ማጎልበት ይጠይቃል። ከውጭ በሕጋዊ መንገድ እንደሚገቡ ምርቶች ሁሉ በሕገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ በድንበር ገብተው ገበያውን የሚቀላቀሉ አሉ። ስለዚህ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች ስለሚገቡ ምርት የሚገዛው አካል የተመረተበት ቀን፤ የተመረተበትን ሀገር መለየት መቻል አለበት። የስታንዳርድ ጉዳይ ሲነሳ አስገዳጅ ደረጃ የሆኑ ለምሳሌ የቆርቆሮ የብረታብረትና የህጻናት ወተትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶች አሉ።
እነዚህ ምርቶች የጥራት ተጠቃሚው ችግር አለባቸው ብሎ ከተጠራጠረ ለሚመለከታቸው አካል መጠቆም ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን አጠቃላይ እንደሀገር ጥራትን ልናረጋግጥ አንችልም።
የሸማቾች ጥበቃ ሕግ ያለ ሲሆን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን በሚያመርቱት ምርት እንዲሁም በተለየ ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ የተሰማሩ አካላት በገንዘብ፤ በእስራትም የሚቀጡበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ተጠቃሚዎች ከመንግሥት ጋር መተባበር አለባቸው።
የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ሶስተኛ ወገን ነው። ፍተሻ የሚሰጠው የተስማሚነት ምዘናን አጠቃላይ ሥርዓቱን በማረጋገጥ አክሬዲት ማድረግ ነው።
የተስማሚነት ምዘና ግን የምርት ጥራት ሲያረጋግጡ ሚወስዱት ናሙና ነው። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በጣም ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ያንን ወካይ ናሙና ወስደው ፈትሸው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ደረጃውን ስለሚያሟሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ይችላሉ የሚለውን የሚሰጡት ለተቆጣጣሪው አካል ነው። ተቆጣጣሪው አካል በተሰጠው የጥራት ደረጃ ውጤት ተመስርቶ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።
በሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ናሙና ወስዶ የሚያረጋግጥበት ሂደት አለ። ነገር ግን እያንዳንዱ ምርት ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ ጊዜ ያለፈባቸው፤ በትክክል ያልታሸጉ፤ ከአያያዝ፤ ከማጓጓዝ ጋር የሚመጡ ችግሮችን በተገቢው ሁኔታ ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ችግሮች ሲኖሩ ለተቆጣጣሪው አካል ጥቆማ መስጠት አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ግን በተቆጣጣሪ አካል ብቻ ሥራውን በተገቢው ሁኔታ መሥራት አይቻልም። ስለዚህ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ስለምርት ጥራት ደረጃ ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። ስለሆነም የሚሰጠውን በሙሉ መቀበል ብቻ ሳይሆን መብቱን መጠየቅ መቻል አለበት። ስለዚህ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር የሸማቾች ጥበቃ ተቋቁሞ እየሠራበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ያስመረቁት የጥራት ማረጋገጫ መንደር ላብራቶሪዎች አሉና ምንአልባትም ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት፤ ከሸማቹ ጋር የሚገናኙ ነበሩና የእናንተ ሥራ ከእነዚህ ጋር ያለው ግንኙነት ምነድን ነው?
አቶ ቦንሳ፡– የጥራት መንደር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እያሉ ለዚች ሀገር ጥራት እንደሚያስፈልጋት ያስቡ ነበር። በተለይ ጥራት ያስፈልጋታል ብለው 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ፈንድ ተደርጎ ትልልቅ ህንጻዎችና ላብራቶሪዎች ዓለም በቴክኖሎጂ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የታጠቁ አንዳንድ ሀገራትም ላይ የሌሉ ቴክኖሎጂዎች እንዲገቡ ተደርገዋል። እነዚህ ለምርምር እና ለፍተሻ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።
ሀገራችን ዓለምአቀፍ የንግድ ተቋም አባል ለመሆን እየሠራች ነው። የአፍሪካ የንግድ ቀጣና አባል ሆነን የተወሰኑ ምርቶች ወደ ትገበራ እየገቡ ነው። እንዲህ አይነት ለሆኑ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ሥርዓት የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት በጣም ወሳኝ ናቸው። የጥራት መሠረተ ልማት የሚባሉት የደረጃዎች ኢንስቲትዩት፤ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና፤ የኢትዮጵያ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት አንድ ላይ ሆነን እየሠራን ነው።
ነገር ግን ቁጥጥሩን የምንከታተለው እኛ አይደለንም። የምንሠራው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ጥራትን፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን፤ ላብራቶሪዎቻቸውን፤ የሰው ኃይል የመፈተሽ፤ ፈቃዳቸውን የመፈተሽ ሥራ ነው።
ተቆጣጣሪው በተለይ ባለስለልጣን የሚባለው የቁጥጥር ሥራ ወይም ደግሞ በሕግ እንዲቆጣጠሩ የተሰጣቸው አካላት ናቸው የሚቆጣጠሩት። ተቋማቱን በመጠቀም ገቢ እና ወጪ ምርቶችን የሚቆጣጠሩት አስቀድሜ በጠቀስኩት በተለይ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር የሬጉላቶሪ ዘርፉን የሚያስተባብር ተቋም እንደመሆኑ እነዚህን አስተባብሮ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትንም የሚወጡትንም ምርቶች ጥራታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ውጤታማ ለመሆን መሠራት ያለበት እንዴት ነው? አምራቹ ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለተጠቃሚ ያቀርብ ዘንድ በሀገር ደረጃ ምን እየተካሔደ ነው?
አቶ ቦንሳ፡– ባደጉት ሀገራት ፖሊስ በማቆም ወይም በቅጣት እና በሌላ ጫና አይደለም። አምራቹ እራሱ ደረጃውን ያልጠበቀ ምርት ካመረተ ራሱ ገበያው ከገበያ ውጭ እንደሚያደርገው ያውቀዋል። ምክንያቱም አንድ ምርት ደረጃውን የጠበቀ ነው ተብሎ ከተነገረ ያንን መልካም ስሙን መልሶ ለማግኘት ዋጋ ይከፍላል። ምክንያቱም ተጠቃሚው ግንዛቤ ያለው ነው።
ስለዚህ ተቆጣጣሪው አካል እነዚህን ሁኔታዎች የማመቻቸት ነው እንጂ እንደ ታዳጊ ሀገራት አይደለም። ስለሆነም በዚያ ደረጃ ለመድረስ ግንዛቤ መፍጠር መቻል አለብን። በተለይ ተጠቃሚው በደንብ መጠየቅ መቻል አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከታች ከሙዓለ ሕጻናት ጀምሮ መደበኛ እና እስከ ከፍተኛ ያሉት ድረስ ስለጥራት በአግባቡ ሊሠራበት ይገባል።
ጥራት ባህል ነው። የሚጀምረውም ከቤት ነው። ጥራት የማይነካው ነገር የለም። ስለዚህ አጠቃላይ ጥራት ላይ ያለን ግንዛቤ እየጨመረ ከሔደ እና ኅብረተሰቡ ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ከቻለ ምን አገባኝ አይነት ሳይሆን በአግባቡ ልንሠራበት የሚገባ ነው።
ዛሬ ምንም እንዳልተፈጠረ የምናልፈው ከሆነ ነገ ደግሞ በወደፊት ሕይወታችን ላይ፣ በልጆቻችን እና በሀገር ላይ የሚመጣ ነገር ስለሚሆን እርሱን በባለቤትነት በውሰድ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች የሚዲያ ተቋማት ሁሉ ጥራት አሁን የሕልውና ጉዳይ ነውና ትኩረት ሰጥተው ግንዛቤ ቢፈጥሩ መልካም ነው እላለሁ። የምንወዳደረው በጥራት ነው፤ የምናሸንፈው እንደሀገር ነው። ይህንን ማሟላት ካልቻልን አደጋ ነው።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሀገራት ምርቶች ወደ እኛ ሀገር ይገባሉ። መከልከል ደግሞ አይቻልም። ስለዚህ መቆጣጠር የሚቻለው ምን ያህል የጥራት ደረጃቸውን አሟሉ በሚል በመፈተሽ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ አቅም ማጎልበት ያስፈልጋል። የሀገራችንንም አምራቾች እንዳይጎዱ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ አካባቢን ሊበክሉ የሚችሉ ጉዳዮች ወደ ሀገራችን ዘልቀው እንዳይገቡ መቆጣጠር የምንችለው ጥራት ላይ ያለን ግንዛቤ እና አቅም መፍጠር ላይ የተሠራ ስለሆነ እሱ ላይ እንደመንግሥትም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። እናም በሰው ኃይልም፣ በተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችም በዓለም አቀፍ እውቅናም በአፍሪካ ደረጃ ካሉት አክሬዲቴሽን ተቋማት የመጀመሪያዎቹ ውስጥ ነን። ጥራት ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ እናመሰግናለን
አቶ ቦንሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በሞገስ ተስፋ እና አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም