እዚሁ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የተናገሩትን እያነበብኩኝ በነበረበት ቅጽበት ሰሞኑን በፌስቡክ ገጽ የለጠፍኩት ጥያቄ ትውስ አለኝ። ከዚያ በፊት ፕሮፌሰር መረራ መጪውን ምርጫ አስመልክቶ የሰጡትን አስተያየት ላስቀድም። ፕሮፌሰሩ በአጭሩ የምርጫ ይራዘም ባዮችን ሀሳብ አይደግፉም። ከንግግራቸው ተከታዩ ይበልጥ ስቦኛል። “… ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲኖር ማስቻል ይጠይቃል፤ ከዚያ ውጭ የሚፈጠሩ ነገሮች በሙሉ አገሪቷን ይበትኑ ይሆናል እንጂ የሚያመጡት ትርፍ ስለማይኖር የኢህአዴግ አመራሮች ይህንን ደጋግመው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት በየቦታው ያሉ ቀውሶች መንስኤያቸው አንድ ገዢ ፓርቲ ስልጣንን በበላይነት ይዞ በከፋፍለህ ግዛ ሴራ አገሪቱን ሲመራ በመቆየቱ፤ የአስተዳደርና ፖለቲካዊ ችግሮች ባለመፈታታቸው፤ በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ የመጣ መንግሥት ባለመኖሩ ነው። ብሔራዊ መግባባት ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል። ከዚያ ውጪ ግን ምርጫውን ማራዘም መፍትሔ አያመጣም፤ እንደውም ለበለጠ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።
በሕዝብና በመንግሥት መካከል ለተፈጠረው ሰፊ ክፍተት ምርጫው ራሱ መልስ ሊሆን ይችላል። በሀቅ ወደ ምርጫ የምንገባ ከሆነ ሕዝቡ በመረጣቸው ተወካዮቹ ወደ መመራት ይሄዳል። ስለዚህ በእኔ ግምት የሚቻለውን ያህል ጥረት ተደርጎ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ምርጫው መካሄድ አለበት።..”
ቀደም ወደአለው ሀሳቤ ልመለስ። ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ (በፌስቡክ) አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ይቻል እንደሆን ጥያቄ አዘል አስተያየት አስፍሬ ነበር። በቂም ባይሆን ምላሾችን አግኝቻለሁ። መጀመሪያ እንደመነሻ ወደአቀረብኩት ጥያቄ ልለፍ።
“በአንፃራዊነት ሠላምና መረጋጋት ባልሰፈነበት፣የፖለቲካ ሀይሎች ለመገናኛ ብዙሀን ፍጆታ ከመተቃቀፍ የዘለለ መግባባት ባልደረሱበት፣ የብሄር ተኮር ፖለቲካው ባልሰከነበት፣ እዚህም እዚያም ግጭት ማስነሳት የሚችሉ ሀይሎች ማስታገስ ባልተቻለበት፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከግጭት ቀጣናነት ባልፀዱበት… በዚህ ሰዓት…ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ የሆነ ምርጫ እንደምን ማካሄድ ይቻላል?” የሚል ነበር። ጥያቄው አቋም አዘል ወይንም ጋዜጠኞችና የህግ ባለሙያዎች (Leading question) የሚሉት ዓይነት ነበር። ይህን የተጠቀምኩት እኔም ብዥታ ውስጥ በመውደቄ እንጂ የምርጫው መካሄድ ወይንም ያለመካሄድ አጀንዳ ጋር የተለየ ጥቅም ያለኝ ሆኖ አይደለም።
ከተሰጡኝ አስተያየቶች መካከል አንድ ወዳጄ (ስማቸውን ያልጠቀስኩት ባለማስፈቀዴ ነው) እንዲህ ብሎኛል። “ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው። ፍሬ ያለው ውይይትና ክርክር በሰው ዘንድ ተፈላጊ አይመስልም። ጥላቻው፣ ይዋጣልን ባዩና ስድቡ ነው በገበያው የናኘው። መበታተናችን ነው፣ ካልተደማመጥን መተላለቅ ነው ቢባልም ሰሚ አልገኝ አለ። አሁን መስጊድ ማቃጠልን ምን ይሉታል? ምክር የምንሰማ አልሆንንም። በመከራ አርጩሜ መሸንቆጥ አይቀርልንም። መነጋገር ካልቻልን መተራረድ ነው ዕጣችን፣ ወደዚያም በታላቅ ሞራል እየገሰገስን ነው። ሕዝቡ የሚፈልገው ይሔን ከኾነ ምንም ማድረግ አይቻልም።
ምርጫውም የበለጠ ስድቡ፣ ጥላቻው፣ ቂሙ፣ ፉከራው የሚጋጋልበት ነው። የኦሮሞ ፓርቲዎች የተዘጋጁት ከምኒልክ ጋር የምርጫ ውድድር ለማድረግ ነው። ዳውድ ራሳቸው፣ አሁን ማንነትና ነጻነት እንጂ አማራጭ ሃሳብ አያስፈልግም ብለዋል። የአብን አመራር የኾነው ጋሻው በቅርቡ በተደረገ ክርክር አዴፓን እንደ legitimate ድርጅት ቆጥሮ፣ የጥቅም ስሌት የያዘ ፕራግማቲክ አካሔድ ለማሳየት በመሞከሩ፣ ከተመልካች ያገኘው ውርጅብኝ ገበያው የሚፈልገው ጥላቻና ስድብ መኾኑን፣ አብን በዚህ ከቀጠለም ከባድ ዋጋ እንደሚከፍል ያሳየ ነው። እነፊንፊኔ ኬኛ፣ የቅማንት ክልል ወዘተ ቀጣዮቹ የጦርነት አጀንዳዎች እንጂ የድርድር ጥያቄዎች አይመስሉም። ደቡብ 20 ትንንሽ ተኾነ በኋላም፣ የድንበርና ወረዳ ይገባኛል ጥያቄዎች የግጭት አጀንዳ መኾናቸው ይቀጥላል። ባጭሩ፣ ምሁሩ ኃላፊነት ካልተሰማው፣ ስንፍና፣ጥቅመኝነትና ጮሌነት ዋና ዕሴቶቻችን ሆነው ከቀጠሉ፣ የጥላቻ ፋይልን ዘግተን ወደፊት ካላየን፣ አማራጩ መፍረስ ብቻ ነው።”
ሌላኛው ወዳጄ እንዲህ ይላል። “አስቸጋሪ ነው። ግን አማራጭ የለም። …ስለዚህ ከግንቦት በኋላ የአሁኑ ፓርላማም የሥራ ዘመኑን ስለሚያጠናቅቅ ይበተናል። ምርጫ ካልተደረገ የተበተነ ፓርላማ ባለበት ወታደራዊ አገዛዝ ካልሆነ በቀር ማንም ፓርቲ ወይም ግለሰብ ህጋዊም፣ ህገመንግስታዊም፣ በአለምአቀፍ ማህበረሰብ ተቀባይነት የሌለው፣ በመላ የአገራችን ህዝቦችም ምንም አይነት ህዝባዊ ውክልና የሌለው ህገወጥ መንግስት፣ አምባገነን መንግስት ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘመንን እንደመገረብ ይቆጠራል።
ሌላኛዋ ወዳጄ ቆጣ ብላ ይህን አስፍራለች። “እኔ በበኩሌ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚለው ወገን ከምርጫው በፊት የአገሪቱን መረጋጋት የሚፈልገው አልመሰለኝም።…”
እርግጥ ነው፤ የምርጫው መካሄድ የሠላሙን ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ እንዳያደርሰው የሚሰጉ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም። በቅርቡ ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር በነበረው መድረክ ከተንጸባረቁት መካከል በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ያለመረጋጋት ችግር የዚህ ዓመት ጠቅላላ ምርጫ ዋና ፈተና ሊሆን እንደሚችል በአደባባይ ተነግሯል። አዲስ በጸደቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የምርጫ እና የፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ በተደረገ ውይይት ያለመረጋጋት ችግር ከጊዜ እጥረት ጋር ተደማምሮ የምርጫው ፍትሃዊነትና ታማኝነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል።
እንደኢህአፓ ዓይነቱ ዕድሜ ጠገብ የፖለቲካ ሀይሎች አሁን አገሪቱ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመገምገም የምርጫው መካሄድ የባሰ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ሀሳብ ሲሰጡ ከርመዋል። ኢህአፓ እንደሚለው “በአገሪቱ አሁን ባለው የጸጥታ ሥጋትና ጫፍ የረገጠ ብሔርተኝነት ምክንያት የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ መጪው ምርጫ መራዘም አለበት።”
የኢህአፓ ከፍተኛ አመራርና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ቆንጅት ብርሃን እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት ጫፍ የረገጠበት ደረጃ ደርሷል። አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ አዳጋች በመሆኑ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ፓርቲያቸው ምርጫውን በአግባቡ ማካሄድ ይቻላል ብሎ አያምንም።
በተለይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጫፍ የረገጠ ዘረኝነት እንደሚስተዋል ገልጸው፤ በዚህ ሁኔታ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች እንዴት አድርገው ነው ከህዝቡ ጋር የሚገናኙት፤ የት ሄደው ነው ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚቀሰቅሱት ሲሉ ጠይቀዋል።
የመንግሥት የመጀመሪያው ስራ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን አለበት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ህብረ ብሔራዊ ድርጅቶች የትም ተንቀሳቅሰው ከህዝቡ ጋር ተገናኝተው የራሳቸውን መራጮች የሚቀሰቅሱበትና ምርጫውን የሚሳተፉበት ሁኔታ ማስተካከል ያስፈልጋል» ብለዋል።
የኢህአፓ ሥጋት በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት እየተባባሰ የመጣውን ብሄር እና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችን መነሻ ያደረገ ይመስላል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰቱ ግጭቶች ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር ሰሚር እንዳሉት የአምባገነንነት መንሰራፋት፣ የብሄር እና ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍሎች ለግጭቶች ዋንኛ መንስኤዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ የለውጥ እርምጃዎችና መጪ ሁኔታዎች ላይ አተኩሮ በፎረም ፎር ስተዲስ በቅርቡ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡ ምሁራን አንዱ የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር ካሣሁን ብርሃኑ መጪው ምርጫ መራዘም እንዳለበት አሳስበዋል። እንደእሳቸው ገለጻ ከሆነ “ከ1953 ጀምሮ በሀገሪቱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ አለመፈጠሩ እስካሁን ለዘለቀው ፖለቲካዊ አለመብሰል ሀገሪቱን ዳርጓታል። የእርስ በእርስ መወነጃጀልና መጠራጠርም ሀገሪቱን ዋጋ እንዳስከፈላት ምሁሩ አስረድተዋል። በሀገሪቱ የበሰለ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠርም መጀመሪያ ጠንካራና ትክክለኛ የፓርቲ መሠረት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መፈጠር ወሳኝ ነው። አሁን ሀገሪቱ ባልተረጋጋችበት፣ በርካታ የህግ ማስከበር ችግሮችና መፈናቀሎች ባሉበት ሁኔታ በ2012 ምርጫ ማካሄድ የማይቻልና ሀገሪቱን ለበለጠ ምስቅልቅሎሽ መዳረግ በመሆኑ ምርጫው ቢያንስ በአንድ አመት ሊራዘም ይገባል።…”
በሌላ በኩል ምርጫ ቦርድ በእርግጠኝነት መጪው ምርጫ እንደሚካሄድ ሰሞኑን በቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በኩል ይፋ አድርጓል። ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞም ቅድመ ዝግጅቶችን መጀመሩንም የሚጠቁሙ ዜናዎች ሲለቀቁ ሰንብተዋል።
ወደ ውህደት እያመራ ያለው ኢህአዴግ ቀደም ሲል በምርጫው ለመሳተፍ የያዘውን አቋም አጠንክሮ እንደገፋበት ምስክር የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሰሞኑን በኦስሎ የኖቤል ሽልማታቸውን በተቀበሉበት መድረክ ላይ ዘንድሮ ምርጫ እንደሚካሄድ መጠቆማቸው ነው።
ከዚህ ቀደምም የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ ቁልጭ ብሎ ከወጡ ነገሮች አንዱ የመጪው ምርጫ ጉዳይ ይገኝበታል። ሥራ አስፈጻሚው በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል። “ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫም ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት 2012 ላይ መካሄዱ አስፈላጊነት ላይ አቋም በመያዝ እንደ ድርጅትም እንደ መንግስትም ዝግጅት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል”። እርግጥ ነው፤ ከዚያ በፊትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በግልጽ መጪው ምርጫ እንደሚካሄድ መናገራቸው የሚታወስ ነው። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ስለመጪው ምርጫ ኢህአዴግ ብቻውን እንደማይወስን መጠቆማቸው ምናልባት እንዲራዘም ፍላጎት ሳይኖራቸው አይቀርም በሚል ለትችት አጋልጧቸው ቆይቷል።
ከሁሉ በላይ የሚገርመው ኢህአዴግም ሆነ ሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጎራ ለይተው መጪው ምርጫ ይካሄድ ወይንስ ይራዘም የሚል አተካራ ውስጥ ገብተው መሰንበታቸው ነው። ፓርቲዎቹ በሕገመንግሥቱ በየአምስት ዓመቱ አንድ ጊዜ እንደሚካሄድ የተቀመጠውን ድንጋጌ ሳያከብሩ ስለምርጫ መራዘም/አለመራዘም ጉዳይ መብሰልሰላቸው ገራሚ ነበር። እርግጥ ነው፤ ብዙዎቹ የሚነሱ ሃሳቦች “በሀገሪቷ ሠላምና መረጋጋት የለም፣ በዚህም ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም” የሚል መከራከሪያ ሲቀርብበት የቆየ ነው። መንግሥት ግን ሠላምና መረጋጋቱ ከአቅሜ በላይ ሆኗል ሲል ባልተደመጠበት ሁኔታ ሌሎች አማራጮችን ከማየት ይልቅ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ለመደራደር መፈለጋቸው ለትዝብት የዳረጋቸው ጉዳይ ነበር።
በዚህ ሰዓት በግል ግምገማ የሚታይ፣ የሚዳሰስ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ የሚገኙት ኢዜማ እና አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ናቸው ብል ያጋነንኩኝ አይመስለኝም። እነ ኢዜማ በቀጥታ ደጋፊዎቻቸውን በማግኘት ሥራቸውን እያከናወኑ ሲሆን የብልጽግና ፓርቲ ሕዝባዊ ፍላጎቶች መሠረት ያደረጉ ስራዎችን በማከናወን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የቅስቀሳ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል እነ ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ ከሶስት ወራት በኋላ ወደሥራ የሚያስገቡትና በሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ድጋፍ የሚገነባው የዳቦ ፋብሪካ እንደ አንድ አብነት መጥቀስ ይቻላል። አዲሱ ፓርቲ የእውቅና ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ አስገብቶ እየተጠባበቀ መሆኑ ብዙ እንዳይራመድ የገታው ይመስላል። በዚህ ጸሀፊ ግምገማ ሌሎች የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች የቅስቀሳ ሥራዎች ስለመጀመራቸው የታዘበው ነገር የለም።
እንደማሳረጊያ
አሁን መጪው ምርጫ ይካሄድ ወይንስ ይራዘም በሚል የሚነሱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄዎች ናቸው። ውይይቶች መካሄዳቸው ሁሉም ወገን ከቆመበት ጽንፍ ወደ መሀከለኛው ቦታ እንዲመጣ የሚያግዝ ነው። በዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሲቪል ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃን እና ራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከባባድ ኃላፊነቶች ከፊታቸው ተደቅነዋል። እናም እንደሕዝብና ቤት ቆጠራው ብዙ ሀብት ፈስሶ “ምርጫ ማካሄድ አይቻልም” በሚል የውሃ ቅዳ መልስ ጨዋታ ሳይገባ ከወዲሁ ሁሉም ወገን በሰለጠነ መንገድ ይወያይ፣ ለአገር የሚጠቅመውንና ለዘላቂ ሠላምና መረጋጋት የሚበጀውን መንገድ ያሳይ፣ ይጠቁም። (ማጣቀሻዎች፡- አዲስዘመን ጋዜጣ፣ ኢትዮ ኤፍኤም ራዲዮ፣ የጀርመን ድምጽ፣ድሬቲዩብ ኦንላይን ሚዲያ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ…)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 14/2012
ፍሬው አበበ