የቆራሱማ ምንነትና አገልግሎት ለከተሜው ባዕድ ወይም እንግዳ ይሆን ካልሆነ በስተቀር ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ እልፍ ወገኔ ባህሉ ዕድሜ ጠገብ ስለሆነ ብዙ ትንተና አልሰጥበትም። ጥቂት ማስተዋወቂያ ማድረግ ካስፈለገ ግን፤ ‹‹ቆራሱማ›› የወተት ዕቃዎች የሚታጠኑበት ነባርና ባህላዊ የከብት አርቢዎች ግሩም ሙያ ነው። ከአካባቢ አካባቢ ስሙ ይለያይ ይሆናል እንጂ የላሚቷ የወተትና የወተት ተዋፅኦ ምርቶች የሚከማቹባቸውና የሚዘጋጁባቸው ዕቃዎች (ማለቢያው፣ ጮጮው፣ መናጫው ወዘተ.) በሙሉ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በባለሙያ እህቶቻችንና እናቶቻችን እጅ በ‹‹ቆራሱማ›› ይታጠናሉ። በቆራሱማ በታጠነ ዕቃ የሚቀርብ ወተት፣ እርጎው፣ ቅቤው፣ አይቡና አጓቱ ጣዕማቸውና መጣፈጣቸው ይህ ቀረሽ የሚባል አይደለም። ወተቱ በጉሮሮ ሲንቆረቆር ልዩ ጣዕም አለው። እርጎው እንደ ዳቦ ይገመጣል። አይቡ በሽሚያ ይበላል። ቅቤው በጥሬው ላሱኝ ላሱኝ ይላል። አጓቱ እንደ ወይን ይጠጣል።
ዜጎችንና ‹‹ቆራሱማ››ን ምን አገናኛቸው?
የዜጎች ኑሮም ጣዕምና ጥፍጥና እንዲኖረው አመለካከታችንና የተዛባው የእርስ በእርስ ግንኙነታችን እንደ ወተት ዕቃዎች አዘወትሮ ቢታጠን ይበጃል እንጂ አይጎዳም። የማጥንቱ ባለሙያዎችና ጠቋሚዎች ደግሞ ማኅበራዊ ሃያሲያን፣ የቅርብ ተመልካቾችና በርካታ ባለድርሻ አካላት ናቸው። ዜጎች በዋነኛነት የሚታጠኑት “ቅንነት” በሚሉት ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ ‹‹ቆራሱማ›› ነው። ቅንነት ሲታጠን ይፈካል፣ ሲዘነጉት ደግሞ ይደበዝዛል። ሌሎቹ የዜጎች የ‹‹ቆራሱማ›› ማጥንቶች “መከባበር፣ መፋቀር፣ መከባበርና መተዛዘን” የሚባሉት ቅመሞች ናቸው። መቻቻል የሚለውን ቃል ነፍሴ ይጠየፈዋል። ቻይ እና አስቻይ የሚል ትርጉም ፈጥኖ ወደ አእምሮዬ ስለሚመጣ “ተቻችሎ የኖረው ሕዝብ” የሚለው የፖለቲከኞች ኮቾሮ ገለጻ በፍጹም አይጥመኝም።
ሕዝብ ለሺህ ዘመናት አብሮ የኖረው ተፋቅሮ፣ ተዋዶ፣ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ ተጋምዶ፣ ተከባብሮ፣ መከራና ደስታን በጋራ እየተጋራ፤ ጥፋትም ሲፈጠር በጥበብና በማስተዋል ይቅር እየተባባለና እየተቃቀፈ፣ ያለውን እየተከፋፈለና እየተለዋወጠ እንጂ አንደኛው ወገን ትሩፋት አመንጪ ሌላኛው ወገን ተመፅዋች ሆኖ አይደለም። ስለዚህም ‹‹መቻቻል›› የሚለው ቃል ከፖለቲካው መዝገብና ከፖለቲከኞች አንደበት ቢወገድ ደስታውን አልችለውም።
ዛሬ ዛሬ ግን ይህ በመከባበር የተሸመነውና በፍቅር የተቆራኘው የሕዝብ ትስስር ውሉ እየላላ፣ ቋጠሮው እየተተረተረ የኑሯችን፣ የአስተሳሰባችንና የህሊናችን ጣዕም ሀገራዊ ኦናነት ተጣብቶት የጎመዘዘ ይመስለኛል። ስለዚህም የሀገራዊ የጥፍጥና መዓዛችን ከእኛም አልፎ ተርፎ ለሌሎች ደምቆ እስኪገኝ ድረስ በበጎነትና በመፈቃቀር ልንተቃቀፍ ይገባል። ሕዝብ ስንል በጅምላ ፍረጃ መበየናችን እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል። ሕዝብ ስንል፣ ብሔሩና ባህሉ በደማቅ ቀለማት የተሸመነውን፣ ቋንቋና ባህሉ የተንሰላሰለውን፤ ነጋዴውን፣ ተማሪውን፣ አርሶ አደሩን፣ የመንግሥት ሎሌውን፣ የፀጥታ ኃይሉን፣ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን፣ እናትና አባቶችን፣ ጎልማሶችና አረጋዊያንን በለመድነው አባባል ብሔር ብሔረሰቦችን ማለታችን ነው።
“ሕዝብ” ስለሚለው ብርቱ ስያሜ የአንጋፋው ደራሲ የከበደ ሚካኤል ድንጋጌ ይበልጥ ያግዘን ይመስለኛል፤ “ሕዝብ በትውልድ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት መገናኘት ብቻ ሳይሆን፤ ባለፈው ኑሮ ደስታንና መከራን፣ በአንድነት የተካፈለ፣ በአስተዳደሩም በልዩ ልዩ ሥራ የተሳሰረ፣ ለወደፊቱም እሠራዋለሁ በሚለውና ስለ ሀገሩና ስለ መንግሥቱ ያለው ተስፋ አንድ የሆነ ማለት ነው።” በቅንነት ያልታጠኑ አንዳንድ ፖለቲካና “ምላስ አደር” የሆኑ “ጯሂዎች” ከደራስያችን የተዋስነውን ይህንን ጥቅስ “አሃዳዊ አስተሳሰብ” ብለው መፈረጃቸውን ደጋግመን ሰምተናል። የፎረሸ አስተሳሰብ ነው።
በግሌ በማስተውላቸው በርካታ ሀገራዊ ህፀፆች የስሜት ኦናነት (ባዶነት) ከተሰማኝ ውሎ አድሯል። የባሰ ክፉውን ያርቅልን እንጂ አንዳች ችግር አፍጥጦ ቢመጣ “የፈተናችን አሳር በቀላሉ ይበርድ ይሆን ወይ?” እያልኩ ራሴን በራሴ እመጠየቅ ደረጃ ላይ ከደረስኩ ሰነባብቻለሁ። የውስጥ ህመሜን ያባባሱት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያስተዋልኳቸው በርካታ ማሕበራዊ ቁስሎች ናቸው። ቤተ እምነቶችን የሚያቃጥሉ እምነት አለኝ ባዮች በጠራራ ፀሐይ ሰይጣናዊ ተግባር ሲከውኑ፣ የሕዝብ አውራ ጎዳናዎችን ዘግተው ተሽከርካሪ በማስቆም ወገኖቻቸውን በድንጋይ እየወገሩ የሚዘፍኑ አለሌዎች፣ ቆንጨራ የሚሠነዝሩና ከሕግ በላይ ሉዓላዊ ነን የሚሉ “ባሻኝ አደር” ወጣቶችን ፈጥረናል። እግዚኦ!
ተፋቅሮ፣ ተዋልዶና ተከባብሮ የኖረን ሕዝብ በፖለቲካ ስካር ናውዘው ያፈናቀሉ “የእብሪት ሕመምተኞችን” ያስተዋልነው በዚሁ በእኛው ዕድሜ ነው። ጉዳዩ በእኛ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ብቻ ሳይሆን ውርሱ ለልጅ ልጆቻችንም እንደሚተላለፍ ምልክቶችን እያየን ነው። ስለዚህ ነው መራራውን የክፋት ድርጊት እንደ ዋግምት የሚነቅል፣ ይቅርታና ፍቅር የሚያላብሰንን የ‹‹ቆራሱማ›› ጭስ ብንታጠን ያምርብናል፣ ያደምቀናል፣ ያስውበናል፣ ጎምዛዛውን ጣዕማችንንም ይለውጥልናል የምንለው።
ለዕውቀት ሸመታ የነገ ተስፋ አስታጥቀን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የላክናቸው ልጆቻችን ለእኩይ ተግባር በተሰማሩ “የትውልዳችን የእንግዴ ልጆች” ለሞት፣ ለአደጋና ለመፈናቀል ሲዳረጉ እያስተዋልን ነው። “ለምረቃህ እንደምንም ብዬ እገኝልሃለሁ” ብላ የልጇን ደስታ በጉጉት የምትጠብቅ ምስኪን እናት “የልጅሽን አስከሬን መጥተሽ ተረከቢ” ስትባል መሪር ሀዘን ልቧን ያንኮታኮተው ወላዲት በቀሪ ዘመኗ “ኑሮ ከተባለ” ምን ዓይነት ኑሮ ልትኖር እንደምትችል ለመገመት አይከብድም። ይህን መሰሉ ድርጊትና ክፉ ዜና በሌሎች ሀገራት ተፈጸመ ሲባል በግሌ ወይ አላነበብኩም አለያም አልሰማሁም። ይህንን መሰሉ የጭከና ተግባር ያውም በተስፈኞች ልጆቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው በእኔ ሀገር ብቻ እንጂ በሌሎች ሕዝቦች መሃል ድርጊቱና የክፋቱ ክብደት ስለመታወቁ እጠራጠራለሁ። እናስ ለትምህርት የላክናቸው ልጆቻችን ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱና በማስተዋል ቆራሱማ እንዲታጠኑ መምከሩ ወቅቱ አይደለም ትላላችሁ?
ሌላም እናክል። የባሰ ክፉ ቀን እንዳይመጣ እንደ እምነታችን ፈጣሪን የምንማጠነው የአብዛኞቹ የሀገራችን ስግብግብ ነጋዴዎች የተረገመ እኩይ ድርጊት ትዝ ሲለን ይመስለኛል። ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር በርካታ ሠራተኞችን ቀጥረው በርበሬን ከሸክላ፣ ቅቤን ከጎጂና ባዕድ ነገሮች፣ እንጀራን ከሠጋቱራ፣ ዘይትን በገዳይ ኬሚካል እየደባለቁ የመገቡን ጨካኞች ነገ ተነገወዲያ አንዳች ሀገራዊ መናጋት ቢፈጠር የፊጥኝ አስረው እንደሚሸጡን ጥርጥር አይገባኝም። በሀገር አማን የኮንስትራክሽን ብረቶች እየሰወሩ፣ የሲሚንቶ ምርት እየሸሸጉ፣ ጤፍ እየደበቁ፣ ስኳር እያከማቹ ለግፍ የጨከኑ ነጋዴዎች ነን ባዮችን ወደ ቀልብያቸው እንዲመለሱ አይደለም ህሊናቸውን በ‹‹ቆራሱማ›› ጭስ ማጽዳት፤ በርበሬ እየታጠኑ በአደባባይ ቢገረፉ ቅጣቱ ቢያንስባቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይሆንም።
የሃይማኖት አባቶች ውግዘት ሰሚ ካጣ፣ የሕግ ጉልበት ከላላ፣ የሽማግሌዎች የእርቅ ድካም ፍሬ አልባ ከሆነ፣ የወላጆች ምክር ጆሮ ከተነፈገው፣ የጎልማሶች ቁጣ ካልተከበረ፣ የመምህራን ምክር ከተሰለቸ ሀገራዊ ነጋችን ምን ሊመስል ይችል ይሆን? በቅንነት፣ በፍቅር፣ በሰላም፣ በእርቅ፣ በመግባባት፣ በመነጋገር፣ በመደማመጥ ‹‹ቆራሱማ›› ብንታጠን ይህ የከበበን የመከራ ደመና የባሰ አሳር ሳይደፈድፍብን የሚገፈፍ ይመስለኛል።
ነባር ባህሎቻችንም ፍተሻና ማጥንት ያስፈልጋቸዋል፤
“የሀገራችን ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ፣ ቸርና ርህሩህ ነው” የሚሉትን መሰል የተዘወተሩ አባባሎች መለስ ብሎ መፈተሹ አይከፋም። እርግጥ ነው የዛሬው አበሳችን መዘዙ እየተመዘዘ ያለው የሕዝባችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ውሉ ስለላላ አይደለም። የመዘዙ መዛዦች እነማን እንደሆኑና ዓላማቸውም ምን እንደሆነ ነጋ ጠባ እየተወራ አሰልችቶናል። እርግጥ ነው እንደ ሕዝብ በታሪካችን ውስጥ እንግዳ የተቀበልንባቸው አጋጣሚዎች በሃይማኖትም ሆነ በስደት፣ በንግድም ሆነ በባህል ጉዳዮች ዘርፋቸውና መልካቸው ብዙ የሚባል ነው። አቅፈን የሸሸግናቸው፣ ቆርሰን ያበላናቸው፣ ቤተኛ አድርገን ከሹመት እስከ ሽልማት ያከበርናቸውና ያደነቅናቸው ባዕዳን እንግዳ ግለሰቦችና ቡድኖች ብዛታቸው ተቆጥሮ አይዘለቅም። ለትናንት እውነታችን ምሥጋና ይግባውና ዛሬስ እንደዚያ ነን? በግሌ “የፉከራችንን ያህል ሳይሆን ኑሯችን ምስክር ነው” ብዬ ደምድሜያለሁ።
በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የሚኖሩ በርካታ ወገኖቻችን እንግዶችን በመቀበሉ ረገድ ኑሮ ይስመርላቸውም አይስመርላቸው እስከ ዛሬ ከእጃቸው እንዳልወጣ ይገባኛል። በክብር ጠብቀውና ነባር እሴታቸውን ተንከባክበው እንደያዙ አልዘነጋሁም። እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ባህሌ፣ ባህሌ እያልን የምንዘምርላቸውና የምንፎክርባቸው ጉዳዮቻችን የተረት ተረት ያህል በተወሩ ነበር። ከክልሌ ውጣልኝ፣ እኔ ዘንድ አትድረስብኝ፣ በሚለው ጊዜ ወለድ በሽታ ተጠቅተን በመደናገጣችን እየደበዘዘና መልኩ እየወየበ ላለው ለእነዚህን መሰል ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ይቅር የመባባልና የመፀፀት ‹‹ቆራሱማ›› ታጥነን ለፈውስ መዘጋጀቱ ጊዜ የሚሰጠው አይመስለኝም።
ዘርዝረን በማንዘልቃቸው በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ታመናል። ከአጥንት ስብራት የከፋውና ወጌሻ የማይደርስበት ቅስማችን በብዙ ጉዳዮች ተንኮታኩቷል። ቁዘማና ትካዜ መገለጫችን ሆኗል። አንዱ ችግር ሲደፈን ሌላው ችግር አፈትልኮ እየወጣ አናውዞናል። የነገን መልካም ሀገራዊ ተስፋ አትኩረን ከማየት ይልቅ፤ ሰላማችንና የዕለት ዳቧችን ጉዳይ እያባነነን ዓይናችንን ወደ ፈጣሪ፣ ለእንጀራችን ወደ ማዕዳችን እንዳፈጠጥን አለን። ዳቦ ማግኘቱም ብርቅ ሆኖብን አሳር እያበላን ይገኛል። ፈጥነን፣ ተግተን፣ አንድ ሆነን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደ አንድ ሕዝብ የሚፈውሰን የ‹‹ቆራሱማ›› ማጥንት ካላገኘን በስተቀር አደጋችን እየከፋ እንዳይሄድ ስጋት ከገባን ሰነባብቷል።
ሀገራችንም “በወይባ ጭስ ትታጠን”፤
ሀገራችንን የምንመስለው በሴቴ፤ ያውም በተወዳጅ እናት አንቺ እያልን ነው። የወይባ ጭስ የሚታጠኑትም እህቶቻችንና እናቶቻችን “አንቺዎች” ናቸው። ጉዳዩ ወንዶችን አይመለከተም። የወይባ ጭስ ከምንና እንዴት ይዘጋጃል ለሚለው ጥያቄ ባለሙያዎች ቢመልሱት ይበጃል። አገልግሎቱን የሚሰጡትና ወይባ የታጠኑት ወይዛዝርት ደጋግሞው እንደመሰከሩት ከሆነ ግን ጭሱ ለተጠቃሚዋ እህት ወይም እናት ለወገብ ሕመምና ለማህፀን ችግር ፍቱን መድኃኒት ነው ብለውናል። ዘመናዊ ሐኪሞች በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ሙያዊ ትንታኔ ሥራዬ ብዬ አላደመጥኩም።
ዛሬ ዛሬ ስሜታችን ቢጠቁርም እምዬ እያልን የምንጣራት ሀገራችን እስከ ዛሬ ስትታጠን የኖረችው ፖለቲከኞቿ ከውጭ ያጋበሱትን ፍልስፍና እንደነበር “የሟቹ አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ፍጻሜ ትምህርት ሰጥቶናል። ጆሯችንንና ህሊናችንን ደፍነን አንሰማም አናይም ብለን እንጂ በዘመነ ደርግ ታጥነን ያጨናበሰንና በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ተንኮታኩቶ ቀባሪ ካጣው ሶሻሊዝም ብዙ በተማርን ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ ሀገር በቀሉን “የመደመር – የወይባ ጭስ” እንሞክረው ብለን ለመታጠን ዳር ዳር እያልን ነው። እንደሚመስለኝ ግን ሀገራዊው የመደመር ፍልስፍና እየተቃናና እየተመከረበት ከሄደ የተሻለ መኖሪያችንና መበልፀጊያችን ሊሆን እንደሚችል ብን እያለ የሚያውደን የጭሱ መዓዛ በጥቂቱም ቢሆን ለበጓችን እንደሆነ ጅምሩ ጠቁሞናል። ስለ ፍጽምናውና አዋጭነቱ ለመመስከር ግን እንደ ሃሳቡ አመንጭ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመሃላ አጅበን ለማረጋገጥ ማጥንቱ ገና በአግባቡ ስላላጠነን በሙሉ አፋችን ለመመስከር አንደፍርም። የመደመሩን የፍልስፍና ስሌት ጉዳይ ለጊዜው በይደር አቆይተን በተግባር እያሽመደመዱን ባሉት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥቂት ቁዘማ እናድርግ።
ሀገር ስንል ከወንዝ፣ ከተራራው፣ ከሸንተረሩ፣ ከባህልና ከታሪኩ፣ ከቋንቋና ከእምነቱ ቀድሞ የሚታወሰን የፖለቲካ ሥርዓቱ ነው። ከፖለቲካ ሥርዓቱ ተሽቀዳድሞ ደግሞ አለሁ የሚለን የሀገር መሪዎቻችን አቋምና ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ቢሉ ከሀገርም ሆነ ከሕዝብ ፊት ቀድመው የሚታዩት፣ የሚመሰገኑትም ሆኑ የሚረገሙት መሪዎች ስለሆኑ ነው። “የሀገር መልክ የመሪዎች መልክ ነው” የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
ሀገር በሰላምና በፍቅር “የወይባ ጭስ” መታጠን አለባት ስንል አለምክንያት አይደለም። ሀገሬን የፖለቲካ ግርግር ደዌ፣ የእብሪተኞች ተንኮል፣ የአልጠግብ ባዮች ክፉ ራስ ወዳድነት ወገቧን እያሽመደመደ ያጎበጣት ይመስለኛል። ለምን ይመስለኛል እላለሁ፤ እርግጥ ነው እንጂ። ነገ ተነገወዲያ ትውልድ የምትፈጥርበት ማህፀኗም በደዌ እንዳይለከፍ ከወዲሁ አጥብቀን ልንሰራ ይገባል።
መንግሥት በግልጸኝነትና በታማኝነት ሕዝብን አክብሮ በትህትናና በአክብሮት የወይባ ጭስ ይታጠን ስንል አለምክንያት አይደለም። በወይባ ጭስ በመሰልነው በጎ አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ አንዳንድ የመንግሥት ሹማምንት ባዕድ አካል እየነሰነሱ ሕዝቡን እንደሚያስነጥሱ መንግሥት ራሱ ይጠፋዋል ብዬ አልገምትም። ዕድልና ጊዜ ባገጣጠመላቸው ሦስት አራት መኪና እየተንደላቀቁ የማይረኩ፣ በተዋበ ቤት ውስጥ እየኖሩ የደሃውን ጎጆ የሚያራቁቱ፣ በተመደበላቸው ሽፍን የፕሮቶኮል መኪና ልጆቻቸውን በታላላቅ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች ውስጥ በቦዲ ጋርድ አስጠብቀው እያስተማሩ የድሃ ልጆች መፈናቀልና ሞት ግድ የማይሰጣቸው የ“ፖለቲካ ወለድ ሹመኞች” ጉዳይ ትናንትም ሆነ ዛሬ መፍትሔ ያገኘ አይመስለንም። እንደውም ትናንት ይሻላል መሰለኝ።
ለምሳሌ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በያዙ ሰሞን ራሳቸው የሚመሩትን የካቢኔ ስብሰባ ጨምሮ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤት ሹማምንት የሚመሯቸው ስብሰባዎች በሙሉ ወይ ከሥራ ሰዓት በኋላ፣ አለያም ከሥራ ቀናት ውጭ እንደሚሆን ኮስተር ብለው አውጀውልን ነበር። ይህ ውሳኔ እርሳቸውን ይመልከት አይመልከት እርግጠኛ ባልሆንም ከእሳቸው በታች ያሉት “ፖለቲካ ወለድ ሹማምንት” ግን እንኳን መመሪያውን ሊተገብሩ ቀርቶ እንዲያውም አብሰውታል። አንድ የመንግሥት ሹም በቢሮው ላይ ከማግኘት ይልቅ እግዜርን ተስሎ መጠበቁ ይቀላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዕድል ገጥሞን ባገኘናቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ አቅፈው ሰላም እያሉ ግርምት ፈጥረውብናል። ሚኒስትሮቻቸውንና ሹማምንቶቻቸውን ደግሞ ልብ ብላችሁ አይታችሁ ከሆነ እንኳን ለሰላምታ የሚቀርባቸውን ሰው በፈገግታ አፀፋውን ሊመልሱ ቀርቶ ገና በሩቁ ተኮሳትረው ሲገፋተሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል።
የፋሽስት ጣሊያን ወታደር ወዳጅ አድርጋ በሀገሯ ሴቶች ላይ ፊቷን ያዞረችን አንዲት ጥቅም ያሳወራት ሴት ሠፈርተኛው እንዲህ በማለት ለአዝማሪ አሳጣት ይባላል፡
“አርኩም ይሄድና፤ ሶልዲውም ያልቅና፣
ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና።
‹‹አርክ›› የጣሊያን ወታደር፣ ‹‹ሶልዲ›› ደግሞ ገንዘባቸው መሆኑ ነው። ልብ ያለው ልብ ቢያደርግ አይከፋም።
ሰሞኑን መሥሪያ ቤቶችን ኦና እያደረገ ያለው “የብልፅግናን ፓርቲ” ለማስተዋወቅ እየተባለ በሚደረገው የመላ ሠራተኞች ተከታታይ ስብሰባ ጉዳይ ብዙ ማለት ቢቻልም “ሕዝቡ ስለሚከፍለው ታክስ” ብላችሁ የመንግሥትንና የፓርቲን ተግባር ለዩልን እያልን ሰሚ ከተገኘ አቤቱታ እናቀርባለን። ሳይታሰቡ እየወጡ ሳይተገበሩ ስለሚታጠፉት መንግሥታዊ አዋጆችና ደንቦች ጉዳይም አቤቱታ አለን። ለመንግሥት ሹማምንት ስለተመደቡት ‹‹V8›› መኪኖች ጉዳይና ስለሚከወነው ቴያትር ብዙ ማለት ይቻላል። መሻሻል አድርጌያለሁ እያለ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችን ስለሚያስለቅሰው የገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ጉዳይ ተደጋግሞ ቢጮኽም እስካሁን እፎይ ማለት አልተቻለም። የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይማ ተከድኖ ቢያር ይሻላል። የሞተር ብስክሌትና የከባድ መኪኖች የአገልግሎት ሰዓት ገደብ መቼ ተወስኖ መቼ እንደተነሳ ይታወቃል።
ሰሞኑን ተረቆ ለፓርላማው የቀረበው የኤክሳይዝ ቀረጥ ጉዳይ ሀገር እያጯጯኸ መሆኑ ለማንም ባዕድ አይደለም። ባለሙያዎችና ምሁራን ባልጠፉበት ሀገር በተቋማት ሙያተኞች ብቻ ተረቆ ሊተገበር ዳር ዳር የሚለው አዋጅ ሲፀድቅ ድሮ ድሮ፤ ዛሬም ቢሆን መኪና ያለው ሰው እንደ ተሳካለት ይቆጠር ነበር። ወደፊት ግን የፅድቅ መገለጫ ተደርጎ እንደሚታመን የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ደንግጎልናል። መኪና ከዕለት መገልገያነት አልፎ እንደ “ቅዱስ ዕቃ” የተባረከው በሀገሬ ብቻ ነው። በአዋጅ የታዘዝነውን ሳንወድ በግድ አሜን ብለን እንቀበላለን። ጤፍ፣ ስኳር፣ ምስር፣ የሽሮ እህል፣ ነጭ ሽንኩርት ወዘተ. በቅርቡ የቅንጦት ዕቃ መሆናቸው በአዋጅ እንደሚገለጽልን መጠበቁ ብልህነት ነው። በእነዚህን መሰሉ የሀገራችን ጉዳዮች “በማስተዋል የወይባ ጭስ ታጥነን” መፈወሱ አስፈላጊ አይደለም ትላላችሁ።
“ተው ቻለው ሆዴ፤ ተው ቻለው ሆዴ፣
ሲያልፍ ለሚያልፍ ቀን ምነው መናደዴ።”
አለ አሉ ግራ የገባው አዝማሪ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 14/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ