የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ጠላቶች የጥፋት ባህሪ እስስታዊ ነው፡፡ ሀገር ይበትናል ለውጥ ያደናቅፍልናል ያሉትን የብጥብጥ ስትራቴጂ በሙሉ እየቀያየሩ መጠቀማቸው ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ምርጫ ይሁን የአዲስ ፓርቲ ምሥረታ ፤ጥምቀት ይምጣ ዒድ ለእነዚህ እኩያን የሚታያቸው እንዴት አድርገን ብናበጣብጥ የጥፋት ዓላማችን ይሳካልናል የሚለው ነው፡፡
የእነዚህ የጥፋት ኃይሎች የቀደመ ሰሞን አጀንዳ የብልጽግና ፓርቲ ምስረታን ተከትሎ ፌዴራሊዝም ሊፈርስ ነው ልትጨፈለቅ ነው የሚል ነበር፡፡ ይሁንና የፓርቲው አመራሮች በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃን ተከስተው እውነታውን በማፍረጥረጣቸው የመዘዙት የጥፋት ካርታ መክኗል፡፡ ስለሆነም የትጨፈለቃለህ እና የትዋጣለህ ቅስቀሳቸው አየር ላይ በንኖ መክኖ እንዲቀር ላደረገው ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር መስጠት ግድ ይላል፡፡
በጥፋት ኃይሎች ባህሪ ሀገርን ለመበተንና ለማናጋት የተመረጠው ሌላ አጀንዳ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በብሔር ከፋፍሎ ማጋጨት ነበር፡፡ ስፖርታዊ ውድድርን መሠረት አድርገው የፈጠሩት ግጭትም የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመትን አስከትሏል፡፡ የትምህርት ፕሮግራሙ ላይ መደነቃቀፍ በመፍጠርም የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላም በእጅጉ ተፈታትኗል፡፡ በተማሪዎች፣ በመንግሥትና ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት ርብርብ ችግሩ የታቀደለትን ዓላማ ባያሳካም በተማሪዎች፣ በወላጆችና በሀገር ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ የማይካድ ነው፡፡
ሀገራችን በሰላም ዙሪያ በሠራችው ሥራ በመሪዋ በኩል የኖቤል ሽልማት ማግኘቷ፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው፤ ለረጅም ዘመናት በድህነት ትታወቅ የነበረች ሀገር የራሷን ሳተላይት ማምጠቋ ለጥፋት ኃይሎች ሀዘን እንጂ ደስታን አይፈጥርላቸውም፡፡ እርስ በርስ በመናቆር የሚታወቁ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በአንድ መድረክ ተቀምጠው መወያየት ጭንቀታቸው ነው፡፡ የእነዚህ ኃይሎት ዓላማ ሰባራ ሰንጣራ ምክንያት ፈልጎ ሀገር ማፍረስ ነውና ቅዱስ ተግባራት በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በሀይማኖት መቻቻል ለዓለም ተምሣሌት ናቸው፡፡ ሙስሊም ክርስቲያኑና ዋቄፈታው በልዩነት ውስጥ አንድነትን አጽንተው ተዋደውና ተቻችለው ሺዎች ዓመታትን በፍቅር ኖረዋል፡፡ እየኖሩም ይገኛሉ፡፡ ሙስሊሞች ለቤተክርስቲያን ፤ክርስቲያኖች ለመስጊድ ግንባታ የገንዘብ ፣የጉልበትና የሞራል ድጋፍ ያደረጉበት ሁኔታም ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት መቻቻል የደረሱበትን ደረጃ ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
ይህን መሰል ተምሣሌታዊ የእምነት መቻቻል ባለበት ሁኔታ ነው የጥፋት ኃይሎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የብጥብጥና ሃገር የማፍረስ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ የሚታየው፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ለሃይማኖቱ ያለውን ክብርና ቅንዓት የሚያውቁት የጥፋት ኃይሎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ቅስቀሳ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ማበረታታት ነው፡፡
ይህን እኩይ ዓላማቸውን ዕውን ለማድረግ ቤተእምነቶች የጥቃት ዒላማ ሆነው ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርገዋል፡፡ በጅግጅጋ፣በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች፣እንዲሁም በአማራ ክልል ሞጣ አካባቢ የደረሱ በእምነት ተቋማት ላይ ያነጠጠሩ ጥቃቶች የክሰሩ ፖለቲከኞች የወደቀ አጃንዳቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማስፈን በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ማሳያ ነው፡፡
የዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ስትራቴጅስቶች ግብ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠልና ማፍረስ አይደለም፡፡ ይሄን ተከትሎ የአንደኛው እምነት ተከታይ በሌለው ላይ ተነስቶ ፍጅት እንዲፈጠር እንጂ፣ ይሁንና በመላ ኢትዮጵያውያን የሚያስደንቅ ስክነትና ጨዋነት የታለመው የዕልቂት ዕቅድ በተደጋጋሚ ከሽፏል፡፡ይልቁኑ ክርስቲያኖች ጉዳት ለደረሰባቸው መስጊዶች፤ ሙስሊሞች ደግሞ ለተጎዱ አብያተ ክርስቲያኖች ድጋፍ በማድረግ ታላቅነታቸውንና አብሮነታቸውን ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡
በመግቢያችን እንደገለጽነው የኢትዮጵያ ጠላቶች እስስታዊ የጥፋት ባህሪ ተለዋዋጭ ነው። የጥፋት ዓላማቸውን ያሳካልናል ብለው ካሰቡ የማይጠቀሙት አማራጭ እንደሌለ ከተደጋጋሚ ተግባራቸው ለመመልከት ችለናል፡፡ ፌዴራሊዝም፣ ብሔርና ሃይማኖት፣ ሃገር የማፍረስ ዓላማቸውን በቀላሉ ያሳኩልናል ብለው ከሚጠቀሙባቸው ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ስለሆነም በየትኛውም ጭምብል ይምጡ የእነዚህን ሃገር በታኞች ዓላማ መረዳትና ነቅተናል ብሎ እኩይ ዓላማቸውን ማፍረስ የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2012