በርካታ የሀገርና የህዝብ ሀብት ባለፉት ዓመታት በሙስና መመዝበራቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሳ ከርሟል። ይሄ ሀብት ተመዝብሮ በሀገር ውስጥ በተለያየ መልኩ እንዳለም ይገለጻል፡፡ እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገር ሸሽቷል በሚልም የማጣራት ስራዎች በሀገር ደረጃ እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል። በሀብት ምዝበራው እጃቸው አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩ አካላትም ጉዳያቸው በህግ እየታየ ነው።
ይሁን እንጂ የሙስና ወንጀል ውስብስብና ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተፈለገው መጠን በተለይ ወደ ውጭ ሀገራት የሸሹ ሀብቶችን የማስመለሱና ተጠርጣሪ ወንጀለኞችንም ተጠያቂ የማድረጉ ስራ በሚፈለገው መጠን ውጤት እያስገኘ አይደለም። ይህ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የጸረ ሙስና ትግሉ ተዳክሟል የሚል ትችት እንዲሰነዝር አድርጎታል።
የቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 ዓ.ም ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መቀየሩን ተከትሎ ከተጨመሩለት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል ምርመራን መምራትና ማስተባበር ዋነኛው ነው። በዚህም በአገሪቱ ላይ የተፈጸሙ ከባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ ምርመራ በመምራትና በማስተባበር በወንጀሉ ላይ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል። ለአብነትም በቀድሞ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ በውሃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን እንዲሁም በመንግሥት ግዥ ኤጀንሲ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ምርመራ ተደርጎባቸው ክስ መመሥረቱ ይታወሳል።
በ2011 በጀት ዓመት በሙስና ወንጀሎች ሀብትን ለማስመለስ እና ለማስከበር በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተሰራው ስራ 138 ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ተደርጓል። በ2012 በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በጸረ ሙስና ትግሉ በተሰሩ ሥራዎች ያለ አግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግስት ካዝና በጥሬ ገንዘብ ማስመለሱን እና በሙስና ወንጀል በተመዘበረ ሀብት ላይ ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል።
ሌሎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና ከሀገር ለማሸሽ የወጣ ሀብት ለማስመለስም የሀብት ማስመለስ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አስታውቋል። በዚህም ሀብቱ የሸሸባቸውን ሀገራት የመለየት ስራ ተሰርቷል። ከሀገራቱ ጋር ውይይት ተጀምሮ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በወንጀል የተገኘ ሀብት የማስመለስ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል። በ2012 በጀት ዓመትም በሀብት ማስከበርና ማስመለስ እንዲሁም ማስወረስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ በያዘው ዕቅድ መሰረት ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በመታገልና ያለአግባብ በመንግሥት ላይ ኪሳራ ባደረሱ አካላት ላይ ዐቃቤ ሕግ ምርመራ በማድረግ ክስ መስርቷል። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።
የሙስና ወንጀል ውስብስብ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ሀብትና ንብረት በተለያዩ ስሞች ወደተለያዩ ሀገራት እንዲሸሽ ይደረጋል። ውስብስብነቱን በመረዳትና ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ያመች ዘንድ በሙስና ወንጀል የተገኙትን ሀብቶች የሚያስመልስና የሚያስወርስ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ የሚሠሩ ማስተባበሪያዎችን በማደራጀት በበጀት ዓመቱ በሙስና ወንጀሎች ዙሪያ ስኬታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሯል። የጸረ ሙስና ትግሉ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉንና ምርመራዎች ጊዜን መሠረት አድርገው መረጃዎችንና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ የሚከናወን ከመሆኑም በተጨማሪ በትኩረትና በጥንቃቄ መመራት አለበት።
የሙስና ወንጀል ውስብስብ በመሆኑ የፍትሕ አካላት ጉዳይ ብቻ ሊሆን አይገባም። ህብረተሰቡም የሚያውቃቸውን ጉዳዮች በመረጃና በማስረጃ አስደግፎ በማቅረብ ለሙስና ትግሉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት። ከሀገር ውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሸሸውን የሀገርና የህዝብ ሀብት በማስመለሱ በኩል አሁንም የተጠናከረ ስራ መስራት ያስፈልጋል። ወደ ውጭ ሀገር የሸሹ ሀብቶችን የማስመለሱ ሂደት የኅብረተሰቡን ሰፊ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ወንጀሉንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኘው ዜጋ የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች አበረታች ቢሆንም አሁንም የጸረ ሙስና ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2012